Tuesday, July 05, 2016

የተቆለፈበት ቁልፍ!


ጫት፦ በእርግጥም ካለመስራት እኩል በትክክል አለመዝናናትና አለማረፍም የሰውን ጭንቅላት ምን ያክል እንደሚጎዳ  ብዙ ሰው ልብ የሚል አይመስልም።በመቃም ወይም ዘወትር በመጠጣት ለመዝናናት መሞከር ለአእምሮ ጤናን ሳይሆን ጫናን የሚፈጥር ሱስ እንደሚሆን ግልጽ ነው።ለምሳሌ ጫት  የሰውን አእምሮ አሰራር ሊያውኩና ሱስንም ሊፈጥሩ የሚችሉ ኬሚካሎች የያዘ ቅጠል ነው ።ካቲኖንና ካቲኖል የሚባሉ ንጥረ ነገሮችን  የሰውን ስሜትና መነሳሳት ከፍ በማድረግ ምርቃናን በመፍጠር በሱስ ከጠመዱ በኋላ ቃሚውን ካላገኘ መንቀሳቀስ የማይችል ትጥገኛ ማሽን ያደርገዋል።በሃራራና ምርቃና መካከልም እየዋዠቀ ቆይቶ በመጨረሻ ፍጻሜው ውድ የሆነ አዕምሮው ከጥቅም ውጭ ወደመሆን  ሲመጣ የጀዝባነትን ጎራ ይቀላልቀላል።ከዚህ በተጨማሪ በጫት የተፈጠረውን ምርቃና ለማገዝ ማጨስ የተልለመደ ሲሆን ያንን የናረ ስሜት ላምርገብ ደግሞ መጠጥ የግድ ይላል።ሌሎች መጠጥ የማያዘወትሩ ሰዎች ደግሞ የእንቅልፍ ክኒን አይነት መድሃኒቶች ሱስ ሳያስቡት ከጫቱ ጋር በተጣማጅ ይጠናወታቸዋል።ይሄ እንግዲህ በጥርስ፣ በጨጓራና በኪስ የሚፈጥረው በሽታ ሳይቆጠር መሆኑ ነው።

ሰዎች በሚቅሙበት ጊዜም የጊዜ ባቡር አፈጣጥኑ ስለሚቀየር በብዛት የሚቅሙ ሰዎች በዕድሚያቸው ላይ ቁሟር መጫወታቸው አይቀርም።እንኳን በጫት ታግዞ እንዲሁም ባህላችን የጊዜ ጸር ነው።በአንድ ወቅት በጥቂት የሃገሪቱ ክፍሎች ብቻ  ከሃይማኖታዊና ባህላዊ ወግ ጋር  ተመጥኖ ላገልግሎት ይውል የነበረው ጫት ዛሬ ከጥቂት የሃገሪቱ ክፍሎች በቀር ከዳር እስከዳር አካሎ ማየቱ አሳዛኝም አስፈሪም ነው።ከናዝሬት እስከ አዲስ አበባ ባለውም አስፋልት ዙሪያ ዘመናዊ ቃሚዎች መኪናቸውን ደርድረው እየቦዘኑ ሲዝናኑ ማየት ችግሩን ገና ፋሽን እንጂ ፍርሃርት እንዳልፈጠረ ያሳያል።ከባለስልጣን እስከ ነጋዴ ፣ ከምሁር እስከ ስራ አጥ፣ወንድና ሴት ሳይል በጫት አባዜ ተይዘው አለመቃም የሚያሳፍረበትና እንደሞኝ የሚያስቆጥርበት ጊዜ ላይ መድረሳችን ነበር ማሳፈር ያለበት።ቡናን የሚቀናቀን የውጭ ምንዛሬ አምጭ ተክል መሆኑ ከኮሎምቢያ ኮኬይንና ከ አፍጋኒስታን ሄሮይን የኛንስ ጫት ሕጋዊ ከመሆኑ በቀር ምን ይለየዋል?

ቴክኖሎጂው ቢኖረን ኖሮ ጫትም ወግ ደርሶት በክንድ የሚወጋና ባፍንጫ የሚሳብ የተጣራ ካቲኖን ሳይሆን አይቀርም ነበር።በምግብ ራሱን ያልቻለ ህዝብ ፀረ አዕምሮ የሆነ ተክል በየአገሩ እንደ ቁም ነገር ሲልክ አዕምሮ ቢስነት እንጅ እድገት ሊሆን አይችልም።በየከተማው እንደ አሸን የፈሉት ጫት ቤቶች የትውልዱን አዕምሮ ለመግደል እንደተቋቋሙ መርዝ ቤቶች እንጅ የአገርንም ሆነ የሰውን ህይወት በምንም መንገድ ሊረዱ እንደሚችሉ  ቢዝነሶች ሊታዩ አይገባም።ጫት መቃም ከአዕምሮ ህመም ጋር በከፍተኛ ደረጃ መያያዙም በሰው አንጎል ውስጥ ገብቶ ከሚፈጥረው  የኬሚካል መዛባት ጋር በቀጥታ የተያያዘ ነው።የተወሰኑ ሰዎች እየቃሙ የአዕምሮ በሽተኛ አልሆኑም ማለት በሚያንዳልጥ መሬት ላይ ትላንት የሄዱ ሰዎች ወድቀው ስላልተሰበሩ ዛሬ ሰውን ሁሉ አሰልፎ በጭቃው ላይ እንደማስሮጥ ነው።

እንደ እኛ አገር ባለ አንድም ከሱስ የማገገሚያ ሆስፒታልና ማዕከል በሌለበትና የህክምና ዋጋው ለሰለጠኑትም አገሮች ወገብ ሰባሪ ሆኖ እያለ እንደ ጫትና ሃሽሽ አይነት አደገኛ እፆች እድሚያቸው ባልደረሱ አዳጊ ሕጻናት ሳይቀር እንደ እንጀራ ሲበላ ማየቱ መንግስትን ብቻ ሳይሆን የትውልድ ሃላፊነት አለብኝ የሚል ሰውን ሁሉ ተጠያቂ ያደርጋል።እንኳን እነዚህ አደገኛ ዕፆች አልክሆልም ቢሆን  ዕድሚያቸው ለጋ በሆነና አዕምሮአቸው በማደግ ላይ  ባሉ ወጣቶች እንዳይወሰድ ሕጋዊና ማህበራዊ ከለላ ያስፈልጋል።ለዚህም በየሆቴሉ ጨቅላ ተማሪዎችን የሚያማልሉ የቀን ፓርቲዎችና የየሰፈሩ ጠላት ካቲካላ ቤትችም ትልቅ ግፍ በትውልዱ ላይ እየሰሩ መሆኑ ተገልጦ መነገር  አለበት።

ፊስቱላ፦ፊስቱላ ማለት ቃሉ ሁለት የተለያዩ የሰውነት ክፍሎችን ተፈጥሮአዊ ባልሆነ መንገድ የሚያገናኝ ቀዳዳ ወይም መንገድ ማለት ነው።በተለይ በተመጣጠነ ምግብ እጥረትና እድሚያቸው ለአቅመ ወሊድ ያልደረሱ በጣም ወጣት ሴቶች አርግዘው ለመውለድ ሲሞክሩ በማህጸን መተላለፊያ ያለው የልጁ ጭንቅላት የማህጸኑን ግድግዳ ከፊኛና ከሬክተም ጋር በአጥንቱ ላይ አጣብቆ ለረጅም ሰዓት ሊያቆየው ይችላል።የልጁ ክብደትና መጠን ትልቅ ከሆነ ወይም በወሊድ ጊዜ አቀማመጡ የተዛባ ከሆነ ደግሞ ችግሩ የባሰ ይሆናል።ችግሩ ያጋጠማቸው ሴቶች በቶሎ ወደ ሆስፒታል ሂደው ሕክምና ካላገኙና በዚህ ሁኔታ በምጥ ውስጥ ከቆዩ፤ከአጥንት ጋር ተጣብቆ የቆየው የማህጸናቸው ክፍልም ሆነ የፊኛቸውና የአንጀታቸው ክፍል በቂ ደም ስለማያገኝ በአካባቢው ያሉ ሴሎች ይሞታሉ።ይህም ከዚህ የተነሳ ከሚመጡ የወሊድ ቁስለቶች ጋር ተያይዞ በሚፈጠረው ኢንፌክሽን ታግዞ ፊስቱላ የምንለውን ቀዳዳ በፊኛና በማህጸን ወይም በሬክተምና በማህጸን መካከል ወይም ሁለቱንም ይፈጥራል።ቶሎ ህክምና ካላገኘም ሊሰፋ ይችላል።

ከዚህም የተነሳ ሽንታቸውንም ሆነ ሰገራቸውን መቆጣጠር ወደ ማይችሉበት ደረጃ  እንዲደርሱ ስለሚያደርጋቸው ሰገራና ሽንታቸው እየተቀላቀለ በማህጸናቸው ያለማቋረጥ እንዲፈስ ያደርጋል።ይህም ሊፈጥር የሚችለውን መሸማቀቅና ማህበራዊ መገለል ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም።ትዳራቸውን ያጣሉ፣ማንም ከነሱ ጋር መሆንም መኖርም አይፈልግም።እነርሱም ቆሻሻ እንደነካው እርኩስ ዕቃ ከቤተሰብም ከህብረተሰብም ተገልለው የአካል ብቻ ሳይሆን የመንፈስም የስሜትም የማህበራዊ ህይወትም ሰለባና  ስንኩል ይሆናሉ። ይሄ ነው እንግዲህ ፊስቱላ ማለት።ሌላው ደግሞ ያለ ዕድሜ በህጻናት ላይ በሚደረግ የውሲብ ጥቃት ፣ለካንሰር በሚደረግ የጨረርና የቀዶህክምናና በመሳሰሉት ምክንያቶች የሚመጣ ሲሆን ያ በጣም ጥቂት ፐርሰንቱ ነው።ችግሩ በሁሉም ቦታ የሚከሰት ሲሆን በብዛት የሚታየው ግን በገጠሩ የሃገራችን ክፍል ነው። የገጠር ሴት ልጆች ያለዕድሚያቸው አግብተው ስለሚያረግዙና ለህክምና እርዳታና ለማዋለድ አገልግሎት ሩቅ ስለሆኑ ችግሩ በዋናነት የሚታየው እዛ ነው።

ፊስቱላ በአንዲት ሴት ህይወት ላይ የሚፈጥረው አካላዊ፣ቤተሰባዊ፣ስነልቦናዊ፣፣መንስፈሳዊና ማህበራዊ ቀውስ ልክ የለውም ።ይኸውም መስመራቸውን ስተው በሚወጡ የሰውነት ፈሳሾችና እነሱንም መቆጣጠር ካለመቻሉ ጋር በተያያዘ የሚመጣ ጦስ ነው።እነዚህን አሳዛኝና ክቡራን ወጣቶች የፊስቱላ ችግር ገፈት ቀማሽ ያደረጋቸው ከበስተጀርባ ያለው ያስተሳስብ ፊስቱላ እስኪጠገን ችግሩ እንደሚቀጥል ጥርጥር የለውም።የአስተሳሰብ ፊቱላ የለም ይባል ይሆን በየቤቱና በየመስሪያቤቱ  በብዙ ሰዎች አስተሳሰብ ላይ ከፍተኛ ማህበረሰባዊ ቀውስ የፈጠረውን አዕምሮአዊ ፊስቱላ ማየት ቀላልላይሆን ይችላል።በአዕምሮአቸው ውስጥ ሥርዓትንና ውበትን ተላብሰው  እንዲሰሩ የተፈጠሩ ስሜት፣ ባህል፣እምነት ፣ፍላጎት፣ግንኙነት፣አመለካከትና የመሳሰሉት የአስተሳሰብ ክፍሎች በትክክል ሳይዳብሩ ተደበላልቀውና ሚዛን አጥተው፤በባለቤቱም በዙሪያው ባለው ሰውም ላይ የሚፈጥሩት ተጽዕኖ ቀላል አይደለም።

ምንጭ፦የተቆለፈበት ቁልፍ 
በምህረት ደበበ

No comments:

Post a Comment