Saturday, May 12, 2018

ያማል 3

እና እደነገርሁሽ
የረዚደንት ቁጣ አይቶ መሳቀቁ
ሲኔር መጣ አልመጣ ሰውነት ማለቁ
ፖርተር ማፈላለግ ከነርስ መዳረቁ
ዱቲ አድሮ ለሞርኒንግ ሽር ጉድ ማለቱ
X ray ማስነሳት BF ማሰራቱ
የወለደች እናት ጫማ መፈለጉ
ሞቶ የወጣን ፅንስ "alive" ማድረጉ
ያለ ዲሰፖዜብል
ቪጎ ማስተካከል ካቴተር መንቀሉ
የደሞዝ ቅናሹን አምኖ መቀበሉ
ምን ብዬ ልንገርሽ ያማል ይሄ ሁሉ
ታማሚ አስታሚ ወላጅ አስወላጁ
አጥማቂ ሰቫኪው አስቀዳሽ ሰጋጁ
የፈቃድ ባርነት በአንድነት ሲያውጁ
ጨካኝ በበዛባት በዚች የምጥ ዓለም
ከዚህ የበለጠ ሌላ ህመም የለም
ጌች ቀጭኑ ዘታችቤት 02/09/10

Tuesday, May 08, 2018

ተፈስሒ በሏት

ፀሐይን  የምትወልድ ውብ ደማቅ ጨረቃ፣
ቀድመው ያኸለሟት ቴክታና ጴጥርቃ፤
እናትና ገረድ ድንግልና ሰማይ፣
ሐመልማልና እሣት ሐርና ወርቅ ፈታይ፤
መሰረታቲሃ ውስተ አድባር  ውእቱ፣
ብሎ ያወደሳት ዳዊት በትንቢቱ፣
ተወልዳለችና የአምላክ እናቱ፣
ከበሮ ይመታ ይድመቅ ማኅሌቱ።
ጠላት ኃይሉን ይጣ ይንቀጥቀጥ ዓለሙ፣
የሕርያቆስ  ልጆች ድምፃችሁን አሰሙ፣
ተፈስሒ በሏት ካህናት አዚሙ።
ትንቢት  ተፈፅሟል ያስተጋባ ቃሉ፣
ተወልደ ብዕሲ በውስቴታ በሉ።
ጌች ቀጭኑ ዘታችቤት ግንቦት 1/2010 ዓ.

በለቅሶ  ሚዘሩ በደስታ  ያጭዳሉ፣
ብሎን  ነበር  ንጉሥ በማይሻር  ቃሉ፤
እንባችን  ፍሬ አጣ ዋይታችን መከነ ፣
ምነው  በኛ ዘመን ትንቢት  ቅዠት ሆነ?

ከተኩላዎች መሃል

በንፁህ  መነጽር ማስተዋል ለቻለ፣
ለአቤል  መስዋዕትነት  ቢላው  የተሳለ፣
ከተኩላዎች መሃል ንጹህ  በግም አለ።
እርም አርጎ ትቶ ጥንብን  ለጥንብ አንሳ፣
ወደ ላይ ለመምጠቅ ክንፉን የሚያነሳ፤
ብቻውን  የሚኖር በጆፌዎች መንደር፣
ለአመነበት ጉዳይ የማይደራደር፤
ስለ ድንቅ ብቃቱ  ብዙም ያልተባለ፣
በቁራዎች ሰፈር ነጭ ንሥር አለ።
ይውጠው  ይመስል  ድንቁርናን ቁጣ፣
አባት ለገደለው የልጅ ልጅ ሲቀጣ፤
ቀድሞ ሰው መሆኑን አውቆ የተረዳ፣
ታናናሾቹ  ላይ  ደርሶ   ማይፈነዳ፤
አውቆ ለማሳወቅ ሁሌም  የሚተጋ፣
በጎሜ በነገር  ሰውን  የማይወጋ፣
ከእግዜር  የተቸረ በፀጋ ላይ ፀጋ፤
ስሜትን  የሚያድስ የጥርሱ  ፈገግታ፣
ሰው  አየሁ  በህልሜ ትላንትና   ማታ።
ገጾች  ስገለብጥ  በህልሜ  መዳፍ ላይ፣
እንደዚህ የሚል  ቃል ይነበባል  ከላይ፤
እንደ ሣተኖቹ አንተም ሁን  ሣተና፣
እኩል  የፈጠረህ  የአዳም  ዘር  ነህና።

Ped OPD ይካቲ 17/2010 ዓ.ም ከሌሊቱ 7:30 ተፃፈ

Thursday, February 22, 2018

ልጆች ልከን ነበር

ልጆች ልከን ነበር ከተማ እንዲማሩ፣
ጨለማው ኑሮአችን በእውቀት እንዲያበሩ።
እነሱ እቴ ምርጦች ከሰው የተለዩ¡
እንኳን ቀለም ዘልቀው እውቀት ሊገበዩ፤ 
ያጵሎስ የጳውሎስ ብለው ሲለያዩ፣ 
የእምነት ቃላቸውን በክህደት ለውጠው፣
በብልጭልጭ ነገር በደስታ ተውጠው፣
በትምክህት በኩራት እንደተወጠሩ፣
የከፈቱትን በር ሳይዘጉት አደሩ፤
በሄዱበት መንገድ ሳይመጡበት ቀሩ።
አሁን ግን ነቅተናል ዘይደናል መላ፣
ማን ቁማር ይበላል ከእንግዲህ በኋላ?
ሴቷን በሚስትነት ለጦፈ ነጋዴ፣
ወንዱንም ማስጠበቅ ገዝቶ የበግ አዴ።
Farmed : 23/05/2010 ዓ.ም

Saturday, January 06, 2018

ሲዋንን ያለፈ

ከሰላም እንቅልፉ  ከምትቀሰቅሰው፣
ጓደኛህን በቁም አሁን  አሞጋግሰው፤
ብላ በምትመክረኝ በቀይዋ ብዕሬ፣
በጥዋት ተነሳሁ ላሞካሽህ  ዛሬ።
ልክ እንደ አባ ኮስትር እንደ በላይ ሁላ፣
ካሰበበት ሳይደርስ ትጥቁ የማይላላ፣
ያበቅላል ወንድ ልጅ ዱር ቤቴ ዳንግላ።
አንዱ በሃይማኖት ሌላው በሰፈሩ፣
አንገቱን ሊያስደፉት  ሲለፉ ሲጥሩ፣
ገድለው ሊያዳፍኑት ጉድጓድ ሲቆፍሩ፤
ጀግና የጀግና ዘር መሆኑን ሳያውቁ፣
በቆፈሩት ጉድጓድ እየገቡ አለቁ።
የጎጃም እናቱ አትውለጅ ምከኝ፣
እንደ በላይ ጀግና ከንቱ ላታገኝ።
የሚል ጎጅ ምክር አልመክርሽም እኔ፣
በፍቅሩ ሰው ገዳይ እያየሁ ከጎኔ።
አርግዥ እንጅ ጸንሽ ውለጅ መንታ መንታ፣
ተከብሮ  ሚያስከብር በቆመበት ቦታ፣
አውቆ የሚያሳውቅ ተሟግቶ ሚረታ።
ጀግንነትን በጦር ያደረገው ማን ነው?
ወንድነትን በሰይፍ ያደረገው ማን ነው
?
ወድቋል በቃ ሲሉት
ሲዋንን ያለፈ ለእኔ እሱ ጀግና ነው።
ጅማ ጤና ጣቢያ: ታኅሣስ 13/2010 .

Friday, January 05, 2018

ሽርሙጥና

ሽርሙጥና ይቅር ያለው ማነው ደፍሮ?
ብቻውን ይከርማል ጉዱ ነው ዘንድሮ።
ሽፍታ በሚገዛት አንኳን በዚች ምድር፣
ጡንቻ በምትመግብ ጭንቅላት ፆም ሲያድር፣
ለጊዜው ባለ አባት ክብሩን የገበረ፣
በዓለመ መላእክት ሸርሙጣ ነበረ።
ተፈጥሮም እንደ ሰው ትሸረሙጣለች፣
ለጠንካራ ክንዶች ምስጢር ትገልጣለች፤
ለሃይለኞች ብቻ ክብሯን ትሰጣለች።
ፍትሕ አይገባውም እግዜሩም ያዳላል፣
ከሌለው  ላይ ወስዶ ላለው ይጨምራል።
ኪሱ ለወፈረ ትክሻው ለሰፋ ቢሰጥ ድንግልና፣
ታዲያ ምኑ ላይ ነው ነውሩ ሽርሙጥና???
ታች ቤት ታኅሣስ 22/2010 ዓ.ም