Monday, August 20, 2018

እንትን አፍጥ

 
አሁን የቆምሁባት ተራራ እንትን አፍጥ ትባለለች። “ተራራ ሲወጡ የሚፈጥባቸው ነገር አለ እንዴ?” የሚለውን ጥያቄ ለሴቶቻችን እንተወውና እዚች ተራራ ላይ ቆሜ አንድ ጊዜ ወደ ላይ አንድ ጊዜ ወደ ታች እያፈጠጥሁ ነው። የሚታየው ሁሉ እጅግ ይማርካል ሊያዘረዝር የተዘጋጀ የገብስ ቡቃያ፣ የተዳገረ ቦቆሎ፣ የለሰለሰ የጤፍ መሬት እርሻ ። ኧረ በወላዲተ-አምላክ እዚጋ ደግሞ በግራ ጎኗ እቅፍ ሙሉ እንጨት የያዘች ልጃገረድ፣ በአርባ ሽንሽን ቀሚስ ውስጥ ከፍ ዝቅ የሚል ትልቅዬ መቀመጫ፣ያለ ጡት ማስያዣ የቆመ አጎጥጎጤ ጡት፣ ሊፕስቲክ አይቶ የማያውቅ ሳሙኝ ሳሙኝ የሚል ከንፈር፣ ፣ የሚሽኮረመሙ ዓይኖች ፣ ባለ ዲምፕል ጉንጭና ባለ ንቅሳት ግንባር ወይኔ ቀጭኑ ማበዴ ነው መሰል!
በመሄድና በመቆም መሀል ፈዝዠ ይኸን ሁሉ ስመለከት የመነኩሴ ምራቅ የሚያህል የዝናብ ጠብታ መሀል ጆሮዬ ላይ ሲላተም የፈጠረው አሰቃቂ ድምጽ ከቁም ቅዠቴ ቀሰቀሰኝ። ድምፁ ሁሉንም የታች ቤት ነዋሪዎች ያስደነገጠ ነበር። አንዳንድ ቧልተኞች እንደሚሉት ከሆነ አማኔ ሊጠጣ ወደ አፉ ያለውን ቡና መልሶ “እሰይ አትሂድ ስለው ሲንቀለቀል ሂዶ አስገቡለት” ሲል ሰምቶ አንቱካ ምናባህ በማለት ተቆጥቶታል። መሲና ቅድስቴ ጸሎት ቤት ውስጥ የድንግል ማርያምን ሥዕለ አድህኖ ታቅፈው ተገኝተዋል። እንዳሌና ሲስተር አዘነጋሽ በአርምሟቸው ፀንተው ያሳለፉት ሲሆን ረቂቅ “ውይ ጌችዬን ምን ነክቶብኝ ይሆን” የሚል ቃል አምልጧታል። ስሌሎች የተጣራ መረጃ አላገኝሁም። እኔስ ምን ሆንሁ? እኔማ ወንድነቴን ልጅቱ እንድታይልኝ ፈልጌ ይሁን የአዲስ አበባው ጉዴ ትዝ ብሎኝ “ዘራፍ የበላይ አሽከር” ብዬ አካባቢውን ስቃኝ ማንም አልነበረም።
ባለፈው ቅዳሜ ዕለት አ.አ ከአውቶብስ ተራ ወደ ጎጃም በረንዳ በሚወስደው መንገድ እየተጓዝሁ አንዱ ሰላቶ በቀኝ ጎኔ በኩል (ያባቴ አምላክ ጎኑን ይንቀለውና) በጫማ ጥፊ መታ መታ ሲያደርገኝ ፊቴን እንደ መከራ አጥቁሬ ከፈረስ ጭራ በቀጠነ ድምጽ ስልኬስ አልሁት በግራ ጎኔ የቆመውን ግሪሳ። የፊቴ መኮሳተር አስፈርቶት ይሁን የድምፄ መቅጠን አሳዝኖት አላውቅም እሽ ብሎ ስልኬን መለሰልኝ። እኔም መንገድ ዳር ወድቆ ከማደር የጠበቀኝን አምላክ እያመሰገንሁ ወደ አዲሱ ገበያ በታክሲ። ከቅዳሜው ትዝታየ ስመለስ ልጃገረዲቱም ከአካባቢው ተሰውራለች። ዝናቡም መጣሁ መጣሁ ይላል፤ ጉርጥ ጉርጥ የሚያህል የዋልካ ጭቃ እየዘለለ ቦት ጫማየ ውስጥ ይከተታል፤ እኔም ጉዞዬን ቀጥያለሁ።“ጉች ጉች ያለ ጡት በል ደህና ሰንብት አንተን ማግኘት ርቋል ከዕለተ ምፅዓት” የሚለውን ዘፈን እያንጎራጎርሁ።
ሾላሜዳ:ሐምሌ 13/2010ዓ.ም