Thursday, February 04, 2016

ሰማይ ሆዱ ባባ !










ዘመኑ ምቀኛ ትውልዱ ጠማማ፣

ሰማዩ አመፀኛ ልመናን ማይሰማ፣

ሲያሰቃየን ከርሞ በድርቅ እያስጠማ፤

የምናደርገውን አሳጥቶን መላ፣

መፍትሄ ሲቸገረን እርስበርስ ስንብላላ፣

በረሃብ ላለማለቅ ስንገባ መኀላ፣

በውኃ ቀጠነ ልጅ አባቱን ሲቀትል፣

እናት በልጆቿ ጡቷን ስታሽ ስትምል፣

ገዥም ተገዥው ላይ መሳሪያውን ሲስል፤

ከንፁኀን ሰፈር ሲወርድ የቦምብ ናዳ፣

ከባህታዊያን ደጅ ፈንጅ ሲፈነዳ፤

?እረኞች? በጎችን ከጋጥ ሲያባርሩ፣

በጎችም በረግገው ሲሉ ይብላኝ ዱሩ፣

ተኩላዎች በደስታ ሲጮሁ ሲያቅራሩ፤

መሬት ይህን አይታ ልቧ ሲደነግጥ፣

መሠረቷ ሲናድ አቋሟ ሲናወጥ፣

መላው አካላቷ ሲሼክ ሲንቀጠቀጥ፤

ሰማይ ሆዱ ባባ ሰውነቱ ራደ፣

ጥፋቱን አመነ አመዱን አመደ፣

"ማሩኝ ልካሥ" አለ ለመነ ማለደ፣

በዝናቡ ፈንታ ዐሣን አወረደ።


                                    ጌታነህ ካሴ
                                    ጥር  25/2008ዓ.ም    

No comments:

Post a Comment