Monday, September 26, 2016

የነጋበት ማምሸት

እውነትን ተናግሮ የመሸበት ማደር፣
መባሉን ሰምተናል ትውፊቱ ሲነገር።
ዛሬ ጊዜው ከፍቶ ስንታይ የጎሪጥ፣
እውነቱን ተናግሮ አይረባም መጋፈጥ።
የመሸበት ማደር  ቀርቷል ትላንትና፣
እውነት ተናጋሪን ማን ያስመሸውና።
እንዲህ ሁኗል ዛሬ ተረቱ ሲለወጥ፣
እውነት የሚናገር እንዳወራ ያምልጥ።

ምንጭ ሀሞት የግጥም ስብስብ 
በኄኖክ ስጦታው

Sunday, September 25, 2016

ቁጩ !

ሴት አያቴ "ቲቪ ክፈትልኝ" ለማለት "ቲቢውን አብራው" ትለኛለች ። የኢቲቪን አማርኛ ልዋስና አንዳንድ ጥርሶች ስለጎደሏት ብቻ አይመስለኝም ቲቪን "ቲቢ" የምትለው። ኢትቪ ሲከፈት ሳሏ ስለሚነሳባትም ጭምር ነው። ኢቲቪ ሳምባዋን ሳይነካው አለቀረም። ሴት አያቴ ከጎረቤት ጋር ቡና እየጠጣች አጫዋቾቿ የማይመስል ነገር ካወሩም በተመሳሳይ መልኩ ሳሏ ይነሳባታል። መቼ ለታ እትዬ ዘነቡ የተባሉ ጎረቤቷ  ቀበሌ ተሰብስበው ከመጡ በኋላ በረካ ላይ ደርሰው ቡና እየጠጡ "ሰምተሻል ኢትዮጵያ ልትመነደግ ነው..."ብለው ወሬ ሲጀምሩ አያቴ ሳሏ ተነስቶባት "ትን" ብሏት ለጥቂት አላህ አተረፋት።

ኢቲቪ በሴት አያቴ ሳንባ ላይ ብቻ ሳይሆን በወንድ አያቴ ጨጓራ ላይም ቀላል የመቁሰል አደጋን አስከትሏል። ወንድ አያቴ ባሩድ በደረቱ የሚመክት አርበኛ ነበር ። ችግሩ ምንም እድሜ ቢጫነው ኢቲቪ ካላየሁ ብሎ ችክ ይላል። "ጋሼ ቲቪ ምን ይሰራልሃል ቁርዓን የምትቀራበትን ዓይንህን በከንቱ አታድክም ፤ይቅርብህ" ስለው  "ተው ልጄ እንደሱ አይባልም! ጥልያን ደፍራን ቢሆንስ  በምን እናውቃለን? አገር ነቅቶ መጠበቅ ነው እንጅ"  ይላል። ኢቲቪ ካላየ አገር የተወረረ ይመስለዋል። በቲቪ ውስጥ አገር ከሚጠብቅ ወለወል ላይ  ቤት  ቢሰራ ይሻለው ነበር ። ሆኖም በደከመ ዓይኑ ዘወትር የሚያየው ቴሌቪዥን የረባ ነገር ሊያሳየው ስላልቻለ ለጨጓራ ህመም ተዳረገ። እንዲያም ሆኖ ከዛሬ ነገ በቲቪው ውስጥ የረባ ያገር ጉዳይ አያለሁ በሚል የሞጨሞጨ ዓይኑን ቲቢ መስኮት ላይ ተክሎ ያድራል። ኢቲቪ በበኩል "አንዳንድ የወልውልና የቆቦ ነዋሪዎች ጠግበው ማደራቸውንና መጸዳጃ ቤት መጠቀም መጀመራቸውን ገለጡ" እያለ  ልማትን ከማወጅ ውጭ ሌላ ለወንድ አያቴ የሚሆን ጨዋታ አላውቅ አለ።

Saturday, September 24, 2016

ዓይን


ዓይን የሰውነት መብራት ናት።እንግዲህ ዓይንህ ጤነኛ ብትሆን ሰውነትህ ሁሉ ብሩህ ይሆናል። ዓይንህ ግን ታማሚ ብትሆን ሰውነትህ ሁሉ የጨለመ ይሆናል።

The eye is the window of our body !.

at the end of ophthalmology course.