Friday, February 26, 2016

ስማችሁ የለም

በሰማያዊው ዙፋን ዘንድ አንድ ውሳኔ ተላለፈ፡፡ «እነዚህ የኢትዮጵያ ሰዎች ሃይማኖተኞች ናቸው፡፡ ስለዚህም ዓለም ከማለፉ በፊት አስቀድመው ተጠርተው ዋጋቸውን ሊቀበሉ ይገባል» የሚል፡፡ አንድ ሊቀ መልአክ እልፍ አእላፍ መላእክትን አስከትሎ ከሰማይ ሲወርድ ታየ፡፡ በኢትዮጵያ የሚኖሩ ሰዎችንም ሁሉ ለሰማያዊ ፍርድ ሰበሰባቸው፡፡ ወዲያውኑ በመንግሥተ ሰማያት በር ላይ ሁለት ዓይነት ሰልፎች ታዩ፡፡ አንደኛው ሰልፍ ረዥም፤ ሌላኛው ሰልፍ ግን አጭር ነበር፡፡ ረዥሙ ሰልፍ ባለበት ቦታ ገበሬዎች፣ ወዛደሮች፣ የዕለት ሥራ ሠራተኞች፣ እናቶች፣ አባቶች፣ ሕፃናት፣ ሊስትሮዎች፣ የቤት ሠራተኞች፣ ሾፌሮች፣ መሐንዲሶች፣ ሐኪሞች፣ አስተማሪዎች፤ ማን ያልተሰለፈ አለ፡፡ ከጥቂቶቹ በቀር ብዙዎቹ መንግሥተ ሰማያት የመግቢያ ካርድ ማግኘት ቻሉ፡፡ይህንን ሁኔታ ሲመለከቱ በአጭሩ ሰልፍ በኩል የተሰለፉት የልብ ልብ ተሰማቸው፡፡ መጀመርያውኑ ለብቻቸው ሰልፍ የሠሩት ከሕዝብ ጋር ላለመደባለቅ እና ላለመምታታት ብለው ነበር፡፡ እንዴት ሲያስተምሩት፣ ሲያስመልኩት፣ሲያስሰግዱት፣ ሲያሳልሙት፣ ከኖሩት ሕዝብ ጋር አብረው ይሰለፋሉ? መጀመርያ ነገር እነርሱ ያስተማሩት ሕዝብ መንግሥተ ሰማያት ከገባ እነርሱ የማይገቡበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ ሁለተኛ ደግሞ ወደፊትም ቢሆን በመንግሥተ ሰማያት ለየት ያለ የክብር ቦታ ሊጠብቃቸው ስለሚችል ለየት ብለው መሰለፋቸው ተገቢ ነው፡፡


ይህንን እያሰቡ እና እያወሩ እያለ አንድ መልአክ ወደ እነርሱ ሰልፍ መጣ፡፡ተሰላፊዎቹ በኩራት ገልመጥ ገልመጥ አሉ፡፡ እንዲያውም «ከመካከላችን ማን ይሆን ቀድሞ የሚገባው» የሚለው ነገር ሊያጨቃጭቃቸው ነበር፡፡ አንዳንዶች በተከታዮቻቸው ብዛት፣ አንዳንዶች በነበራቸው መንፈሳዊ ሥልጣን፣ አንዳንዶች ባገኙት የካሴት እና የመጽሐፍ ገቢ፣ ሌሎችም በሕዝቡ ዘንድ በነበራቸው ተደናቂነት፣ የቀሩትም ደግሞ በንግግር እና በድምጽ ችሎታቸው እየተማመኑ እኔ እበልጣለሁ እኔ እቀድማለሁ ሲባባሉ መልአኩ «እናንተ እነማን ናችሁ?» የሚል ያልተጠበቀ ጥያቄ ጠየቃቸው፡፡ ሁሉም መልአክነቱን ተጠራጠሩት፡፡ አገር ያከበራቸውን፣ሕዝብ ያረገደላቸውን፣እነርሱን ለማየት እና ለመንካት አዳሜ የተንጋጋላቸውን፣ በየፖስተሩ፣ በየካሴቱ፣ በየመጽሐፉ፣ በየመጽሔቱ «ታዋቂው» እየተባሉ ሲቀርቡ የኖሩትን፤ ሰይጣን ያወጣሉ፣ መንፈስ ይሞላሉ፣ ጠበል ያፈልቃሉ፣ እየተባሉ ሲያርዱ ሲያንቀጠቅጡ የኖሩትን፤ ሲዘምሩና ሲያስተምሩ ወፍ ያወርዳሉ የተባሉትን፤ ገንዘብ ከፍሎ መንፈሳዊ ቦታ ተሳልሞ ለመምጣት ሕዝብ ቢሮአቸውን ደጅ ሲጠናቸው የኖሩትን እነዚህን ጉምቱ ጉምቱ ሰዎች የማያውቅ መልአክ እንዴት ሊኖር ቻለ? ተጠራጠሩ፡፡«ለምንድን ነው ለብቻ ሰልፍ የሠራችሁት? ለምን ከሕዝቡ ጋር አልተሰለፋችሁም?» መልአኩ ይበልጥ የሚገርም ጥያቄ አመጣ፡፡ ተሰላፊዎቹ እርስ በርሳቸው ተያዩ፡፡ ከመካከል አንድ በነገሩ የተበሳጨ ሰባኪ «እንዴት እንደዚህ ያለ ጥያቄ በዚህ በመንግሥተ ሰማያት በር ላይ እንጠየቃለን? እስካሁንም ተሰልፈን መቆየት አልነበረብንም፡፡ እኛን ለመሆኑ የማያውቅ አለ? ስንት ሕዝብ ያስከተልን ሰባክያን፤ ስንት ሕዝብ የፈወስን አጥማቂዎች፣ ስንት ሕዝብ ያስመለክን አስመላኪዎች፣ ስንቱን ያስረገድን ዘማሪዎች፤ ስንቱን የታደግን ፈዋሾች፣ ስንቱን የመራን የእምነት መሪዎች፤ ስንቱን በባዶ እግሩ ያስኬድን ባሕታውያን፤ ስንቱን ለገዳም ያበቃን መነኮሳት፤ ሕዝብ ተሰብስቦ የሾመን «ሐዋርያት»፤ እንዴት እነማን ናችሁ ተብለን እንጠየቃለን?» ሁሉም በጭብጨባ ደገፉት፡፡

Saturday, February 20, 2016

ከዘንዶ አፍ የወጣች ርግብ

በወላጆቼ ቁጥጥር ስር አጥቸው የኖርሁትን ነጻነት እስከማጣጥም ድረስ ስለጓጓሁ  የዩኒቨርሲቲት መግቢያ ቀን የተነገረ ዕለት የተሰማኝ ደስታ የተለየ ነበር። ከቤት ትምህርትቤት ከትምህርትቤት ወደ ቤት ከዚህ ውጭ የትም ቦታ መሄድ አይፈቀድልኝም። እናቴ ለትምህርት ካላት ፍቅርና ለነገ ማንነቴ ከምትሰጠው ከፍተኛ ግምት አንጻር ዩኒቨርሲቲት እንድገባ ታበረታታኛለች እንጅ ከእርሷ ርቄ እንድሄድ  አትፈልግም። አላቻለችም እንጅ ወደ ቅርብ ዩኒቨርሲቲ ለማስቀየር  ሁሉ አስባ ነበር። ዘንድሮ ከእስር የተፈታሁ ያክል ይሰማኝ ጀምሯል።ከቀናት በኋላ ግን ከጓደኞቼ ጋር በዲፓርትመንትም በመኝታም በመለያየታችን ብቸኝነት  እየተሰማኝ መጥቷል። ትምህርቱ የቡድን ስራው አስጨንቆኛል። ቀናት ነጎዱ ወራትም ተቆጠሩ፣መንፈቀ ዓመትም ሆነ። ቁንጅናየ የግቢው መነጋገሪያ እንደሆነ ከሰማሁ ጀምሮ በራሴ ብተማመንም ሕይዎት እያስጠላኝ፤የፈለጉትን በልተው ፤የልብስ ዓይነት የልብስ ፋሺን እያቀያየሩ የሚያጌጡ የግቢያችን ተማሪዎች ኑሮ እያስቀናኝ መጥቷል።"ሰሞኑን ደግሞ ምን በወጣሽ ነው ታፍነሽ የምትኖሪው? የምትሞችበትን ቀን ለማታውቂው ስለምን ራስሽን ታጨናንቂያለሽ ይልቁኑ እንደጓደኞችሽ ነጻ ሁኝ የቤትሽ ይበቃሻል። አንቺኮ ባትማሪም በቁንጅናሽ ብቻ ተከብረሽ መኖር የምትችይ ሴት ነሽ ። ስለዚህ ፈታ በይ" የሚል አንዳች ስሜት ያስጨንቀኛል።


በዚህ ላይ የሁለቱ ጓደኞቼ የተለያየ ምክር ግራ አጋብቶኛል። አንደኛዋ ጓደኛዬ ከቤተክርስቲያን የማትለይ፣ በግቢ ጉባኤ አገልግሎት የምሳተፍና ኮርስ የምትከታተል ታታሪ ተማሪ ናት። የሚገርመኝ ግን ሌሎች ተማሪዎች ሌሊትም ቀንም እያጠኑ የእርሷን ያህል ውጤት ማስመዝገብ አለመቻላቸው ነው። እርሷ ቤተክርስቲያን እንድሄድ፣ኮርስ እንድማር እንድጾም፣እንድጸልይ ብትመክረኝም እኔ ግን ምክሯን ለመቀበል አልፈልግም። ባገኘችኝ አጋጣሚ ሁሉ ስለምትመክረኝ ባላገኛት እመርጣለሁ። ሌላኛዋ ጓደኛየ ደግሞ ደስ ሲላት የምትማር፣ደስ ሳይላት የምትተኛ ፣አምሽታ የምትገባ፣ አርፍዳ የምትነሳ ሰነፍ ተማሪ ናት። በውጤት ግን በዚህም በዚያም ተሯሩጣ  ወይ [A] ያም ባይሆን [B] ታስሞላለች ። ስለምንም ስለማንም የማትጨነቅ ፣የወደደችውን የምታደርግ ሴት መሆኗና  ነጻነቷ ያስቀናኛል። እንደሷ እንድሆን የምታደርገው ጥረትም ተመችቶኛል። ድንግልናዬን ለባለሃብት ብሸጥ መክበር እንድምችል ፤ ከዚያ በኋላ ደስተኛ እንድምሆንና ጭንቀቴም እንደሚቀልልኝ  ከመከረችኝ ወዲህ ያለችኝን ሁሉ ማድረግ እንደሚገባኝ አምኛለሁ። የእናቴ የገቢ ምንጭ በመቀነሱ  ለኮፒ ለማስታወሻ መግዣና ለዓመት በዓል ካልሆነ በስተቀር በቂ ገንዘብ አትልክልኝም። ገንዘብ አልበቃሽ እያለኝ በወር የሚቆረጥልኝ ገንዘብ እያነሰ ቢመጣም ምኞቴ ግን እየጨመረ ሄዷል። ስለዚህም የአንደኛዋ ጓደኛየ ምክር ሕየወቴን ለመለወጥ ጥሩ አማራጭ እንደሆነ ተገነዘብሁና እርሷ ከመረጠችልኝ ሰው አስማማችኝና ቀጠሮ ይዘን ተገናኘን።

ትላንትና ዛሬ

ትላንት እንደቆሸሽኩ ዛሬም አላታጥብኩም፣
በንጽሕ ሰው አምሳል ሰው መሆን አልቻልኩም፣
የራሴን ሳሙና ከመሸጥ አልዳንኩም።
ትላንት በደለኛ ትላንት አረመኔ፣
አምና በሲዖል ውስጥ ዛሬም በኩነኔ፣
ቁሞ የወደቀ ማነው ልክ እንደ እኔ?
የበደሉ ቅርጫት የክፉ ሰው ጓዳ፣
ሰውን ቁሞ ወቃሽ የኃጢአት ባልዕዳ፤
የፈርሰ ጎጆ ዝናብ የሄደበት፣
ለመቆም ያልቻለ ጊዜው ያለፈበት።
ከዓመት ዓመት ሲበር በኃጢአት በወሬ፣
በሰው ላይ ስቀልድ እየኖርሁ አብሬ፣
ስላልሰራሁበት በንስሐ አድሬ፣
ትርጉም የላቸውም ትላንትና ዛሬ።
 

 

 

                  ምንጭ፦ ሐመር መጽሔት
                            ኅዳር 2006 ዓ.ም

Thursday, February 18, 2016

መንፈሳዊነት ምንድነው ?

ለመሆኑ መንፈሳዊነት ምንድን ነው? ረዥም ቀሚስ መልበስ ነው? ፀጉርን በአሮጌ ሻሽ መሸፈን ነው? ገላን ያለመታጠብ ነው? አንገትን መድፋት ብቻ ነው? ቀስ ብሎ መናገር ነው? ኋላ ቀርነት ነው? አይመስለኝም፡፡ ቴሌቭዥን አለማየት፣ኢሜይል አለመጠቀም ነው? ከጸሎት መጻሕፍት በቀር ሌላ ነገር አለማንበብ ነው? መንፈሳዊነትኮ በመንፈስ ቅዱስ መመራት ነው፡፡ ራስን ማሸነፍ ነው፡፡ አእምሮን እና ልቡናን ቀና እና ሰላማዊ ማድረግ ነው፡፡ ለመሆኑ የውስጡ መንፈሳዊነት አይደለም እንዴ ወደላይ መገለጥ ያለበት፡፡ ስለ ሐዋርያት ስንናገርኮ የነፍሳቸው ቅድስና ለሥጋቸው፣ የሥጋቸው ቅድስና ለልብሳቸው፣ የልብሳቸው ቅድስና ደግሞ ለጥላቸው ተረፈ ነው የምንለው፡፡ መንፈሳዊነቱ ከውስጥ ወደ ውጭ እንጂ ከውጭ ወደ ውስጥ አልነበረም፡፡ አንዳንድ ጊዜ «መንፈሳዊነት» ከ «መንፈሳይነት» ጋር እየተመሳሰለ የምንቸገር ይመስለኛል፡፡ ዲያቆን ኤፍሬም እሸቴ ነው ይህችን ቃል ያመጣት፡፡ ከሁለት ቃላት «መንፈሳዊ» እና «መሳይ» ከሚሉ ቃላት ቆራርጦ «መንፈሳይ» የሚል ቃል ፈጠረ፡፡ ትርጉሙም «መንፈሳዊ መሳይ» ማለት ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች መንፈሳውያን ይመስላሉ እንጂ አይደሉም፡፡

Sunday, February 14, 2016

ማተብ የማሰር ልማድ

      
     ማተብ{ማዕተብ} አንደኛው ፍች ምልክት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ቡራኬ ማለት ነው።ሥርወ ግሡም"አተበ"አመለከተ፤ባረከ የሚለው የግዕዝ ቃል ነው። ምልክት ሁል ጊዜ አንድን ነገረ ከሌላው ለመለየት-የሚያስችለው በመሆኑ ዓለም ይጠቀምበታል።ሐዋርያው ቅዱስ ዻውሎስ ውወደ ሮሜ ሰውች በላከው መልክቱ በአራትኛው ምዕራፍ ስለ አብርሃም ሲናገር"ሳይገረዝም በነበረው እምነት ያገኘ የጽድቅ ማኅተም የሆነ የመገረዝን ምልክት ተቀበለ"ብሏልወላጆችም መንታ ሲወልዱ የትናው ቀድሞ እንደተገኘ ለማስታወስ ምልክት ያደርጋሉ።ለምሳሌ በኦሪቱ ፋሪስና ዛራ ሲወለዱ አዋላጇ ቀድሞ በተወለደው አውራ ጣት ላይ ክት አስራበት እንደነበር ይናገራል። የኢትዮዽያዊያን ክርስቲያኖች ማተብ የማሰር ልማድ የመጣው ለረዢም ጊዜ የቤተክርስቲያናችን ሞግዚት ሆና ከቆየችው ከእስክንድርያ ቤተክርስቲያን ነው።በእስክንድርያ ኢቀ ዻዻስ ቴዎዶስዮስ ዘመን በሃገሩ የነበረው ዐላዊ ንጉስ በመሆኑ የክርስትናን አስተማሪዎች እያሰረ ያስደበድብ ነበር።ስለዚህም ቴዎዶስዮስ ካልሆነ ሰው ጋር ተጋፍጦ ከመቀሰፍና ሥራን ከማቋረጥ ዘወር ብሎ መዓቱን ማሳለፍ ይሻላል በማለት ሲሸሽ፤ያዕቆብ  ልዘ አልበርዲአክርስትና ትምህርት ቀናተኛ የሆነ ሐዋርያ በሽሽግ ያስተምር ነበር።ይህንም የተቀደሰ ስራውን ለማሰናከልና ለማቋረጥ የሚሹ አንዳንድ ቦዘንተኞች በስብሰባው ላይ እየተገኙ ያስተማራቸውን ያስቱበት ያሻክሩበት ስለነበር የእርሱ የሆኑትን ለይቶ ለማወቅ ሲል በ አንገታቸው ላይ አድርገው ለምልክትነት እንዲጠቀሙበት ማተብ አሰረላቸው፤ያሰረላቸውም ማተብ ሶስት አይነት ባንድ ላይ የተገመደ ሲሆን ጥቁር፣ቀይ ቢጫ ነበር።ይኸውም ጥቁሩ መከራ እቀበላለሁ፣ቀዩ ደሜን አፈሳለሁ፣ቢጫው ትንሳኤ ሙታንን ተስፋ አደርጋለሁ የሚል እንደነበር ይነገራል።ያዕቆብ ዘ አልበርዳኢም ያስተምር የነበረበት ዘመን አምስተኛው መቶ ዓመት እንደነበር ይገመታል{ሃይማኖተ አበው፣ድርሳነ ያዕቆብ}

Sunday, February 07, 2016

ፕርሚየር ሊግ ወይስ ስሌቭ ሊግ

   
 
መንገደኛው በበቅሎ ጀርባ በምድር ተሽከርካሪ ወይም በሰማይ በራሪ ተጭኖ ከከተማ አልወጣም። መንገድ የለመደበት እግሩ ግን አላረፈም። ከሰፈር ሰፈር ከታክሲ ታክሲ እየቀያየረ ይጉዋዛል። ምን ይሁን ብላችሁ ነው? ለፈተህ ግረህ ብላ አይደል የተባልነው? አላርፍ ባዩ እግሬ ወደ አንድ ገዳም  ለመጓዝ ዕቃወቼን ሼክፌ ትራንስፖርት እየጠበቅሁ ሳለሁ አካባቢየን ሳማትር ነበር መንገደኛው ልቤ ለአእምሮየ ውስጥ ውስጡን የሚያመላልሰው፣ የሚያወጣ የሚያወርደው የቤት ስራ ሰጠው። ታዲያ ይህ የሆነው ባለፈው ሰሞን አውሮፓ ክለቦች የፍጻሜ ጨዋታ ሰሞን ነበር። በዚህ የውድድር  ዓመቱ ፍዛሜው ዕለት አዘውትራችሁ ሻይ ቡና እያላችሁ  የሚነበብ ነገር የምታነቡበት ሻይ ቤት{ ካፌ} በር  "እንኳን ለአውሮፓ  ሻምፒዮን ሊግ የፍፃሜ ጨዋታ አደረሳችሁ" የሚል ለአንድ ሃይማኖታዊ ክብረ በዓል ወይም እንደ አድዋ ዓይነት ሀገራዊ የድል ቀን የደረሳችሁ የሚያስመስል የደስታ መግለጫ ተለጥፎ ብታገኙት ምን ትላላችሁ? መንገደናውን ገርሞታል። እናንተ "አሜን" ብላችሁ ታልፉታላችሁ? ወይስ "ሰወቹ ምን ነካቸው? ምን እየሉ እንደሆነ ታውቋቸዋል?" የሚል ጥያቄ ራሳችሁን ትጠይቃላችሁ? እኔ ግን የሚያበሳጭ ሆኖ አገኘሁትና በርግጥ ተናደድሁ።


መቼም ለመንገደኛው ይህን ያክል የነገ ዳፋው ያስፈራራው ምን እንደሚሆን ሁላችሁም የየራሳችሁን ግምት እንደምትሰጡ አልጠራጠርም። የጊዜው ፈርኦን በቴለቪዥን ዲ.ኤስ.ቲቪ በተባለ ድርጅት አጋፋሪነት የኢትዮዽያችንን አየር እየጣሰ የአውሮፓ በተለይም የእንግሊዝ እግር ኳስ ክለቦች{ፕሪሚየርሊግ}ጨዋታ ፍቅርን፣የዕለትተዕለ ኑሩዋችን አካል ስላረገው ጉድ ነው። ለዚህ እግር ኳስ ስርጭት የሰጠነው ጊዜና እያሳለፍንበት ያለው ሃብት ከቀን ወደ ቀን ለሌሎች ለህይወታችን አስፈላጊና መሰረታዊ ለሆኑ ነገሮች ከምናውለው ጊዜና ሃብት ጋር ለመስተካከል እሽቅድድም የያዘ ነው  የሚመስለኝ። ይህ አባባል ማሰራጨቱን በስራነት ይዘው እየኖሩበት ያሉትን ላይጨምር ይችላል። "እንኳን አደረሳችሁ" የሚለውን ቃል እስከ ዛሬ የምንጠቀምበት ለታላላቅ ሃይማኖታዊ በዓላት በመድረሳችን ምክንያት ደስታችንን ለመለዋወጥ እግረ መንገዳችንን ቸርነቱን ያልነፈገንን አምላክ ለማመስገን ነበር። አራት ኪሎ አንድ ካፌና ሪስቶራንት በር ላይ ተለጥፎ ያየሁት የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት ግን ከተለመዱት በተለየ ምክንያት "እንኳን ለ2011/12 ዓ.ም የእንግሊዝ ፕሪሚይር ሊግ የፍፃሜ ጨዋታ ቀን አደረሳችሁ" ይላል። ደጋግሜ አነበብሁት መጀመሪያ ላይ ሳቅሁ የትዝብት ሳቅ። ቆይቸ ግን ተናደድሁ ቅጥል እስክል ድረስ።

Thursday, February 04, 2016

ሰማይ ሆዱ ባባ !










ዘመኑ ምቀኛ ትውልዱ ጠማማ፣

ሰማዩ አመፀኛ ልመናን ማይሰማ፣

ሲያሰቃየን ከርሞ በድርቅ እያስጠማ፤

የምናደርገውን አሳጥቶን መላ፣

መፍትሄ ሲቸገረን እርስበርስ ስንብላላ፣

በረሃብ ላለማለቅ ስንገባ መኀላ፣

በውኃ ቀጠነ ልጅ አባቱን ሲቀትል፣

እናት በልጆቿ ጡቷን ስታሽ ስትምል፣

ገዥም ተገዥው ላይ መሳሪያውን ሲስል፤

ከንፁኀን ሰፈር ሲወርድ የቦምብ ናዳ፣

ከባህታዊያን ደጅ ፈንጅ ሲፈነዳ፤

?እረኞች? በጎችን ከጋጥ ሲያባርሩ፣

በጎችም በረግገው ሲሉ ይብላኝ ዱሩ፣

ተኩላዎች በደስታ ሲጮሁ ሲያቅራሩ፤

መሬት ይህን አይታ ልቧ ሲደነግጥ፣

መሠረቷ ሲናድ አቋሟ ሲናወጥ፣

መላው አካላቷ ሲሼክ ሲንቀጠቀጥ፤

ሰማይ ሆዱ ባባ ሰውነቱ ራደ፣

ጥፋቱን አመነ አመዱን አመደ፣

"ማሩኝ ልካሥ" አለ ለመነ ማለደ፣

በዝናቡ ፈንታ ዐሣን አወረደ።


                                    ጌታነህ ካሴ
                                    ጥር  25/2008ዓ.ም    

Tuesday, February 02, 2016

ብላቴናው አይዞኝ

ፊቱን ቢያዞርብህ ሙድ ቢይዝ ዘመኑ፣
ብላቴናው አይዞኝ ያልፋል ሰቀቀኑ።
በርታ ጠንክር የሚል ባይኖርም ከጎኔ ፣
ሁለት  ሃብታት አሉኝ ችግር እና ወኔ።
ለአቡነ ተክሌ ክንፍ ለያዕቆብ መንሰላል፣
አይሳነው ልዑል  ሁሉንም ያድላል ።
ለ'ኔም በዝቶልኛል ጸጋ በረከቱ፣
ቢያድለኝ ቢያድለኝ ባይረካ ስሜቱ፣
ወኔን ደረበልኝ ማጣትን በብርቱ።
           
                        ጌታነህ  ካሴ