Monday, June 27, 2016

ታማችኋል !!!

በአፍላ ትጀምራላችሁ በወረት ትተውታላችሁ። ያወቃችሁትን ትረሳላችሁ ያላወቃችሁትን ለማወቅ ትጥራላችሁ፤የያዛችሁትን ትረግጣላችሁ፤የረገጣችሁትን ትይዛላችሁ፤ምኞታችሁ ልክ የለውም፤አምሮታችሁ ብዙ ነው።የአማራችሁን ስታገኝ ወዲያው ይሰለቻችኋል።ተው የተባላችሁትን ትሽራላችሁ የተከለከላችሁትን ትደፍራላችሁ፤የተፈቀደላችሁን ችላ ትላላችሁ።ቤተመቅደስ እንዳትገቡ ብትከለከሉ ወደ ፊት ቤተመቅደሱን በመስታውት ሰራታችሁ ቤተመቅደስ ባትገቡም እንኳን ሁሉን ከወጭ ሆናችሁ ማየት ትፈልጋላችሁ።ሁሉንም ማወቅ ትፈልጋላችሁ በአንዱም ግን አትጠቀሙበትም።ሁሉም አላችሁ ግን ባዷችሁን ናችሁ።ሃይማኖት እንጅ እምነት የላችሁም።

መድሃኒት ባሳይህ መቀመሚያውን ነገሬህ ማርከሻውን ሳልገልጥልህ መጀመሪያውን ብቻ ሞጭልፈህ ትተኸኝ ትሄዳለህ።ጥበበን "ሀ ግእዝ "ብየ ላስተምርህ ብሞክር  መንደር ውስጥ በቃረምካት እውቀትህ ተመክተህ በመሰላቸት "ሆ ሳብዕ" ብለህ ቀድመህ ትዘጋዋለህ። የግል ታሪካችሁ ቢታይ ወጥነት የጎደለው ከዚህም ከዚያም የተልከፈከፈ የተማሪ ኮፈዳ ውስጥ ያለ እህል ይመስላል።ተምራችሁ እውቀት ስታገኙ ሰርታችሁ ገንዘብ ስታፈሩ ከላይ የሆናችሁበትን ሃገር ለቃችሁ "ሰፋ ወዳለው እንሂድ" ብላችሁ እንደገና ከታች ትጀምራላችሁ።ትቀጥላላችሁ በመጨረሻ ከጀመራችሁበት ትገኛላችሁ ።ቸኩላችሁ ትወስናላችሁ ወዲያው ትጸጸታላችሁ።በጽኑ ታማችኋል።

Wednesday, June 22, 2016

ኦርቶዶክሳዊ የቅዱሳት ሥዕላት አሣሣል

ቅዱሳት ሥዕላት "ቅዱስ" እና "ሥዕላት" ከሚሉት ቃላት የተገናኘ ወይም የተሰናሰለ ቃል ሲሆን፤ሥዕል በቁሙ፣ መለክ፣ የመልክ ጥላ፣ንድፍ፣አምሳል፣ንድፍ ውኃ፣በመጽሔት፣ በጥልፍ፣በስፌት ወይም በቀለም በወረቀት ገዝፎ ተጽፎ፤ከእብን ከእፅ ከማዕድን ታንጦ፡ተቀርጦ ተሸልሞ አጊጦ የሚታይ የሚዳሰስ ነገር ነው።(ኪ.ወ.ክ፡673) ሥዕል ነጠላ ሲሆን ሥዕላት ደግሞ ብዛትን ያመለክታል።ቅዱሳት የሚለው ቃል ደግሞ "ቀደሰ" ከሚለው የግእዝ ግሥ የተወሰደ ሲሆን ትርጉሙም  ለየ፣አከበረ፣መረጠ ማለት ነው።ከዚህ በመነሳት ቅዱሳት ሥዕላት ለእግዚአብሔር የተለዩ፣የተቀደሱ፣ ልዩ፣ ምርጥ፣ንጹህና ጽሩዕይ የሆኑ የቤተመቅደሱ መገልገያ ንዋያተ ቅድሳት በመሆናቸው ቅዱሳት ተብለው ይጠራሉ።

ዳግመኛም የቅዱሳንን ታሪክና ማንነት በጊዜው ላልነበርን በመንፈስ ዓይን ፤እንድናይ ስለሚያደርጉን፤አንድም ሥጋዊውን ዓለም ከሚያንጸባርቁ ዓለምውያን ሥዕላት ፈጽመው የተለዩ በመሆናቸው፤አንድም የቅዱሳኑ ቅድስና ሥዕላቱን ቅዱስ ስላሰኛቸው፤አንድም በሥዕላቱ አድሮ እግዚአብሔር ስለሚፈጽማቸው ገቢረ ተዓምራት የተነሳ ሥዕላቱ "ቅዱሳት ሥዕላት" ተብለው ይጠራሉ።በአጠቃላይ በኢትዮዽያ ኦርቶዶክስ ተውህዶ ቤተ ክርስቲያን "ቅዱሳት ሥዕላት" ተብለው የሚጠሩት የቅዱስ እግዚአብሔር፣ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ፣የቅዱሳን መላእክት፣የቅዱሳን ነቢያት፣የቅዱሳን ሐዋርያትና የሌሎች ቅዱሳን ጻድቃን ማንነት ሕይወትና ታሪክ የሚያሳዩ ሥዕሎች ናቸው።ቤተክርስቲያን ሐዋርያዊት እንደመሆኗ መጠን የምትፈጽማቸው አገልግሎቶችና ሥርዓቶች ዶግማና ቀኖናን እንዲሁም ትውፊትን መሰረት ያደረጉ ናቸው።ይህ ደግሞ ኦርቶዶክሳዊያን ቅዱሳት ሥዕላት በእግዚአብሔር ፈቃድ ሐዋርያዊ ቀኖናን ተከትለው የሚሳሉ የቤትክርስቲያን ንዋያተ ቅዱሳት ናቸው እንጂ እንዴው በዘፈቀደ የሚዘጋጁ የኪነጥበብ ስራወች አለመሆናቸውን ያስገነዝባል።

Monday, June 13, 2016

ዩኒቨርሲቲ መግባት፡ ምርምርና ሀልዎተ እግዚአብሔር

ተማሪ ወደ ከፍተኛ የትምርት ተቋም የሚሄድበት ዋና ዓላማው ጽንሰ ሃሳባዊውንና ተግብራዊውን የዕውቀት ውኃ ምንጭ ከሚሆነው ተቋሙ ለመቅዳትና ለሚጠበቅበት የነገ ኃላፊነት ማዋል እንደሆነ እሙን  ነው።በዩኒቨርሲቲ ቆይታውም ትምህርቱን ለመቀበልና ተመርቆ ለመውጣት ከሚያስችሉ ነገሮች አንዱ ለእውቀት የተዘጋጀ አእምሮ ይዞ መገኘቱ ነው።ይህ ለእውቀት የተዘጋጀ አእምሮው በእውቀት መጎልመስን ጨምሮ ለተለያዩ ጠቃሚ ምርምሮች፣የፈጠራ ስራዎች፣ አዳዲስ አስተሳስቦችና የችገር ምልከታዎች እንደሚያበቃ በሁሉም ማህበረሰብ ዘንድ ይታመናል።ሆኖም ይህ ለእውቀት የተዘጋጀ አእምሮው በራሱ በትምህርቱ ሂደትም ይሁን በዙሪያው ከበው በሚገኙ ተጽዕኖዎች የተነሳ በአሉታዊ መልክ ተቀርጾ ከመነሻው በተቃራኒ እንዲቆም ሲደረግ ይስተዋላል።በዙሪያው ከበው የሚገኙትን ተጽዕኖዎች የዛሬ ትኩረታችን ባለመሆናቸው በመተው በራሱ በትምህርቱ ሂደት ውስጥ የሚመጡትን ተያያዥ ተጽዕኖዎች ብቻ ለማንሳት እንሞክራለን።ይህም ዘመናዊ ትምህርትንና ሳይንሳዊ ምርምሮችን አዝለው የሚመጡት ሃይማኖት አልበኝነትና የግብረገብነት ችግሮች መንፈሳዊ ሰው እንዴት ማየትና ማለፍ አለበት እኛስ ምን ምን ቅድመ ዝግጅቶችን ማድረግ ይጠበቅብናል?፤ትምህርቶቹስ በራሳቸው ከሃይማኖት የሚያርቁ ናቸውን? የሚሉትን በተወሰነ መልኩ ለማየት እንሞክራለን።

Thursday, June 09, 2016

ጥበብ ያልተቀላቀለበት ትምህርት!

መምህሩ የመግቢያ ሰዓቱን ጠብቆ ከበር ብቅ ሲል የተማሪው መንፈስ ይዋከባል። ሁሉም ባለው ቶሎ የመጻፍ ችሎታ መምህሩ የተናገሩን ሀሳብ ለመያዝ አስቀድሞ ደብተሩን ወይም ወረቀቱን ገልጦ ብዕሩን ደቅኖ ይጠብቃል። መምህሩ ንባቤ ቃላቸውን ሲጀምሩ ቀና ብሎ ለመመልከት ፋታ ያለው ተማሪ አይገኝም። ጠቃሚውን መርጦ መጻፍ ያልተለመደ ነገር ነው። ሁሉንም ለቅልቆ መገኘት ለጥናት ባይጠቅምም ሙሉውን ጽፌዋለሁ በሚል መተማመን ሊመጣ የሚችለውን መደናገጥ ይቀንሳል። ግማሽ ሰዓት ሳይተኙ ተኝቸ ጊዜየን አባከንኩት በሚል ስሜት ባንኖ መነሳት፣የወረቀት ኮሽታ በተሰማ ቁጥር አጥንተው ነጥቡን ሰቀሉብኝ በሚል ሰቀቀን ተነስቶ ከወርቀት ጋር መፋጠጥ፣ከምግብ ጠረዼዛ ወደ መታጠቢያው  የሚወሰደውን የምግብ ሰሀን ይዞ ወደ ውጭ መውጣት፣በመንገድ ላይ እያሉ ድንገት ደብተርን መግለጥ ቋሚ ክስተቶች ናቸው።

የውጥርቱንና የነገሩ ትኩሳት የሚጨምሩት ደግሞ ስራቸውን በወቅቱ ማጠናቀቅ ያልቻሉ ወይም በማጣደፋቸው ተማሪን የበደሉ የማይመስላቸው ወይም ከሃላፊነት ይልቅ የግል ጥቅም አድልቶባቸው ጠፍተው የከረሙ መምህራን ናቸው።"ተጨማሪ ክፍለጊዜ ያስፈልገናል" በማለት በተማሪ መዋከብ የራሳቸውን ክብር የጨመሩ የሚመስላቸውም ጥቂት አይደሉም። ታዲያ ሴሚስተሩ ሲያልቅ እንደጠጠሩ ሳይብራሩ የሚያልፉትን ሃሳቦች ጠያቂ የላቸውም።የሚጠይቅም ካለ እንደ ጊዜ አባካኝ ይቆጠራል። ይህ አይነቱ ንዴት ተጨማምሮበት "ለምን ብዙ ክፍለጊዜ አቃጠሉብን?" በማለት ለመጠየቅ ደግሞ መምህሩ ለሚወስድበት እርምጃ የሚከራከርበት መንገድ የለውምና ይሰጋል። በተማሪዎችም ዘንድ በማያውቀው ውይይት ገብቶ እንደዘባረቀ ተናጋሪ ወይም  መምህሩን ተዳፋሪ ተቆጥሮ ይሳቅበታል።በአንፃሩ እንደ አዋቂ የሚቆጠረው መምህሩ ፈተና የሚያወጣበትን አካባቢና የፈተናውን አይነት አጠያይቆ ማወቅ የቻለ፣የሚቻለውን ሞክሮ ፈተናውን ከሚራባበትና በምስጢር ከሚቀመጥበት አስወጥቶ ማየት የቻለ ነው።