Saturday, February 20, 2016

ከዘንዶ አፍ የወጣች ርግብ

በወላጆቼ ቁጥጥር ስር አጥቸው የኖርሁትን ነጻነት እስከማጣጥም ድረስ ስለጓጓሁ  የዩኒቨርሲቲት መግቢያ ቀን የተነገረ ዕለት የተሰማኝ ደስታ የተለየ ነበር። ከቤት ትምህርትቤት ከትምህርትቤት ወደ ቤት ከዚህ ውጭ የትም ቦታ መሄድ አይፈቀድልኝም። እናቴ ለትምህርት ካላት ፍቅርና ለነገ ማንነቴ ከምትሰጠው ከፍተኛ ግምት አንጻር ዩኒቨርሲቲት እንድገባ ታበረታታኛለች እንጅ ከእርሷ ርቄ እንድሄድ  አትፈልግም። አላቻለችም እንጅ ወደ ቅርብ ዩኒቨርሲቲ ለማስቀየር  ሁሉ አስባ ነበር። ዘንድሮ ከእስር የተፈታሁ ያክል ይሰማኝ ጀምሯል።ከቀናት በኋላ ግን ከጓደኞቼ ጋር በዲፓርትመንትም በመኝታም በመለያየታችን ብቸኝነት  እየተሰማኝ መጥቷል። ትምህርቱ የቡድን ስራው አስጨንቆኛል። ቀናት ነጎዱ ወራትም ተቆጠሩ፣መንፈቀ ዓመትም ሆነ። ቁንጅናየ የግቢው መነጋገሪያ እንደሆነ ከሰማሁ ጀምሮ በራሴ ብተማመንም ሕይዎት እያስጠላኝ፤የፈለጉትን በልተው ፤የልብስ ዓይነት የልብስ ፋሺን እያቀያየሩ የሚያጌጡ የግቢያችን ተማሪዎች ኑሮ እያስቀናኝ መጥቷል።"ሰሞኑን ደግሞ ምን በወጣሽ ነው ታፍነሽ የምትኖሪው? የምትሞችበትን ቀን ለማታውቂው ስለምን ራስሽን ታጨናንቂያለሽ ይልቁኑ እንደጓደኞችሽ ነጻ ሁኝ የቤትሽ ይበቃሻል። አንቺኮ ባትማሪም በቁንጅናሽ ብቻ ተከብረሽ መኖር የምትችይ ሴት ነሽ ። ስለዚህ ፈታ በይ" የሚል አንዳች ስሜት ያስጨንቀኛል።


በዚህ ላይ የሁለቱ ጓደኞቼ የተለያየ ምክር ግራ አጋብቶኛል። አንደኛዋ ጓደኛዬ ከቤተክርስቲያን የማትለይ፣ በግቢ ጉባኤ አገልግሎት የምሳተፍና ኮርስ የምትከታተል ታታሪ ተማሪ ናት። የሚገርመኝ ግን ሌሎች ተማሪዎች ሌሊትም ቀንም እያጠኑ የእርሷን ያህል ውጤት ማስመዝገብ አለመቻላቸው ነው። እርሷ ቤተክርስቲያን እንድሄድ፣ኮርስ እንድማር እንድጾም፣እንድጸልይ ብትመክረኝም እኔ ግን ምክሯን ለመቀበል አልፈልግም። ባገኘችኝ አጋጣሚ ሁሉ ስለምትመክረኝ ባላገኛት እመርጣለሁ። ሌላኛዋ ጓደኛየ ደግሞ ደስ ሲላት የምትማር፣ደስ ሳይላት የምትተኛ ፣አምሽታ የምትገባ፣ አርፍዳ የምትነሳ ሰነፍ ተማሪ ናት። በውጤት ግን በዚህም በዚያም ተሯሩጣ  ወይ [A] ያም ባይሆን [B] ታስሞላለች ። ስለምንም ስለማንም የማትጨነቅ ፣የወደደችውን የምታደርግ ሴት መሆኗና  ነጻነቷ ያስቀናኛል። እንደሷ እንድሆን የምታደርገው ጥረትም ተመችቶኛል። ድንግልናዬን ለባለሃብት ብሸጥ መክበር እንድምችል ፤ ከዚያ በኋላ ደስተኛ እንድምሆንና ጭንቀቴም እንደሚቀልልኝ  ከመከረችኝ ወዲህ ያለችኝን ሁሉ ማድረግ እንደሚገባኝ አምኛለሁ። የእናቴ የገቢ ምንጭ በመቀነሱ  ለኮፒ ለማስታወሻ መግዣና ለዓመት በዓል ካልሆነ በስተቀር በቂ ገንዘብ አትልክልኝም። ገንዘብ አልበቃሽ እያለኝ በወር የሚቆረጥልኝ ገንዘብ እያነሰ ቢመጣም ምኞቴ ግን እየጨመረ ሄዷል። ስለዚህም የአንደኛዋ ጓደኛየ ምክር ሕየወቴን ለመለወጥ ጥሩ አማራጭ እንደሆነ ተገነዘብሁና እርሷ ከመረጠችልኝ ሰው አስማማችኝና ቀጠሮ ይዘን ተገናኘን።


ሰውየው ሽማግሌ ናቸው ። አባት ብቻ ሳይሆን አያት እንደሚሆኑኝ  ሰውነታቸው ይመሰክራል። "ኧ... የቁንጅናሽን ዝና ሰምቻለሁ ። ድምጽሽን ለመስማት ዓይንሽን ለማየት በመታደሌ ዕድልኛ ነኝ። ኧ... ይገርምሻል፤ ስልክሽን ለማግኘት የልፈነቀልሁት ድንጋይ የለም። ዛሬ ግን ኧ ..."በርካታ ማሞካሻ ቃላትን እየመረጡ የፈለግሁትን ሁሉ እንደሚያደጉልኝ በተስፋ ይሞሉኝ ጀመር። ቤት እንደሚከራዩልኝ በየ ወሩ ገንዘብ እንደሚቆርጡልኝ ቃል ሲገቡልኝ ስሜቴ ልዩ ነበር። ደስታየ ጨመረ ተስፋየም ለመለመ። በየቀኑ የሚሰጡኝን የገንዘብ መጠንና በግቢው ውስጥ ካሉ የሃብታም ልጆች በላይ ዘንጬ መታየቴን ሳስብማ ጭራሽ ደስታዬ ጨመረብኝ። ሰዓቱ እየመሸ ነው። ጀምበሯ ጠልቃ ጨለማው በግርማ ነግሷል። እራት ልንበላ ሆቴል ገብተናል። ሁሉም ነገረ አዲስ ስለሆነብኝ ብፈራም "የኔ እምቤት እንደወንድም ቁጠሪኝ፤ምንም እንዳትፈሪኝ አይዞሽ" የሚሉ የማረጋጊያ ቃላቶቻቸው አሸነፉኝና ክብረ ንጽህናየን ልሸጥላቸው ተስማማሁ። ወደ ምናድርበት ክፍል ገብተን ልንተኛ ስንዘጋጅ በቅርብ ርቀት ያለ አንድ ታላቅ ድምጽ በጆሮዬ እየተወርወረ ይገባል። ቃሉን መስማት ባልፈልግም ላለመስማት  አልቻልሁም። ሰባኪው "ሰው ግን ክቡር ሆኑ ሳለ አያውቅም፤እንደሚጠፉ እንስሶች መሰለ ተብሎ ተጽፏል። ግን ማን ይሰማል?  ድንግልናችሁን ያለጊዚያችሁ የምትጥሉ ሴቶች ወዮላችሁ፤ ወዮታ አለባችሁ ተብሎ ተነግሯል። ግን ማን ያስተውላል? እያለ ወጣቶችን ይገስጻል።


"ትምህርቱ ቀጥሏል "እስኪ ራሳችንን እንጠይቅ። ጨለማን ተገን በማድረግ ገናለገና ወላጆቻችን አያዩንም በማለት በየጭፈራና በየምሽት ቤቱ ምን እያደረግን ነው? ሰው ሆነን ቤተሰቦቻችንን፣ ቤተክርስቲያናችንንና ሃገራችንን ማገልገል ሲገባን እንዴት በገንዘብና በጊዚያዊ ስሜት ተሸንፈን ቅዱሱን ገላችንን በረከሰ ገበያ እናውላለን? ቅዱስ ዻውሎስ በመልክቱ 'እንግዲህ ለምኞት እንዳትታዘዙ በሚሞት ስጋችሁ ኀጢአት አይንገስ። ስለሥጋችሁ ድካም እንደ ሰው ልማድ እላለሁ፤ብልቶቻችሁ ዓመፃ ሊያደርጉ ለርኩሰትና ለዓመፃ ባሪያወች አድርጋችሁ እንዳቀረባችሁ እንዲሁ ብልቶቻችሁ ሊቀደሱ ለጽድቅ  ባሪያወች አድርጋችሁ አሁን አቅርቡ። ስጋችሁ የክርስቶስ ብልት እንደሆነ አታውቁምን? እንግዲህ የክርስቶስን ብልቶች ወስጀ የጋለሞታ ብልቶች ላድርጋቸውን? አየገባም። ወይስ ሥጋችሁ ከእግዚአብሔር የተቀበላችሁት በእናንተ የሚኖር የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደሆነ አታውቁምን? በዋጋ ተገዝታችኋልና ለራሳችሁ አይደላችሁም ስለዚህ በሥጋችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ' በማለት የነገረንን ቃል በተገባር እናውለው" ይላል። ሰንውቴ በመጠጥ ቢዝልም ሰባኪው እየተናገር ያለው ነገር እኔ ስላማደርገው በመሆኑ በትኩርት አዳምጠው ነበር። ከትምህርቱ ጋር እናቴ  "ልጄ የዩኒቨርሲቲ ሕይወት ላወቁበትና በትግስት ለተውጡት በረከት ፤ክብርቸውን ላጡንበትና ለቀለዱበት ውርደት መሆኑን  አትርሺ፤አደራሽን ልጄ እንዳታሳፍሪኝ።ተመርቀሽ ስትመለሽ በተክሊል እንድድርሽ ራስሽን ጠብቂ" እያለች ስታስጠነቅቀኝ የነበረው ሁሉ ትዝ ስላለኝ ሕሌናዬ ተረበሸብኝ። ወጥቼ እንዳልሄድ መሽቷል፤እንድላድር የሰማሁት ቃል ከብዶኛል። ትምህርቱ አልቋል። እኔ ግን ከተመሰጥሁበት ሃሳብ የሚመልሰኝ አጣሁ፤የሚያስረሳኝ መስሎኝ እየደጋገምሁ ብጠጣም ከአእምሮየ ሊወጣ አልቻለም።


"ምነው? ምን ሆነሻል? ዘና በይ እንጂ! አትጨነቂ ሁሉንም ነገር ለእኔ ተይው" አሉኝ ሽማግሌው። ተደብቼ በማየታቸው። እርሳቸው እኔ የምሰማውን አይሰሙም፤ቢሰሙም "ይሄ ስለሴቶች እንጅ ስለእኛ የተነገረ አይድለም፤ወይም ደግሞ የእኔ እመቤት አትስሚው። ይልቁን ቁንጅናሽን ዋጋ ስጭና ተደሰቺ።"እንደሚሉኝ  ከሁኔታቸውና ከሚነግሩኝ ወሬ ዝርክርክነት መገንዘብ ችያለሁ። ሰውየው ፍላጎታቸውን ሳይፈጽሙ እንደማይለቁኝ ባውቅም እንደምንም ብየ ማምለጥና ወደ ግቢ ለመግባት አሰብሁ። ግን እንዴት ልወስን? ደግሞ መጠጡ ስለጎዳኝ መንገድ ላይ የምወድቅ መስሎ ታየኝ። ይህንን ሃሳቤን ከሰውየው ጋር ላገናኘችኝ ጓደኛዬ ስልክ ደውዬ ሳማክራት "አንቺ አብደሻል እንዴ? በገንዘብ ላይ ገንዘብ ከምታገኝበት ዕድልና በክብር ከምታድሪበት ቤት ወጥተሽ ጎዳና ላይ ከአውሬ ጋር የምታድሪው ምን ነክቶሻል? 'ጨዋ ልጅ ናት' ብየ አስተዋውቄሽ እኔን ጭምር ታዋርጅኝ በይ ዝም ብለሽ እደሪ። እኔ አምሮብኝ የምማረው  እኮ እነጋሽየ ጋር ስወጣ በማገኘው ገንዘብ ነው። ይህንን እድል ዳግመኛ አታገኝውም። እንዲያውም ከተመቸሻቸው አንዱን ቤታቸውን ሊያወርሱሽ ይችላሉ።"አለችኝ። ሀሳቤን ቀይሬ "ገንዘቡን ከተቀበልሁ በኋላ ንስሐ እገባ አይደል" ብየ አብሪያቸው ላድር ብፈልግም "ኃጠትን እያወቁ ሰርቶ 'ንስሐ እገባለሁ' ማለት እግዚአብሔርን መገዳደር ነው። ስለዚ ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ እንደሚባልው ከመውደቃችን፣ከመቀሰፋችን በፊት ራሳችንን እንጠብቅ" የሚለው የሰባኪው ትምህርት ታውሰኝ። በተለይ "ድንግልናችሁን ያለጊዜው የምትጥሉ ወዮላችሁ" የሚለውን ሳስብማ ሰውነቴ ተንቀጠቀጠብኝ።


 ከሰውየው ጋር ባድር የሚገጥመኝን ሁሉ ወድኋላ አስታውስ ጀመር። ባረግዝ እኔም የሚወለደው ልጅም የቫይረሱ ተሸካሚ መሆናችንና ከግቢ ተባርሬ ጎዳና ላይ መውደቄን፤ቁንጅናዬ ጠፍቶ ምጽዋት ጠያቂና የሰወች መሳለቂያ መሆኔን ባሰብሁ ጊዜ ከክፍሉ ወጥቼ ሮጥኩ። ሰውየው መኪናቸውን ይዘው ቢከተሉኝም ምን ኃይል እንዳገዘኝ አላውቅም ሳይደርሱብኝ ከግቢያችን ደርስኩ። በሩ ሳይዘጋ በመድረሴ ፈጣሪዬን አመሰገንሁት። ሰዓቱ በመንጎዱ ግቢው ጸጥ ብሏል። ያቃጠረችኝን ልጅ ቁጣ ታግሼ ከመንፈሳዊቷ ጓደኛዬ ጋር አደርኩ። ሁሉን ነገር ሳስረዳት ከውርደት እንድድን  ማምለጫ መንገዱን ያመቻቸልኝን እግዚአብሔርን እያመሰገነች አለቀሰች። በጥዋት ስነሳ ሰውነቴ ይንቀጠቀጣል። ማታ የነበረውን ሁኔታ እይሳትወስሁ አለቅስኩ። ጓደኝዬ ከእርሷ የንስሐ አባት ጋር አገናኘችኝና እርሳቸውም "በጽድቅ የሚገኝ ጥቂት ነገር በዓመጽ ከሚገኝ ከብዙ ትርፍ ፤መልካም ስም ከብዙ ባለጠግነት፤መልካም ሞገስ ከብርና ከወርቅ ይበልጣል። በጠማማ መንገድ ከሚሄድ ባለጠጋ  ያለ ነውር የሚሄድ ደሃ ይሻላል።" እያሉ ካስተማሩኝ በኋላ ያለ ጊዜውና ያለሰዓቱ ክብርን አሳልፎ መስጠት ኃጢአት መሆኑን፤ላለፈው ይቅር እንዲለኝ ለሚመጣውም እንዲጠብቀኝ ንስሀ ገብቼ እግዚአብሔርን እንድማፀንና ከቤቱ እንዳልርቅ መክረው አስጥንቅቀው መለሱኝ። ከዚህ ቀን ጀምሮ ከቤተክርስቲያን ተለይቼ አላውቅም። ሕይወቴም እየተስተካከለልኝ መጥቷል። ከዓለማዊ ትምህርቴ ውጭ በሚኖረኝ ትርፍ ጊዜ የግቢ ጉባኤ ኮርሶችን መከታተል በትምህርቴም ጥሩ ውጤት ማስመዝገብ ጀምሪያለሁ። የሚያስጨንቀኝ ክፉ አስተሳሰብና መንፈስ አሁን የለም። ብቸኝነት ሲሰማኝ ለንስሐ አባቴ ሳማክራቸው ይቀልልኛል። ሙሉ ቀሚስና ትእምርተ መስቀል ለብሼ ወደ ቤተ ክርስቲያን መሄድ ከጀምርሁ ወዲህ ቀድሞ በሱሪ ስዘንጥ የሚያውቁኝ ሁሉ ይገረማሉ። ያስቸግሩኝ  የነበሩ ወንዶችም ማክበር ጀምረዋል። ሌሎች ጓደኞቼም እንደ እኔ ቤተ ክርስቲያን መሄድና የሰርክ መርሃ ግብር መከታተል ጀምረዋል። በዚህ ዓመትም የመመርቂያ ጽሁፌን ለመስራት ዝግጅቴን አጠናቅቂያለሁ።ለዚህ ያበቃኝ ልዑል እግዚአብሔር ስሙ ይክበር ይመስገን ። 

 

                                                           ምንጭ፦ ጉባኤ ቃና ዘኦርቶዶክስተዋህዶ
                                                                          ይካቲት  2007 ዓ.ም

No comments:

Post a Comment