ማተብ{ማዕተብ} አንደኛው ፍች ምልክት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ቡራኬ ማለት ነው።ሥርወ ግሡም"አተበ"አመለከተ፤ባረከ የሚለው የግዕዝ ቃል ነው። ምልክት ሁል ጊዜ አንድን ነገረ ከሌላው ለመለየት-የሚያስችለው በመሆኑ ዓለም ይጠቀምበታል።ሐዋርያው ቅዱስ ዻውሎስ ውወደ ሮሜ ሰውች በላከው መልክቱ በአራትኛው ምዕራፍ ስለ አብርሃም ሲናገር"ሳይገረዝም በነበረው እምነት ያገኘ የጽድቅ ማኅተም የሆነ የመገረዝን ምልክት ተቀበለ"ብሏልወላጆችም መንታ ሲወልዱ የትናው ቀድሞ እንደተገኘ ለማስታወስ ምልክት ያደርጋሉ።ለምሳሌ በኦሪቱ ፋሪስና ዛራ ሲወለዱ አዋላጇ ቀድሞ በተወለደው አውራ ጣት ላይ ክት አስራበት እንደነበር ይናገራል። የኢትዮዽያዊያን ክርስቲያኖች ማተብ የማሰር ልማድ የመጣው ለረዢም ጊዜ የቤተክርስቲያናችን ሞግዚት ሆና ከቆየችው ከእስክንድርያ ቤተክርስቲያን ነው።በእስክንድርያ ኢቀ ዻዻስ ቴዎዶስዮስ ዘመን በሃገሩ የነበረው ዐላዊ ንጉስ በመሆኑ የክርስትናን አስተማሪዎች እያሰረ ያስደበድብ ነበር።ስለዚህም ቴዎዶስዮስ ካልሆነ ሰው ጋር ተጋፍጦ ከመቀሰፍና ሥራን ከማቋረጥ ዘወር ብሎ መዓቱን ማሳለፍ ይሻላል በማለት ሲሸሽ፤ያዕቆብ ልዘ አልበርዲአክርስትና ትምህርት ቀናተኛ የሆነ ሐዋርያ በሽሽግ ያስተምር ነበር።ይህንም የተቀደሰ ስራውን ለማሰናከልና ለማቋረጥ የሚሹ አንዳንድ ቦዘንተኞች በስብሰባው ላይ እየተገኙ ያስተማራቸውን ያስቱበት ያሻክሩበት ስለነበር የእርሱ የሆኑትን ለይቶ ለማወቅ ሲል በ አንገታቸው ላይ አድርገው ለምልክትነት እንዲጠቀሙበት ማተብ አሰረላቸው፤ያሰረላቸውም ማተብ ሶስት አይነት ባንድ ላይ የተገመደ ሲሆን ጥቁር፣ቀይ ቢጫ ነበር።ይኸውም ጥቁሩ መከራ እቀበላለሁ፣ቀዩ ደሜን አፈሳለሁ፣ቢጫው ትንሳኤ ሙታንን ተስፋ አደርጋለሁ የሚል እንደነበር ይነገራል።ያዕቆብ ዘ አልበርዳኢም ያስተምር የነበረበት ዘመን አምስተኛው መቶ ዓመት እንደነበር ይገመታል{ሃይማኖተ አበው፣ድርሳነ ያዕቆብ}
ከሣቴብርሃን ሰላማ በአራትኛው መቶ ዓመት ወደ ሃገራችን መጥቶ የክርስትና ትምህርት ፋናን ሲተክል ያመነ የተጠመቀውን ካላመነው ለመለየት ከግንባሩ ላይ በመብጣት ምልክት ያደርግ ነበር ይባላል።ግን የመብጣቱና ደም የማፍሰሱ ዘዴ በህዝቡ ዘንድ ሙሉ በሙሉ ስላልተደገፈ ከዚህ ጊዜ በኋላ እንደቀረ ይነገራል።አሁንም ሳይቀር ሰሜናዊያን ከግንባራቸው ላይ ምልክት የሚታይባቸው ከዚሁ ሲያያዝ መጥቶ ነው ይባላል።ምንም እንኳን መቼ እንደተጀመረ ከስንተኛው መቶ ዓመት ጀምሮ እንደምጸራበት በቂ መረጃ ባይገኝም ቤተክርስቲያናችን ማተብ የማሰርን ልማድ በደንብ ታከብራለች፤በቤተክርስቲያናችን ሥነ፡ሥርዓት መሰረት አንድ ህፃን ወይም አንድ ሰው ሲጠመቅ ሦስት የተለያየ ቀለም ያላቸው ፈትሎች በ አንድ ላይ ተገምደው ለዚሁ የተወሰነው ጸሎት ተደርሶባቸው ለተጠማቂው ይታሰርልታል፤ክሩም ነጭ ቀይና ሰማያዊ ሲሆን፤ነጩ ሐዲስ ህግን[ወንጌልን]እጠብቃለሁ፤ቀዩ በክርስቶስ ፍጹ ድኅነት እንደማገኝ አምናለሁ፤ሰማያዊውም ሰማያዊ ሕግን በመጠበቅ ሰማያዊ ሕይወትን ተስፋ አደርጋለሁ ማለት እንደሆነ የኢትዮድያ ሊቃውንት ያትታሉ።ስለዚህም ቤተ ክርስቲያናችን ይህን ምልክት በ አንገቱ ላይ በማድረግ አባልነቱን ታጸናለታለች። የማተብ ማሰር ሁኔታ ከሊቃውንቱ ይልቅ በህዝቡ ዘንድ በጣም የጠበቀ ሆኖ ይታያል።ከዚሁም የተነሳ በሕዝባዊ አነጋገር ዕገሌ ማተብ የለውም ሲባል ሃይማኖት የለውም በእምነቱ ያልጠበቀ ወላዋይ በተናገረው የማይቆም እግዚአብሔርን የማይፈራ ማለት ሲሆን ዕገሌ ማተብ ያለው ሰው ነው ሲባል ደግሞ ከማለ የማይከዳ የማይዋሽ የማይቀጥፍ እውነቱን እውነት ሐሰቱን ሐሰት የሚል የተናገሩት ከሚጠፋ የወለዱት ይጥፋ በሚለው ምሳሌያዊ አነጋገር ተደግፎ የሚራመድ ማለት ነው።አሁንም በጊዚያችን ሃሳብ የተመሰረተ ባሕላዊ ሙዚቃ <<ባለማተቢቱ>>በሚል መነሻ ይጀምራል።የድርሰቱም ጠቅላላ ሃሳብ ወደተቀደሰው ጋብቻ ስትገቢ የሁለታችንንም አንድነት ተረድተሽ ቀይ ስታይ ቀይ ጥቁር ስታይ ጥቁር ሳጦት ሆኝ በሰላም ልጆች ሽን የምታሳድጊው ኢትዮዽያዊ የትባረክሽ ነሽ በማለት በሃይማኖት ክልል ውስጥ ሆና ሲመቻት ብቻ ሳይሆን በመከራም ባለቤቷን አክብራ የምትኖረውን ሴት የሚያሞግስ ነው።ይህም ራሱ ባለማተብ ማለት በሕዝብ ምን ያህል ግልፅ እንደሆነ ያስረዳል።
ምንጭ፦ http://www.ethiopianorthodox.org/amharic/archivee/miscellenous/mateb.pdf
No comments:
Post a Comment