Wednesday, November 16, 2016

ፍቅር፣ወጣትነትና መንፈሳዊነት

ብዙ ወጣቶች በጋራ የሚያውቋቸው ዘወተር የሚነጋገሩባቸው ሕይወታቸውን እስከመለወጥ የሚደርሱባቸው ብዙ ነገሮች አሉ። ከእንዚህ ነገሮች መካከል ከተቃራኒ ጾታ ጋር ያላቸው ግንኙነት አንዱ ነው ።ይህ በእድሚያቸውና በተፈጥሮአዊ ለውጣቸው ምክንያት የሚመጣ ጠባይ በመሆኑ ወጣቶቹ መንፈሳውያን ሆኑም አልሆኑ የዚህ ነገር ተጋሪዎች ናቸው ።ለአቅመ ሔዋንና ለአቅመ ዓዳም ከደረሱበት ጊዜ አንስቶ አስተሳስባቸውና አመለካከታቸው ፣በትምህርት ቤትም ሆነ በሥራ ከሚያገኟቸው በጾታ ተቃራኒዎቻቸው ከሆኑት ጋር ያላቸው ጉድኝት እንደ ሕፃንነቱ ወቅት አይሆንም ።ራሳቸውን ይመረምራሉ።እነርሱ ስላልደረሱበት ነገር ለማወቅ ያላቸው ጉጉት ይጨምራል።በሚያነቧቸው መጽሔቶች፣ ጋዜጦች፣ መጽሐፍት፤በሚመለከቷቸው ፊልሞችና ድራማዎች በየመንገዶች ከሚያዩዋቸው ነገሮች በመነሳት እነርሱም ያንን የሚያደርጉበትን ቀን ይናፍቃሉ ።ይህ ናፍቆትና ፍላጎትም ያድግና በተግባር ይተረጎማል።በዚህም መክን ያት የብዙ ወጣቶች ሕይዎት ሊበላሽ ይችላል።

በሃገራችንም ሆነ በየሰንበት ትምህርት ቤቶቻችን ወጣቶች ከተቃራኒዎች ጋር ሊኖራቸው ስለሚገባው ግንኙነት ለማወቅ የሚችሉባቸው አጋጣሚዎች ብዙ የሉም።በግልፅ ሊያውቋቸው የሚገቡ  ነገሮች በነውርነት ተሸፍነው ስለሚታለፉ ኋላ ለወጣቶቹ ሕይወት እንቅፋት ይሆናሉ።እስከ ጋብቻቸው እለት ድረስ ራሳቸውን ጠብቀው ለመቆየት ፣ከጋብቻ በፊት በሚፈጸሙ ግንኝነቶች ላለመሰናከል ማወቅ የሚገቧቸውን ቁምነግሮች ባለመረዳታቸው ይጎዳሉ።አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ከሆነ ብዙ ወጣቶች ቅድመ ጋብቻ በሚፈጠሩ የግብረ ሥጋ ግንኝነቶች የሚመላለሱ ናቸው ።በዚህም ምክንያት የሚከሰቱ የተለያዩ እክሎች አሉ።በበሽታ መጠቃት፣የላጊዜና ያለ ዕድሜ ማርገዝ፣ያለጊዜ የተረገዘውን ጽንስ ማሰወረድ ፣ለማስወረድ በሚደረግ ሙከራም ሕይወትን ማጣት፣ከትምህርትና ከሥራ መስተጓጎል፤ከዚህ ሁሉ ነገር በኋላም በመነፈስ ጭንቀት መሰቃየት የጥፋተኝነት ስሜት መሰማት፣ወዘተ...  ሊጠቀሱ የሚችሉ ነገሮች ናቸው።

Sunday, October 23, 2016

ሦስት ዓመት ከመንፈቅ

ይህ ዘመን እመቤታችን ከኢየሩሳሌም ውጪ የኖረችበት ዘመን ነው ፤ጌታ በተወለደ በሁለት ዓመቱ ሰብአ ሰገል በመጡበት ወራት ከሄሮድስ ቁጣ የተነሳ ድንግል ከነ ልጇ በከተማ መቀመጥ አልቻለችም።ሰይጣን የሰው ልጆችን የመዳን ስራ ሲጀምር ሲመለከት ዝም አላለም፤ገና ይወርዳል፣ይወለዳል፣ሲባል ትንቢቱን  በመስማቱ እነ ኢሳይያስን  በመጋዝ አስተርትሮ ፣በኩላብ አሰቅሎ አስገድሎ ነበር። ሲወለድም የተወለደውን ሕጻን ማሳደድ ጀመረ። በተለይም ሊወለድ ሃያ አምስት ቀን ሲቀረው  መላእክት የሚወለድበትን ስፍራ ቤተልሔምን ተገተው ይጠብቁ ነበርና አጋንንት በጣኦታት አድረው መመለክ ስለተሳናቸው ጣኦታቱም ወድቀው ወድቀው በማለቃቸው ይህንን ምልክት አድርጎ ዲያብሎስ አዳኝነቱን ጀመረ።

የአባቶቻችን አዳኝ እርሱ በእመ አምላክም ላይ ከሰው እስከ አጋንንት የክፋት ሰራዊቶችን አስከትሎ ለሰልፍ ተነሳ ። አስቀድሞ በመጽሐፍ ለዚች ቀን የተነገረው የመጀመሪያው ትንቢታዊ ቃል በዚህ ጊዜ ተፈጸመ። "በአንቺና በሴቲቱ በካከል በዘርሽና በዘሯም ላይ ጠላትነትን አደርጋለሁ" ይህ ቃል በገነት ውስጥ ከተነገሩ የወደፊት የሰው ህይወት ጠቋሚ ቃላት አንዱ ሲሆን እመቤታችንና "የቀደመው እባብ" ተብሎ በሚጠራው ጥንተ ጠላታችን በሰራዊተ አጋንንት እና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መካከል የሚደርገውን ጦርነት የሚያመላክት ቃል ነው ።

Thursday, October 06, 2016

ጾመ ጽጌ

ጽጌ ጾም በቤተክርስቲያናችን ከመስከረም 26 እስከ ህዳር 5 ያሉ አርባ ቀናት ዘመነ ጽጌ (ወርሃ ጽጌ) እንደሚባሉ ይታወቃል። የቤተክርስቲያናችን የሥርዓት መድብል የሆነው ፍትሐ ነገስት ጾምን እንዲህ ይተረጉመዋል ። “ጾምስ በታወቀው ዕለት ፣በታወቀው ሰዓት ሰው ከምግብ የሚከለከለው መከልከል ነው። ይህም ኃጢአቱን ለማስተስረይ ዋጋውን ለማብዛት እርሱ ወዶ ህግን ለሰራለት  እየታዘዘ፤ የፈቲውን ኃይል ያደክም ዘንድ፤ ሥጋም ለነባቢት ነፍሥ ትታዘዝ ዘንድ ነው” /ፍት.ነገ.ፍት.መን.አንቀጽ 15፥564/። 

ጾም ከመንፈሳዊ ተጋድሎዎች አንዱ ነው። ለፈቃደ ሥጋም  መንፈሳዊ ልጓም ነው። ሰው ፈቃደ  ሥጋን እየገታ ነፍሱን  የሚያለመልምበት ስንቅ ነው። “ጾም ቁስለ ነፍስን የምፈውስ ፣ ኃይለ  ፍተዎትንም የምታደክም ፣ የበጎ ምግባራት ሁሉ መጀመሪያ ፣ጸጋ እግዚአብሔርን የምታሰጥ፣የጽሙዳን ክብራቸው ፣የድንግልና የንጽሕና ጌጣቸው መገለጫቸው ፣የጸሎት ምክንያት/እናት/ የእንባ መገኛ ምንጭ፣አርምሞን የምታስተምር፣ለበጎ ሥራ ሁሉ የምታነቃቃ ፣ሰውነትን በእግዚአብሔር ፊት በማዋረድ ትኅትናን ገንዘብ ለማድረግ የምትረዳ መድኃኒተ ነፍስ ናት።/ማር ይስሐቅ አንቀጽ 4 ምዕራፍ 6/

የጾም ዓይነቶች 
ጾም በዓይነቱ በሁለት ሊከፈል ይችላል:የአዋጅና የግል። የአዋጅ ጾም በይፋ ለህዝቡ ተነግሮ በአንድነት የሚጾም የትዕዛዝና የህግ ጾም ነው። በሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት መሰረት ሁሉም እንዲጾማቸው መጀመሪያቸውና መጨረሻቸው ተቀምሮ፣ጊዜና ወቅት ተወስኖላቸው የተደነገጉ ሰባት የአዋጅ/የሕግ/ ዓጽዋማት አሉ። እነዚህም ዐብይ ጾም /ጾመ ዐርባ /፣ ጾመ ሐዋርያት /የሰኔ ጾም/፣ ጾመ ፍልሰታ /ጾመ ማርያም/፣ ጾመ ነቢያት/የገና ጾም/፣ጾመ ድራረ ጥምቀት /ገሃድ ወይም ጋድ/፣ ጾመ ሰብአ ነነዌ፣ ጾመ ድኅነት/የረቡዕና ዓርብ ጾም/ ናቸው። ጾም እንዲህ ወራት ተወስኖለት በቁጥር የተወሰነ  በጊዜ የተገደበ ይሁን እንጂ የዘለዓለም ህይወትን ለመውረስ የሚረዳን የጽድቅ መሰረት ፣የገነት በር፣ በአጠቃላይ  የክርስቲያኖች ኑሮ  ስለሆነ ከተዘረዘሩት የህግ አጽዋማት በላይ ከዓመት እስከ ዓመት የሚጾሙ በገዳም ፣በበረሃ ያሉ መነኩሳትና ባሕታውያን አሉ። “ስለ ጽድቅ የሚራቡና የሚጠሙም ብጹዓን ናቸው ፤እነርሱ ይጠግባሉና  እዳለ ።/ማቴ 5፥6፣ኢሳ 41፥55/።

Monday, September 26, 2016

የነጋበት ማምሸት

እውነትን ተናግሮ የመሸበት ማደር፣
መባሉን ሰምተናል ትውፊቱ ሲነገር።
ዛሬ ጊዜው ከፍቶ ስንታይ የጎሪጥ፣
እውነቱን ተናግሮ አይረባም መጋፈጥ።
የመሸበት ማደር  ቀርቷል ትላንትና፣
እውነት ተናጋሪን ማን ያስመሸውና።
እንዲህ ሁኗል ዛሬ ተረቱ ሲለወጥ፣
እውነት የሚናገር እንዳወራ ያምልጥ።

ምንጭ ሀሞት የግጥም ስብስብ 
በኄኖክ ስጦታው

Sunday, September 25, 2016

ቁጩ !

ሴት አያቴ "ቲቪ ክፈትልኝ" ለማለት "ቲቢውን አብራው" ትለኛለች ። የኢቲቪን አማርኛ ልዋስና አንዳንድ ጥርሶች ስለጎደሏት ብቻ አይመስለኝም ቲቪን "ቲቢ" የምትለው። ኢትቪ ሲከፈት ሳሏ ስለሚነሳባትም ጭምር ነው። ኢቲቪ ሳምባዋን ሳይነካው አለቀረም። ሴት አያቴ ከጎረቤት ጋር ቡና እየጠጣች አጫዋቾቿ የማይመስል ነገር ካወሩም በተመሳሳይ መልኩ ሳሏ ይነሳባታል። መቼ ለታ እትዬ ዘነቡ የተባሉ ጎረቤቷ  ቀበሌ ተሰብስበው ከመጡ በኋላ በረካ ላይ ደርሰው ቡና እየጠጡ "ሰምተሻል ኢትዮጵያ ልትመነደግ ነው..."ብለው ወሬ ሲጀምሩ አያቴ ሳሏ ተነስቶባት "ትን" ብሏት ለጥቂት አላህ አተረፋት።

ኢቲቪ በሴት አያቴ ሳንባ ላይ ብቻ ሳይሆን በወንድ አያቴ ጨጓራ ላይም ቀላል የመቁሰል አደጋን አስከትሏል። ወንድ አያቴ ባሩድ በደረቱ የሚመክት አርበኛ ነበር ። ችግሩ ምንም እድሜ ቢጫነው ኢቲቪ ካላየሁ ብሎ ችክ ይላል። "ጋሼ ቲቪ ምን ይሰራልሃል ቁርዓን የምትቀራበትን ዓይንህን በከንቱ አታድክም ፤ይቅርብህ" ስለው  "ተው ልጄ እንደሱ አይባልም! ጥልያን ደፍራን ቢሆንስ  በምን እናውቃለን? አገር ነቅቶ መጠበቅ ነው እንጅ"  ይላል። ኢቲቪ ካላየ አገር የተወረረ ይመስለዋል። በቲቪ ውስጥ አገር ከሚጠብቅ ወለወል ላይ  ቤት  ቢሰራ ይሻለው ነበር ። ሆኖም በደከመ ዓይኑ ዘወትር የሚያየው ቴሌቪዥን የረባ ነገር ሊያሳየው ስላልቻለ ለጨጓራ ህመም ተዳረገ። እንዲያም ሆኖ ከዛሬ ነገ በቲቪው ውስጥ የረባ ያገር ጉዳይ አያለሁ በሚል የሞጨሞጨ ዓይኑን ቲቢ መስኮት ላይ ተክሎ ያድራል። ኢቲቪ በበኩል "አንዳንድ የወልውልና የቆቦ ነዋሪዎች ጠግበው ማደራቸውንና መጸዳጃ ቤት መጠቀም መጀመራቸውን ገለጡ" እያለ  ልማትን ከማወጅ ውጭ ሌላ ለወንድ አያቴ የሚሆን ጨዋታ አላውቅ አለ።

Saturday, September 24, 2016

ዓይን


ዓይን የሰውነት መብራት ናት።እንግዲህ ዓይንህ ጤነኛ ብትሆን ሰውነትህ ሁሉ ብሩህ ይሆናል። ዓይንህ ግን ታማሚ ብትሆን ሰውነትህ ሁሉ የጨለመ ይሆናል።

The eye is the window of our body !.

at the end of ophthalmology course.

Monday, August 29, 2016

አሸባሪው ማነው?

በቀይዋ ብዕሬ የከተብኩት ሁሉ፣
አንዴ ከኔ ወጥቷል እስኪ ተቀበሉ።
እውነትን ሊናገር አፉን የከፈተ፣
ንቅዘቶችን ነቅሶ ድክመትን ያተተ፤
በዚች ጉስቁል አገር ምሳር በበዛበት፤
በሚቀጥለው ቀን ለእርሱ ወዬውለት!!
ለምን!?
ፈራጅ ነው ዘራፊ፤ ተዘራፊው ሌባ፤
ትችት ያሳስራል፤በማሸበር ደባ።
የታል!?
"ነፃ አውጪው" የት አል!?
ሆኗል ጨቋኝ መሪ
"ለምን" ባይን ፈራጅ፤"በሽብር ፈጣሪ"፤
ደፍሮ የሚናገር ዘብጥያ ታሳሪ።
ማነው!?
ፀረ-ሰላም ማንነው!? ማነውስ ነፃ አውጪ!?
አሸባሪ ማነው!? ማንኛው ነው ቀጪ!?
ወንጀለኛ ማን ነው!? ማነውስ ታሳሪ!?
ፀረ-ሰላም ከሳሽ! እራሱ መስካሪ
"ለምን"ባይ ተከሳሽ ላገር ተቆርቋሪ
!!
ምንጭ፦ሀሞት የግጥም ስብስብ
በኄኖክ ስጦታው

Tuesday, August 23, 2016

ሐርሞኒ

"ሐርሞኒ" የሚለው ቃል ጥሬ ትርጉሙ "ለተሻለ ውጤት ተጣጥሞ መገኘት" የሚል ይሆናል።ሐርሞኒ የነገሮች ሞገዳዊ ንዝረት (vibration)ተጣጥሞ የመፍሰስን ወይም ደግሞ የመጓዝን ዘይቤ የሚያመለክት ፊዚክሳዊ የተፈጥሮ ህግ ነው።አንድ ሙዚቀኛ አሪፍ ቃና ያለው ዘፈን ለማስማት የድምፅ አወጣጡን ከመሳሪያው ቅንብር ጋር ማስማማት ይጠበቅበታል። እንዲሁም አንድ ዳንሰኛ ከሙዚቃው ጋር በህብረት ካልደነሰ በስተቀረ ሳቢነት አይኖረውም። ሐርሞኒ ማለት እንግዲህ መጣጣም፣ቅኝት፣ግጥም፣መስማማት የሚለውን ትርጓሜ ይይዛል። ሁሉም ነገር ከኢነርጂ የተሰራ እንደመሆኑ መጠን የሚወክልበት ንዝረታዊ ሞገድ አለው።

የሐርሞኒ ጉዳይ የሞገድ ጉዳይ ነው። ሁለት የተለያዩ ሞገዶች ተመሳሳይ የአቅጣጫና የንዝረት ሞገድ ባላቸው ቁጥር የበለጠ ተጣጥመው ይፈሳሉ። ይህ መሰሉ የሞገዶች መጣጣም (in phase)በመባል ይጠራል። እንዲሁም ሞገዶቹ የተለያየ የአቅጣጫ ፍሰት ካላቸው (out of phase)በመባል ይጠራሉ።ሞገዶቹ በመጀመሪያው የሞገድ ጥምረት ውስጥ በሚሆኑበት ጊዜ እርስ በርስ የመደመር እና የመድመቅ ባህርይ ያላቸው ሲሆን በአንፃሩ ደግሞ በተቃራኒ አቅጣጫ በሚሆኑበት ጊዜ እርስ በእርስ የመጠፋፋት ባህርይን ይላበሳሉ።ለምሳሌ አንድን የሬድዮ ጣቢያ ድምፅ "ጃም" በማድረግ ድምፁ እንዳይሰማ ልናደርገው የምንችለው ድምፁ ከሚተላለፍበት የድምይዝ ሞገድ በተቃራኒ የሚፈስ ሞገድ በመልቀቅ ነው ።የትኛውም ነገር በሞገድ የሚገለፅ ነው ።ምናልባት የሞገዱ መጠን ሊያንስ ወይም ሊበዛ ግን ይችላል።ሐርሞኒም ይህን መሰል የተፈጥሮ ህግ የሚያንፀባርቅ ህግ ነው።

Monday, August 08, 2016

ፍልሰታ

 ፍልሰታ ማለት ፈለሰ ከሚለው የግእዝ ቃል የተገኘ ሲሆን ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ማዛወር የነበሩበትን ሀገር ለቆ ወደ ሌላ ሀገር መሰደድ መፍለስ ማለት ነው፡፡ ጾመ ፍልሰታ ሲባልም የእመቤታችን ሥጋ ከጌቴሰማኒ ወደ ገነት መፍለስን በኋላም በገነት በእፀ ሕይወት ሥር ከነበረበት መነሣቱን ለማመልከት የሚነገር ነው፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም 64 ዓመት በዚህ ዓለም ኖራ በሞት ከተለየች በኋላ እንደ አንድ ልጅዋ ሞታ መነሣቷንና እርገቷን ያዩ ዘንድ ሐዋርያት ከነሐሴ 1 እስከ 16 የጾሙት ጾም ነው፡፡ ጾመ ፍልሰታ ከሰባቱ አበይት አጽዋማት አንዱ ሆኖ በቀኖና እንዲጾም ከተወሰነበት ጊዜ ጀምሮ ምእመናን ይጾሙታል፡፡

እመቤታችን በ5485 ዓ.ዓ ከአባቷ ከኢያቄም ከእናቷ ከሐና “እም ሊባኖስ ትወጽእ መርዓት፡፡ ከሊባኖስ ሙሽራ ትወጣለች” ተብሎ በተነገረው መሠረት ነሐሴ 7 ቀን ተጸነሰች፡፡ ግንቦት አንድ ቀን ሊባኖስ በምትባል ወረዳ በብጽዓት እንደተወለደች የቤተክርስቲያን ታሪክ በሰፊው ያስረዳል፡፡ በጾም በጸሎት በአስተብቁኦት የተገኘች ናት፡፡ ንጽሕት በመሆኗም ማኅደረ እግዚአብሔር ሆናለች፡፡እመቤታችን ከእናትና ከአባቷ ዘንድ ሦስት ዓመት፣ በቤተ መቅደስ 12 ዓመት፣ ከልጅዋ ከወዳጅዋ ከኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ 33 ዓመት ከሦስት ወር፣ ከዮሐንስ ወልደ ነጐድጓድ ዘንድ 14 ዓመት ከዘጠኝ ወር ጠቅላላ ድምር 64 ዓመት ሲሆናት ጥር 21 ቀን በ49 ዓመተ ምሕረት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይታለች፡፡

Friday, August 05, 2016

ቤትህን አስተካክል

በእጅህ ያኖርኩትን የብርሃን ፀዳል መቅረዙን
                  ከስፍራው መጥቼ ሳልወስደው፣
ከዝናም በኋላ ደመናት ሳይሸሹ ፀሐይ
              ሳትጨልም ቀኑን ሳልጋርደው፣
ከማሳው ያለውን ፍሬ አልባ ዘርህን ማለዳ
            መጥቼ ከእርሻው ላይ ሳልነቅለው፣
የሰጠሁህን ሀብት ከመዳፍ ከጉያህ በአንድ
          ጀምበር እድሜ አውጥቼ ሳልጥለው፣
እፍ ያልኩበትን ነፍስ ከውስጥህ ለይቼ
         ወደነበረበት ስፍራ ሳልመልሰው፣
አእምሮ አለህና ነቅተህ ተዘጋጅተህ አደራህን 
                    ፈጽም አስተውል አንተ ሰው።
ከምን ላይ እንደቆምክ በየት ስፍራ እንዳለህ
                        ሕሊናህን መርምር፣
ድንገት ጥሎህ ሳይሔድ ሳይከዳህ ሳይተውህ
                        የቆምክበት ምድር።
ቤትህን አስተካክል የፍቅር አንድነት መሠረት
                        የለውም ጥላቻ ተሞልቷል፣
ውስጡ ተቦርቡሮ ምሰሶው ተሰብሮ ጣሪያው
                     ተነቃቅሎ ውጪው ብቻ ቀርቷል።
እርም አለ በእጅህ ላይ እርምህን ሳትጥል 
          አይጸዳም አይቆምም የቤትህ መሠረት፣
በከንቱ እንዳትጥለው የደከምክበትን የአባትህን
                              ርስት የያዝከውን እምነት።
ይለናል እግዚአብሔር ለኔም ለአንተም
                   ለአንቺም ቃሉን እያሰማ፣
ልብ ያለው ልብ ይበል የአዋጅ ቃል ተነግሯል
                                   በአገር በከተማ።
ማነው እጀ ንጹሕ ባሕር ከፍሎ የሚወስድ
                                ሕዝብን የሚያሻግር?
ሃይማኖት ካለባት ከሐገረ እግዚአብሔር
                            ከቃል ኪዳን ምድር።
ማነው የታረቀ ቀድሞ ከእራሱ ጋር አብሮት
                       ከሚኖረው ከሕሊናው ጋራ፣
ከግቡ የሚያደርስ ታሪክ የሚሠራ ከሕዝብ
                          የሚቀበል ይኼንን አደራ።
የማን ቃል ይሰማ ማን ነው የሚነግረን ማንን
                                               እንመልከት፣
መብራቱ ሳይጠፋ ዘይቱን ሳንጨርስ ሳያልቅብን
                                                    ድንገት።
ደረስ ከተፍ ሲል ሙሽራው ሲመጣ ሁሉንም
                          ከእጃችን አራግፈን ጨርሰን፣
ማን ይከፍትልናል ብንጮህ ብናለቅስ በሩን
                    ብናንኳኳ ከደጃፍ ላይ ቆመን።
ለተተኪው ትውልድ ያዘነው ሰው ማነው፣
ከአባቱ ከእናቱ ምንድን ነው የሚወርሰው?
አንቺ እናት ለልጅሽ ምን አዘጋጅተሻል?
የሚጠይቅ ትውልድ መኖሩን አውቀሻል።
መልስ ይዘህ እንደሆን አንተ አባት ተናገር፣
ልጅህ ሲጠይቅህ የአንድነትን ነገር።
ማነኝ ከየት መጣሁ ምንድን ነው እምነቴ፣
የሚል ሕፃን አለን በቤትህ በቤቴ።
አሁን ነው ማስተዋል ምን እያረግን ነው?
ተተኪውን ትውልድ ማነው ያስተዋለው?
የሁላችን ድካም የሁላችን ጥረት፣
ዛሬ ማቃናት ነው የነገውን ሕይወት።
ሁሉ ሰው ሲኖረው ተከታይ ሲያፈራ፣
ዙሪያውን ሲከበው በዘራው አዝመራ፣
መልካም ነው ግሩም ነው ብሎ ሲገፋበት፣
ማነው ያስተዋለው የጥንቱን አንድነት?
ጎዳናው ሲያጓጉዝ ሲያራምድ አይተነው፣
ባሰበበት ስፍራ ሁሉንም ሲያደርሰው፣
ጊዜያዊውን ድንኳን ቋሚ ቤት አርገነው፣
እኛ እንዲህ ነን እያልን ለሰው ስናሳየው፣
ስንቱ ግራ ገባው ምስኪን ወገናችን፣
ትቶን ገደል ገባ ወጣና ከእጃችን።
ምን ቃል ተናግረነው በምን ቃል ይመለስ፣
ልዩነት መናናቅ ሞልቶት የእኛን መንፈስ።
እስኪ መልሱልኝ መልስ አይጠፋም ከሰው፣
ደርሶ ከትውልዱ ማነው ያስተዋለው?
እኛው አምጥተነው ከእኛው ቃል ተምሮ፣
የአምናው መለያየት ሲቀጥል ዘንድሮ፣
የተሻለ ነገር ሲጠፋ ከእጃችን፣
ስንቱ ዳግም ሔደ እያየን በዓይናችን።
የሥጋ ሥራ ነው ይብቃን መለያየት፣
ታሪክ ለመለወጥ እንቁም በአንድነት።
ይኽን ዘረኝነት ከቤት ካላስወጣን፣
የአጵሎስ የጳውሎስ ነን ከሚል ቃል ካልጸዳን፣
ውሸት ነው አይሆንም ከእግዚአብሔር ጋር ኑሮ
አንዱን አንዱ ንቆት ሰው በጸብ ተሳስሮ።
ዛሬም አሮጌ ልብስ ምነው ማጥለቃችን፣
ሁልጊዜ ድህነት ሀብት እያለ እጃችን።
ክርስቶስ የሰጠን ውድ የተወደደ፣
አዲሱ ልብሳችን የታል ወዴት ሔደ?
የሞተልን አምላክ ስላረገው ነገር፣
የዓለም መድኃኒት ነው ብለን ስንናገር፣
እንዲህ በእግዚአብሔር ቤት በዓሉ ሲከበር፣
አሮጌ ልብሳችን ምነው አይቀየር?
ክፋት እና ጥፋት በደል መተላለፍ፣
ለጎሣ እና ለዘር ለነገድ መሰለፍ፣
ሥርዓት ማበላሸት መሠረትን ማፍረስ
ደርሶ ክፉ መሥራት እውነትን ማደፍረስ፣
ቂም በቀል ጥላቻ ጥልና ክርክር፣
አሮጌ ልብስ ነው አይጠቅመንም ይቅር።
ርኅራኄ ትሕትና ሰላም እና ፍቅር፣
ትዕግሥትና አንድነት ደስታ መልካም ግብር፣
ሊለበስ ግድ ይላል በሰውነታችን፣
ክርስቶስ የሰጠን አዲሱ ልብሳችን።
አንድነት ሲሰበክ እኛ ስንስማማ፣
ብርሃን ይሆናል የዛሬው ጨለማ።
በአንድ ገበታ ላይ የቆረስን ሰዎች፣
ለምን ተፈራራን አባት እና ልጆች?
ጨርሶ ሲዘጋጅ ኖኅ መርከቡን ሠርቶ፣
ትውልድን ለማትረፍ ከእግዚአብሔርቃል ሰምቶ
ጥንድ ጥንድ አድርጎ አእዋፍ እንስሳቱን፣
ማነው ያመጣለት ከጫካ አራዊቱን?
አንበሳ እንዴት ሰማ ነብርን ማን ነገረው?
ከጓደኛው ጋራ መንገድ የጀመረው።
ርግብ እንዴት መጣች ቁራው ከማን ሰማ፣
ለማምለጥ የቻለው ድቅድቁን ጨለማ።
ሰውስ ከኖኅ ሰማ የአባት ቃል ሲናገር፣
ድንቅ የሆነው ምሥጢር የእንስሳቱ ነገር።
እንደምን ተረዱ እንዴት ነው የምናምን፣
ትውልዱ እንደሚተርፍ መርከቡ እንደሚያድን።
በምድር የሚሳበው በአየር የሚበረው፣
በበረት የሚያድር በጫካ የሚኖረው፣
ኖኅና መርከቡን በሩቅ ተመልክተው፣
ከቁጣ አመለጡ ተሸሸጉ ገብተው።
እግዚአብሔር ለሁሉም በቋንቋቸው ነግረህ፣
ኖኅና መርከቡን ያሳየህ አንተ ነህ።
ወደ እኛ እንመለስ የት ነን የት ቆመናል፣
ስንት መርከብና ስንት ኖኅ አይተናል?
አንድ መርከብ አለች አንድ ኖኅ ያለባት፣
እርሷን እንከተል ግብ መድረሻችን ናት።
ከእንስሳት የምንበልጥ የሰው ልጅ ተብለን፣
እንዴት በአንድ መርከብ መሰብሰብ ከበደን?
እናንት ሰባክያን ወንጌል የያዛችሁ፣
ካህናት ሊቃውንት ዕውቀት የበዛችሁ፣
ደግሞም መዘምራን ቃል የተሞላችሁ፣
በአንድነት ተነሡ ለአንድነት ብላችሁ።
በዐውደ ምሕረት ቆሞ ዘማሪው ሲዘምር፣
የሥነ - ጽሑፍ ሰው ቅኔ ሲደረድር፣
ከጫፍ ጫፍ ይሰማ ያስተጋባ ቃሉ፣
ለዓለም እንዲሰበክ የጌታ ወንጌሉ።
ገና ነው ኮረብታው አልተደለደለም፣
ሸለቆው አልሞላም ተራራ አልተናደም።
እናንተ መምህራን ደግሞም ካህናቱ፣
አደራ አለባችሁ ከፊት ይልቅ በርቱ።
አሁንም ሊሰበክ ይገባዋል ቃሉ፣
ወንጌልን ባንሰብክ ወየውልን በሉ።
ሌላ ሙሴ አይመጣም ባሕር የሚከፍል፣
በሰው የሚወደድ ቃል የሚያደላድል።
ወንጌል የተሰጠው ቃልን እንዲናገር፣
ሌላ ጴጥሮስ ማነው ከእናንተ በስተቀር?
በተለየ ፍቅሩ እንዲያ የወደደን፣
በግልገል በጠቦት በበግ የመሰለን፣
እንዳንጠፋበት ነው ተኩላው እንዳይነጥቀን፣
እያስጠነቀቀው ለጴጥሮስ የሰጠን።
የአደራ ልጆች ነን እኛ ምእመናን፣
አደራ አለባችሁ በክርስቶስ ሥልጣን።
ሰብካችሁ አንድ አርጉን ይኼ ነው ሙሴነት፣
ሌላ ቃል የሚሰብክ ማንን እንመልከት?
ከእናንተ ጋራ ነው ዛሬም ለዘላለም፣
ክህነት የሰጣችሁ አምላክ መድኃኔዓለም።
የምድሩ ቀላል ነው ይቺማ ምን አላት፣
ወንጌል በእጃችሁ ነው ገነት ለማስገባት።
ይኽን ያህል ሥልጣን ኃይል ነው ያላችሁ፣
ዳግም ያስተጋባ ይሰማ ቃላችሁ።
አንተም አንቺም እኔም በዚህ ቤት ያለነው፣
ስለ ቅድስት እምነት ወንጌል የተማርነው።
በአንድነት ከመቆም የሚያግደን የለም፣
የአደራ ልጆች ነን የመድኃኔዓለም
የአደራ ልጆች ነን የመድኃኔዓለም።

አብርሃም ሰሎሞን ጥቅምት 2003 ዓ.ም. 

Saturday, July 23, 2016

አበጀ በለው(2)

የእግዚአብሔር ዳኝነት የእግዚአብሔር እውነት፣
የሚጠበቅበት የድሆቹ መብት፣
እጅና እግሩን ታስሮ በግፍ ሰንሰለት፣
ያለ አንድ ጠበቃ ያለ አንድ ረዳት፣
ፍርድ ለመቀበል ቀርቦ ፍርድ ቤት፣
በቀማኞችና በሌቦች ችሎት፣
ይሙት በቃ ብለው ሁሉም በአንድነት፣
የአመፅ ፍርድ ፈርደው ገድለው ሲቀብሩት፤
ይህን ግፍ አዬና አበጀም አስተውሎ፣
በጦር እንደወጉት ልቡ ባዘን ቆስሎ፣
መንፈሱ በቁጣ እንደ እሣት ተቃጥሎ፣
የእውነትን ደመኞች ለመበቀል ብሎ፣
ወረደ በረሃ ቤት ንብረቱን ጥሎ።
ዳኞች ዳኝነትን ከቀበሩት ገድለው፣
የእግዜርን አደራ እምነቱን አጉድለው፣
የሰጠናቸውን ስልጣን ተከልለው፣
እኛኑ ሲያጠቁን ጠባቂዎች መስለው፣
መቀማት ሲመርጡ  መጠበቁን ጥለው፣
ካሾች እኛ ስንሆን እነሱ በድለው፣
አርደው ሲጨርሱን አንድ በአንድ አናጥለው፣
እንደ ቧዘዘ ከብት ጠባቂ እንደሌለው፣
ለመብት ሲከላከል ሊሞት እንደማለው፣
እንደ ቆራጡ ወንድ እንደ አበጀ በለው፣
እኛስ ለመብታችን የማንታገለው ፣
ከጅልነት በቀር ምን ምክንያት አለው?
የመበታችን ፋና የአርነትን ጮራ፣
የሚለይበትን ሰው ከእንስሳ ተራ ፣
ከፍ አድርጎ ይዞ ሲሄድ እያበራ፣
በነሴ በረሃ በጎንቻ ተራራ፣
ግፈኞች ከበውት ከቀኝ ከግራ፣
ቀን ከሌት ሲያድኑት ወንጀል እንደ ሰራ፣
ለምቾቱ አያስብ ለህይወቱ አይፈራ፣
እንደ አምላክ ስለሰው ሲቀበል መከራ፣
መሄዳችን ላይቀር ነገ ስንጠራ፣
ወደ ማንቀርበት ወደ ሙታን ስፍራ፣
የበሉትን ቀጥቶ የጊዜን አደራ፣
የማይቀረውን ሞት መሞት ከእርሱ ጋራ፣
የሚያጸድቅ ነበር ወዲያው የሚያኮራ።

ምንጭ፦ፍቅር እስከ መቃብር 

Friday, July 08, 2016

ለጽጌረዳ (Y.F)

ሰላምና ጤና ደስታና ፍቅር ምን ጊዜም ቢሆን ካንቺ አይለዩ። የሰው ልጅ እስካሁን ድረስ  አንዱ ለሌላው ያለውን እውነተኛ ፍቅር ለመግለፅ ያልተጠቀመባቸው ቃላት ይኖራሉ ብየ አላስብም። ምርጥ፣ ወርቃማ፣ እንቁ የሆኑ ቃላትም ቢሆኑ ላንቺ ያለኝን ፍቅር በትክክልና ሙሉ በሙሉ የመግለፅ  አቅም የላቸውም። የፍቅር ታላቅነት ከምንምና ከማንም በላይ ነውና ፍቅር ከኃይሎች ሁሉ የሚበልጥ ኃያል ነውና። ፍቅር እውነት ነው፤እውነትም ፍቅር ነው፤ የሁለቱ ድምር ደግሞ አንቺው ነሽ። ላንቺ ያለኝን እውነተኛ ፍቅርና መልካም ምኞት መግለጫ አጥቼ ፈዝዤ ተቀምጬ መውደዴን ማፍቅሬን ለመግለፅ ወኔ ቢጠፋኝ ጉልበት ቢከዳኝ ፍቅርሽ ቢብስብኝ መንገድ ፈለጌ ማፍቀሬ እንዲገባሽ የተቻለኝን ሁሉ ለማድረግ ሞከርኩ። ነገር ግን ፍቅሬን ለመግለፅ የተጠቀምኩባቸው መንገዶች አላማቸውን መፈፀም ተሳናቸው። ፍቅሬን ከመግለፅ በተቃራኒው የጥላቻሽ አጋፋሪ ሆነው ተገኙ። 

የማወራሽ ተረት ተረት ወይም ልብ ወለድ አይደለም። ከአንጎለ ገቢር አፍልቄ፣ ላለፉት አራት ዓመታት በውስጤ ታምቆ ከኖረው የፍቅርሽ ወላፈን ጨምቄ፣ ከልቤ መዝገብ ፈልቅቄ፣ ያወጣሁት  ህያው እውነት ነው እንጅ። እኔ ላንቺ ያለኝን ፍቅር በምንና እንዴት አድርጌ ላስረዳሽ እንደምችል ባላውቅም ውሎየም አዳሬም  አንቺ ብቻ ስትሆኝብኝ ጭንቅ ጥብብ ሲለኝ ማደረገውን ሳጣ ይኸው ዛሬም ከዕድሜሽ ላይ ሁለት ወይም ሦስ ደቂቃ  ልወስድብሽ ጨከንኩ። መቼም ይህንን እንደማትነፍጊኝ ተስፋ አደርጋለሁ። እኔ እንኳን ከሃብት ሁሉ የምትበልጠውንና ማንም በገንዘብ ይገዛት ዘንድ የማይቻለውን ንጹህ ልቤን ሰጥቸሽ  አይደል? አንቺ ስጦታዬን ለመቀበል ፈቃደኛ ባትሆኝም ቅሉ። ሙሉ ማንነቴን ላንቺ ሰጥቼ ይኸው አራት ዓመት ሙሉ ተሰቃየሁልሽ እኮ። ለነገሩ ሰው የቤቱን ሀብት ሁሉ ስለፍቅር ቢሰጥ ያከብሩታል እንጅ በፍፁም አይንቁትም። ፍቅር ከሞት የበረታች ናትና፤ ቅንዐትም እንደ ሲኦል የጨከነች ናትና፤ ላንቃዋም እንደ እሣት ላንቃ እንደ ነበልባልም ነውና። 

Tuesday, July 05, 2016

የተቆለፈበት ቁልፍ!


ጫት፦ በእርግጥም ካለመስራት እኩል በትክክል አለመዝናናትና አለማረፍም የሰውን ጭንቅላት ምን ያክል እንደሚጎዳ  ብዙ ሰው ልብ የሚል አይመስልም።በመቃም ወይም ዘወትር በመጠጣት ለመዝናናት መሞከር ለአእምሮ ጤናን ሳይሆን ጫናን የሚፈጥር ሱስ እንደሚሆን ግልጽ ነው።ለምሳሌ ጫት  የሰውን አእምሮ አሰራር ሊያውኩና ሱስንም ሊፈጥሩ የሚችሉ ኬሚካሎች የያዘ ቅጠል ነው ።ካቲኖንና ካቲኖል የሚባሉ ንጥረ ነገሮችን  የሰውን ስሜትና መነሳሳት ከፍ በማድረግ ምርቃናን በመፍጠር በሱስ ከጠመዱ በኋላ ቃሚውን ካላገኘ መንቀሳቀስ የማይችል ትጥገኛ ማሽን ያደርገዋል።በሃራራና ምርቃና መካከልም እየዋዠቀ ቆይቶ በመጨረሻ ፍጻሜው ውድ የሆነ አዕምሮው ከጥቅም ውጭ ወደመሆን  ሲመጣ የጀዝባነትን ጎራ ይቀላልቀላል።ከዚህ በተጨማሪ በጫት የተፈጠረውን ምርቃና ለማገዝ ማጨስ የተልለመደ ሲሆን ያንን የናረ ስሜት ላምርገብ ደግሞ መጠጥ የግድ ይላል።ሌሎች መጠጥ የማያዘወትሩ ሰዎች ደግሞ የእንቅልፍ ክኒን አይነት መድሃኒቶች ሱስ ሳያስቡት ከጫቱ ጋር በተጣማጅ ይጠናወታቸዋል።ይሄ እንግዲህ በጥርስ፣ በጨጓራና በኪስ የሚፈጥረው በሽታ ሳይቆጠር መሆኑ ነው።

ሰዎች በሚቅሙበት ጊዜም የጊዜ ባቡር አፈጣጥኑ ስለሚቀየር በብዛት የሚቅሙ ሰዎች በዕድሚያቸው ላይ ቁሟር መጫወታቸው አይቀርም።እንኳን በጫት ታግዞ እንዲሁም ባህላችን የጊዜ ጸር ነው።በአንድ ወቅት በጥቂት የሃገሪቱ ክፍሎች ብቻ  ከሃይማኖታዊና ባህላዊ ወግ ጋር  ተመጥኖ ላገልግሎት ይውል የነበረው ጫት ዛሬ ከጥቂት የሃገሪቱ ክፍሎች በቀር ከዳር እስከዳር አካሎ ማየቱ አሳዛኝም አስፈሪም ነው።ከናዝሬት እስከ አዲስ አበባ ባለውም አስፋልት ዙሪያ ዘመናዊ ቃሚዎች መኪናቸውን ደርድረው እየቦዘኑ ሲዝናኑ ማየት ችግሩን ገና ፋሽን እንጂ ፍርሃርት እንዳልፈጠረ ያሳያል።ከባለስልጣን እስከ ነጋዴ ፣ ከምሁር እስከ ስራ አጥ፣ወንድና ሴት ሳይል በጫት አባዜ ተይዘው አለመቃም የሚያሳፍረበትና እንደሞኝ የሚያስቆጥርበት ጊዜ ላይ መድረሳችን ነበር ማሳፈር ያለበት።ቡናን የሚቀናቀን የውጭ ምንዛሬ አምጭ ተክል መሆኑ ከኮሎምቢያ ኮኬይንና ከ አፍጋኒስታን ሄሮይን የኛንስ ጫት ሕጋዊ ከመሆኑ በቀር ምን ይለየዋል?

Monday, June 27, 2016

ታማችኋል !!!

በአፍላ ትጀምራላችሁ በወረት ትተውታላችሁ። ያወቃችሁትን ትረሳላችሁ ያላወቃችሁትን ለማወቅ ትጥራላችሁ፤የያዛችሁትን ትረግጣላችሁ፤የረገጣችሁትን ትይዛላችሁ፤ምኞታችሁ ልክ የለውም፤አምሮታችሁ ብዙ ነው።የአማራችሁን ስታገኝ ወዲያው ይሰለቻችኋል።ተው የተባላችሁትን ትሽራላችሁ የተከለከላችሁትን ትደፍራላችሁ፤የተፈቀደላችሁን ችላ ትላላችሁ።ቤተመቅደስ እንዳትገቡ ብትከለከሉ ወደ ፊት ቤተመቅደሱን በመስታውት ሰራታችሁ ቤተመቅደስ ባትገቡም እንኳን ሁሉን ከወጭ ሆናችሁ ማየት ትፈልጋላችሁ።ሁሉንም ማወቅ ትፈልጋላችሁ በአንዱም ግን አትጠቀሙበትም።ሁሉም አላችሁ ግን ባዷችሁን ናችሁ።ሃይማኖት እንጅ እምነት የላችሁም።

መድሃኒት ባሳይህ መቀመሚያውን ነገሬህ ማርከሻውን ሳልገልጥልህ መጀመሪያውን ብቻ ሞጭልፈህ ትተኸኝ ትሄዳለህ።ጥበበን "ሀ ግእዝ "ብየ ላስተምርህ ብሞክር  መንደር ውስጥ በቃረምካት እውቀትህ ተመክተህ በመሰላቸት "ሆ ሳብዕ" ብለህ ቀድመህ ትዘጋዋለህ። የግል ታሪካችሁ ቢታይ ወጥነት የጎደለው ከዚህም ከዚያም የተልከፈከፈ የተማሪ ኮፈዳ ውስጥ ያለ እህል ይመስላል።ተምራችሁ እውቀት ስታገኙ ሰርታችሁ ገንዘብ ስታፈሩ ከላይ የሆናችሁበትን ሃገር ለቃችሁ "ሰፋ ወዳለው እንሂድ" ብላችሁ እንደገና ከታች ትጀምራላችሁ።ትቀጥላላችሁ በመጨረሻ ከጀመራችሁበት ትገኛላችሁ ።ቸኩላችሁ ትወስናላችሁ ወዲያው ትጸጸታላችሁ።በጽኑ ታማችኋል።

Wednesday, June 22, 2016

ኦርቶዶክሳዊ የቅዱሳት ሥዕላት አሣሣል

ቅዱሳት ሥዕላት "ቅዱስ" እና "ሥዕላት" ከሚሉት ቃላት የተገናኘ ወይም የተሰናሰለ ቃል ሲሆን፤ሥዕል በቁሙ፣ መለክ፣ የመልክ ጥላ፣ንድፍ፣አምሳል፣ንድፍ ውኃ፣በመጽሔት፣ በጥልፍ፣በስፌት ወይም በቀለም በወረቀት ገዝፎ ተጽፎ፤ከእብን ከእፅ ከማዕድን ታንጦ፡ተቀርጦ ተሸልሞ አጊጦ የሚታይ የሚዳሰስ ነገር ነው።(ኪ.ወ.ክ፡673) ሥዕል ነጠላ ሲሆን ሥዕላት ደግሞ ብዛትን ያመለክታል።ቅዱሳት የሚለው ቃል ደግሞ "ቀደሰ" ከሚለው የግእዝ ግሥ የተወሰደ ሲሆን ትርጉሙም  ለየ፣አከበረ፣መረጠ ማለት ነው።ከዚህ በመነሳት ቅዱሳት ሥዕላት ለእግዚአብሔር የተለዩ፣የተቀደሱ፣ ልዩ፣ ምርጥ፣ንጹህና ጽሩዕይ የሆኑ የቤተመቅደሱ መገልገያ ንዋያተ ቅድሳት በመሆናቸው ቅዱሳት ተብለው ይጠራሉ።

ዳግመኛም የቅዱሳንን ታሪክና ማንነት በጊዜው ላልነበርን በመንፈስ ዓይን ፤እንድናይ ስለሚያደርጉን፤አንድም ሥጋዊውን ዓለም ከሚያንጸባርቁ ዓለምውያን ሥዕላት ፈጽመው የተለዩ በመሆናቸው፤አንድም የቅዱሳኑ ቅድስና ሥዕላቱን ቅዱስ ስላሰኛቸው፤አንድም በሥዕላቱ አድሮ እግዚአብሔር ስለሚፈጽማቸው ገቢረ ተዓምራት የተነሳ ሥዕላቱ "ቅዱሳት ሥዕላት" ተብለው ይጠራሉ።በአጠቃላይ በኢትዮዽያ ኦርቶዶክስ ተውህዶ ቤተ ክርስቲያን "ቅዱሳት ሥዕላት" ተብለው የሚጠሩት የቅዱስ እግዚአብሔር፣ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ፣የቅዱሳን መላእክት፣የቅዱሳን ነቢያት፣የቅዱሳን ሐዋርያትና የሌሎች ቅዱሳን ጻድቃን ማንነት ሕይወትና ታሪክ የሚያሳዩ ሥዕሎች ናቸው።ቤተክርስቲያን ሐዋርያዊት እንደመሆኗ መጠን የምትፈጽማቸው አገልግሎቶችና ሥርዓቶች ዶግማና ቀኖናን እንዲሁም ትውፊትን መሰረት ያደረጉ ናቸው።ይህ ደግሞ ኦርቶዶክሳዊያን ቅዱሳት ሥዕላት በእግዚአብሔር ፈቃድ ሐዋርያዊ ቀኖናን ተከትለው የሚሳሉ የቤትክርስቲያን ንዋያተ ቅዱሳት ናቸው እንጂ እንዴው በዘፈቀደ የሚዘጋጁ የኪነጥበብ ስራወች አለመሆናቸውን ያስገነዝባል።

Monday, June 13, 2016

ዩኒቨርሲቲ መግባት፡ ምርምርና ሀልዎተ እግዚአብሔር

ተማሪ ወደ ከፍተኛ የትምርት ተቋም የሚሄድበት ዋና ዓላማው ጽንሰ ሃሳባዊውንና ተግብራዊውን የዕውቀት ውኃ ምንጭ ከሚሆነው ተቋሙ ለመቅዳትና ለሚጠበቅበት የነገ ኃላፊነት ማዋል እንደሆነ እሙን  ነው።በዩኒቨርሲቲ ቆይታውም ትምህርቱን ለመቀበልና ተመርቆ ለመውጣት ከሚያስችሉ ነገሮች አንዱ ለእውቀት የተዘጋጀ አእምሮ ይዞ መገኘቱ ነው።ይህ ለእውቀት የተዘጋጀ አእምሮው በእውቀት መጎልመስን ጨምሮ ለተለያዩ ጠቃሚ ምርምሮች፣የፈጠራ ስራዎች፣ አዳዲስ አስተሳስቦችና የችገር ምልከታዎች እንደሚያበቃ በሁሉም ማህበረሰብ ዘንድ ይታመናል።ሆኖም ይህ ለእውቀት የተዘጋጀ አእምሮው በራሱ በትምህርቱ ሂደትም ይሁን በዙሪያው ከበው በሚገኙ ተጽዕኖዎች የተነሳ በአሉታዊ መልክ ተቀርጾ ከመነሻው በተቃራኒ እንዲቆም ሲደረግ ይስተዋላል።በዙሪያው ከበው የሚገኙትን ተጽዕኖዎች የዛሬ ትኩረታችን ባለመሆናቸው በመተው በራሱ በትምህርቱ ሂደት ውስጥ የሚመጡትን ተያያዥ ተጽዕኖዎች ብቻ ለማንሳት እንሞክራለን።ይህም ዘመናዊ ትምህርትንና ሳይንሳዊ ምርምሮችን አዝለው የሚመጡት ሃይማኖት አልበኝነትና የግብረገብነት ችግሮች መንፈሳዊ ሰው እንዴት ማየትና ማለፍ አለበት እኛስ ምን ምን ቅድመ ዝግጅቶችን ማድረግ ይጠበቅብናል?፤ትምህርቶቹስ በራሳቸው ከሃይማኖት የሚያርቁ ናቸውን? የሚሉትን በተወሰነ መልኩ ለማየት እንሞክራለን።

Thursday, June 09, 2016

ጥበብ ያልተቀላቀለበት ትምህርት!

መምህሩ የመግቢያ ሰዓቱን ጠብቆ ከበር ብቅ ሲል የተማሪው መንፈስ ይዋከባል። ሁሉም ባለው ቶሎ የመጻፍ ችሎታ መምህሩ የተናገሩን ሀሳብ ለመያዝ አስቀድሞ ደብተሩን ወይም ወረቀቱን ገልጦ ብዕሩን ደቅኖ ይጠብቃል። መምህሩ ንባቤ ቃላቸውን ሲጀምሩ ቀና ብሎ ለመመልከት ፋታ ያለው ተማሪ አይገኝም። ጠቃሚውን መርጦ መጻፍ ያልተለመደ ነገር ነው። ሁሉንም ለቅልቆ መገኘት ለጥናት ባይጠቅምም ሙሉውን ጽፌዋለሁ በሚል መተማመን ሊመጣ የሚችለውን መደናገጥ ይቀንሳል። ግማሽ ሰዓት ሳይተኙ ተኝቸ ጊዜየን አባከንኩት በሚል ስሜት ባንኖ መነሳት፣የወረቀት ኮሽታ በተሰማ ቁጥር አጥንተው ነጥቡን ሰቀሉብኝ በሚል ሰቀቀን ተነስቶ ከወርቀት ጋር መፋጠጥ፣ከምግብ ጠረዼዛ ወደ መታጠቢያው  የሚወሰደውን የምግብ ሰሀን ይዞ ወደ ውጭ መውጣት፣በመንገድ ላይ እያሉ ድንገት ደብተርን መግለጥ ቋሚ ክስተቶች ናቸው።

የውጥርቱንና የነገሩ ትኩሳት የሚጨምሩት ደግሞ ስራቸውን በወቅቱ ማጠናቀቅ ያልቻሉ ወይም በማጣደፋቸው ተማሪን የበደሉ የማይመስላቸው ወይም ከሃላፊነት ይልቅ የግል ጥቅም አድልቶባቸው ጠፍተው የከረሙ መምህራን ናቸው።"ተጨማሪ ክፍለጊዜ ያስፈልገናል" በማለት በተማሪ መዋከብ የራሳቸውን ክብር የጨመሩ የሚመስላቸውም ጥቂት አይደሉም። ታዲያ ሴሚስተሩ ሲያልቅ እንደጠጠሩ ሳይብራሩ የሚያልፉትን ሃሳቦች ጠያቂ የላቸውም።የሚጠይቅም ካለ እንደ ጊዜ አባካኝ ይቆጠራል። ይህ አይነቱ ንዴት ተጨማምሮበት "ለምን ብዙ ክፍለጊዜ አቃጠሉብን?" በማለት ለመጠየቅ ደግሞ መምህሩ ለሚወስድበት እርምጃ የሚከራከርበት መንገድ የለውምና ይሰጋል። በተማሪዎችም ዘንድ በማያውቀው ውይይት ገብቶ እንደዘባረቀ ተናጋሪ ወይም  መምህሩን ተዳፋሪ ተቆጥሮ ይሳቅበታል።በአንፃሩ እንደ አዋቂ የሚቆጠረው መምህሩ ፈተና የሚያወጣበትን አካባቢና የፈተናውን አይነት አጠያይቆ ማወቅ የቻለ፣የሚቻለውን ሞክሮ ፈተናውን ከሚራባበትና በምስጢር ከሚቀመጥበት አስወጥቶ ማየት የቻለ ነው።

Sunday, May 15, 2016

ለአንቺ


ባህር ወደታች ምን ያህል ጥልቅ ነውዓለምስ ወደጎን ምን ያህል ይሰፋልፀሐይ ምን ያህል ትርቃለችከዋክብት ምንኛ ይበዛሉየሰው ልጅ ልቦና ምን ያህል ርቀት ይመሰጣልአእምሮው እስከየቱ ጥግ እስከምን አጥናፍ ድረስ ያስባልሁሉም ወሰን አለው። ሁሉም ዳር ድንበር ጥግ አለው።ምድር ምንም ፍጹም ነገርን እንደማታስተናግድ ትባላለች። ፍጽምና የለባትም ይባላል። ሁሉም ጎዶሎ እንደሆነ ይነገራል። ሁሉም ሙሉ ለመሆን አንዳች ሌላ ግብዓት ይሻል። ቀን ያለፀሐይ፤ ምሽት ያለ ጨረቃና ከዋክብት፤ ዝናብ ያለደመና፤ ደስታ ያለመከራ፤ ድል ያለውጊያ አይገኙም። ዓለም ራሷ ምኗም ሙሉ አይደለም። አንዱ ከአንዱ ጋር ይደጋገፋል።ትዕግስት ጠረፍ አለው፤ ጽናት ገደብ አለው፤ ሸክም ልክ አለው። የሰው ልጅ «ከዚህ በላይ አልችልም፤ ከዚህ በላይ አልታገስም፤ ከዚህ በላይ ይከብደኛል» የሚለው ጠርዝ አለው። ይደክማል። ይሰለቻል። ቢታገስ እንኳን ያማርራል፤ ቢጸናም ተስፋው ይዝላል፤ ቢሸከምም ደርሶ አውርዶ ሊጥል ይናፍቃል።ሰው ስልቹ ነው። ሰው ወረተኛ ነው። ዛሬ የያዘው ወርቅ ነገ መዳብ ይመስለዋል። ዛሬ ያመሰገነውን ነገ ሊኮንነው ይችላል፤ አሁን ለሳቀለት አፍታም ሳይቆይ ይነክሰዋል። ሰው ወረተኛ ብቻ አይደለም። ደግሞም ራሱን ወዳድ ነው። ለእርሱ እንደተመቸው ብቻ፤ ለእርሱ እስከሆነለት ብቻ ነው ምንም ነገር ቢሆን የሚፈልገው።

Saturday, April 30, 2016

አደናጋሪው ጩኸት !

መላዋ እየሩሳሌም የጩኸት ድምጽ ይሰማባታል፤ከወትሮዋ በተለየ ሁኔታ ጩኸት በዝቶባታል። ከወዲያ ወዲህ እየተመላለሱ ህዝቡን የሚያሳምፁ ካህናቱና ሊቃነ ካህናቱም ወገባቸውን ታጥቀው ይመላለሱባታል። የከተማዋን ሽብር የተመለከቱ ሁሉ  ገበያ ቀን ነበርና ግራ ተጋቡ በሚሰሙት ጩኸት ተደናገሩ፣የጩኸቱን ምክንያት ተረድቶ ማስርዳት የሚችል ግን አንድም ሰው የለም ብቻ ሁሉም ይጮሃል። በመንገድ አልፈው የሚሄዱትም "ቤተመቅደስን አፍርሰህ በሦስት ቀን የምተሰራው"  እያሉ ይጮሁ ነበር። ከቤተ መንግስትም ሆነ ከቤተ ክህነቱ ባለስጥናት  ጩኸቱን ለማስቆም  የደፈረ ማንም የለም። ሦስት ዓመት ከሦስት ወር በተደረገው ተዓምራት በሕሙማን አድረው ይጮሁ የነበሩ አጋንንት ዛሬ ደግሞ በአይሁድ ልቡና አድረው ይጮሃሉ። ጩኸቱ ግን ይለያያል። ያን ጊዜ" ልታሳድደን መጣህን? "የሚል ሲሆን ዛሬ ግን "ስቀለው! ስቀለው!" የሚል ሆኗል። ነገሩ እየጠነከረ መጥቶ ጩኸቱ ምክንያት የሆነው ንጉሠ አይሁድ ኢየሱስ ክርስቶስ ታስሮ ወደ ሊቀ ካህናቱ ግቢ ደርሰ። 


ሊቀ ካህናቱ ሀና ሥልጣን ዘመኑን ጨርሶ ለቀያፋ ያረከበ ቢሆንም ስለምግልናው በጀመሪያ በተከሳሹ ላይ ፍርድ እንዲሰጥ የተጠየቀው እርሱ ነበር። ነገር ግን እርሱም ቢሆን ጩኸቱ ለማስቆም አቅም አልነበረውም። ሲጀመርም ጩኸቱን መርቆ የከፈተው ማን ሆነና? የእርሱ የልጅ ባል ቀያፋ አይደለምን? "ስለ ህዝቡ ሁሉ አንድ ሰው ቢሞት ይሻላል" ብሎ። በዚህ በሊቃነ ካህናቱ የተጀምረው ጩኸ ወደ ሕዝቡ ወረደ በሊቀ ካህናቱ ግቢ የፍርድ ሂደቱ እየተካሄደ ባለበት ወቅት  ሌላ አዲስ ጩኸት ተከሰተ ፤የሰባኪው ዶሮ ጩኸት ተከሶ የመው  የክርስቶስ ፍርድ ሳይጠናቀቅ ደቀመዝሙሩ ዼጥሮስም ተከሶ ቆመ። በሕሊና ዳኝነት ወንጀለኛ መሆኑ ስለተረጋገጠ ምስክር እንኳን ሳያስፈልገው እራሱ በሰጠው የእምነት ቃል ማስረጃነት ዳኛው አስቸኳይ ውሳኔ ስለሰጡ ዼጥሮስ ስለራሱ እያለቀሰ ወ። ምንላባትም የኸቱ ምስጢር ገብቶት ስለራሱ ይጮህ የነበረ ብቸኛ ሰው ሳይሆን አይቀርም። ሌሊቱን በሙሉ አንድ ጊ እንኳን ሳይተኙ በጩኸት ከሐና ወደ ቀያፋ ከቀያፋም ወደ ሐና እያመላለሱት ሲጮሁ አደሩ። ሲነጋም የካህናት አለቆች ህዝቡ ሁሉ አሉ የትባሉትን ሽማሌዎች ጠርተው የሞቱን ጦማር አጸደቁት ። ከሳሽ ሳይኖር በደሉ ሳይዘረዘር  እንዲሞት የተወሰነበት የመጀመሪያ ሰው።

Tuesday, April 26, 2016

ሀቁን ካንቺ ልስማ

ሰላም ላንቺ ይሁን ለንጽህት እናቴ
ሳዝን መጽናኛየ ስደክም ብርታቴ፣
የመኖሬ ምስጢር የህይወቴ አንድምታ፣
ከሰማይ የተላክሽ የንጉሥ ስጦታ ፣
አማናዊት መርከብ ምሥለ ጎልጎታ፣
የሸክሜ ማቅለያ የምስጢር ዋሻዬ፣
ከጭንቀት ማምለጫ ጥላ ከለላዬ፣
ሰላም ላንቺ ይሁን ሰላም ነሽ እማዬ?
የምነግርሽ አለኝ ጆሮ ስጭኝ እማ!
እኒያ ጡት ነካሾች ሲሰድቡሽ ብሰማ፣
ውስጤ ተቃጠለ ሕሊናዬ ደማ፣
እውነቱን ንገሪኝ ሀቁን ካንቺ ልስማ፤
እውነቱን ንገሪኝ ሀቁን ካንቺ ልስማ።
ምን ጥፋት ሰርተሽ ነው? ምን በድለሻቸው?
አሻግረው ስላዩሽ ሚያንገሸግሻቸው።
ቆይ ምን ብተሰሪ ነው?
እኮ ምን ሰርተሽ ነው? ምንድን ነው ነገሩ?
እናጠፋታለን ብለው ሚፎክሩ።
ለምስጢር ያልበቃሁ ብሆንም ጎስቋላ፣
ትዕዛዝሽን ያልጠበቅሁ አደራ ምበላ፣
አፈር ትቢያም ብሆን ቢበዛም ሀጢአቴ፣
ቃላት መገጣጠም ባይችል አንደበቴ፣
እውነቱን ልወቀው ንገሪኝ እናቴ፤
እውነቱን ልወቀው ንገሪኝ እናቴ።

Sunday, March 27, 2016

አንደበት እና ጾም !

የተከበርክ ምላሴ ሆይ፡አርምሞን ገንዘብ አድርግ።አንተም ብዕረ አርምሞ የሚል ቃልን ጽፈህ ልቦናየን ለሚያውከው  ለዓይኔ መልእክት እንዲደርሰው አድርግ።ሥጋየ ፈቃድ በተነሳበት ጊዜ የጌታየን፣የፈጣሪዬን መከራውንና ግርፋቱን አስብ ዘንድ  ልቦናየ ይህን እያሰበ  እንዲበረታ እንዲህ ከሆነ ለዓለማዊ ህይዎት ሙት እሆናለሁ።ሣጋዊ ምኞትና ፍላጎት በነገሰበት ሕይዎት ለ አርባ አቅናት እንደ ጌታ ት ዝዛና ሕግ ልቡናዬን በንጽህና ለመጠበቅ ይቅርታ ለሚያሰጠው ህይዎት የተገባሁ እንድሆን።የ አባቶችን ምክር እቀበላለሁ፣የቅዱሳንን ፍኖት እከተላለሁ በከንፈሮቼ ላይ መዝጊያን አኑር ምክን ያቱም ብዙ መማር ስለሚገባኝ ነው  የምናገራቸውን ቃላርት እመጥን፣ሰውነቴን ለመቆጣጠር እችል ዘንድ፤ አንደበት የነስን ሩጫ ያሳድፋልና ሞገደኛ በሆነ የጻለ ሾተል ሰዎችን የሚገድል ሰው በቀላሉ ትንሽ ቁጥር ያላቸውን ሰዎች ያንበረክካል።ክንፍ ያላትን ከወጋች የንማትነቀለውን የምላስ ጦር የወረወረ ሰው(በ አላማም ያለ አላማም)አላማውን አይስትም።የቀረቡትን ሁሉ ያቆስላል ፤የመረዘውን ሁሉ ይገድላል።በጾም ወራት ሕሌና ፍጹም መረጋጋት ያስፈልገዋል።ከምድራዊ ሃሳቦች ሁሉ የጸዳ ከሰዎች ተለይቶ ብቻውን ከ አምላኩ ጋር የሆነ ሊሆን ይገባል።ሕሊና የኃዘን ደመና ሊያንዣብብበት ይገበዋል። ውጤቱም እርጥበት እንባን የሚያስከትል መራር ኃዘን ነው።


 ታላላቅ ነገሮችን ለመቆጣጠር የሚፈልግ ሰው ትንንሽ ነገሮችን መቆጣጠር ይኖርበታል። የምላሴን ኃይል ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር  ያለብኝ ከንፈሮቸ ምንም አይነት ቃላት እንዳያፈሱ ተስፋ አድርጌ  ለሰው ልጆች መርዙ የማይነቀል ገደይ እንደ ምላስ ያለ የለምና ነው። ምላስ ዘወትር ግልቢያን እንደሚናፍቅ  ከፊት ለፊት ያለውን ሁሉ ቀድሞ ለማለፍ እንደ ሚጋልብ ፈረስ ነው። ምላስ የተዘጋጀ የተደገነ ቀስት ነው። ሁሉን ማየት የሚቻለው ማን ነው? እጅ በአቅራቢያ የሚገኘውን ትንሽ ነገር በቀላሉ ይጨብጣል ፤እግርም ሁሉንም የመሬት ክፍል አይረግጥም፤አይንም ሰሜንና ደቡብን አይመለከትም፤ምላስ ግን የማይደርስበት ቦታ የለም። ምድርን ሁሉ ያካልላል ለነፍሰ ገዳዮችና ጣኦትን ለሚያመልኩ፣ሐሰትን ለሚዎወዱ አድጋ ነው በእብደታቸው ላይ ሌላ እብደት ይጨምርላቸዋልና። የፈጠነን ምላስ ሊያስቆም የሚችል ምድራዊ ኃይል የለም። ለመናገር የቸኮለ ከንፈርንም እንዲሁ ሰውም ቢሆን ውሽንፍርም ቢሆን፣የበረዶ ግግርም ጎርፍም፣ተራራም ቢሆን ባለ ቀስቱ ቅርብ ነው። ቀስቱ የተደገነ ነው፤ቀስቱ በደጋን ላይ ነው። አንድ ጣቱን ደጋን ላይ አድርጎ  አክሮ ቀስቱን ይወረውራል፤በረው የታለመላቸውን አላማ ይመታሉ። ሰማያዊያን ምድራዊያንም ቢሆኑ አያመልጧቸውም። ሕያዋንንም ሙታንንም ያለፉትን የሚኖሩትንና የሚመጡትን ሁሉ ይገድላል። የምላስ ቀስት እንዳይወረወርባቸው የሚጥብቁትንም የማይጠብቁትንም የተጣላቸውንም ወዳጆቹንም አይምርም።

Wednesday, March 16, 2016

አቤት ቆሻሻ !

በሀገራችን የዘመን አቆጣጠር ከ1980ዎቹ አጋማሽ አስከ1990 ዎቹ አጋማሽ ድረስ አልፎ አልፎ አዲስ አበባ ስታዲየም መግባትን አዘወትር ነበር ። በተለይ ብሔራዊ ቡድናችን ጨዋታ ሲኖረውና ኢትዮጵያ ቡና ከቅዱስ ጊዮርጊስ ግጥምያ ሲኖራቸው አልቀርም ነበር ።ታዲያ በስቴድየሙ ቆይታዬ የሚያረካኝ ከጫወታው ይልቅ ከመስመር ያልወጡ የደጋፊዎች ብሽሽቅ ፣ ቀልድና ትርርብ ነበር ። ከሁሉም ከሁሉም ደስ የማይልና ጋጠወጥ ድርጊት ሲያጋጥም ታዳምያኑ በሙሉ በአንድ ድምጽ የሚያሰሟት የተቃውሞ መዝሙር መቼም ቢሆን አልረሳትም ። ትዝም ትለኛለች ። "አቤት ቆሻሻ ፣ አቤት ቆሻሻ ፣ አቤት ቆሻሻ " አቤት . . .እንደ አጋጣሚ ሆኖ ወጉ ደርሶኝ ቃሊቲን በጎበኘሁ ጊዜም ይህችን "ቆሻሻ " የምትባለውን ቃል በተደጋጋሚ የሚጠሩበትን ሰዎች አይቻቸውም ነበር ። እነዚህም " ቆሻሻ " ተብለው የሚጠሩ ሰዎች በግረሰዶማዊነት ተይዘው የተፈረደባቸው ሰዎች ናቸው ።" ቆሻሾቹ " ማደሪያቸው ሽንት ቤት ፤ መዋያቸው የቆሻሻ ገንዳ ስር ነበር ። ይህን ሁኔታ መንግስት አዝዞ በወንጀላቸው እንዲቀጡ የወሰመባቸው ሳይሆን እስረኛው በራሱ ህግ አውጥቶ ድርጊቱን መፀየፉንና በኢትዮጵያም የተጠላና ሥፍራ የማይሰጠው መሆኑን ማሳየቱና ማረጋገጡም ነው ። 


እነዚህን በቃሊቲ " ቆሻሾች " ተብለው የሚጠሩትን መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ "ቀላጮች " እያለ ይጠራቸዋል ። " . . . አመንዝሮች ወይም ቀላጮች ወይም ከወንድ ጋር ዝሙት የሚሠሩ" 1ኛ ቆሮ 6፣9 ይሁንና ዓለም በተባለች በሰፊዋ ስታዲየም ዛሬ ዛሬ ደግሞ የሚገራርሙ ነውረኞችና ቆሻሻ ድርጊት ፈጻሚዎች ከሚገባው በላይ ቁጥራቸው እጅጉን ከፍ ብሎ በመታየት ላይ ነው ። በተለይ በሀገራችን በኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ ይህ አስያፊ ድርጊት እጅግ በረቀቀ መንገድ እንዲስፋፋ እየተደረገ መሆኑን ማሳያ የሚሆኑ ዋቢዎችን መጥቀስ ይቸላል ። ድርጊቱን አስከፊ የሚያደርገው ደግሞ የድርጊቱ ፈጻሚዎች በተለየ ሁኔታ ለዚህ ቆሻሻ ተግባር የሚመለምሉት ጨቅላ ህጻናትን መሆኑ ነው ። በተለይ እንደ አባት የሚታይ መምህር ለትምህርት የላካችሁትን ጨቅላ ልጃችሁን ሲጫወትበት መስማት ይዘገንናል ። ባለፈው ሰሞን አንድ መምህር ይህን ቆሻሻ ተግባር በህጻናት ልጆች ላይ ፈጽሞ በመገኘቱ በፍርድቤት የነበረውን ክርክር ላየ ድርጊቱ ወደፊት ከባድ እየሆነ ለመምጣቱ ምልክትም ነው ። የአውራ አምባው ዳዊት ከበደ በፌስቡክ ገጹ ላይ በግልጽ ይህ አስፀያፊና ቆሻሻ ተግባር በውቢቷ ሀዋሳ ከተማ በግልጽ በተከፈተ የመዝናኛ ክለብ ውስጥ ለውጭ ሀገርና ለሀገር ውስጥ ቆሻሾች ህጻናትን እንደሚቀርቡና እንደሚቸበቸቡ የክለቡን ስም ጠቅሶ መዘገቡን ስናይ በጣም ያስፈራል ። ይህ ድርጊት ሲፈጸም የአካባቢው መስተዳድር አያወቀውም ለማለት አይደፈርም ።

Monday, March 07, 2016

ደጉ ሳምራዊ

እነሆም አንድ ሕግ አዋቂ ፈሪሳዊ ኢየሱስን ሊፈትነው ተነስቶ፦ መምህር ሆይ የዘለዓለምን መንግስት እንድወርስ ምን ላድርግ? አለው። እርሱም በሕግ የተጻፈው ምንድር ነው? እንዴትስ ታነባለህ?አለው። ፈሪሳዊውም መልሶ ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ኀይልህም ውደድ፣ባለእንጀራህን እንደርስህ  ውደድአለው። ኢየሱስም እውነት መለስህ ይህንን አድርግ በሕይወትም ትኖራለህአለው። ፈሪሳዊው ግን ራሱን ሊያጸድቅ ወዶ ነበርና ኢየሱስን ባለንጀራየስ ማን ነው ? አለው። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለ አንድ ሰው ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ ወረደ በወንበዴዎችም እጅ ወደቀ፤እነርሱም ደግሞ ገፈፉት፤ደበደቡትም፤በህይዎትና በሞት መካከልም ትተውት ሄዱ። ድንገትም አንድ ካህን በዚያ መንገድ ወረደ፤አይቶትም ገለል ብሎ አለፈ። እንዲሁም አንድ ሌዋዊ ወደዚያ ስፍራ መጣና አይቶት ገለል ብሎ አለፈ። አንድ ሳምራዊ ግን ሲሄድ ወደ እርሱ መጣ አይቶትም አዘነለት፤ቀርቦትም ዘይትና የወይን ጠጅ በቁስሎቹ ላይ አፍስሶ አሰራቸው፤በራሱ አህያም ላይ አስቀምጦት ወደ እንግዶች መቀበያ ወሰደው ጠበቀውም። በማግስቱም ሁለት ዲናር አውጥቶ ለባለቤቱ ሰጠና 'ጠብቀው ከዚህም በላይ የምትከስረውን ሁሉ እኔ ስመለስ እከፍልሃለሁ' አለው። እንግዲህ ከእነዚህ ከሦስቱ በወንበዴዎች እጅ ለወደቀው ባልንጀራ የሆነው ማንኛው ይመልሃል? አለው  እርሱም ምህረት ያደረገለትአለ። ኢየሱስም ሂድ አንተም እንዲሁ አድርግአልው።

በሕይዎት ጎዳና ስንጓዝ ምን እንድሚያጋጥመን አንውቅም። ቀደም ሲል በቀረበው ታሪክ ውስጥ ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ ይጓዝ የነበረው ሰው መጨረሻ አስከፊ እንደነበር አይተናል። ይህ ሰው ምን እንደሚያጋጥመው ቀደም ብሎ የተረዳ ቢሆን ኖሮ ጉዞውን በሌላ አቅጣጫ ወይም በሌላ ቀን ባደረገ ነበር። በህይወታችን ብዙ ፈተናወች ይገጥሙናል። ብዙ ጊዜ ወደፊት የሚገጥመን ነገር ምን እንደሆነ ሳናውቅ የጉዟችንን መስመር እንወስናለን። ሕይወት የእጣ ፈንታ ጉዳይ እንደመሆኗ አንዳንዴ መልካም ነገር አንዳንዴ ደግሞ ክፉ ነገር ያጋጥመናል። ምርጫችን ጥፋትን ሊያስከትልብን ይችላል፤ሞትን እስከማስከተል ድረስ። አንዲት የቤት እመቤት ከዕለታት  አንድ ቀን ያጋጠማቸውን ታሪክ እንደሚከተለው ይገልፃሉ። ባልፈው ሳምምንትአሉ አንድ ወጣት ልጅ የቤቴን በር አንኳኳ። በሬን ከፍቸ ስጠይቀው ስሙንና የዩኒቨርሲቲ ተማሪ መሆኑን የሚገልጽ መታወቂያ ወረቀት አውጥቶ አሳየኝ። ሥራ ፈላጊ መስሎኝ ለእርሱ የሚስማማ ሥራ እንደሌለኝ ገልጨለት መታወቂያውን ስመልስለት ሌላ ወረቀት በተጨማሪ አውጥቶ አሳየኝ። ሥራ አይደለም  የምፈልገው የእኔ እናት እባክዎን ሊረዱኝ ይችላሉአለኝ። የሰጠኝን ወረቀቅት ስመለከት የኤች አይ ቪ ቫይረስ በደሙ እንዳለብት አወቅሁ።


ቀደም ሲል አንዲት የሴት ጓደኛ ነበረችኝ እናምብሎ ሊቀጥል ሲል አቋረጥሁትና ይብቃህ የኔ ልጅ ሁሉንም ነገር ልትነግረኝ አያስፈልግምአልሁት። እባክዎ እናቴ ሰውነቴ በበሽታው እጅግ ተዳክሟል፤ሆኖም አገሬ መግባት አለብኝ ወደ አገሬ የምሄድበት ጥቂት ገንዘብ እንዲሰጡኝ እለምነዎታለሁአለኝ። ልጁን በጥሞና ተመለከትሁት፤ ዕድሜው ሃያወቹ ውስጥ ያለ ይመስላል፤ሰውነቱ ግን በበሽታው ተጎድቶ የደከመና የመነመነ ነው። ለጉዞው እንዲሆነው በማለት ጥቂት ገንዘብ ሰጠሁት፤እንዲሁም ምግብ አቀረብሁለት። እግዚአብሔር ይስጥዎ በጣም አመሰግናለሁ ውለታወን መቸም አልረሳውምብሎኝ ሄደ። ለዓይኔ እየራቀ ሲሄድ እንባየን መቆጣጠር አልቻልሁም። ወጣቶችን በአፍላ የምርታማነት ዘመናቸው የሚቀጭ እንዴት ያለ በሽታ ነው? የዚህ ልጅስ ህይወት ምን ትርጉም ይኖረዋል? ልጃቸውን ለትልቅ ደረጃ የተመኙት ወላጆቹስ በዚህ ሁኔታ ሲቀበሉት ምን ዓይነት ከባድ ኀዘን ይሰማቸው ይሆን?ብዬ አዘንኩ። ይህ ወጣት ግን አንድ ፍላጎት ብቻ ያለው ይመስላል አገሩ ገብቶ መሞት።


1) እርስዎ ከላይ  በታሪኩ በተጠቀሱት በቤት እመቤቲቱ ቦታ ቢሆኑ ምን ያደርጉ ነበር?  ወጣቱን  ዘወር በል  ብለው ያባርሩት ነበር ወይስ እንደ ወይዘሮዋ ምግብና ገንዘብ ይሰጡት ነበር?
2) በወላጆቹ፣ በእህትና በወንድሞቹ ቦታስ ቢሆኑ ወደ ቤት ተመልሶ ሲመጣ  እንዴት ነው የሚቀበሉት?
3) እንዲህ ዓይነት ሁኔታ አጋጥሞዎት ያውቃል?
4) እርስዎ እንደ ወጣቱ ላለመሆን ምን እያደረጉ ነው?
5) ኤች አይ ቪ እያደረሰ ስላለው ችግር ያለዎት አስተሳሰብ ምንድን ነው?

Tuesday, March 01, 2016

አድዋ - ያባከንነው ድላችን

ይህች ሀገር ብዙ የተከፈለባት ምድር ናት! ለውድቀቷ የተጉ የመኖራቸውን ያህል፣ ብዙዎች ሕይወታቸውን ከፍለው ለዛሬ ያበቋት ሀገር ናት፡፡… እኒህ ባለውለታዎቿ ሰው እንደመሆናቸው፣ የሰው ልጅ በዘመኑ የሚፈጽመውን ስህተት የፈጸሙ ቢሆን እንኳን፣ እናት ላሏት ኢትዮጵያ የከፈሉት ዋጋ ከዋጋ በላይ ነው፡፡ ይህንን መካድ፣ አለማክበርና ማባከን አለመታደል ነው፡፡ ራስንም ለውርደት አሳልፎ መስጠት! ስለዚች ሀገር ነጻነትና ክብር ብዙዎች በብዙ መልኩ ደክመዋል፡፡ መከፋታቸውን ችለውና ከራሳቸው ሀገራቸውን አስቀድመው ስለ እሷ ታትረዋል፡፡ በክፉ ቀንም አንገታቸውን ለሰይፍ፣ እግራቸውን ለጠጠር፣ ደረታቸውን ለአረር ሰጥተው ስለ ክብሯ ወድቀዋል፡፡ “የዛሬን አያድርገውና” ለኢትዮጵያውያን ስለ ሀገር ክብርና ስለ ሕዝቦች ነጻነት ሕይወትን መክፈል ታላቅነት ነበር፡፡ በዚህ አብዝታ የተመካችው ንግሥት ጣይቱ፤ አያውቀንም ላለችው የኢጣሊያ መንግሥት ወኪል አንቶኔሊ እንዲህ ነው ያለችው፡- “… የኢትዮጵያን ሰው ባታውቀው ነው፡፡ ለሀገሩ መሞት ማለት ለሀበሻ ጌጡ ነው፡፡ ሂድ ባሻህ ጊዜ ተመለስ ተሰናድተን እንጠብቅሃለን፡፡”ይህች ሀገር ዛሬ ላይ የደረሰችው ብዙ ዋጋ ተከፍሎባት ነው፡፡ ከክፍያም በላይ የሕይወት ዋጋ ተከፍሎባት፡፡ በዚህም አባቶቻችን እኛን አልፎ የአፍሪካውያንን አንገት ከተደፋበት ቀና ያደረገ፣ ዓለምንም “አጃዒብ” ያሰኘ አኩሪ ገድል ፈጽመዋል። ይህ ማንም የማያብለው የታሪክ ሀቅ ነው፡፡ ደረቅ ሀቅ!


ያም ሆኖ ታላላቅ ገድሎቻችንን ልናከብራቸውና ልንማርባቸው ሲገባ፣ ከንቱ እጅ እንደገባ ወርቅ ሁሉ አልባሌ ቦታ ተትተውና ቸል ተብለው ባክነዋል። ድሎቻችን ወደ ፊት መስፈንጠሪያችን ሊሆኑ ሲገባ ግብ የለሽ የቸከ ተረት አድርገናቸዋል። ድሎቹ የሰጡንን መነቃቃትና አቅም ከድርጊት ይልቅ በመተረት እናባክናለን፡፡ ለዘመናት እየሆነ ያለው ይኸው ነው፡፡ እውነቱን መቀበል ቢገደንም ቅሉ፣ እየሆነ ያለው እንዲሁ ነው፡፡ ድሎቻችንን ለዘመናት አባክነናል፡፡ አሁንም ለመማር ዝግጁ አንመስልም። በዓለም የነጻነት ታሪክ ውስጥ እንደ ተአምር ከሚቆጠሩት ክስተቶች አንዱ የሆነው አንጸባራቂው የአድዋ ድልም እንዲሁ ከዚህ መባከን አላመለጠም።… አድዋ! ስለ አድዋ ድል በየጊዜው የሚባለውን ሰብስበን እንበለው፡፡ የአድዋ ድል ነጮች የጥቁር ህዝቦች የበላይ ነን ብለው ለዓመታት ቀንበራቸውን ባጸኑበት፣ ጥቁሮችም ይህንኑ አምነው ለዘመናት በተገዙበት ዘመን ሀበሾች በነጮች ላይ የተቀዳጁት አንጸባራቂ የነጻነት ድል ነው፡፡… ይህ ክስተት የዓለምን አስተሳሰብ ቀይሮአል፡፡ እንኳንም በባርነት ቀንበር ተቀይደው የነበሩትን ጥቁሮች ቀርቶ የቅኝ አገዛዙ ተዋናዮቹን ሳይቀር እምነታቸውን አስፈትሾአል፡፡

Friday, February 26, 2016

ስማችሁ የለም

በሰማያዊው ዙፋን ዘንድ አንድ ውሳኔ ተላለፈ፡፡ «እነዚህ የኢትዮጵያ ሰዎች ሃይማኖተኞች ናቸው፡፡ ስለዚህም ዓለም ከማለፉ በፊት አስቀድመው ተጠርተው ዋጋቸውን ሊቀበሉ ይገባል» የሚል፡፡ አንድ ሊቀ መልአክ እልፍ አእላፍ መላእክትን አስከትሎ ከሰማይ ሲወርድ ታየ፡፡ በኢትዮጵያ የሚኖሩ ሰዎችንም ሁሉ ለሰማያዊ ፍርድ ሰበሰባቸው፡፡ ወዲያውኑ በመንግሥተ ሰማያት በር ላይ ሁለት ዓይነት ሰልፎች ታዩ፡፡ አንደኛው ሰልፍ ረዥም፤ ሌላኛው ሰልፍ ግን አጭር ነበር፡፡ ረዥሙ ሰልፍ ባለበት ቦታ ገበሬዎች፣ ወዛደሮች፣ የዕለት ሥራ ሠራተኞች፣ እናቶች፣ አባቶች፣ ሕፃናት፣ ሊስትሮዎች፣ የቤት ሠራተኞች፣ ሾፌሮች፣ መሐንዲሶች፣ ሐኪሞች፣ አስተማሪዎች፤ ማን ያልተሰለፈ አለ፡፡ ከጥቂቶቹ በቀር ብዙዎቹ መንግሥተ ሰማያት የመግቢያ ካርድ ማግኘት ቻሉ፡፡ይህንን ሁኔታ ሲመለከቱ በአጭሩ ሰልፍ በኩል የተሰለፉት የልብ ልብ ተሰማቸው፡፡ መጀመርያውኑ ለብቻቸው ሰልፍ የሠሩት ከሕዝብ ጋር ላለመደባለቅ እና ላለመምታታት ብለው ነበር፡፡ እንዴት ሲያስተምሩት፣ ሲያስመልኩት፣ሲያስሰግዱት፣ ሲያሳልሙት፣ ከኖሩት ሕዝብ ጋር አብረው ይሰለፋሉ? መጀመርያ ነገር እነርሱ ያስተማሩት ሕዝብ መንግሥተ ሰማያት ከገባ እነርሱ የማይገቡበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ ሁለተኛ ደግሞ ወደፊትም ቢሆን በመንግሥተ ሰማያት ለየት ያለ የክብር ቦታ ሊጠብቃቸው ስለሚችል ለየት ብለው መሰለፋቸው ተገቢ ነው፡፡


ይህንን እያሰቡ እና እያወሩ እያለ አንድ መልአክ ወደ እነርሱ ሰልፍ መጣ፡፡ተሰላፊዎቹ በኩራት ገልመጥ ገልመጥ አሉ፡፡ እንዲያውም «ከመካከላችን ማን ይሆን ቀድሞ የሚገባው» የሚለው ነገር ሊያጨቃጭቃቸው ነበር፡፡ አንዳንዶች በተከታዮቻቸው ብዛት፣ አንዳንዶች በነበራቸው መንፈሳዊ ሥልጣን፣ አንዳንዶች ባገኙት የካሴት እና የመጽሐፍ ገቢ፣ ሌሎችም በሕዝቡ ዘንድ በነበራቸው ተደናቂነት፣ የቀሩትም ደግሞ በንግግር እና በድምጽ ችሎታቸው እየተማመኑ እኔ እበልጣለሁ እኔ እቀድማለሁ ሲባባሉ መልአኩ «እናንተ እነማን ናችሁ?» የሚል ያልተጠበቀ ጥያቄ ጠየቃቸው፡፡ ሁሉም መልአክነቱን ተጠራጠሩት፡፡ አገር ያከበራቸውን፣ሕዝብ ያረገደላቸውን፣እነርሱን ለማየት እና ለመንካት አዳሜ የተንጋጋላቸውን፣ በየፖስተሩ፣ በየካሴቱ፣ በየመጽሐፉ፣ በየመጽሔቱ «ታዋቂው» እየተባሉ ሲቀርቡ የኖሩትን፤ ሰይጣን ያወጣሉ፣ መንፈስ ይሞላሉ፣ ጠበል ያፈልቃሉ፣ እየተባሉ ሲያርዱ ሲያንቀጠቅጡ የኖሩትን፤ ሲዘምሩና ሲያስተምሩ ወፍ ያወርዳሉ የተባሉትን፤ ገንዘብ ከፍሎ መንፈሳዊ ቦታ ተሳልሞ ለመምጣት ሕዝብ ቢሮአቸውን ደጅ ሲጠናቸው የኖሩትን እነዚህን ጉምቱ ጉምቱ ሰዎች የማያውቅ መልአክ እንዴት ሊኖር ቻለ? ተጠራጠሩ፡፡«ለምንድን ነው ለብቻ ሰልፍ የሠራችሁት? ለምን ከሕዝቡ ጋር አልተሰለፋችሁም?» መልአኩ ይበልጥ የሚገርም ጥያቄ አመጣ፡፡ ተሰላፊዎቹ እርስ በርሳቸው ተያዩ፡፡ ከመካከል አንድ በነገሩ የተበሳጨ ሰባኪ «እንዴት እንደዚህ ያለ ጥያቄ በዚህ በመንግሥተ ሰማያት በር ላይ እንጠየቃለን? እስካሁንም ተሰልፈን መቆየት አልነበረብንም፡፡ እኛን ለመሆኑ የማያውቅ አለ? ስንት ሕዝብ ያስከተልን ሰባክያን፤ ስንት ሕዝብ የፈወስን አጥማቂዎች፣ ስንት ሕዝብ ያስመለክን አስመላኪዎች፣ ስንቱን ያስረገድን ዘማሪዎች፤ ስንቱን የታደግን ፈዋሾች፣ ስንቱን የመራን የእምነት መሪዎች፤ ስንቱን በባዶ እግሩ ያስኬድን ባሕታውያን፤ ስንቱን ለገዳም ያበቃን መነኮሳት፤ ሕዝብ ተሰብስቦ የሾመን «ሐዋርያት»፤ እንዴት እነማን ናችሁ ተብለን እንጠየቃለን?» ሁሉም በጭብጨባ ደገፉት፡፡

Saturday, February 20, 2016

ከዘንዶ አፍ የወጣች ርግብ

በወላጆቼ ቁጥጥር ስር አጥቸው የኖርሁትን ነጻነት እስከማጣጥም ድረስ ስለጓጓሁ  የዩኒቨርሲቲት መግቢያ ቀን የተነገረ ዕለት የተሰማኝ ደስታ የተለየ ነበር። ከቤት ትምህርትቤት ከትምህርትቤት ወደ ቤት ከዚህ ውጭ የትም ቦታ መሄድ አይፈቀድልኝም። እናቴ ለትምህርት ካላት ፍቅርና ለነገ ማንነቴ ከምትሰጠው ከፍተኛ ግምት አንጻር ዩኒቨርሲቲት እንድገባ ታበረታታኛለች እንጅ ከእርሷ ርቄ እንድሄድ  አትፈልግም። አላቻለችም እንጅ ወደ ቅርብ ዩኒቨርሲቲ ለማስቀየር  ሁሉ አስባ ነበር። ዘንድሮ ከእስር የተፈታሁ ያክል ይሰማኝ ጀምሯል።ከቀናት በኋላ ግን ከጓደኞቼ ጋር በዲፓርትመንትም በመኝታም በመለያየታችን ብቸኝነት  እየተሰማኝ መጥቷል። ትምህርቱ የቡድን ስራው አስጨንቆኛል። ቀናት ነጎዱ ወራትም ተቆጠሩ፣መንፈቀ ዓመትም ሆነ። ቁንጅናየ የግቢው መነጋገሪያ እንደሆነ ከሰማሁ ጀምሮ በራሴ ብተማመንም ሕይዎት እያስጠላኝ፤የፈለጉትን በልተው ፤የልብስ ዓይነት የልብስ ፋሺን እያቀያየሩ የሚያጌጡ የግቢያችን ተማሪዎች ኑሮ እያስቀናኝ መጥቷል።"ሰሞኑን ደግሞ ምን በወጣሽ ነው ታፍነሽ የምትኖሪው? የምትሞችበትን ቀን ለማታውቂው ስለምን ራስሽን ታጨናንቂያለሽ ይልቁኑ እንደጓደኞችሽ ነጻ ሁኝ የቤትሽ ይበቃሻል። አንቺኮ ባትማሪም በቁንጅናሽ ብቻ ተከብረሽ መኖር የምትችይ ሴት ነሽ ። ስለዚህ ፈታ በይ" የሚል አንዳች ስሜት ያስጨንቀኛል።


በዚህ ላይ የሁለቱ ጓደኞቼ የተለያየ ምክር ግራ አጋብቶኛል። አንደኛዋ ጓደኛዬ ከቤተክርስቲያን የማትለይ፣ በግቢ ጉባኤ አገልግሎት የምሳተፍና ኮርስ የምትከታተል ታታሪ ተማሪ ናት። የሚገርመኝ ግን ሌሎች ተማሪዎች ሌሊትም ቀንም እያጠኑ የእርሷን ያህል ውጤት ማስመዝገብ አለመቻላቸው ነው። እርሷ ቤተክርስቲያን እንድሄድ፣ኮርስ እንድማር እንድጾም፣እንድጸልይ ብትመክረኝም እኔ ግን ምክሯን ለመቀበል አልፈልግም። ባገኘችኝ አጋጣሚ ሁሉ ስለምትመክረኝ ባላገኛት እመርጣለሁ። ሌላኛዋ ጓደኛየ ደግሞ ደስ ሲላት የምትማር፣ደስ ሳይላት የምትተኛ ፣አምሽታ የምትገባ፣ አርፍዳ የምትነሳ ሰነፍ ተማሪ ናት። በውጤት ግን በዚህም በዚያም ተሯሩጣ  ወይ [A] ያም ባይሆን [B] ታስሞላለች ። ስለምንም ስለማንም የማትጨነቅ ፣የወደደችውን የምታደርግ ሴት መሆኗና  ነጻነቷ ያስቀናኛል። እንደሷ እንድሆን የምታደርገው ጥረትም ተመችቶኛል። ድንግልናዬን ለባለሃብት ብሸጥ መክበር እንድምችል ፤ ከዚያ በኋላ ደስተኛ እንድምሆንና ጭንቀቴም እንደሚቀልልኝ  ከመከረችኝ ወዲህ ያለችኝን ሁሉ ማድረግ እንደሚገባኝ አምኛለሁ። የእናቴ የገቢ ምንጭ በመቀነሱ  ለኮፒ ለማስታወሻ መግዣና ለዓመት በዓል ካልሆነ በስተቀር በቂ ገንዘብ አትልክልኝም። ገንዘብ አልበቃሽ እያለኝ በወር የሚቆረጥልኝ ገንዘብ እያነሰ ቢመጣም ምኞቴ ግን እየጨመረ ሄዷል። ስለዚህም የአንደኛዋ ጓደኛየ ምክር ሕየወቴን ለመለወጥ ጥሩ አማራጭ እንደሆነ ተገነዘብሁና እርሷ ከመረጠችልኝ ሰው አስማማችኝና ቀጠሮ ይዘን ተገናኘን።

ትላንትና ዛሬ

ትላንት እንደቆሸሽኩ ዛሬም አላታጥብኩም፣
በንጽሕ ሰው አምሳል ሰው መሆን አልቻልኩም፣
የራሴን ሳሙና ከመሸጥ አልዳንኩም።
ትላንት በደለኛ ትላንት አረመኔ፣
አምና በሲዖል ውስጥ ዛሬም በኩነኔ፣
ቁሞ የወደቀ ማነው ልክ እንደ እኔ?
የበደሉ ቅርጫት የክፉ ሰው ጓዳ፣
ሰውን ቁሞ ወቃሽ የኃጢአት ባልዕዳ፤
የፈርሰ ጎጆ ዝናብ የሄደበት፣
ለመቆም ያልቻለ ጊዜው ያለፈበት።
ከዓመት ዓመት ሲበር በኃጢአት በወሬ፣
በሰው ላይ ስቀልድ እየኖርሁ አብሬ፣
ስላልሰራሁበት በንስሐ አድሬ፣
ትርጉም የላቸውም ትላንትና ዛሬ።
 

 

 

                  ምንጭ፦ ሐመር መጽሔት
                            ኅዳር 2006 ዓ.ም

Thursday, February 18, 2016

መንፈሳዊነት ምንድነው ?

ለመሆኑ መንፈሳዊነት ምንድን ነው? ረዥም ቀሚስ መልበስ ነው? ፀጉርን በአሮጌ ሻሽ መሸፈን ነው? ገላን ያለመታጠብ ነው? አንገትን መድፋት ብቻ ነው? ቀስ ብሎ መናገር ነው? ኋላ ቀርነት ነው? አይመስለኝም፡፡ ቴሌቭዥን አለማየት፣ኢሜይል አለመጠቀም ነው? ከጸሎት መጻሕፍት በቀር ሌላ ነገር አለማንበብ ነው? መንፈሳዊነትኮ በመንፈስ ቅዱስ መመራት ነው፡፡ ራስን ማሸነፍ ነው፡፡ አእምሮን እና ልቡናን ቀና እና ሰላማዊ ማድረግ ነው፡፡ ለመሆኑ የውስጡ መንፈሳዊነት አይደለም እንዴ ወደላይ መገለጥ ያለበት፡፡ ስለ ሐዋርያት ስንናገርኮ የነፍሳቸው ቅድስና ለሥጋቸው፣ የሥጋቸው ቅድስና ለልብሳቸው፣ የልብሳቸው ቅድስና ደግሞ ለጥላቸው ተረፈ ነው የምንለው፡፡ መንፈሳዊነቱ ከውስጥ ወደ ውጭ እንጂ ከውጭ ወደ ውስጥ አልነበረም፡፡ አንዳንድ ጊዜ «መንፈሳዊነት» ከ «መንፈሳይነት» ጋር እየተመሳሰለ የምንቸገር ይመስለኛል፡፡ ዲያቆን ኤፍሬም እሸቴ ነው ይህችን ቃል ያመጣት፡፡ ከሁለት ቃላት «መንፈሳዊ» እና «መሳይ» ከሚሉ ቃላት ቆራርጦ «መንፈሳይ» የሚል ቃል ፈጠረ፡፡ ትርጉሙም «መንፈሳዊ መሳይ» ማለት ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች መንፈሳውያን ይመስላሉ እንጂ አይደሉም፡፡

Sunday, February 14, 2016

ማተብ የማሰር ልማድ

      
     ማተብ{ማዕተብ} አንደኛው ፍች ምልክት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ቡራኬ ማለት ነው።ሥርወ ግሡም"አተበ"አመለከተ፤ባረከ የሚለው የግዕዝ ቃል ነው። ምልክት ሁል ጊዜ አንድን ነገረ ከሌላው ለመለየት-የሚያስችለው በመሆኑ ዓለም ይጠቀምበታል።ሐዋርያው ቅዱስ ዻውሎስ ውወደ ሮሜ ሰውች በላከው መልክቱ በአራትኛው ምዕራፍ ስለ አብርሃም ሲናገር"ሳይገረዝም በነበረው እምነት ያገኘ የጽድቅ ማኅተም የሆነ የመገረዝን ምልክት ተቀበለ"ብሏልወላጆችም መንታ ሲወልዱ የትናው ቀድሞ እንደተገኘ ለማስታወስ ምልክት ያደርጋሉ።ለምሳሌ በኦሪቱ ፋሪስና ዛራ ሲወለዱ አዋላጇ ቀድሞ በተወለደው አውራ ጣት ላይ ክት አስራበት እንደነበር ይናገራል። የኢትዮዽያዊያን ክርስቲያኖች ማተብ የማሰር ልማድ የመጣው ለረዢም ጊዜ የቤተክርስቲያናችን ሞግዚት ሆና ከቆየችው ከእስክንድርያ ቤተክርስቲያን ነው።በእስክንድርያ ኢቀ ዻዻስ ቴዎዶስዮስ ዘመን በሃገሩ የነበረው ዐላዊ ንጉስ በመሆኑ የክርስትናን አስተማሪዎች እያሰረ ያስደበድብ ነበር።ስለዚህም ቴዎዶስዮስ ካልሆነ ሰው ጋር ተጋፍጦ ከመቀሰፍና ሥራን ከማቋረጥ ዘወር ብሎ መዓቱን ማሳለፍ ይሻላል በማለት ሲሸሽ፤ያዕቆብ  ልዘ አልበርዲአክርስትና ትምህርት ቀናተኛ የሆነ ሐዋርያ በሽሽግ ያስተምር ነበር።ይህንም የተቀደሰ ስራውን ለማሰናከልና ለማቋረጥ የሚሹ አንዳንድ ቦዘንተኞች በስብሰባው ላይ እየተገኙ ያስተማራቸውን ያስቱበት ያሻክሩበት ስለነበር የእርሱ የሆኑትን ለይቶ ለማወቅ ሲል በ አንገታቸው ላይ አድርገው ለምልክትነት እንዲጠቀሙበት ማተብ አሰረላቸው፤ያሰረላቸውም ማተብ ሶስት አይነት ባንድ ላይ የተገመደ ሲሆን ጥቁር፣ቀይ ቢጫ ነበር።ይኸውም ጥቁሩ መከራ እቀበላለሁ፣ቀዩ ደሜን አፈሳለሁ፣ቢጫው ትንሳኤ ሙታንን ተስፋ አደርጋለሁ የሚል እንደነበር ይነገራል።ያዕቆብ ዘ አልበርዳኢም ያስተምር የነበረበት ዘመን አምስተኛው መቶ ዓመት እንደነበር ይገመታል{ሃይማኖተ አበው፣ድርሳነ ያዕቆብ}

Sunday, February 07, 2016

ፕርሚየር ሊግ ወይስ ስሌቭ ሊግ

   
 
መንገደኛው በበቅሎ ጀርባ በምድር ተሽከርካሪ ወይም በሰማይ በራሪ ተጭኖ ከከተማ አልወጣም። መንገድ የለመደበት እግሩ ግን አላረፈም። ከሰፈር ሰፈር ከታክሲ ታክሲ እየቀያየረ ይጉዋዛል። ምን ይሁን ብላችሁ ነው? ለፈተህ ግረህ ብላ አይደል የተባልነው? አላርፍ ባዩ እግሬ ወደ አንድ ገዳም  ለመጓዝ ዕቃወቼን ሼክፌ ትራንስፖርት እየጠበቅሁ ሳለሁ አካባቢየን ሳማትር ነበር መንገደኛው ልቤ ለአእምሮየ ውስጥ ውስጡን የሚያመላልሰው፣ የሚያወጣ የሚያወርደው የቤት ስራ ሰጠው። ታዲያ ይህ የሆነው ባለፈው ሰሞን አውሮፓ ክለቦች የፍጻሜ ጨዋታ ሰሞን ነበር። በዚህ የውድድር  ዓመቱ ፍዛሜው ዕለት አዘውትራችሁ ሻይ ቡና እያላችሁ  የሚነበብ ነገር የምታነቡበት ሻይ ቤት{ ካፌ} በር  "እንኳን ለአውሮፓ  ሻምፒዮን ሊግ የፍፃሜ ጨዋታ አደረሳችሁ" የሚል ለአንድ ሃይማኖታዊ ክብረ በዓል ወይም እንደ አድዋ ዓይነት ሀገራዊ የድል ቀን የደረሳችሁ የሚያስመስል የደስታ መግለጫ ተለጥፎ ብታገኙት ምን ትላላችሁ? መንገደናውን ገርሞታል። እናንተ "አሜን" ብላችሁ ታልፉታላችሁ? ወይስ "ሰወቹ ምን ነካቸው? ምን እየሉ እንደሆነ ታውቋቸዋል?" የሚል ጥያቄ ራሳችሁን ትጠይቃላችሁ? እኔ ግን የሚያበሳጭ ሆኖ አገኘሁትና በርግጥ ተናደድሁ።


መቼም ለመንገደኛው ይህን ያክል የነገ ዳፋው ያስፈራራው ምን እንደሚሆን ሁላችሁም የየራሳችሁን ግምት እንደምትሰጡ አልጠራጠርም። የጊዜው ፈርኦን በቴለቪዥን ዲ.ኤስ.ቲቪ በተባለ ድርጅት አጋፋሪነት የኢትዮዽያችንን አየር እየጣሰ የአውሮፓ በተለይም የእንግሊዝ እግር ኳስ ክለቦች{ፕሪሚየርሊግ}ጨዋታ ፍቅርን፣የዕለትተዕለ ኑሩዋችን አካል ስላረገው ጉድ ነው። ለዚህ እግር ኳስ ስርጭት የሰጠነው ጊዜና እያሳለፍንበት ያለው ሃብት ከቀን ወደ ቀን ለሌሎች ለህይወታችን አስፈላጊና መሰረታዊ ለሆኑ ነገሮች ከምናውለው ጊዜና ሃብት ጋር ለመስተካከል እሽቅድድም የያዘ ነው  የሚመስለኝ። ይህ አባባል ማሰራጨቱን በስራነት ይዘው እየኖሩበት ያሉትን ላይጨምር ይችላል። "እንኳን አደረሳችሁ" የሚለውን ቃል እስከ ዛሬ የምንጠቀምበት ለታላላቅ ሃይማኖታዊ በዓላት በመድረሳችን ምክንያት ደስታችንን ለመለዋወጥ እግረ መንገዳችንን ቸርነቱን ያልነፈገንን አምላክ ለማመስገን ነበር። አራት ኪሎ አንድ ካፌና ሪስቶራንት በር ላይ ተለጥፎ ያየሁት የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት ግን ከተለመዱት በተለየ ምክንያት "እንኳን ለ2011/12 ዓ.ም የእንግሊዝ ፕሪሚይር ሊግ የፍፃሜ ጨዋታ ቀን አደረሳችሁ" ይላል። ደጋግሜ አነበብሁት መጀመሪያ ላይ ሳቅሁ የትዝብት ሳቅ። ቆይቸ ግን ተናደድሁ ቅጥል እስክል ድረስ።

Thursday, February 04, 2016

ሰማይ ሆዱ ባባ !


ዘመኑ ምቀኛ ትውልዱ ጠማማ፣

ሰማዩ አመፀኛ ልመናን ማይሰማ፣

ሲያሰቃየን ከርሞ በድርቅ እያስጠማ፤

የምናደርገውን አሳጥቶን መላ፣

መፍትሄ ሲቸገረን እርስበርስ ስንብላላ፣

በረሃብ ላለማለቅ ስንገባ መኀላ፣

በውኃ ቀጠነ ልጅ አባቱን ሲቀትል፣

እናት በልጆቿ ጡቷን ስታሽ ስትምል፣

ገዥም ተገዥው ላይ መሳሪያውን ሲስል፤

ከንፁኀን ሰፈር ሲወርድ የቦምብ ናዳ፣

ከባህታዊያን ደጅ ፈንጅ ሲፈነዳ፤

?እረኞች? በጎችን ከጋጥ ሲያባርሩ፣

በጎችም በረግገው ሲሉ ይብላኝ ዱሩ፣

ተኩላዎች በደስታ ሲጮሁ ሲያቅራሩ፤

መሬት ይህን አይታ ልቧ ሲደነግጥ፣

መሠረቷ ሲናድ አቋሟ ሲናወጥ፣

መላው አካላቷ ሲሼክ ሲንቀጠቀጥ፤

ሰማይ ሆዱ ባባ ሰውነቱ ራደ፣

ጥፋቱን አመነ አመዱን አመደ፣

"ማሩኝ ልካሥ" አለ ለመነ ማለደ፣

በዝናቡ ፈንታ ዐሣን አወረደ።


                                    ጌታነህ ካሴ
                                    ጥር  25/2008ዓ.ም    

Tuesday, February 02, 2016

ብላቴናው አይዞኝ

ፊቱን ቢያዞርብህ ሙድ ቢይዝ ዘመኑ፣
ብላቴናው አይዞኝ ያልፋል ሰቀቀኑ።
በርታ ጠንክር የሚል ባይኖርም ከጎኔ ፣
ሁለት  ሃብታት አሉኝ ችግር እና ወኔ።
ለአቡነ ተክሌ ክንፍ ለያዕቆብ መንሰላል፣
አይሳነው ልዑል  ሁሉንም ያድላል ።
ለ'ኔም በዝቶልኛል ጸጋ በረከቱ፣
ቢያድለኝ ቢያድለኝ ባይረካ ስሜቱ፣
ወኔን ደረበልኝ ማጣትን በብርቱ።
           
                        ጌታነህ  ካሴ

Saturday, January 30, 2016

አስተርእዮ ለማርያም

በዓሉ አስተርእዮ መባሉ ግን ሁለት ነገርን ያሳያል አንድ ወራቱ ማለት ጥር ጌታችን በጥምቀቱ ምስጢረ ሥላልሴን ከዚያም ጋር አምላክነቱን ለዓለም የገለፀበት በመሆኑ ሲሆን ሁለተኛ የአምላክ እናት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አምላክን በወለደችበት ስብሐተ መላእክትን በሰማችበትና ባየችበት የልደት ወራት  አካባቢ ከዚህ ዓለም በሞት ተለታ ወደ ሰማይ ስትወጣ በስማይም በምድርም ለሰውም ለመላእክትም  ከልጇ ከኢየሱስ ክርስቶስ ከባሕርይ አባቱ አብ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ የተሰጣት ጸጋና ክብር መገለጡን ያሳያል "አስተርእዮ" ማለት መታየት መገለጥ ማለት ነውና።የኢትዮዽያ ሊቃውንት በዚህ ቃል ሐሳባቸውን ያስተባብራሉ ቅዱስ ያረድ አምላክ ከድንግል በሥጋ መወለዱን በዚህም በአካለ መጠን ለዓለም መገለጡን አተርእዮ ብሎ ሲናገር ሌላው ደግሞ{ደራሲ ሊቅ }የትንቢት አበባ እግዚአብሔር የእኛ ሥጋ የሆነውን ያንቺን ሥጋ ለብሶ በምድር እንደተገለጠ ለእኛም እንደታወቀ ድንግል ሆይ የመገኛችን መመኪያ ዛሬ ለእናታችን ለማርያም በሰማይ በፍጹም ደስታ መገለጥ ሆነ እያልን እናመሰግንሻለን ብሏል።እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጥር 21 እሁድ ቀን በ49 ዓ.ም በ64 ዓመቷ አርፋ ከዚህ ዓለም ወደ ዘለዓለማዊ ህይወት በምትሸጋገርበት ዕለት{በዕረፍቷ ቀን} ቅዱሳን ሐዋርያት አስከሬኗን ወደ ጌተሴማኒ መቃብር በሚወስዱበት ጊዜ አይሁድ ለምቀኝነት አያርፉምና ከዚህ ቀደም ልጇን ኢየሱስን "ሞተ፣ ተነሳ፣ አረገ ደግሞ በክፉወችና በበጎወች ለመፍረድ ይመጣል" እያሉ ሲያውኩን ነበር። አሁን ደግሞ ይህችን እናቱን ዝም ብንል "ሞተች ተነሳች" እያሉ ሊያውኩን አይደል አሁንም "ኑ በእሳት እናቃጥላት" ብለው ከእነርሱ መካከል አንዱ ታውፋኒያ ወይም ሶፍንያስስ የሚባለውን ልከው አስከሬኗን ለማቃጠል የተጠቀሰው ሰው ተረማምዶ በድፍረት የአልጋውን ሸንኮር ሲጨብጥ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል ከሁለት ትክሻው በሰይፍ ቀጣው። ሁለቱ እጆቹም ከአልጋው ሸንኮር ላይ ተንጠልጥለው ቀሩ።ይህም ቅጣቱ ስላስደነገጠው በይበልጥም ምክር ስለሆነው ወዲያውኑ ልጇ ኢየሱስ ክርስቶስ የባህርይ አምላክ እርሷም ወላዲተ አምላክ መሆኗን አምኖ በልጇ ቸርነት በእርሷ አማልጅነት ተማምኖ ምህረትና ይቅርታን ስለለመነ በቅዱሳን ሐዋርያት ጸሎት በእመቤታችን አማላጅነት እጁጆቹ እንደነበሩ ተመልሰውልታል።ሥጋዋንም ቅዱሳን ሐዋርያት ለጊዜው ጌቴሴማኒ በተባለው ቦታ አሳርፈውታል በሶስተኛው ቀን ግን መላእክት ከዚያ አፍልሰው  በገነት በዕፀ ህይወት ስር አኑረውታል።ከመቃብር እስከተነሳችበት ዕለት ድረስ ለሁለት መቶ  አምስት ቀኖች በዚያው ቆይቷል።ክርስቶስ ለሚመጣበት ለ2500 ዓ.ም ምሳሌ ነው። 200 የ 2ሽህ 5ቱ የ500 በዚህ ጊዜ የሰው ሁሉ ትንሳኤ ይሆናል።በዕለተ እረፍቷ ብዙ ፍጹም በረከት ተሰጥቷል።የፈውስ ጸጋ ከደረሳቸው አንዱ ታውፋንያ ነው።በዚህ ዕለት የተደረገውን ሁሉ የታሪክ መጻህፍት ዘርዝረው ያስረዳሉ።በዚህ የተጠቀሰው ግን በአጭሩ ነው።ስለዚህ በእረፍቷ ምክንያት ጥር 21 ቀን የተጀመረው በዓል መታሰቢያ በየወሩበ 21 ቀን እንዲታሰብ የኢትዮዽያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሥርዓት ስለሆነ ወሩ በገባ በ21ቀን የእረፍቷ በ29 ቀንም አምላክን የመውለዷ መታሰቢያ ይከበራል።ይህም በቀድሞ መባቻ በዓል ፈንታ የገባ ነው። ያ ጥላ ምሳሌ ስለነበር አምናዊ ተተክቶበታል።

                                                                        ምንጭ፦መጽሐፈ ታሪክ ወግስ

Wednesday, January 27, 2016

ቀና በል ቀን አለ

ሽንፈትህ ቢነገር ገዝፎ እንደ ተራራ፣
ስህተትህ ቢተረክ መውደቅህ ቢወራ።
ተዋርዶም ተንቆም ሰው መሆን ስላለ፣
አንገትህን አትድፋ ቀና በል ቀን አለ።

             ይህ ግጥም ከ"hand out" ጀርባ ላይ የተገኘ ነው ።

Tuesday, January 12, 2016

ጣፋጭ ፍሬን ላፍራ

የልቤን ቋጠሮ ቂም በቀል አንስተህ፣
ክፋት ምቀኝነት ቁጡነቴን ፍቀህ፣
መራሩን አንደበት በጣፋጭ ለውጠህ፣
ቀና ሰው እንድሆን ይጎብኘኝ መንፈስህ።
ቁጥቋጦ ቋጥኙ ይመንጠር ይወገድ፣
ሸክፈው ምላሴ በቃልህ ይሞረድ፣
ጉልበቴ ይንበርከክ ሰውነቴም ይራድ፣
መንፈስህ ይኑረው በልቤውስጥ መንገድ።
ቀዳዳው ተደፍኖ  ጎድጓዳው ይሞላ፣
ትዕቢትን ይናቀው ጥልቻንም ይጥላ
ትሕትናን በመልበስ ጥል ከእሱ ይከላ፣
መቅደስህ እንዲሆን መላው የእኔ ገላ።
ሕሌናዬ ሁሉ በጎ ነገር ያውጣ፣
በፊትህ የሚኖር ከህግህ ያልወጣ።
መልካም መሬት ይሁን የልቦናየ እርሻ፣
ጥፋጭ ፍሬን ላፍራ እስከመጨረሻ።


                      ምንጭ ፦ሐመር ዘኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነሐሴ 2004ዓ.ም

Friday, January 08, 2016

ተወልደ ኢየሱስ በቤተልሔም ዘይሁዳ

 

      በጌታችን በአምላካችን በኢየሱስ ክርስቶስ የተደረገልን ሥርየትና ዕርቅ ግልጥ ሆኖ የተጀመረው በነገረ  ልደት ነው።የጌታችን ልደት በነገረ ድኅነት ትልቅ ስፍራ የያዘና እግዚአብሔር ሰው ሆኖ ዓለምን ያዳነበት ጥበቡ ፍጹም ልዩ መሆኑን ያሳየ ነው።መስተፃርራን የነበሩ ሰማይና ምድር፣ሰውና መላእክት በአንድነት ለምስጋና ታድመዋል።የእረኞች አንደበት  ከመላእክት ጋር ለሰማያዊ ምስጋና ብቁ የሆነበት፣ግዕዛን የሌላቸው እንስሳት ሰራኢ መጋቢያችን፣በዘባነ ኪሩቤል በሰማያት የምትገለጥ አንተ ነህ ሲሉ እስትንፋሳቸውን የገበሩለት፣የምድር ነገስታት በስልጣንህ ሽረት በመንግስትህ ህልፈት የሌለብህ የነገስታት ንጉስ አንተ ነህ ሲሉ ወርቅን ለመንግስቱ፣ዕጣንን ለክህነቱ፣ከርቤን ለሕማሙ ዕጅ መንሻ ያበረከቱለት፣ወላዲተ አምላክ ቅድስት ድንግል ከጻድቁ ዮሴፍ ጋር ያን ልዩ ክብር ያዩበት፤ይህ ልደት በእውነት ልዩ ነው።ቅዱስ ኤፍሬምሶሪያዊ በረቡዕ ውዳሴ ማርያም በጌታ ልደት የተደረገልን ድንቅ የማዳን ስራ በተናገረበት ድርሳኑ እንዲህ ነበር ያለው፦"በጨለማና በሞት ጥላ ውስጥ ለሚኖሩ ሰዎች ታላቅ ብርሃን ወጣላቸው፤በቅዱሳን የሚያድር እግዚአብሔር እኛን ለማዳን ልዩ ከሆነች ድንግል ሰው ሆኗልና ኑ ይህንን ድንቅ እዩ፣ስለተገለጠልን ምስጢር ምስጋና አቅርቡ ሰው ያማይሆን ሰው ሆኗልና ቃል ተዋህዷልና ቅድምና የሌለው ሥጋ ጥንታዊ ቀዳማዊ ሆነ፣ዘመን የማይቆጠርለት መለኮት ዘመን ተቆጠረለት።" ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ "ይህች ቤተልሔም መንግስተ ሰማያትን መሰለች" አለ፤የጌታን ልደት በተናገረበት አንቀጽ።በአባታችን በቀዳማዊ አዳም ምክንያት ያጣናትን ልጅነት ሊሰጠን ዳግማዊ አዳም ክርስቶስ የመንግስተ ሰማያትን የምስጋና ኑሮ በቤትልሔም ገልጧልና።ስለዚህ ነገር ነብየ እግዚአብሔር ሚክያስ  "አንቺ ቤተልሔም ኤፍራታ አንቺ ከይሁዳ አእላፍ መካከል ትሆኝ ዘንድ ታናሽ ነሽ  ከአንቺ ግን አወጣጡ ከቀድሞው ጀምሮ ከዘላለም የሆነ በእሳራኤል ላይ ገዥ የሚሆን ይወጣልና.." በማለት የተነበየውም ስለዚህ ነበር፤ሚክ5፡2 "ወአንቲኒ ቤተልሔም ምድረ ኤፍራታ ኢትቴሃቲ እምነገሥተ ይሁዳ እስመ እምኔኪ ይወጽእ ንጉስ ዘይርዕዮሙ ለህዝብየ እስራኤል" እንዲል ቅዱስ ኤፍሬም።