Friday, July 08, 2016

ለጽጌረዳ (Y.F)

ሰላምና ጤና ደስታና ፍቅር ምን ጊዜም ቢሆን ካንቺ አይለዩ። የሰው ልጅ እስካሁን ድረስ  አንዱ ለሌላው ያለውን እውነተኛ ፍቅር ለመግለፅ ያልተጠቀመባቸው ቃላት ይኖራሉ ብየ አላስብም። ምርጥ፣ ወርቃማ፣ እንቁ የሆኑ ቃላትም ቢሆኑ ላንቺ ያለኝን ፍቅር በትክክልና ሙሉ በሙሉ የመግለፅ  አቅም የላቸውም። የፍቅር ታላቅነት ከምንምና ከማንም በላይ ነውና ፍቅር ከኃይሎች ሁሉ የሚበልጥ ኃያል ነውና። ፍቅር እውነት ነው፤እውነትም ፍቅር ነው፤ የሁለቱ ድምር ደግሞ አንቺው ነሽ። ላንቺ ያለኝን እውነተኛ ፍቅርና መልካም ምኞት መግለጫ አጥቼ ፈዝዤ ተቀምጬ መውደዴን ማፍቅሬን ለመግለፅ ወኔ ቢጠፋኝ ጉልበት ቢከዳኝ ፍቅርሽ ቢብስብኝ መንገድ ፈለጌ ማፍቀሬ እንዲገባሽ የተቻለኝን ሁሉ ለማድረግ ሞከርኩ። ነገር ግን ፍቅሬን ለመግለፅ የተጠቀምኩባቸው መንገዶች አላማቸውን መፈፀም ተሳናቸው። ፍቅሬን ከመግለፅ በተቃራኒው የጥላቻሽ አጋፋሪ ሆነው ተገኙ። 

የማወራሽ ተረት ተረት ወይም ልብ ወለድ አይደለም። ከአንጎለ ገቢር አፍልቄ፣ ላለፉት አራት ዓመታት በውስጤ ታምቆ ከኖረው የፍቅርሽ ወላፈን ጨምቄ፣ ከልቤ መዝገብ ፈልቅቄ፣ ያወጣሁት  ህያው እውነት ነው እንጅ። እኔ ላንቺ ያለኝን ፍቅር በምንና እንዴት አድርጌ ላስረዳሽ እንደምችል ባላውቅም ውሎየም አዳሬም  አንቺ ብቻ ስትሆኝብኝ ጭንቅ ጥብብ ሲለኝ ማደረገውን ሳጣ ይኸው ዛሬም ከዕድሜሽ ላይ ሁለት ወይም ሦስ ደቂቃ  ልወስድብሽ ጨከንኩ። መቼም ይህንን እንደማትነፍጊኝ ተስፋ አደርጋለሁ። እኔ እንኳን ከሃብት ሁሉ የምትበልጠውንና ማንም በገንዘብ ይገዛት ዘንድ የማይቻለውን ንጹህ ልቤን ሰጥቸሽ  አይደል? አንቺ ስጦታዬን ለመቀበል ፈቃደኛ ባትሆኝም ቅሉ። ሙሉ ማንነቴን ላንቺ ሰጥቼ ይኸው አራት ዓመት ሙሉ ተሰቃየሁልሽ እኮ። ለነገሩ ሰው የቤቱን ሀብት ሁሉ ስለፍቅር ቢሰጥ ያከብሩታል እንጅ በፍፁም አይንቁትም። ፍቅር ከሞት የበረታች ናትና፤ ቅንዐትም እንደ ሲኦል የጨከነች ናትና፤ ላንቃዋም እንደ እሣት ላንቃ እንደ ነበልባልም ነውና። 

በቃ ምን ልበልሽ የሊዮናርዶ ዳቪንቼ "ሞናሊዛ" በዓለም ህዝብ ዘንድ ምን ያክል ቦታ እንዳላት ታውቂ የለ? አዎ አንቺ ደግሞ ለእኔ ከዚያች ከሞናሊዛ በላይ በልቤ ውስጥ ትልቅ ቦታ ይዘሽ የተቀመጥሽ ልዩ ፍጥረት ነሽ። አንቺ እኮ ለእኔ እንደ ጽጌረዳ ውብ ነሽ እንደ አደይ አበባም ያማርሽ ነሽ። ነገር ግን አላማ ይዞ እንደ ተሰለፈ ሰራዊት ታሰፈሪኛለሽ። እነሆ አንቺ ለእኔ ውብ ነሽ፤ በዓይነ ርግብ መሸፈኛሽ ውስጥ ዓይኖችሽ እንደ ርግቦች ናቸው፤ ፀጉርሽ በገለዓድ ተራራ እንደሚወርድ እንደ ፍየል መንጋ ነው፤ጥርሶችሽ ታጥበው እንደ ተሸለቱ ሁሉም መንታ እንደ ወለዱ ከእነርሱም መካን እንደሌለባቸው መንጎች ናቸው፤ ከንፈሮችሽ እንደ ቀይ ሐር ፈትል ናቸው፤ ከዝምታሽ በቀር አፍሽም ያማረ ነው፤ በዓይነ ርግብ መሸፈኛሽ ውስጥ ጕንጭና ጕንጭሽ እንደ ተከፈለ ሮማን ናቸው፤አንገትሽ ለሰልፍ ዕቃ መስቀያ እንደ ተሠራው እንደ ዳዊት ግንብ ነው፤ ሺህ ጋሻ የኃያላንም መሣሪያ ሁሉ ተንጠልጥሎበታል። ሁለቱ ጡቶችሽ መንታ እንደ ተወለዱ፥ በሱፍ አበባ መካከል እንደሚሰማሩ እንደ ሚዳቋ ግልገሎች ናቸው። ከዚህ በላይ መግለፅ ብችል ምንኛ ደስ ባለኝ! ግን ቃላት ያጥሩኛል። 

ጽጌ አሁን የምጽፍልሽ አንቺን ለማናደድ ፈልጌ ወይም እንደማትወጅኝ ሳላውቅ ቀርቼ አይደለም። እኔ እንድጽፍልሽ እንደማትፈልጊም በደንብ አውቃለሁ። ብቻ ማደርገው ቢጠፋብኝ ጭንቀቴ ትንሽ ቀለል ቢልልኝ ብዬ ነው። እናማ የእኔ ውድ አንብበሽ ስትጨርሽ ልብሽ ከራራልኝና ፈቃድሽ ከሆነ ምላሽሽን በድምፅም ሆነ በጽሁፍ ብትገልጭልኝ ለመቀበል ዝግጁ ነኝ። ያም ባይሆን ግን ፍቅር ከሞት የበረታች ናትና፤ ብዙ ውኃም ፍቅርን ያጠፋት ዘንድ አይችልምና ፤ ፈሳሾችም አየሰጥሟትምና፤ፍቅር እንዲሁ ያለዋጋ መውደድ እንጅ ሰጥቶ መቀበል አይደለምና እስከ ዘላለሙ እ...ወ...ድ...ሻ...ለ...ሁ...!!! አፍቃሪሽ!


ይህ ጽሑፍ "The Role" በተሰኘው የጅማ ዩኒቨርሲቲ ዓመታዊ መጽሔት ላይ የወጣ ነው።

No comments:

Post a Comment