Friday, September 28, 2018

ውረድ ከመንበሬ

ምነው ይጨንቀኛል ባርባር ይለው ሆዴ?
ትውልዴ ተቆጥሮ ልሳኔ ተጣርቶ ላይቀር መታረዴ
ምነዋ መስገብገብ ለነፍሴ መጓጓት መኖርን መውደዴ?
ወልዳ መሳም ላትችል ነፍሰ ጡሯ እናቴ
እስከ መቼ ድረስ
አንገቴን ላቀርቅር ይንበርከክ ጉልበቴ
ሰላም ላውርድ ብዬ ሀገር ላቅና ብዬ
ፈገግ ብዬ ባቅፍህ ደስ ያለኝ መስዬ
ያረድኸው ወንድሜ ደሙ ሲከረፋኝ
መግደል መሸነፍ ነው ብለህ ብትደልለኝ
እንዴት አልናደድ እንዴትስ አይከፋኝ
እንዴት አይዘን ልቤ እንዴት አይገምልለኝ
በርግጥ አውቂያለሁ ገብቶኛል ጥፋቴ
ሀገሬን ለቁራ አደራ መስጠቴ
የቁራ ልጅ ቁራ ቁራ የወለደው
ከመገንባት በፊት ማፍረስ የለመደው
አመራር ላስተምር አገዛዝ ላለምደው
ሀገር አቅና ብዬ መንበር ላይ ብጥደው
መሰረቱን ጣለ
ቤት ሊሰራ ነው ስል ያው መልሶ ናደው
የባለጌ ክንዱ ቢሆንም ደንዳና
ማፈራረስ እንጅ መስራት የት ያውቅና
የጋለሞታ ልጅ ያልተቆነጠጠ
ተለቅቆ ያደገ ተሳድቦ እየሮጠ
አጥፍቶ በመጥፋት ሆኖ አስተዳደጉ
መናድ ይመስለዋል  የነጻነት ጥጉ
ውረድ ከጫንቃዬ ከእንግዲህ  ይበቃል
የሚያጠግብ እንጀራ ሊጡ ያስታውቃል
እርካቤን ወዲህ በል ውረድ  ከመንበሬ
አርማዋ ከፍ ይበል በደም ያቆየኋት ኢትዮጵያ ሀገሬ
 ኪቶመስከረም 8/2011 .