Monday, June 13, 2016

ዩኒቨርሲቲ መግባት፡ ምርምርና ሀልዎተ እግዚአብሔር

ተማሪ ወደ ከፍተኛ የትምርት ተቋም የሚሄድበት ዋና ዓላማው ጽንሰ ሃሳባዊውንና ተግብራዊውን የዕውቀት ውኃ ምንጭ ከሚሆነው ተቋሙ ለመቅዳትና ለሚጠበቅበት የነገ ኃላፊነት ማዋል እንደሆነ እሙን  ነው።በዩኒቨርሲቲ ቆይታውም ትምህርቱን ለመቀበልና ተመርቆ ለመውጣት ከሚያስችሉ ነገሮች አንዱ ለእውቀት የተዘጋጀ አእምሮ ይዞ መገኘቱ ነው።ይህ ለእውቀት የተዘጋጀ አእምሮው በእውቀት መጎልመስን ጨምሮ ለተለያዩ ጠቃሚ ምርምሮች፣የፈጠራ ስራዎች፣ አዳዲስ አስተሳስቦችና የችገር ምልከታዎች እንደሚያበቃ በሁሉም ማህበረሰብ ዘንድ ይታመናል።ሆኖም ይህ ለእውቀት የተዘጋጀ አእምሮው በራሱ በትምህርቱ ሂደትም ይሁን በዙሪያው ከበው በሚገኙ ተጽዕኖዎች የተነሳ በአሉታዊ መልክ ተቀርጾ ከመነሻው በተቃራኒ እንዲቆም ሲደረግ ይስተዋላል።በዙሪያው ከበው የሚገኙትን ተጽዕኖዎች የዛሬ ትኩረታችን ባለመሆናቸው በመተው በራሱ በትምህርቱ ሂደት ውስጥ የሚመጡትን ተያያዥ ተጽዕኖዎች ብቻ ለማንሳት እንሞክራለን።ይህም ዘመናዊ ትምህርትንና ሳይንሳዊ ምርምሮችን አዝለው የሚመጡት ሃይማኖት አልበኝነትና የግብረገብነት ችግሮች መንፈሳዊ ሰው እንዴት ማየትና ማለፍ አለበት እኛስ ምን ምን ቅድመ ዝግጅቶችን ማድረግ ይጠበቅብናል?፤ትምህርቶቹስ በራሳቸው ከሃይማኖት የሚያርቁ ናቸውን? የሚሉትን በተወሰነ መልኩ ለማየት እንሞክራለን።

ከላይ ከመነሻችን ወጣትነትና ተማሪነት  ለለውጥ በተዘጋጀ አእምሮ ገጽታ ማንሳታችን ይዘን ወደ ዩኒቨርሲቲ ከሚገባ አዲስ ተማሪ ጋር አብረን ዩኒቨርሲቲ እንግባ።ማንኛውም ሳይንሳዊ ምርምር  ከምንም(de novo)የሚጀምር ሳይሆን መድረሻውን የሚያደላድልበት ለድምዳሜው ማነጻጸሪያ ምልክት  የሚሆነው መነሻ (premises)እንዳለው የታወቀ ነው።ይህ መነሻ ነጥብ እውነትነቱ ከመጀመሪያው ታምኖበት እሱን የሚቃረን አዲስ ግኝት ከመጣ ደግሞ ላለመቀበል፤እሱን የሚደግፍ አዲስ ሃሳብ ከመጣ በነበረው እውቀት ላይ ጨምሮ ለመቀበል ተመራማሪው አምኖ የሚሰማራበት/የሚሰማራለት ነው።እንዲህ አይነት መነሻ አቋም ያለው ለለውጥ የተዘጋጀ ተመራማሪ መሆኑን ልብ እንበል!!ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም የሚመጣ ተማሪም ለእውቀት የተዘጋጀ መሆኑን ፣በተለይ ለአእምሮአዊ እድገት የተዘጋጀ መሆኑን ተነጋግረናል።ይህ ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚገባ ተማሪም ከዚህ ከተመራማሪዎች ጋር የሚያመሳሰሉት ነገሮች አሉት።አንደኛው ሁለቱም ጥበብን ለመቅሰም ለለውጥ የተዘጋጁ መሆናቸው ሲሆን፤ሌላኛው ደግሞ ሁለቱም መነሻ መሬት(premises)ያላቸው መሆኑ ነው።አዲስ ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚገባ ተማሪ ልክ እንደ አጥኝው ሊፋለሱ በኋላ በሚመጡት አዲስ የተቃርኖ ግኝቶች ሊናዱ የማይገባቸው መሰረቶች (premises) እንዳሉት መገንዘብ አለበት።እነዚህም መነሻ መሰረቶች ለእውቀት የተዘጋጀው የተማሪ አእምሮ ለለውጥ የማያቀርባቸው፣በዩኒቨርሲቲ ቆይታው  ለሚያጋጥሙት አሉታዊ ገጠመኞች  የማያጋልጣቸው እርሱ ራሱ ወደ ተቋሙ ሲገባ ማንነቱን ይዘው ለዛ ለውጥ እርከን ያበቁት ማንነቶቹ ናቸው።

 ከነዚህ ማንነቶቹ ውስጥ አንዱ ሃይማኖቱ ነው።የአንድ ክርስቲያን ማንነት የሚገነባው  ደግሞ በሃይማኖቱ አጥር ውስጥ በሚገኘው ክርስቲያናዊ ሕይዎት ላይ ነው ።ስለዚህ ኦርቶዶክሳዊ ወጣት ወደ ዩኒቨርሲቲ ሲሄድ ሃይማኖቱንና ክርስቲያናዊ ማንነቱን ይዞ ይሄዳል።ቤተሰቦቹ እርሱን ያሳደጉበት ጨዋነት፣ያለበት ሥነምግባሩ፣ለነገሮች ያለው በጎ እይታ፣እምነቱና ጠቃሚ ባህሉ እስከዚያ እድሜው ድረስ የተገነባባቸው በጎ እሳቤዎች ሁሉ በአጠቃላይ ሰውና እግዚአብሔርን አስደስትበታለሁ ብሎ የሚሳባቸው ማንነቱ ለሱ መነሻዎቹ ናቸው።የትኛውም ተማሪ ከመነሻው አንዳች ጥሩ ነገር ሳይኖረው ወደ ዩኒቨርሲቲ ገባ ማለት የሳይንስ አጥኝው ምርምሩን ያለ መነሻ(premises)እንደጀመረ ነው።ያደግሞተፋልሶ እንጅ ምርምርም ለውጥም ሊሆን አይችልም።አንድ ሰው ደግሞ አንዳች ጥሩ ጠባይ ኖሮት ወደ መጥፎ ጠባይ ሊቀየር ይችላል።ብዙ ተማሪዎች ድሮ ያልነበራቸውን ጠባያት፣ማለትም በሱስ መጠመድን፣ ከመጥፎ ጓደኞች ተጽዕኖ የሚመጡ ችግሮችን ፣ለትምህርታቸው አሉታዊ አመለካከት ማሳየትን ፣በተለያዩ የወጣትነት ፈተና ወድቆ ተስፋ መቁረጥን  ሊያሳይ ይችላሉ።ይህ ደግሞ ከአላማቸውም ሆነ ከሃይማኖታቸው  በተቃራኒ መቆም ነው ። ባስ ካለም ደግሞ ለተለያዩ የፍልስፍናና የክህደት ዝንባሌዎች የሚዳረጉትም በዚሁ በይኒቨርሲቲ ቆይታቸው ሊሆን ይችላል።

ይህ የሚሆነው እውነትንና ጥበብን በመፈለግ መንገድ ላይ ያለ መነሻ መድረሻችን ስናልም ነው።አጥኚው ከመሬት ተነስቶ የሀሰት ድምዳሜዎቹን ደርሸበታለሁ እንደማለት ቀድሞ በውስጡ የነበረውን የኃልዮተ እግዚአብሔር መሰረቱን ንዶ በንባብና በግልብ አመክንዮ ብቻ ተነስቶ ኢአማኒነትን እንደ ትክክለኛ መንገድ ደርሼበታለሁ ቢል ይህ ተፋልሶ እንጂ ምርምርም ጥበብም አይሆንም።ከሳይንስ መሰረታዊ አካሄድ እንኳ ይህንን አቢይ ነጥብ መረዳት እየቻሉ የብዙ ወጣቶች  በዚህ ሕይዎት ውስጥ መጠቃታቸው ያሳዝናል። እዚህ ላይ አብነት የሚሆኑን የባቢሎን የህግ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የነበሩትን ህጻናት እናንሳ።ዳንኤልና ሦስቱ ሕጻናት አናንያ አዛርያና ሚሳኤል ወደ ባቢሎን ሕግ ትምህርት ቤት ሲገቡ የነበራቸውን ማንነት መጽሐፍ ቅዱስ  "ነውር የሌለባቸውንና መልከ መልካሞቹን በጥበብ ሁሉ የሚያስተውሉትን እውቀትም የሞላባቸው አስተዋዮች የሆኑትን"   እያለ ይገልጻል።(ት/ዳን 1:4-7) ይህ ማንነታቸውና ስብዕናቸው ከመንፈሳዊ  ኑሮ የተገኘ በኋላ  በሕግ ትምህርት ቤቱ ለሚያገኙት አዲስ እውቀት  ማመሳከሪያ የሚሆንና ሊኖሩ የሚችሉ ለውጦችን መመርመሪያ ቋሚ ማንነታቸው ነበር።ይህም ከሃይማኖት የተገኘ ማንነት  መሆኑን ማስተዋል ያስፈልጋል።ታዲያ እነዚህ ህጻናት ይህን ቋሚ ማንንነታቸውን የሚቃወም ለውጥ ብቻ ሳይሆን የአሉታዊ ለውጥ መንገድንም  ጭምር እምቢ ብለው ተቃወሙት።ይኸውም ኋላ ላይ  ስለሆድ ምክንያት ለጣዖት  መስገድን የሚያመጣባቸውን  የባቢሎን ጮማና ጠጅ መቃወማቸው ነበር።የድሎትን መዘዝ አስቀድመው አውቀዋልና እንዲሁ በቸልተኝነት አላለፉትም።

መንፈሳዊ ተማሪም በወጣትነት የእውቀት ገበያ ማንም የፍልስፍናና ምንፍቅና (ጮማና ጠጁን)እንደ ወደደ ይሞላበት ዘንድ  ባዶ እንዳይሆን አስተማሩ።አሁን ከቀረበላቸው ጮማና ጠጅ አስቀድመው በሚያውቁት የሃይማኖት ሙላትና  ማንነት አዲሱን ለውጥ ለመመዘን ችለዋልና  የኋለኛውን አዲስ ነገር ናቁት ።በግልብ አመክንዮ የተመራመሩ አይደሉም።ይልቅ ስለነሱ መጽሐፉ እንደነገረን በምግባራቸው  ነውር የሌለባቸው፣ለብስለታቸው አስተዋዮች የተባለላቸው ፣መልከ መልካሞችም የሆኑት ናቸው እንጂ።ከሃይማኖታቸው በተቃራኒ የሚቆም አዲስ ግኝት (በጮማና በጠጅ የመደሰት አማራጭ)ሲገኝ ከምንም ነገር በፊት ያደረጉት ነገር አስቀድሞ እውነትነቱ ተረጋግጦ  በሚታመነው ማመሳከሪያቸው (በሃይማኖታቸው )ሚዛን ላይ ማስቀመጥ ነበር ።ከቀዳሚው እውነት ጋር ተቃርኖ ሲያሳይ ጊዜ የኋለኛውን እንዳይቀበሉ በእምነት እምቢ አሉ። ሌላው ሳይንስ እና ሳይናዊ እውነታዎችን የምናይበት መነጽር የጠራና ክርስቲያናዊ ብርሃን ከሌለው በጠራራ ቀን በጨለማ ሊያስኬደን እንደሚችል ማስተዋል ያስፈልጋል ።ከዚህ በፊት በታተሙ እትሞች እንደተብራራው  ሳይንሳዊ ምርምር በዚህ ምድር ስንኖር ላለብን ኃላፊነት ይጠቅመናል።ሆኖም ሳይሳዊ ምርምር ሕይዎትን የምናጠናበት አንዱ መንገድ እንጂ የሕይወትን  መንገዶች ሁሉ የምናጠናበት ብቸኛ መሳሪያ አይደለም።

 ሳይንሳዊ ምርምር በቦታና መጠነ ቁስ  የሚወሰኑ(mass&volume)ና የኃይል አይነቶችን(energies)በማጥናት ላይ የሚያተኩር ሲሆን፣እነርሱን በመስፈር (measurement)ይመሰረታል።የሕይወት ገጽታወች ግን እጅጉን ከዚህ ሰፋ እንደሚሉ ደግሞ የታወቀ ነው ።የማይሰፈሩ ግን ያሉ ነገሮች አሉ፤ቁስ አካላዊ ያልሆኑ ጉዳዮች አሉ።በአጠቃላይ ከሳይንስ ምርምር ክልል ውጪ(out of scientific range)የሆኑ ብዙ ጉዳዮች አሉ። ፍቅር፣ጥላቻ፣ሀዘን፣ደስታ እነዚህ ሁሉ የሕይወት እውነታ በመሆናቸው ማንም ሰው የሉም ብሎ ጥያቄ አላነሳባቸውም።አንድም ሰው ደግሞ የፍቅርን መኖር በሳይሳዊ ምርምር ያረጋገጠ የለም። ሌሎችንም እንዲሁ።ስለዚህ ሕይወትና እውነትን በማወቅ ጥረት ውስጥ ሳይንስ ውሱንነት(scope limitation)እንዳለው ማሳያ ይሆናሉ። ነገረ እግዚአብሔርንም ስናነሳ ሳይንስ ሊያጠናው የሚችል ጉዳይ አይደለም።ሳይንስ ቁሳዊው ነገሮች ላይ ሲያተኩር ፣ክብር ይግባውና እግዚአብሔር መንፈሳዊ አካል ያለው እንጂ ቁሳዊ አይደለም፤ሳይንስ የሚሰፈር የሚቆጠር ነገር ሲያጠና እግዚብሔር ፍጥረትን ሰፍሮ የሚገዛ እንጂ ራሱ በፍጥረቱ የሚለካ አይደለም።በመሆኑም ኃልዮተ እግዚአንሔርን መመርመር ከሳይንስ አቅም በላይ ነው።ሳይንሳዊ መሳሪያወች (scintific tools)ሳይንስ በሚያጠናበት  መስክ ብቻ የሚገኙትን ጉዳዮች ብቻ ለመስፈር የተዘጋጁ እንጂ፤ከዚያ መስክ ውጭ ላለው ነገር አያገለግሉም።ለምሳሌ የደስታን ሙቀት፣ክብደት፣ ቁመት፣ፒኤች፣ ፍጥነት ወዘተ በሳይንሳዊ መሳሪያዎች መለካት አቻልም።

በእግዚአብሔርና በሰው መካከል ያለውንም መንስፈሳዊ ትስስር ፣መግቦቱን፣ ተስፋውን፣ በሃይማኖት የምትታወቀውን ሰማያዊ ሕይወት፣ በምድራዊ ምርምር ልናውቅ አንችልም።ሳይንሳዊ መሳሪያዎች ሊሰፍሩት ፣ሳይንሳዊ ድምዳሜ ሊያረጋግጠው፣ሊያጠናውና አቅሙም ሊወስነው አይችልም።ምክንያቱንም እግዚአብሔር መንፈስ ነው፣ረቂቅ ነው ።ይህን መንፈሳዊና ረቂቅ እግዚአብሔር መመርመር ከፈለገ ሳይንሳዊው ዓለም መነፈሳዊና ረቂቅ መሳሪያ መጠቀም ይኖርብታል። ነገር ግን እስከ አሁን ዓለም የሚያምንበት መንፈሳዊ መመርመሪያ መሳሪያ የለውም።እግዚአብሔር የሚታወቀው በመንፈሳዊ መሳሪያ(ጾም፣ጠሎት፣እምነት ምግባር፣ፍቅር)እንጂ በቴሌስኮፕ ማይክሮስኮፕ ሊሆን አይችልም።ስለዚህ ሳይንሳዊ ምርምር እግዚአብሔርን ለማወቅ የሚያገለግለን  መነገድ አይደለም።ነገር ግን "እግዚአብሔር የለም" ብሎ ለመናገር ብዙወች ሳይንሳዊ ምርምርን እንደ ምክንያት ይጠቅሳሉ።መንፈሳዊውን የእግዚአብሔርን አኗኗር ሳይንስ አያጠናም ብለናል።ምክንያቱም የሚጠቀምባቸው መሳሪያወች ለዚህ የሚሆኑ አይደሉም፣የሚያተኩሩበት መስክ(field of study)ውም አይደለምና። በራሱ በሳይንስ ህግ አንድን እውነታ የጥናት ትኩረቱ ሆኖ የማያጠናው ከሆነ ትክክል መሆኑን(proving)ሆነ ትክክል ለመሆኑን ማረጋገጥ(disproving) ሳይንሳዊ አካሄድ አይደለም።ማንኛውም ሳይንሳዊ መለኪያ የእግዚአብሔርን አኗኗር መለካት ባለምቻሉ ብቻ የእግዚአብሔርን መኖር disprove አደርጋለሁ ማለት ከራሱ ከሳይንስ ህግ መውጣት ነው። ከእግዚአብሔርም ጋር መጣላት ነው።እንኳን አለመኖሩን በሳይንሳዊ ምርምር የእግዚአብሔርን መኖር ራሱ ማረጋገጥ ቢቻል ኖሮ ሃይማኖት ዋጋ ባልነበራት ነበር።እግዚአብሔርን ማወቅ እርሱ ራሱ ባዘጋጀው የማወቂያ መንገድ እንጂ በስጋዊ ምርምር አይደለምና።ይህችም እግዚአብሔር እግዚአብሔርነቱን እንድናውቅ ያዘጋጀልን መንገድ  ሃይማኖት ናት።

ሆኖም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የምንቀስማቸው እውቀቶች፣የምናደርጋቸው ምርምሮች፣የምናሳያቸው በጎ ለውጦች ፍጥረትን በተሻለ መንገድ ለመረዳት የሚጠቅሙን በመሆናቸው በራሳቸው እንደ ችግር የሚታዩ አይደሉም።እውቀቶቹንና ለውጦቹን የምንመለከትበት ዓይን ግን መንፈሳዊ ካልሆነ ወደ መጥፎ መንገድ ሊወስደን ይችላል።በተለይ ባሁኑ ዘመን ያሉት ምርምሮች እንደሚይሳዩት እስካሁን የነበረው ያለ ፈጣሪ ይህ ዓለም ተገኘ የሚለው አስተሳሰብ ተዓማኒነቱ በተመራማሪዎቹም ዘንድ እየተሸረሸረ "እግዚአብሔር አለ።" ወደሚል እምነት በመምጣት መንገድ ላይ ባሉበት ጊዜ እኛ የድሮውን የእነሱን አስተሳሰብ ይዘን ከአሚነ ስላሴ ብንወጣ ያስገርማል።ስለዚህ አንተ መንፈሳዊ ወጣት ሆይ ጉዞህን ከሚረዳህ ከእግዚአብሔር፣ ከምታንጽህ ከሃይማኖትህ ጋር አድርግ። ሐዋርያው ቅዱስ ዻውሎስ ለመንፈስ ልጁ ለጢሞቲዎስ እንዲህ ብሎ የጻፈለትን እናስተውል።"ልጄ ሆይ አንተም በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ በርታ።በብዙ ምስክሮች ፊት ከእኔ የሰማኸውን ትምህርት ለሌሎች ሊያስተምሩ ለሚችሉ ለታመኑ ሰዎች እርሱን አስተምራቸው።ኢየሱስ ክርስቶስን እንደሚያገለግል በጎ አርበኛ ሆነህ መከራ ተቀበል።ወደ ሰልፍ የሚሄድ አለቃውን ደስ ያሰኝ ዘንድ እንጅ የዚህን ዓለም ኑሮ አያስብምና።የሚታገልም ቢሆን እንደ ህጉ ካልታገለ አክሊልን አያገኝም።የሚደክም አራሽም አስቀድሞ ፍሬውን ሊያገኝ ግድ ነው ያልሁህን አስተውል።እግዚአብሔርም በሁሉ ነገር ጥበብን ይስጥህ። (2ኛጢሞ 2፡1-7) አሜን። 

ምንጭ፦ጉባኤ ቃና ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ


No comments:

Post a Comment