Monday, November 19, 2018

ስሜት ተጋሪዎች

ከድንክ አልጋዬ ላይ ህልም አይቸ ማታ
የባ'ል ገበያ ውስጥ የትዳር ገበታ
መበልት ወይዛዝርት ስሜት ተጋሪዎች
ፍቅርን በድቃቂ ሳንቲም  መንዛሪዎች
ምን አልባት ወደ ፊት ሴተኛ አዳሪዎች
ይህ አይመጥንሽም ይህም አይሆንሽም
ቅቅል አይጋብዝም ክለብ አያመሽም
ያኛው ዝምተኛ ዝጋታም ኮስታራ
ሁል ጊዜ ቁምነገር ቀልድ የማያወራ
ቀብራራ ገጠሬ ቪላ ቤት የሌለው
ገና በማህፀን አምላክ የበደለው
እያሉ በህብረት በማበር ሲዞሩ
በትዕቢት በጉራ እንደተወጠሩ
ከደራው ገበያ ጥሪት ሳይሸምቱ
በጠራራው ፀሐይ እንዲያ እንደዋተቱ
አንዳቸው ሳይዘግኑ ብፌው ባዶ ሆነ
ሰዓቱ መረሸ ገቢያው ተበተነ
ምሱ ፆም ማደር ነው
መውደድን በወረት በብር ለተመነ

ማሳሰቢያ : ህልሜ ወደ ትንቢትነት ከመቀየሩ በፊት ልብ ያለሽ ልብ በይ ።

Saturday, November 17, 2018

.....ላንቺ....


የብዕሬ ጠብታ ላንቺ የሚመጥን ባይሆንም ቀለሙ
በሄድሽበት ሁሉ እንድታስታውሽኝ እስከ ዘላለሙ 
ፃፍልኝ ያልሽኝን ያው ተቀኘለሁልሽ
በግሩም ተፈጥሮሽ ስፍስፍ ብልልሽ
መናኝ በሚያስቱ አስማታም  ጥርሶችሽ
ቀልብን በሚያሣጡ ምትሃተኛ ዓይኖች
አንኳን ሁለት ስንኝ እንኳን ስምንት ቀለም
ህይወት ብታስከፍይ ላንቺ ብዙ አይደለም
አይመረመሬው የሠራሽ ተጠቦ
የውበት ተምሣሌት ጠይም የደም ገንቦ
የሥብዕና ጥግ የሴትነት ልኩ
ምን ብዬ ልግለፅሽ እንዴው በምን መልኩ?
ታዲያ ለዚህ ገላሽ ለዚህ ውብ ተፈጥሮ
ስምሽ ግንባሬ ላይ በደማቅ ተወቅሮ
አገልጋይሽ ልሆን አምላክ ቢፈቅድ ኖሮ
ደከመኝ ሰለቸኝ አልልም  ነበረ
ዳሩ ምን ዋጋ አለው ምኞት ሆኖ ቀረ
©/ ጌታነህ ካሴ ኅዳር 7/2011 .

እንኳን ደስ ያላችሁ


ወንጭፋችን ባዶ
ጎልያድ ከማዶ
ከእጆቼ አታመልጡም እያለ ቢፎክር ቢሸልል ቢያቅራራ
በድሮ ልማዱ ከአሮጌ ሰማይ ላይ ነጎድጓድ ቢያጓራ
ደመና ፀንሶ እሣት ወይ ነበልባል በረዶም ቢያፈራ
ጦርነቱ ከባድ ቀበቶ ሚያስፈታ
የብዙ ጓዶችን እስትንፈስ የገታ
ለመግለፅ የሚከብድ ለወሬ አስቸጋሪ
በሩቁ ለሚያዩት ቢሆንም አስፈሪ
እኛ ግን ተርፈናል ይመስገን ፈጣሪ
አልሃምዱሊላሂ  ከፍ ይበል ንጉሡ
ምጡን እርሱትና ልጃችሁን አንሡ
ተደሰች ተደሰት ጨፍሩ ደንሡ
በአሸናፊነት  ድል ከፍ ይበል ጽዋችሁ
አቮ  ደስ ብሎኛል እንኳን ደስ ያላችሁ 
©/ ጌታነህ ካሴ ኅዳር 3/2011 ዓ.