Sunday, September 25, 2016

ቁጩ !

ሴት አያቴ "ቲቪ ክፈትልኝ" ለማለት "ቲቢውን አብራው" ትለኛለች ። የኢቲቪን አማርኛ ልዋስና አንዳንድ ጥርሶች ስለጎደሏት ብቻ አይመስለኝም ቲቪን "ቲቢ" የምትለው። ኢትቪ ሲከፈት ሳሏ ስለሚነሳባትም ጭምር ነው። ኢቲቪ ሳምባዋን ሳይነካው አለቀረም። ሴት አያቴ ከጎረቤት ጋር ቡና እየጠጣች አጫዋቾቿ የማይመስል ነገር ካወሩም በተመሳሳይ መልኩ ሳሏ ይነሳባታል። መቼ ለታ እትዬ ዘነቡ የተባሉ ጎረቤቷ  ቀበሌ ተሰብስበው ከመጡ በኋላ በረካ ላይ ደርሰው ቡና እየጠጡ "ሰምተሻል ኢትዮጵያ ልትመነደግ ነው..."ብለው ወሬ ሲጀምሩ አያቴ ሳሏ ተነስቶባት "ትን" ብሏት ለጥቂት አላህ አተረፋት።

ኢቲቪ በሴት አያቴ ሳንባ ላይ ብቻ ሳይሆን በወንድ አያቴ ጨጓራ ላይም ቀላል የመቁሰል አደጋን አስከትሏል። ወንድ አያቴ ባሩድ በደረቱ የሚመክት አርበኛ ነበር ። ችግሩ ምንም እድሜ ቢጫነው ኢቲቪ ካላየሁ ብሎ ችክ ይላል። "ጋሼ ቲቪ ምን ይሰራልሃል ቁርዓን የምትቀራበትን ዓይንህን በከንቱ አታድክም ፤ይቅርብህ" ስለው  "ተው ልጄ እንደሱ አይባልም! ጥልያን ደፍራን ቢሆንስ  በምን እናውቃለን? አገር ነቅቶ መጠበቅ ነው እንጅ"  ይላል። ኢቲቪ ካላየ አገር የተወረረ ይመስለዋል። በቲቪ ውስጥ አገር ከሚጠብቅ ወለወል ላይ  ቤት  ቢሰራ ይሻለው ነበር ። ሆኖም በደከመ ዓይኑ ዘወትር የሚያየው ቴሌቪዥን የረባ ነገር ሊያሳየው ስላልቻለ ለጨጓራ ህመም ተዳረገ። እንዲያም ሆኖ ከዛሬ ነገ በቲቪው ውስጥ የረባ ያገር ጉዳይ አያለሁ በሚል የሞጨሞጨ ዓይኑን ቲቢ መስኮት ላይ ተክሎ ያድራል። ኢቲቪ በበኩል "አንዳንድ የወልውልና የቆቦ ነዋሪዎች ጠግበው ማደራቸውንና መጸዳጃ ቤት መጠቀም መጀመራቸውን ገለጡ" እያለ  ልማትን ከማወጅ ውጭ ሌላ ለወንድ አያቴ የሚሆን ጨዋታ አላውቅ አለ።

ወንድ አያቴ ተስፋ አይቆርጥም ። ከዛሬ ነገ የሆነ የአገር ጉዳይ ፣የሆነ የድንበር ጉዳይ፣የሆነ የረባ ነገር በኢቲቪ ለመስማት እንዳቆበቆበ ነው ። በዚህ መሀል "ኅበር ትርዒት" ይጀምራል። መቀመጫቸውን ክፉኛ እየናጡ የሚደንሱ ሴቶች በኢቲቪ መታየት ይጀምራሉ። ይኼኔ ይጠራኛል። "አቤት ጋሼ እለዋለሁ።"  "ና እስቲ ቲቢው ተበላሽቷል መሰለኝ፤አንቴናውን አብጀው" ይላል። "ምን ሆነ" እለዋለሁ። "እንጃ ብቻ የሚንቀጠቀጥ ነግር ይታየኛል።" በመጨረሻ የሴት አያቴ ሳንባና የወንድ አያቴ ጨንጓራ በኢቲቢ ምክንያት በየእለቱ እየተጎዳ እንደሆነ ስመለከት  ኢቲቪ በፈረሰው ማስታወቂያ ሚኒስትር ስር ከሚሆን ማልፈረሰው ጤና ጥበቃ ሚኒስትር ስር ቢሆን ለአስተዳድር እንደሚመች ገመትኩ።

ኢቲቪ በሰፈሬ ስራ አጥ ወጣቶች ዘንድ "ቁጩ"  በመባል ይታወቃል።"ቁጩ" ማለት "በግልፅ የሚታይን ነገር ድርቅ ብሎ መካድ ፣ማበል፣ማስተባበል" ማለት ሲሆን ቃሉ ይበልጥ በቁማር ጨዋታ  ላይ ይዘወተራል። ለምሳሌ አንድ የሰፈራችን ስራ አጥ ወጣት "በናትሽ ፍሬንድ  አራራ በላኝ እስቲ እነ ቾምቤ ቤት ቁጭ ብለን ቁጩ እንከልም" ካለ ትርጉሙ እንደሚከተለው ይሆናል። "ወዳጄ ሆይ  የጫት አራራ እረፍት ነሳኝ ፣እነ ቾምቤ ቤት ሄደን ኢትዮጵያ ቴለቪዥን እንመልከት" ማለት ነው ።አንድ እኛ ስፈር የሚገኝ ቤተ መጽሐፍት ውስጥ የተቀመጠ ወፍራም መዝገበ ቃላት "ቁጩ" የሚለውን ቃል "ቆጨጨ፣ቁጩ(አድራጊ ግስ )፣ቁጨጫ ፣ይቆጭጫል፣ቆምጫጫ፣ ሞጭሟጫ  እያለ ያረባዋል።

በ 97 ምርጫ የሰፍሬ ልጆች "ቅንጅት" የሚባል ውስዋስ መንፈስን ተከትለው ተሰባሰቡ ።በዙ ተባዙ።መስቀል አደባብይንም ሞሏት።ማታ ሰፈራቸው ሲመለሱ ቁጩ ቲቪ ምን እንደምትል ለመስማት እነ ቾምቤ ቤት ተኮለኮሉ።ቁጩ ዋሸች ።ሰልፍ የወጡ ሚሊዮን ጨዋ ዜጎችን ትታ ጥቂት ጎረምሳ ህጻናት የግለሰብ ስም እየጠሩ ሲሳደቡ አሳየች ።ይሄኔ ለኢቲቪ (የክርስትና?)ስም ሰጧት፤ቁጩ! ይህ በሆነ በስምንተኛው ቀን ምርጫ መረጡ ።በነጋታው ተሸነፋችሁ ተባሉ።ቁጩ ናት እንደዚያ ያለቻቸው።ከዚያን ቀን  ጀምሮ ቁጩን ተቀየሟት።እፍርታም! አሏት።ያም ሆኖ የስፈሬ ልጆች አሁንም ቢሆን የተቀየሟትን "ቁጩ"ን ከማየት አልቦዘኑም።ከፕሪምየር ሊግ የትረፈችውን ሰዓታቸውን ቁጩ ላይ በማፍጠጥ ያሳልፋሉ።

በዚህ የተነሳ እንዲያውም አንዳንድ የስፈሬ ልጆች አንዳንድ የቁጩ ቲቪ ቁጩ ጋዜጠኞችን በስም ያውቋቸዋል።ጋዜጠኞችን ብቻ ሳይሆን  አንዳንድ "የምናምን ነዋሪዎች" የሚባሉትንም ሰዎች ያውቋቸዋል።ከአንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ውስጥ አንደኛው እንዲያውም ቤቱ እኛ ሰፈር ነው ።ቀበሌ ውስጥ መታወቂያ ያድላል።የወጣቶች ሊግ ውስጥም የሆነች ሚጢጢ ስልጣን አለችው።ልጁ በስፈር ሲያልፍ አንዳንድ የሰፈሬ ልጆች "እንዴት ነህ አንዳንድ?" እያሉ ይሳለቁበታል።ስሙ አንዳንድ ከመሆኑ በፊት ደምሰው ነበር።አሁን ግን "አንዳንድ" የሚለው ስም አገኗል።መቼ እለት እኛ ቤት አካባቢ በቆመ ስልክ እንጨት ላይ የሆነ የወጣቶች ሊግን የሚመለከት ማስታወቅያ ሲለጠፍ አንዳንድ ከኢትዮጵያ ይልቅ አርሴናልን የሚደግፉ የሰፈሬ ልጆች አገኙትና እንዲህ አሉት። "የሆንክ አንዳንድ ነገር ነህ! ሰው ፕሪምየር ሊግ ውስጥ ይጫወታል አንተ ወጣት ሊግ ውስጥ ትጫወታለህ!" ሆ እንዳያየኝ ጥርሴን በስልክ እንጨቱ ሸፍኜ ሳቅኩኝ።

የሰፈሬ ልጆች ሌላም ነገር ያውቃሉ። ሁል ጊዜ በቁጩ ቲቪ የምትታየዋን ወፍራም በግ። ማን እናዳደለባት የማትታወቅ ይች ያልሸረፈች ጠቦት በግ በቲቪ ስትመጣ የሰፈሬ ልጆች ይስቃሉ። በጓ በሰሜን፣በደቡብ፣በምስራቅና በምዕራብ ኢትዮጵያ የሚገኝ ማንኛውም ሃብታም ገበሬ ለቃለ መጠይቅ በቀርበ ቁጥር ማሳው ላይ ጎምለል ጎምለል ስትል ትታያለች። መቼም የዚች በግ ኩራቷ ለጉድ ነው ። ስትራመድ በግመልኛ ነው። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ይቺው በግ እንደ ሃብታም ቤት ቡችላ ኢንተርቪው ከሚደርገው ሰዉዬ ፊት መጥታ ግትር ትላለች ። ቁጩ በግ ይሏታል የሰፈሬ ልጆች ።ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ሃብታም ገበሬ አይሱዙ መግዛቱን፣ባንክ አንድ ሚሊዮን ብር ማስቀመጡን፣ 18 መጋዝን ፣ 19 ፍሪጅ ፣ 20 ሶፋ እንዳለው፣በብር ላይ ብር በሃብት ላይ ሃብት እየደረበ መሆኑን ፍጥጥ ብሎ በቲቪ ሲናገር በጓ ድንገት አፏን በእጇ ያዘች፤ አፍራ ፤ የሰፈሬ ልጆች ናቸው የነገሩኝ ።
 
ኢቲቪ በተማሩና በተመራመሩ ጓደኞቼ ዘንድ ደግሞ "ቫይረስ" በመባል ይታወቃል። አንድ ተመራምሯል የምለው ወዳጄ "ኢቲቪ የዜጎች 'ኢንተለጀንስ' እንዲያሽቆለቁል አስተዋጽኦ አድርጓል" ሲል ዘወትር ይሟገታል። በዚህ ረገድ ሰፊ ጥናት ለማድረግም የረዥም ጊዜ እቅድ እንዳለው ነግሮኛል። እንዳሰበው ጥናቱን ሰርቶ ካጠናቀቀ ቁጩ እንዲህ የሚል ዜና ትሰራለታለች ብዬ እገምታለሁ፦ "የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት የአድማጭ ተመልካቾቹን የመረጃ ጥማት በማርካት ረገድ ስኬታማ እንደነበረ አንድ ጥናት አመለከተ።

በነገራችን ላይ ይህ ወጣት ምሁር ጓደኛዬ በኢቲቪ የበገነው ገና ዩኒቨርሲቲ ሳለ ነው። አንድ ወቅት በዩኒቨርሲቲ አመጽ ተሳተፈ። የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በአመጽ ጭር አለች። ሁሉም ተማሪ ጊቢውን ለቆ ወጣ። ለቤተሰቡ ሂዶ እርሱና ጓደኞቹ ዩኒቨርሲቲውን ቀውጢ እንዳደረጉትና ከአመጹ መሪዎች አንዱ እርሱ እንደሆነ ፎከረ። እናቱ የድንግል ማርያምን ፎቶ ይዛ "ጭንቅ አማላጅቷ" ስትል መጸለይ ጀመረች። እርሱና ቤተሰቡ ማታ የዜና ሰዓት እስኪደርስ ተቁነጠነጡ። ስለ አመፁ መንግስት በኢቲቪ ቀርቦ አንዳች ልመና እንዲያቀርብ እርግጠኛ ነበር። አይደርስ የለ የዜና ሰዓት ደርሰ። ከትንሽ እኅቱ ጀምሮ እስከ አያቱ ድረስ ሁሉም ቲቪ ላይ አፍጥጠዋል። ዜና አቅራቢው እንደተለመደው "እንደምን አመሻችሁ-ምንም የሌላችሁ" ብሎ እጅግ አጎንብሶ እጅ ነሳ። "በመጀመርያም አርዕስተ ዜና፦በከፍተኛ ተቋማት የትምርት ጥራት እየተረጋገጠ መምጣቱን የ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አንዳንድ ተማሪዎች ገለጹ።"

በዓለም ላይ የኢቲቪን ያህል ያለመታመን አቅም የፈጠረ ሚዲያ ይኖር ይሆን? የበርማን፣የኩባን፣የቻይናን፣የሰሜን ኮሪያን ቁጩዎች አሰብኩ። የአገሬን ቁጩ የሚስተካክለው አይኖርም ። እንዳይታመን ያደረገው ግን ራሱ መሰለኝ። ለምሳሌ መቼ ለታ ዘይት  በአገር በምድር ጠፋ ተባለ ። ኢቲቪ ግን "በአገሪቱ ምንም አይነት የዘይት እጥረት እንዳልተከሰተ ንግድ ሚኒስቴር አስታወቀ።" ሲል  በየቤቱ ሳሎን እየገባ ተናገረ። አባዬ እኛ የተማርን ልጆቹን ሰብስቦ "ሌላ ኢትዮጵያ የምትባል አገር አለች እንዴ?" አለን። "ኸረ በፍጹም" አልነው። "ታድያ በኢትዮጵያ የዘይት እጥረት አልተከሰተም የሚሉት ለምንድን ነው?" አለን ። መልስ አልነበረንም። እሱም ትክዝ ብሎ ቀረ ።

የእማዬ ብስጭት ደግሞ ይብሳል። አንድ ቀን ምርር አላትና ሄዳ ቲቪውን ከላይ መጫን ጀመረች። እህቶቼም እኔም በእማዬ  ድርጊት ደነገጥን "ምን ነካሽ እማዬ? ምን እያድረግሽ ነው?" አልናት፤ በድርጊቷ ተደናግጠን። "ቲቪውን እየጨመቅኩት ነው" አለችን ። "ምን አልን" በአንድ ድምፅ ጤንነቷን እየተጠራጠርን። "ቲቪው ዘይት አለ ብሎ የለ? እስኪ ጨምቄው ዘይት ከቀጣው ልይ ብዬ ነው።" አለችን። የምር በኢቲቪ እንደተበሳጨች ገባን። ብስጭቱ ከሴት አያቴ ወደ እማዬ እየተላለፈ ነው ማለት ነው። ትውልድ ተሻጋሪ የብስጭት ማሽን።

ምንጭ፦ ፒያሳ ማሕሙድ ጋ ጠብቂኝ
በመሐመድ ሰልማን

No comments:

Post a Comment