Thursday, June 09, 2016

ጥበብ ያልተቀላቀለበት ትምህርት!

መምህሩ የመግቢያ ሰዓቱን ጠብቆ ከበር ብቅ ሲል የተማሪው መንፈስ ይዋከባል። ሁሉም ባለው ቶሎ የመጻፍ ችሎታ መምህሩ የተናገሩን ሀሳብ ለመያዝ አስቀድሞ ደብተሩን ወይም ወረቀቱን ገልጦ ብዕሩን ደቅኖ ይጠብቃል። መምህሩ ንባቤ ቃላቸውን ሲጀምሩ ቀና ብሎ ለመመልከት ፋታ ያለው ተማሪ አይገኝም። ጠቃሚውን መርጦ መጻፍ ያልተለመደ ነገር ነው። ሁሉንም ለቅልቆ መገኘት ለጥናት ባይጠቅምም ሙሉውን ጽፌዋለሁ በሚል መተማመን ሊመጣ የሚችለውን መደናገጥ ይቀንሳል። ግማሽ ሰዓት ሳይተኙ ተኝቸ ጊዜየን አባከንኩት በሚል ስሜት ባንኖ መነሳት፣የወረቀት ኮሽታ በተሰማ ቁጥር አጥንተው ነጥቡን ሰቀሉብኝ በሚል ሰቀቀን ተነስቶ ከወርቀት ጋር መፋጠጥ፣ከምግብ ጠረዼዛ ወደ መታጠቢያው  የሚወሰደውን የምግብ ሰሀን ይዞ ወደ ውጭ መውጣት፣በመንገድ ላይ እያሉ ድንገት ደብተርን መግለጥ ቋሚ ክስተቶች ናቸው።

የውጥርቱንና የነገሩ ትኩሳት የሚጨምሩት ደግሞ ስራቸውን በወቅቱ ማጠናቀቅ ያልቻሉ ወይም በማጣደፋቸው ተማሪን የበደሉ የማይመስላቸው ወይም ከሃላፊነት ይልቅ የግል ጥቅም አድልቶባቸው ጠፍተው የከረሙ መምህራን ናቸው።"ተጨማሪ ክፍለጊዜ ያስፈልገናል" በማለት በተማሪ መዋከብ የራሳቸውን ክብር የጨመሩ የሚመስላቸውም ጥቂት አይደሉም። ታዲያ ሴሚስተሩ ሲያልቅ እንደጠጠሩ ሳይብራሩ የሚያልፉትን ሃሳቦች ጠያቂ የላቸውም።የሚጠይቅም ካለ እንደ ጊዜ አባካኝ ይቆጠራል። ይህ አይነቱ ንዴት ተጨማምሮበት "ለምን ብዙ ክፍለጊዜ አቃጠሉብን?" በማለት ለመጠየቅ ደግሞ መምህሩ ለሚወስድበት እርምጃ የሚከራከርበት መንገድ የለውምና ይሰጋል። በተማሪዎችም ዘንድ በማያውቀው ውይይት ገብቶ እንደዘባረቀ ተናጋሪ ወይም  መምህሩን ተዳፋሪ ተቆጥሮ ይሳቅበታል።በአንፃሩ እንደ አዋቂ የሚቆጠረው መምህሩ ፈተና የሚያወጣበትን አካባቢና የፈተናውን አይነት አጠያይቆ ማወቅ የቻለ፣የሚቻለውን ሞክሮ ፈተናውን ከሚራባበትና በምስጢር ከሚቀመጥበት አስወጥቶ ማየት የቻለ ነው።


አልፎ አልፎ የሚከሰተው ደግሞ 'ነቃ አልን' የሚሉ ተማሪዎች ከግራ ከቀኝ ተዋውቀው አስተዋውቀው ተማሪ የሚያባልግ መምህር ከተገኘ ለዚያ ሁኔታዎችን በማቀናበር ጠቃሚ ነጥብ በችሮታ ማግኘት ነው። አይብዛ እንጅ "ሞዴል ፈተና ከዕከሌ ሱቅ ኮፒ ለማድረግ ወስጀው አለ" በማለት በእጅ አዙር ገንዘብ የሚቃርም መምህርም አለ። የፈተና ወቅት ሲቃረብ መቻኮል መዋከቡ እየጨመረ ይመጣል። እሁድና ቅዳሜ ከስራ ቀናት አይለዩም። በተለያየ ምክንያት ትምህርታቸው የተጓተተባቸው መምህራኖች በእረፍት ቀናቶች ተደራቢ ክፍለ ጊዜ በመፍጠር  አድበስብሰው ያጠናቅቁታል። ሌላ አማራጭ የለም። ተማሪው እንደ ስንቅ እየተመናመነች የምትሄደውን ጊዜ  ለዚህ ሁሉ ማቻቻል የግድ ይሆናል። 'ለምን ይሄ ሆነ?' ለሚለው ጥያቄ መልሱ 'ይህ የዩኒቨርሲቲው ያኗኗር ደንብ ነው' የሚል ስለሆነ የቻለውን ያህል ታግሎ ለማደር መሟሟት ነው። በጊዜ እጥረትና ውጥረት ወፍራሙ ሲከሳ ቀጭኑ የበለጠ ሲገረጣ በግልፅ ይነበባል።

ለእንቅልፍ ትንሽ ጊዜ በመስጠት ሌሊቱን በሙሉ ቁጭ ብሎ ማደር፣ ልብስን ሳያወልቁ መተኛት፣ የተለመደ ክስተት ነው። በየኮሪዶሩ ከሚገኙ ወንበሮች በተጨማሪ  በየግቢው የሚገኙ የመዝናኛ ፓርኮች፣ዛፎች፣ድንጋዮችና ሜዳዎች በዚህ ወቅት አብረው የሚዘጋጁ ይመስላሉ።ሦስት ወይም አራት እየሆኑ በየቦታው አፋቸውን እየገጠሙ ደብተራቸውን ከጭናቸው አንጥፈው ይውሉበታል።አንዱ ግሩፕ ቢነሳ እንኳን ሌላው በርቀት የሚጠባበቀው ሮጦ ቦታወቹን ይይዛቸዋል።ቤተመጽሐፍት ሲከፈቱ ጀምሮ እስኪዘጉ ጢም ብለው ውለው ያመሻሉ። ያደረው የታመቀ አየር ሳይተነፍስ በበነጋታውም ሰው ጢም ይልበታል።የትንፋሽ ሙቀት ከውጪ ለሚገባ ፊት ይገርፋል።ጉዳዩ የሚመለከተው ግለሰብ "ሞልቷል" በማለት መግባት ከከለከለ እንደ ሥነ ስርዓት አስከባሪ ሳይሆን እንደ አድሎኛ ወይም ምቀኛ ይቆጠራል።"የህይወት ጉዳይ ነው ጌታዬ" በማለት ገፍተው የሚገቡም አሉ።ሁሉም ወንበር ተይዞ ከተገኘ ሌላ ክፍተት እስክትገኝ ድረስ ዙሪያውን ማንዣበብ የተለመደ ነው።

ድንገት ከበር ወጣ ያለ ወይም መጽሐፍ ለመፈለግ የተነሳ ከተገኘ ወንበሩ በሚያንዣብቡት ይነጠቃል።የእኔ ነበር የሚል ጥያቄ አያዋጣም።የተነሳው ግለሰብ ሲመለስ አይጨቃጨቅም፤ቤተመጽሐፍ መሆኑን አስቦ ጓዙን ጠቅልሎ ይሰደዳል።አንዳንዱ "ምን አይነት ተኩላ ነህ" የሰው ተኩላ!" በማለት ሌላ ማጥኒያ ማሰስ ይጀምራል።ሳይሳካለት ከዋለም ለፈተና የቀረውን ቀን በሕሊናው አስልቶ ይጨነቃል።ያጠናውም ቢሆን ከመቻኮል አይወጣም።ጓደኛን አስታውሶ መገናኘት ባይቀር እንኳን ይቀንሳል።ወይም አጭር የቃል ልውውጥ አድርጎ መሮጥ ነው።ነፍሳቸውም አብራ የምትዋከብ ትመስላለች።ለፈተና ሲቀመጡ ካለው ጭንቀት ብዙም የተለየ አይመስልም።አንዱ ትልቅ መጽሐፍ ተሸክሞ ሲሄድ ወይም ሲያነብ ከታየ ሌላው "አቤት! ሊሰቅለን ነው፣ደብተሩን ጨርሶ እኮ ወደ መጽሐፍ ገብቷል ፤አንቦታል ማለት ነው፤እኔ ገና ደብተሬንም አልጨረስኩም ።"ሲል በራሱ ላይ ተጨማሪ ውጥረትን ይጋብዛል።


በጥናት ጊዜ አንዱ ይነሳና "እነ እከሌ እኮ በፀሐፊዎች አማካኝነት ፈተና እንደወጣላቸው ይወራል። ታዲያ እኛ ምን ዋጋ አለን? አለቀልን በቃ!" ይልና ተስፋው ይመነምናል።"እከሊት ትላንት ከእከሌ ቢሮ ስትገባ ታየች" አሉ ሲባል "ታዲያ እኛ በዚህ ዓለም ምን መኖሪያ ደሴት አለን?" በማለት ሌላው ተስፋውን ያደክማል።ያደረገው ዝግጅት ያናድደዋል። በመሳሰሉት ወሬዎችና ሆን ብለው ለማስጨነቅ ወይም ለማዘናጋት በሚፈጠሩ ወሬዎች የተማሪው መንፈስ እንደወሬው ቅኝት እየተናጠ አቅሉን የበለጠ ያናጋዋል።ከዚያም የፈተናው ቀን ይቀርብና መርሃ ግብሩና የመፈተኛ ክፍሎች  በማስታወቂያ ይገለጣሉ። ጭንቀቱ ጣሪያ ላይ ይደርሳል።ውጥረቱ ይከርራል።ጭንቀት በኪሎ የሚለካ ቢሆን ኖሮ አብዛኛው ተማሪ ከራሱ ክብደት የላቀ የጭንቀት ሚዛን በነበረው።ከዚህ በላይ የሚበቃውን ያክል ተዘጋጅቶ ምንም ያልሰራ የሚምስለውም አለ።ለዚያውም ቤተ መጽሐፍ ሲቆይ ቸካይ፣የክፍሉ ቆሌ፣አይናማው ችግኝ፣ቀዳዳው ሃውልት፣አትንኩኝ፣ ሞት እምቢ ካለዚያም ጨምጫሚ እየተባለ ተቀጥላ ስም ይሰጠዋል።

ሁሉም የራሱን አቅም የሚያየው በሌላው መነፅር ነው።ከራሱ ባሻገር የሌላውንም እንቅስቃሴም በአንክሮ ይከታተላል።ሲሮጡ ካየ ሮጠው የሚጨርሱ ፤ቀስ ሲሉ ጨርሰው የተዝናኑ የሚመስለው ብዙ ነው።"እኔ ቶሎቶሎ ስለማልጽፍ እናንተ የተለየ የጻፋችሁት ይኖራል" በማለት የሌላ ደብተር ተውሶ የሚያስተያይም አይጠፋም ።አይብዛ እንጅ የጓደኛውን ደብተር ተውሶ "ጠፋብኝ" የሚልም አለ።የራሱን ዝግጅት ባለማመን ከፈተና በፊት ሰበብ አስባብ ፈጥሮ ትምህርት እንዲያቋርጥ ፈቃድ የሚጠይቀውም ቁጥር የዋዛ አይደለም።ወይም ራሱን ከሌላ ጋር ማወዳደር ባለምቻሉ ራሱ በሚፈጥረው ግምት ተሸንፎ "ከአሁን በኋላ ሰርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ አይነት ነው።" በማለት ለፈተና ቁጥር ቀናት ሲቀሩት ራሱን ከጥናት ለማላቀቅ ወድዶ የሚሸነፍም አይጠፋም።የህመም ሰበብ ፈልጎ የህክምና ፈቃድ ለማግኘት ወደ ክሊኒክ የሚሮጠውም ቀላል አይደለም።አልፎ አልፎም ብዙ ሳይለፉና ሳይጨነቁ የፈተና ጊዜ ብቻ ተከስተው ከማንም ያላነሰ ውጤት የሚያገኙ ተማሪዎችም አሉ።

እንዲህ እንዲህ እያለ ፍትፍትና ምርቅ በአንድ ላይ እኩል ክፍያ እየተከፈላቸው፤ምርቁ ሳይለቀም ፍትፍቱ ሳይመሰገን በጋርዮሽ በዋዛ ይኖራሉ መምህራን የተጻፈውን ብቻ ያስተምራሉ። 'ጥበብ ያልተቀላቀለበት ትምህርት!'። በእውነት ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለመጭው ዜጋችንም ማሰብ ይገባናል።ስህተትን የሚዳፈሩት የተማሩት ዜጎች ከሆኑ ህብረተሰባችን ትምህርትን እንዴት የጥሩ ነገር መገለጫ አድርጎ ሊወስደው ይችላል? አባቶች "ላዩ ከደፈረሰ ታቹ ሊጠራ አይችላም።" ይላሉ።ትምህርት ካናት ላይ ከደፈረሰ የት ላይ ይጠራል? አስተማሪዎች በሰው ህልውና ላይ ከመፍረዳቸው በላይ የተማሪ አስተማሪ ግንኙነት እንደዚህ መሆኑ የሚገርም ነው። ሙያውን የሚያፈቅር የሙያ ሥነምግባር መንፈስ በህዝባችን ህሊና መጥፋቱ ትልቁ ኪሳራ ነው።ለኢትዮዽያ ሕዝብ ከራሱ ዜጋ የበለጠ የሚበቀለው ሰው የለም። ካልሆነ ከዚህ ሁሉ ጣጣ ዩኒቨርሲቲ "የመምህራን ሕግ የለሽ የግዞት ክልል" ተብሎ ቢሰየም ይሻለዋል።የሰላ ሕግ እያለ ተርጓሚው ግን ጠማማ ነው። ግቢ ያለው ህብረተሰብ ህግን የሚረዳ ሕሊና ያለው ነው። ግን እነሱ ወተትን ሲያጠቁሩ ማርን ሲያመርሩ ጠያቂ የላቸውም። የተማረውም ያልተማረውም ከኋላ ከኋላ እየተከተለ የሚነዳ ጠባቂ ይፈልጋል።በግዳጅ ይህንን ስራ ካልተባለ በስተቀር ለራሱ ሕሊና ብሎ የሚሰራ ዜጋ የለም።

ሰው ህሊናውን ያኮሰሰባት ሕግ ተቀብሮ ተግባር ተጣሞ ለቅሶ ነግሶ የሚኖርባት ዓለም።

ምንጭ፦ ገዐረ
በጥዑም መዓዛ

1 comment: