Monday, June 27, 2016

ታማችኋል !!!

በአፍላ ትጀምራላችሁ በወረት ትተውታላችሁ። ያወቃችሁትን ትረሳላችሁ ያላወቃችሁትን ለማወቅ ትጥራላችሁ፤የያዛችሁትን ትረግጣላችሁ፤የረገጣችሁትን ትይዛላችሁ፤ምኞታችሁ ልክ የለውም፤አምሮታችሁ ብዙ ነው።የአማራችሁን ስታገኝ ወዲያው ይሰለቻችኋል።ተው የተባላችሁትን ትሽራላችሁ የተከለከላችሁትን ትደፍራላችሁ፤የተፈቀደላችሁን ችላ ትላላችሁ።ቤተመቅደስ እንዳትገቡ ብትከለከሉ ወደ ፊት ቤተመቅደሱን በመስታውት ሰራታችሁ ቤተመቅደስ ባትገቡም እንኳን ሁሉን ከወጭ ሆናችሁ ማየት ትፈልጋላችሁ።ሁሉንም ማወቅ ትፈልጋላችሁ በአንዱም ግን አትጠቀሙበትም።ሁሉም አላችሁ ግን ባዷችሁን ናችሁ።ሃይማኖት እንጅ እምነት የላችሁም።

መድሃኒት ባሳይህ መቀመሚያውን ነገሬህ ማርከሻውን ሳልገልጥልህ መጀመሪያውን ብቻ ሞጭልፈህ ትተኸኝ ትሄዳለህ።ጥበበን "ሀ ግእዝ "ብየ ላስተምርህ ብሞክር  መንደር ውስጥ በቃረምካት እውቀትህ ተመክተህ በመሰላቸት "ሆ ሳብዕ" ብለህ ቀድመህ ትዘጋዋለህ። የግል ታሪካችሁ ቢታይ ወጥነት የጎደለው ከዚህም ከዚያም የተልከፈከፈ የተማሪ ኮፈዳ ውስጥ ያለ እህል ይመስላል።ተምራችሁ እውቀት ስታገኙ ሰርታችሁ ገንዘብ ስታፈሩ ከላይ የሆናችሁበትን ሃገር ለቃችሁ "ሰፋ ወዳለው እንሂድ" ብላችሁ እንደገና ከታች ትጀምራላችሁ።ትቀጥላላችሁ በመጨረሻ ከጀመራችሁበት ትገኛላችሁ ።ቸኩላችሁ ትወስናላችሁ ወዲያው ትጸጸታላችሁ።በጽኑ ታማችኋል።

ከታሪክ ፍቅርና ልማትን ሳይሆን ጥላቻንና ጥፋትን ለይታችሁ ትቆፍራላችሁ።ከዚያም ቀጥላችሁ የከበረ ማዕድን እንዳወጣችሁ ሁሉ በኩራት ደረታችሁን ነፍታችሁ ሳታማርጡ ሁሉን በአደባባይ ትዘሩታላችሁ፤እናም ወደ ኋላ ስለታሪካችሁና ቅርሳችሁ ባሰባችሁ ቁጥር ፍርሃትና ሃፍረት ይሰማችኋል።ስለሆነም ከኋላ ታሪካችሁና ክብራችሁ እየራቃችሁ መጣችሁ።የአሸናፊነትንና የተሸናፊነትን ትርጉም የያዙ ሃውሎቱችን በአንድ ላይ ታቆማላችሁ። ለግልፅነትና ለነጻነት እያላችሁ በምታደርጉት ሽኩቻ እርቃን ወደ መሆን ወረዳችሁ።

ቅቤ ላይወጣችሁ ትናጣላችሁ።በዚህ ዓለም ጥድፊያ ታማችኋል።ሃገርችሁን ትንቃላችሁ ጥላችሁ ለመሄድ ትፈልጋላችሁ ከሄዳችሁ በኋላ ደግሞ አፍታ ሳትቆዩ ሃገሬ ናፈቀኝ ትላላችሁ።በቁማችሁ የናቃችሁትን የአገራችሁን አፈር  በሞታችሁ ልትለብሱት ትናፍቃላችሁ።ለሀገሬ አፈር አብቃኝ ብላችሁ በድናችሁን ልካችሁ የወገኖቻችሁን ልብ ትሰብራላችሁ። ግብዝነታችሁ መጠን የለውም።ሁለት ሃገር እንዲኖራችሁ ትፈልጋላችሁ። አንዱን በደም ሌላውን በመታወቂያ ታስባላችሁ። ከአንዱም ግን በአግባቡ አትኖሩም። ዘመናችሁም በምልልስና በመዋተት ያልቃል። ምን እንደምትፈልጉ አታውቁም እናም ፍለጋችሁ አያልቅም።

በዚህ የተነሳ ምስጢር ለመካፈል ቅርስ ለመረከብ የሚያስችል ስብዕና አልገነነባችሁም። እኛ የመገናኛውን ድልድይ ስላልሰራነውና ከናንተ ስለራቅን ሳይሆን ስለማታዩት ወይም ማየት ስለማትፈልጉ አለበልዚያም እንደ ልብ-ወለድ ገፀ-ባህርይ የራሳችሁን ያሸበረቀ አስረካቢ ፈጥራችሁ እውኑን ሳይሆን ምናባችሁን መረከብ ፈልጋችሁ ስለምታጡት ነው። እኛ ደግሞ እናንተ ታዩን ዘንድ አላሸበረቅንም ማሸብረቅም አንፈልግም። በዚህ ምክንያት ለእናንተ ምስጢር ለመነገር ቅርስ ለማውረስ  እጅግ ከባድ ሆኗል። እኛ አባቶቻችን እናምናለን። በእነርሱም ደስ ይለናል። የነገሩንን ተቀብለን ቃልኪዳናቸውን ጠብቀን እንንኖራለን። ጽላተ ሙሴ አክሱም ጽዮን እንዳለች ሲነግሩን "መጋረጃ  ገልጠን ሳጥን ከፍተን እንይ" አላልንም። "ጌታ የተሰቀለበት የግማደ መስቀሉ ክፋይ ግሼን ማርያም አለ" ሲሉን "ቆፍረን አውጥተን እንመልከት" አላልንም። "ቅዱሱ ጽዋ መንዝ ውስጥ አለ" ሲሉን ዋሻ እናስስ አላልንም።

አባቶቻችንን አምነን፤ ሃገራችን የበረከት ምድር መሆኗን ተረድተን፤ የጌታችን የጸጋ ስጦታ ተቀብለን፤ በእምነት እንኖራለን። ምንም የለንም ሁሉም ግን የኛ ነው ፤ድሆች ብንመስልም ባለጸጎች ነን። የተራቆትን ብንመስልም የፀጋ ልብስ አለን። ሐዘንተኞች ብንመስልም ደስተኞች ነን። ስለሃገራችን መባረክ፣ቅድስት ሃገር መሆን፤ ቅዱስ ቅርስ በእጃችን እንዳለ፤ ዓለም እንዲያረጋግጥልን አንፈለግም። "የሌለንን አለን ያልተሰጠንን ተቀበልን" ብለን የምንኮፈስ  ግብዞች አይደለንምና ። የሌለንን ነገር ለመጠበቅና ለመታመን ስንል ሥጋችንን እየጎሰምን በገዳም ለመኖር የምንወስን ጅሎችም አይደለንምና።

ምንጭ፦ እመጓ
በዓለማየሁ ዋሴ እሸቴ

No comments:

Post a Comment