Monday, June 10, 2019

ከከፍታ በላይ

ሰነፍ በሚገዛት የበርባኖች ሀገር በዚች የጉድ ምድር
ጡንቻን በምትመግብ ጭንቅላት ፆም ሲያድር
ሊቃውንት ተንቀው ማይም ቢከበርም
መማር ካለመማር ሳይሻል አይቀርም
.
ዳሩ ምን ዋጋ አለው
"እውቀት ያለ ተግባር" ጭንቀት ይጨምራል
ያለቦታው ሲያድግ ዱባም ይማረራል
ሊቅስ በአላዋቂ ኧረ እንዴት ይመራ'ል?
.
በአደባባይ ሲፈስ   ምሬትህ ገንፍሎ
የቀደዱልህ ቦይ አይያዝህ ጠቅልሎ
በሚመክሩህ መንገድ አትሂድላቸው
ለምሳ ሲያስቡህ ለቁርስ አድርጋቸው
በግራ ሲያጠምዱህ በቀኝ ቅደማቸው
.
ማቃጠል ነው እንጅ  ማንደድ እንደረመጥ
ከጨቋኝ እግር ስር
የምን መልወስወስ ነው የምን መለማ መጥ
ለውጥ ያስፈልጋል ነው ጭማሪ ያሻል ነው አነሰም ጎደለም
ለታካሚህ ስትቆም ገዳይ ቢንጨረጨር የሚገርም  አይደለም
.
ሰምተሃል አንተን ነው ምንድን ነው ዝምታ
በአሽኮለሌ  ጩኸት በአሽቃባጭ ጫጫታ
በእንቅፋት በጉቶው ጉዞህ ካልተገታ
እውነትን ወግነህ ተሟግተህ ስትረታ
ከከፍታህ በላይ ደግሞ አለህ ከፍታ
.
ሰኔ 1/2011ዓ.ም
ዝቋላ ሆስፒታል