Saturday, April 30, 2016

አደናጋሪው ጩኸት !

መላዋ እየሩሳሌም የጩኸት ድምጽ ይሰማባታል፤ከወትሮዋ በተለየ ሁኔታ ጩኸት በዝቶባታል። ከወዲያ ወዲህ እየተመላለሱ ህዝቡን የሚያሳምፁ ካህናቱና ሊቃነ ካህናቱም ወገባቸውን ታጥቀው ይመላለሱባታል። የከተማዋን ሽብር የተመለከቱ ሁሉ  ገበያ ቀን ነበርና ግራ ተጋቡ በሚሰሙት ጩኸት ተደናገሩ፣የጩኸቱን ምክንያት ተረድቶ ማስርዳት የሚችል ግን አንድም ሰው የለም ብቻ ሁሉም ይጮሃል። በመንገድ አልፈው የሚሄዱትም "ቤተመቅደስን አፍርሰህ በሦስት ቀን የምተሰራው"  እያሉ ይጮሁ ነበር። ከቤተ መንግስትም ሆነ ከቤተ ክህነቱ ባለስጥናት  ጩኸቱን ለማስቆም  የደፈረ ማንም የለም። ሦስት ዓመት ከሦስት ወር በተደረገው ተዓምራት በሕሙማን አድረው ይጮሁ የነበሩ አጋንንት ዛሬ ደግሞ በአይሁድ ልቡና አድረው ይጮሃሉ። ጩኸቱ ግን ይለያያል። ያን ጊዜ" ልታሳድደን መጣህን? "የሚል ሲሆን ዛሬ ግን "ስቀለው! ስቀለው!" የሚል ሆኗል። ነገሩ እየጠነከረ መጥቶ ጩኸቱ ምክንያት የሆነው ንጉሠ አይሁድ ኢየሱስ ክርስቶስ ታስሮ ወደ ሊቀ ካህናቱ ግቢ ደርሰ። 


ሊቀ ካህናቱ ሀና ሥልጣን ዘመኑን ጨርሶ ለቀያፋ ያረከበ ቢሆንም ስለምግልናው በጀመሪያ በተከሳሹ ላይ ፍርድ እንዲሰጥ የተጠየቀው እርሱ ነበር። ነገር ግን እርሱም ቢሆን ጩኸቱ ለማስቆም አቅም አልነበረውም። ሲጀመርም ጩኸቱን መርቆ የከፈተው ማን ሆነና? የእርሱ የልጅ ባል ቀያፋ አይደለምን? "ስለ ህዝቡ ሁሉ አንድ ሰው ቢሞት ይሻላል" ብሎ። በዚህ በሊቃነ ካህናቱ የተጀምረው ጩኸ ወደ ሕዝቡ ወረደ በሊቀ ካህናቱ ግቢ የፍርድ ሂደቱ እየተካሄደ ባለበት ወቅት  ሌላ አዲስ ጩኸት ተከሰተ ፤የሰባኪው ዶሮ ጩኸት ተከሶ የመው  የክርስቶስ ፍርድ ሳይጠናቀቅ ደቀመዝሙሩ ዼጥሮስም ተከሶ ቆመ። በሕሊና ዳኝነት ወንጀለኛ መሆኑ ስለተረጋገጠ ምስክር እንኳን ሳያስፈልገው እራሱ በሰጠው የእምነት ቃል ማስረጃነት ዳኛው አስቸኳይ ውሳኔ ስለሰጡ ዼጥሮስ ስለራሱ እያለቀሰ ወ። ምንላባትም የኸቱ ምስጢር ገብቶት ስለራሱ ይጮህ የነበረ ብቸኛ ሰው ሳይሆን አይቀርም። ሌሊቱን በሙሉ አንድ ጊ እንኳን ሳይተኙ በጩኸት ከሐና ወደ ቀያፋ ከቀያፋም ወደ ሐና እያመላለሱት ሲጮሁ አደሩ። ሲነጋም የካህናት አለቆች ህዝቡ ሁሉ አሉ የትባሉትን ሽማሌዎች ጠርተው የሞቱን ጦማር አጸደቁት ። ከሳሽ ሳይኖር በደሉ ሳይዘረዘር  እንዲሞት የተወሰነበት የመጀመሪያ ሰው።


 ይሄ የሞት ውሳኔ ደግሞ ሌላ አደናጋሪ ጩኸት ፈጠረ። ከየት እንደመጣ ሳይታወቅ ያስያዘው ሰው የአስቆሮቱ ይሁዳ መጮህ ጀመረ ገንዘባችሁን ውሰዱ እርሱን ግን ተውልኝ እያለ። እዲጮህ ያደረገው በአመፃ  የሠበሠበው ግንዘብ ነበር። የአመጽ ገንዘብ መች ሰላም አለውና ታንቆ እስኪሞት ድረስ በኃጢአት አስክሮ  ያስጭኸው ነበር። የእርሱን ጩኸት ልብ ብሎ የሚያዳምጥ ግን አልነበረም። እነርሱ የተስማሙበትን ረቂቅ ሰነድ ወደ አገረ ገው ወስደው እንዴት እንደሚያጸድቁትና ተከሶ በቀረበው በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ የሞት ፍርድ  የሚያስፈርዱበትን ነገር እየተማከሩ የነበረበት ወቅት ነበርና። የተማከሩበትን ጉዳይ ረፋዱ ላይ ወደ ነገስታቱ ግቢ ይዘውት ሄዱ። በሊቀካህናቱ ግቢ ሲደነፋ ያደረው ወታደር ሁሉ አሁንም በዺላጦስ ግቢ በር ላይ ቆሞ ይጯጯሃል። ዺላጦስ ግራ ገባው፤ተሰምቶ የማይታወቅ ጩኸት በከተማው ይሰማል። ይሄንን ለማጣራት በአደባባይ ቢገኝም የነገሩ መንስኤ ነው የተባለውን ኢየሱስ ክርስቶስን አመጡለት። በደሉ ምን እንደሆነ የሚያስረዳ መዝገብ እንዲያመጡ ቢጥየቁ ምንም ነገር ስላልነበራቸው "አመጸኛስ ባይሆን ኖሮ ወደ አንተ ባላመጣነውም ነበር" ከማለት ውጪ ሌላ ምንም ያሉት ነገር የለም።  ዺላጦስ ተመልሶ ተከሳሹ ላይ አፈጠጠ። ከሳሾቹ ወንጀሉን ሊገልጹለት ስላልቻሉ ተከሳሹን ወንጀልህን ንገረኝ አለው። ግራ የገባው ዳኛ! በእርግጥ እርሱ የተከሰሰው  በሰው ልጆች ሁሉ በደል ነው።ከርሱ በቀር ይህንን ምስጢር የሚያውቀው ማን አለ? 


ነገር ግን በፈቃዱ ይሞት ዘንድ አለውና ክሱን ለማስተባበል አልሞከረም። አንድም ለሰማዕታት አብነት ሊሆን ነው። ክፉውን በስሜ በሕሀሰት ሲናገሩባችሁ በትዕግስት ተቀበሉት ለማለት ዝም አለ። በአደባባዩ የተሰበሰበው ሕዝብ ግን አሁንም ማጉረምርሙን አልተወም። ከከተማው ያለው ሕዝብም ወደ አደባባዩ መጉረፉን አላቋረጠም። ምክንያቱም የአይሁድ ሊቀ ካህናት የሸንጎውም አባላት በመደር ገብተው ሕዝቡ ሁሉ ወጥቶ "ይሰቀል! ይሰቀል!" የሚለውን ድምጽ እንዲሰጥ ግፊት ያደርጉ ስለነበር ነው። ዺላጦስ ግን እስካሁን በስልጣን ላይ ከቆየባቸው ዘመናት ሁሉ እንዲህ አይነት ተከሳሽ አይቶ ስለማያውቅ በዝምታ ተዋጠ፤ተገረመ። የሚያደረገውን በማጣቱ ወደ ሕዝቡ ወጥቶ  ምንም ወንጀል አላገኘሁበትም ሲላቸው ተረበሹ፤ ጩኸቱ በረታ። እንግዲያውስ ወስዳችሁ እንደ ሕጋችሁ ግደሉት ቢላቸውም በሕጋቸው ማንንም  እንዲገድሉ እንዳልተፈቀደላቸው መለሱለት። እንዲህ ማለታቸው ጌታ የሚሞተው  በሮማውያን ሕግ በመስቀል ነው እንጅ በአይሁድ ሕግ በውግረት እንዳልሆነ ሲያስረዱት ነበር። የጌታ ግን መከራ እጥፍ ድርብ ነበርና ሁሉንም ተቀበለ። ዺላጦስ እንዳስለመዳቸው ለፋስካ በዓል አንድ አንድ እስረኛ ይፈቱ ነበር እኛም በግብፅ እስረኞች ነበርን፣በበዓለ ፋሲካ ተፈታን ሲሉ ይህን ልማድ ያደርጋሉ። 


በዚህ ቀን ካሉት እስረኞች ኢየሱስ የተባለን ክርስቶስን ልፍታላችሁን ወይስ በርባንን ብሎ ቢጠይቃቸው በካህናት ሸንጎ እንደተመከረው ሕዝቡ ሁሉ ድምጻቸውን ለበርባን ሰጡ።ለጊዜው ዓለም የራሱ የሆነውን ነገር ይወዳልና  ያለው ቃል ይፈጸም ዘንድ ይህ ሁሉ ሆነ።ከዚህ ዓለም አይደለሁም ብሎ ለተናገረው ለድግል ማርያም ልጅ ደጋፊ አልነበረውም። መንግስቱ በዚህ ዓለም አይደለችምና፤ስለእርሱ የከራከረ የለም። ፍፃሜው ግን በዚህ ዕለት ክርስቶስ ባይታሰር ኖሮ የበርባን ወንጀል ለት የሚያደርስ ቅጣትን የሚያስከትል ነበር። ዕድል ገጥሞት በእርሱ ፋንታ ክርስቶስ እንዲሞት ተፍረደበት። በዚህም ክርስቶስ ስለወንጀለኞች ተላልፎ እንዲሞት ታወቀ። አይሁድ ባይገባቸውም እርሱ ግን የ አባቶቹን የነቢያትን ቃል ይፈጽም ዘንድ ይህን አደረገ የሁላችንን በደል በራሱ ላይ አኖረ ተብሎ ተጽፏልና ፍርዱ የዘገየባቸው አይሁድ ዺላጦስን ማስፈራት ጀምረዋል ካልፈረድህበት አንተ የቄሳር ወዳጅ አይደለህም እያሉ ጩኸቱን በታላቅ ድምጽ ተያይዘውታል። እርሱም በሥልጣኑ ማዳንም መግደለም የሚያስችል ስልጣን እንዳለው በመንገር ክርስቶስን የንገራግራል። ለሦስት ጊዚያት ያክል መልሶና መላልሶ  ቢመረመረው ለሞት የሚበቃ በደል ባለማግኘቱ ከደሙ ንጹህ እንደሆነ በመግለጽ እነሆ ንጉሳችሁ ብሎ የወደዱትን ያደርጉበት ዘንድ ሠጣቸው ። 


ከሕዝቡ ብዛት የተነሳ የድምጻቸው ሞገድ ከሩቅ እየተሰማ ከተማይቱን እንደ ክረምት ነጎድጓድ ያናውጣት ነበር። ሁሉም ስለ አንድ ሰው ጮኸ። አንዱ ክርስቶስ ስለሁሉ በታላቅ ቃል አሰምቶ እስከሚጮህ ድረስ በአጸደ ሥጋም ሆነ በአጸደ ነፍስ ባሉት ላይ ሁሉ የጩኸት ድምጽ ይሰማባቸዋል። በሲኦል የነበሩ ነፍሳትም  ይሰቀል! ይሰቀል! እያሉ ይጮሁ ነበርና። የጩኸታቸው መደምደሚያ እርሱ በመስቀል ላይ ሆኖ በሚያሰማው ጩኸት ነውና ያን እስኪሰሙ ድረስ ሁሉም ይጮሃሉ። የሕዝቡን ድምጽ በማክበር ንጹህ ፍርድ መፈርድ የተሳነው አገረ ገዥ አሳልፎ ስለሰጣቸው መስቀሉን አሸክመው ወደ ቀራኒዮ ወሰዱት። "ሆሳዕና በአርያም፣ቡሩክ ዘይመጽእ በስመ እግዚአብሔር" እየተባለ ከገባበት ከተማ ይሰቀል! ይወገድ! እየተባለ ወጣ። የሚቀድሙትም የሚከተሉትም  በምስጋና ምድሪቱን ሲያናውጧት  ይህ ማን? ነው ብሎ ያልተገረመና ያልጠየቀ የከተማዋ ነዋሪ የለም። ያኔ ልብሳቸውን እያወለቁ ለንጉሡ ክብር መጎናጽፊያቸውን ሁሉ በጎዳናው ዘረጉለት፤ዛሬ ግን ልብሱን ገፈፉት፤ ቅጠል ጎዝጉዘው በተቀበሉት መንገድ እርሱን ዘረጉት ከፊት የሚቀድሙት ከኋላም በአንድ ዓይነት ዜማ ያንጎራጉራሉ፤ ይሰቀል! ይሰቀል!

 

እያጣደፉ ወስደው ከከተማ ውጭ ሰቀሉት፤አሳባቸው ተፈጸመ። አሁንም ቢሆን ነፍስ ከስጋው ስትወጣ ካላዩ በስትቀር ዕረፍት የለም። ይህን የተመለከትው ክርስቶስ ጩኸታቸውን በጩኸት ደመደመው። ከአዳም ጀምሮ የተነሱ አበው ለጮሁት ጩኸት መደምደሚያ ይሆን ዘንድ በታላቅ ድምጽ ጮኸና ነፍሱን ተወ። የሰው ልጅ ጩኸት የተጀመረው በዚህች ዕለት በገነት ውስጥ ነበር፤ሕልሊናው እየጮኸበት በገነት መካከል ሲመላለስ ለሰማው ድምጽ የሚመልሰው በጎ ምላሽ ስለሌለው ፈርቶ ተደበቀ። ያች በደል ከዚያ እስከ ዛሬ ያላስጮኸችው የሰው ዘር በምድር ላይ አልነበረም። ጻድቅም ይሁን ሀጥእ ይሄን ጩኸት ያልተሳተፈ የለም። ባልሰራው በደል የአባቱ ዕዳ ከፋይ ሆኖ ከትውልድ እስከ ትውልድ ጩኸቱን ተቀባበለው። በዚህን ዕለት ዳግማዊ አዳም ኢየሱስ ክርስቶስ ባደረገው ታላቅ ጩኸት  የዚህ ሁሉ ትውልድ ጩኸት ተጠናቀቀ "ሁሉም ተፈጸመ"። የሕሊናውን ጩኸት እያዳመጠ ከሀዘኑ ብዛት የተነሳ አባታችን አዳም ወደ ምድር ፋይዳ ተጣለ። መርገሙን መሸከም አቅቶት በለቅሶና በእንባ ይህችን ዓለም ተቀላቀላት። ምን ያድርግ ገነት እኮ ማሕጸነ እግዚአብሔር ናት። ከዚያ ውጭ ሲጣል!


ይገርማል ዛሬም እኮ የእናቱን ማሕጸን ለቆ ወደ ዚህ ዓለም የሚመጣ ማንኛውም አዳማዊ በሳቅ አይደለም ወደ ዚህ ዓለም የሚመጣው ፤በለቅሶ "ዋይ" የሚል ድምጽ እያሰማ ነው እንጅ። በዚህ ሁኔታ ለቅሶን በግዱ ደስታን በድዱ እየተለማመደ ያድጋል። መሬታዊ ፍጥረት ነውና ወደ መሬትነቱ ሲመለስም በለቅሶና በዋይታ ይሸኛል። የዚህ ዓለም ኑሮ በዋይታ ተጀምሮ በዋይታ የሚያልቅ አስቸጋሪው የሕይወታችን ክፍል ነው። ቢሆንም ግን ከበስተጀርባው ያለውን ሌላኛውን የሕይወታችንን ክፍል እያሰብን በተስፋ ደስ ይለናል። በጩኸት የተዘጋችው ገነት በጩኸት ተከፈተችልን። የመጀመሪያው አዳም የጮኸው ጩኸት ሲኦልን የሁለተኛው አዳም(ክርስቶስ)ጩኸት ገነትን ከፈተልን። ታስታውሱ እንደሆነ እስራኤል ምድረ ርስትን ሲወርሱ የኢያሪኮን አጥር ያፈርሱት በጩኸት ነበር ። እስራኤል ከአጥር ውጭ ሆኖ ይጮሃል፤ከውስጥ ያሉ አሕዛብም እንዲሁ ይጮሃሉ። ማን መጮህ እንዳለበት እንኳን የማይታወቅበት  አስቸጋግሪ ዕለት! ያኛውም አርብ ነበር። በዚህኛውም አርብ በአፀደ ሥጋም በአጸደ ነፍስም ጩኸት አይቋረጥም። ያኛው እስራኤል በጮኸው ጩኸት ጠላቱን አሳዶ የተስፋይቱን ምድር እንደወረሰ ይሄኛውም እስራኤል በጩኸት የስፋይቱን ምድር መንግስተ ሰማያትን ወረሰ።የገሃነምን ቅጥር አፈርሰ ።የጠላት ዲያብሎስን ኃይል ደመሰሰ። 


እስራኤል ኢያሪኮን ለቆ ወደ ግብጽ ሲገባ ፈርኦን በላከለት ሰረገላ ተቀምጦ ያለ ጩኸት ነበር የመጣው ። ልጆቹ ግን ከግብጽ የወጡት ለአራት መቶ ሰላሳ ዓመታት በጮሁት ጩኸት ሲሆን ኢያሪኮንም የወረሷት በታላቅ ጩኸት ነው። እንዴዚሁም አባታችን አዳም ዲያብሎስ ባዘጋጀለት የኃጢአት ሠረገላ ሲሳፈር ያለጩኸት ተሳፍሮ ወደ ሲኦል የወረደ ሲሆን ከሲኦል የወጣው ግን እርሱና ልጆቹ ያለማቋረጥ ባሰሙት የአምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ጩኸት ነው። በኃጢኣት ምክንያት በሲኦል ደጆች ላይ የደረሰው ግፍ ታላቅ ከመሆኑ የተነሳ የሲኦል በሮች ተነቃቅለው፤የአጋንንት አለቆችም ተሽረው እስኪመለከት ድረስ ሰው ሁሉ ጮኸ። ያለ ጩኸት የገባው ኃጢአት በብዙ ጩኸት ከሰው ተወገደ።
 


                                ምንጭ፦ በሞት የተገለጠ ፍቅር
                                           ሊቀ ሊቃውንት ስምዐኮነ መልአክ

No comments:

Post a Comment