Sunday, February 07, 2016

ፕርሚየር ሊግ ወይስ ስሌቭ ሊግ

   
 
መንገደኛው በበቅሎ ጀርባ በምድር ተሽከርካሪ ወይም በሰማይ በራሪ ተጭኖ ከከተማ አልወጣም። መንገድ የለመደበት እግሩ ግን አላረፈም። ከሰፈር ሰፈር ከታክሲ ታክሲ እየቀያየረ ይጉዋዛል። ምን ይሁን ብላችሁ ነው? ለፈተህ ግረህ ብላ አይደል የተባልነው? አላርፍ ባዩ እግሬ ወደ አንድ ገዳም  ለመጓዝ ዕቃወቼን ሼክፌ ትራንስፖርት እየጠበቅሁ ሳለሁ አካባቢየን ሳማትር ነበር መንገደኛው ልቤ ለአእምሮየ ውስጥ ውስጡን የሚያመላልሰው፣ የሚያወጣ የሚያወርደው የቤት ስራ ሰጠው። ታዲያ ይህ የሆነው ባለፈው ሰሞን አውሮፓ ክለቦች የፍጻሜ ጨዋታ ሰሞን ነበር። በዚህ የውድድር  ዓመቱ ፍዛሜው ዕለት አዘውትራችሁ ሻይ ቡና እያላችሁ  የሚነበብ ነገር የምታነቡበት ሻይ ቤት{ ካፌ} በር  "እንኳን ለአውሮፓ  ሻምፒዮን ሊግ የፍፃሜ ጨዋታ አደረሳችሁ" የሚል ለአንድ ሃይማኖታዊ ክብረ በዓል ወይም እንደ አድዋ ዓይነት ሀገራዊ የድል ቀን የደረሳችሁ የሚያስመስል የደስታ መግለጫ ተለጥፎ ብታገኙት ምን ትላላችሁ? መንገደናውን ገርሞታል። እናንተ "አሜን" ብላችሁ ታልፉታላችሁ? ወይስ "ሰወቹ ምን ነካቸው? ምን እየሉ እንደሆነ ታውቋቸዋል?" የሚል ጥያቄ ራሳችሁን ትጠይቃላችሁ? እኔ ግን የሚያበሳጭ ሆኖ አገኘሁትና በርግጥ ተናደድሁ።


መቼም ለመንገደኛው ይህን ያክል የነገ ዳፋው ያስፈራራው ምን እንደሚሆን ሁላችሁም የየራሳችሁን ግምት እንደምትሰጡ አልጠራጠርም። የጊዜው ፈርኦን በቴለቪዥን ዲ.ኤስ.ቲቪ በተባለ ድርጅት አጋፋሪነት የኢትዮዽያችንን አየር እየጣሰ የአውሮፓ በተለይም የእንግሊዝ እግር ኳስ ክለቦች{ፕሪሚየርሊግ}ጨዋታ ፍቅርን፣የዕለትተዕለ ኑሩዋችን አካል ስላረገው ጉድ ነው። ለዚህ እግር ኳስ ስርጭት የሰጠነው ጊዜና እያሳለፍንበት ያለው ሃብት ከቀን ወደ ቀን ለሌሎች ለህይወታችን አስፈላጊና መሰረታዊ ለሆኑ ነገሮች ከምናውለው ጊዜና ሃብት ጋር ለመስተካከል እሽቅድድም የያዘ ነው  የሚመስለኝ። ይህ አባባል ማሰራጨቱን በስራነት ይዘው እየኖሩበት ያሉትን ላይጨምር ይችላል። "እንኳን አደረሳችሁ" የሚለውን ቃል እስከ ዛሬ የምንጠቀምበት ለታላላቅ ሃይማኖታዊ በዓላት በመድረሳችን ምክንያት ደስታችንን ለመለዋወጥ እግረ መንገዳችንን ቸርነቱን ያልነፈገንን አምላክ ለማመስገን ነበር። አራት ኪሎ አንድ ካፌና ሪስቶራንት በር ላይ ተለጥፎ ያየሁት የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት ግን ከተለመዱት በተለየ ምክንያት "እንኳን ለ2011/12 ዓ.ም የእንግሊዝ ፕሪሚይር ሊግ የፍፃሜ ጨዋታ ቀን አደረሳችሁ" ይላል። ደጋግሜ አነበብሁት መጀመሪያ ላይ ሳቅሁ የትዝብት ሳቅ። ቆይቸ ግን ተናደድሁ ቅጥል እስክል ድረስ።



የፕሪሚየርሊጉ ፈርኦንነት ቁልጭ ብሎ ታየኝና "ሲወጣ እንዳየነው ሲወርድ ለማየት እንታደል ይሆን?" ስል አሰብኩ። ከወጣ በኋላ ደግሞ አፍሪካዊ አምባገነንነት ባህርይን እንደሚወርስ ያስታውቃል-ታዲያ እስከ መቼ። እናም ከወጣበት የክብር ማማ "ውረድ" የሚለውን ዋጋ ሳያስከፍል እንደማይወርድ የመረጃ ዘመንን{ኢንፎርሜሽን ኤጅን} ስም ጠርቶ የማለ መሆኑ ያስታውቃል። በማለት መንገደኛው የትውልዱን አካሄድ ያሰላስል ጀመር። ይህ መስመር ነው እንግዲህ የአዲሱ ቅኝ ግዛት{re-colonization}ቅኝት። ይህ ነው እንግዲህ መዝናኛ በሚሉት ሽፋን ኣዲሱ ቅኝ ገዥ ሆኖ ብቅ ያለው። ከዚህ በኋላ "ቅኝ ገዥ ያልገዛን ብቸኛ ጥቁር ህዝቦች" ብለን መመካታችን ከየት አለ። በነፍጥ ያልተሳካለት አውሮፓዊ ያለነፍጥ ያውም በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን  አዲስ የውዴታ ቅኝ ተገዥ አገኘሁ ብሎ ፈንድቋል። አዎ! ለምን አይፈንድቅ? ቅዱስ ጊዮርጊስን ገበዝ አድርጋ የ19ኛው ክፍለዘመን የታልቅነት ታሪኩ ላይ አድዋ በተባለ ጥቁር ደም ጥላሽት የደፋችበት ሃገር ዛሬ እጅ ስትሰጥ ለምን አይፈንጥዝ? ጮቤ ይርገጥ እንጅ።አፍሪካዊነት የሽንፈት ታሪክ ብቻ ሆኖ ዘላለማዊ እስትንፋስ እንዳይሰጥና በታሪክ መዝገብ እንዳይሰፍር ያደረገች ሃገር ዛሬ ሰተት ብላ እጆቿን በካቴና አስራ ስትመጣ፡ እንዴ አይደስት?ይፈንድቅ እንጅ።



መንገደኛው "ለምን በእግርኳስ ተዝናናን?" የሚል ዓይነት አቁዋም የለውም። እኔ ራሴ ቋሚ ተሰላፊ ባልሆንም መንገደኛው እግሬ ሲያደርሰኝ አንዳንዴ የአገር ውስጥ እግር ኳስ አያለሁ። አሁን አሁን ግን ትንሽ ትልቅ ሳይል ኢትዮዽያዊ ሁሉ ፕሪሚየርሊጉን ከመዝናኛነት ከፍ አድርጎ ዕንደ ዕለት ጉርስ አይቅርብኝ ሲል ስመለከት ፍለጎቴ እየቀነሰ እየወረደ መጥቶ ውድድሩ የማይሞቀው የማይበርደው ዓይነት ሰው እየሆንኩ ነው። እንዲህ እንደ አሁኑ አይነት በርካታ አጋጣሚወች ደግሞ ለዚህ አቋሜ ማጠናከሪያ ሳጋ ናቸው። መቼም እየሆነ ያለውን ነገር ተመልክቶ ሊመጣ ያለውን ነገር ለመገመት በመንፈስ ቅዱስ የተቀባ  ታላቅ ነብይ ወይም የፖለቲካ ተንታኝ አልያም የታሪክ ተመራማሪ መሆን የሚያስፈልግ አስመለኝም። ፕሪሚየር ሊጉን የመሰረታዊ ፍላጎታቸው አካል ያደረጉት ሰወች ቁጥር ከዓመት ዓመት እየጨመረ፣እንደ ልዩ ስልጣኔ ከከተማ ወደ ገጠር አድማሱን እያስፋፋ ነው ቅኝ ገዥው። አብዛኞቹ ጨዋታወች ቅዳሜና እሁድ መከናወናቸው በጀን እንጅ የመንግስት መስሪያ ቤቶች የተወረረ ከተማ በመሰሉ ነበር። በዓመቱ ውስጥ እንግሊዛዊያኑ የገና በዓልን በሚያከብሩበት ወቅት አብዛኛው ህዝባቸው ዕረፍት የሚወስድበት ወቅት ነውና አልባሌ ቦታ ጊዜውን እንዳያሳልፈው በማሰብ የበዓለት ቀን ጨቃታ{Feast Day Games}የሚል መርኅ ግብር አውጥተው ያዝናኑታል። በዚህ ሰሞን ታዲያ ጨዋታው የሚካሔደው ብዙ ጊዜ በእኛ የስራ ሰዓት ነው።


እግር ጥሏችሁ በዚህ ወቅት ወደ አንድ መስሪያ ቤት ጎራ ብትሉ የሰራተኛው ተሽከርካሪ ወንበር ላይ የተሰቀለ ጁባ {ኮት}እንጅ ሰራተኛውን ላታገኙት ትችላላችሁ። ዕድለኛ ካልሆናችሁ በቀር። ይህ እንግዲህ እስከሌሊቱ ሰባትና ስምንት ሰዓት ኳስ ላይ ሲያፈጥ አድሮ እንዲሰራበት ከተዘጋጀለት ጠረዼዛ ላይ ማታ አልጋው ላይ ያላገኘውን እንቅልፍ ለማግኘት የሚታትረው፣ቢሮውን መኝታ ቤቱ ያደረገውን ሳይጨምር ነው። ምነው የሚገዝት ካህን ጠፋ እንዴ? ኧረ በመድኃኒዓለም!  ኧረ በቅዱሳን!  የሚል ሽማግሌ ጠፋሳ? ሰሚ ጠፋኮ  ጎበዝ!  ምነው?  አሁንስ "የእፉኝት ልጆች" ተብሎ ትንቢት የተነገረብን እኛ እንሆን እንዴ? ታዲያ የራሳችን የሆነውን  ነገር መግደል፣መቅበር፣ማጥፍት ስራችን ብለን  ስንያያዘው እየታየ የእፉኝት ልጅ ያለመሆናችን የምናምንበት ምን ማርጋገጫ አለን?በፊታችን ቆሞ በጭካኔ ገፅታው የሚያጉረጠርጥብን በእጁ የያዘውን ጅራፍ ጀርባችን ላይ ለማሳረፍ የቋመጠ የሙሴ ዘመን ክፉ ግብጻዊ ሳያስገድደን ነገ የእምነት እሴቶቻችንን እና የርሳችንን ሃብት ውጦ ድሃ ሊያደርገን የተላከብንን ዘምነኛ ቀሰስተኛ ወራሪ ማቆም አቅቶን ታየው መንገደኛውን። ሰራተኛውን ከስራ እያስተጓጎለ በአዝጋሚው ምርታማነታችን ላይ በደንባራ በቅሎ ላይ የተጨመረ ቃጭል ሲሆን እንዳየነው ሁሉ፤በሌላም በኩል ተማሪውን ከትምህርቱና ከውጤቱ ሲያራርቀው ማየት እየተለመደ ነው።


ድሮ ድሮ ተማሪዎችን በብዙ ድካም ከገቡበት ዩኒቨርሲቲ ጠራርጎ ለሚያስወጣቸው የገና ማዕበል አሰልፈው ከሚሰጧቸው ምክንያቶች አንዱ የተቃራኒ ጾታና እርሱን ተያይዘው የሚመጡ ተፈጥሮአዊ ክስተቱን የምናስተናግድበት መንገድ ደካማ ሆኖ መገኘት ነበር። ዛሬ  ዛሬ ደግሞ ለተማሪዎቹ መዘናጋት የፕሪሚየር ሊጉ ጨዋታ ብቻ ሳይሆን የአርሴ ማንቼ ጎንጭ አልፋ ጭቅጭቅ አንዱ ነው ብሎ ለመገመት ሰፊ ጥናት የሚጠይቅ ጉዳይ ነው ብዬ አላስብም። ኧረ ከጭቅጭቅም ከፍ ብሎ የፕሪሚየርሊጉ ጣጣ ውደ ቡድን ጠብ ከፍ ያለ ግጭት የሚፈጠርባቸው እንዳሉ መንገደኛው ታዝቧል። ይህ ኳስ ሰራተኛውን ከስራው፣ተማሪውን ከትምህርቱ ሲያስተጓጉለው ምነው ሃይ ባይ ጠፋ? ይህን ምን እንለዋለን?ፕሪሚዬርሊግ ወይስ ስሌቭ ሊግ{slave league} ብሎ መንገደኛው ወደፊት ገሰገሰ።
        
                                                                      ምንጭ፦ ሐመር ዘኦርቶዶክስ ተዋህዶ 
                                                                                 ነሐሴ 2004 ዓ.ም

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የዶርም ውስጥ ፕሪይሚዬርሊግ [slave league] መጀመሩን ልብ ይሏል።

No comments:

Post a Comment