Tuesday, May 05, 2020

ዶ/ር በላቸው ደስታ


(Legendary Ethiopian Pharmacist)








በኢትዮጵያ የዘመናዊ የፋርማሲ አልግሎት ታሪክ ስማቸው ጎልቶ ይነሳል።የተወለዱት ዳንግላ ነው። ከአባታቸው ከአለቃ ደስታ ድንበሩ እና ከእናታቸው ከወ/ወሮ ህልሚቱ ኪዳኑ ነሐሴ 03፣ በ1935 ዓ.ም ተወለዱ። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን እዛው ዳንግላና ቻግኒ ተማሩ። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ከፍተኛ ውጤት በማምጣት ጄኔራል ዊንጌት ተቀላቀሉ።

በቀዳማዊ ኃ/ስላሴ ዩኒቨርሲቲ ለመጀመሪያ ጊዜ በሀገሪቱ ከተመረቁ ሶስት የፋርማሲ ባለሙያዎች አንዱ ናቸው። የማህበረሰብ ፋርማሲና የኢትዮጵያ መድሃኒት ፋብሪካ ሰርተዋል። ወደ ቫንኮቨር ካናዳ አቅንተው በብሪቲሽ ኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ የማስተርስና የፒኤችዲ ትምህርታቸውን አጠናቀዋል።

 የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፋርማሲ ት/ቤት ዲን ሆነው ለ9 ዓመት አካባቢ አገልግለዋል። በተቋሙ በቆዩበት ዘመን ተባባሪ ፕሮፌሰር በመሆን በርካታ ጥናቶችን አበርክተዋል። ለረጅም ዓመታት የዘለቀውን የ5 ዓመት የፋርማሲ ስርዓተ ትምህርት በመቅረፅ፣ ት/ቤቱን በአቅምና በትምህርት መሳሪያ በማደራጀት፣ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ፈንድ በማምጣት ትልቅ አስተዋፅኦ አድርገዋል።

 አንጋፋውን የኢትዮጵያ ፋርማሲ ማህበርን ከመሰረቱት ውስጥ አንዱ ናቸው። የማህበሩ የመጀመሪያው ፕሬዘዳንትም ናቸው። በጤና ጥበቃ ሚንስትር የፋርማሲ ዲፓርትመንትን በመመስረት፤ የአሁኑን የኢትዮጵያ የመድኃኒት አቅርቦት ኤጀንሲን (በቀድሞ ስሙ "EPHARMAECOR") በመመስረት ሂደት ውስጥ ትልቅ አስተዋጽኦ ነበራቸው። የሶስት ልጆች አባት የሆኑት ዶ/ር በላቸው ደስታ የጡረታ ዘመናቸውን በባህላዊ ህክምና ላይ ጥናት በማድረግና እራሳቸውን በመደገፍ ነበሩ። በዚህ ዘርፍ እየሰሩት የነበረ ጅምር ስራ እጃቸው ላይ እንደነበር ሰምቻለሁ። ታመው ግሩም ሆስፒታል መግባታቸውን የሰማሁትም ባለፈው ሳምንት ነበር። ህክምና ላይ እያሉ ሚያዚያ 25፣ 2012 ዓ.ም በ77 ዓመታቸው አርፈዋል። ዶ/ር በላቸው ለህዝብና ለሙያው ባደረጉት አስተዋጽኦ ሲታወሱ ይኖራሉ።
ፈጣሪ ነፍስዎን በአፀደ ገነት ያሳርፍ‼️

ዘላለም ጥላሁን አ.ፕ አ.አ ዩኒቨርሲቲ


No comments:

Post a Comment