Sunday, October 23, 2016

ሦስት ዓመት ከመንፈቅ

ይህ ዘመን እመቤታችን ከኢየሩሳሌም ውጪ የኖረችበት ዘመን ነው ፤ጌታ በተወለደ በሁለት ዓመቱ ሰብአ ሰገል በመጡበት ወራት ከሄሮድስ ቁጣ የተነሳ ድንግል ከነ ልጇ በከተማ መቀመጥ አልቻለችም።ሰይጣን የሰው ልጆችን የመዳን ስራ ሲጀምር ሲመለከት ዝም አላለም፤ገና ይወርዳል፣ይወለዳል፣ሲባል ትንቢቱን  በመስማቱ እነ ኢሳይያስን  በመጋዝ አስተርትሮ ፣በኩላብ አሰቅሎ አስገድሎ ነበር። ሲወለድም የተወለደውን ሕጻን ማሳደድ ጀመረ። በተለይም ሊወለድ ሃያ አምስት ቀን ሲቀረው  መላእክት የሚወለድበትን ስፍራ ቤተልሔምን ተገተው ይጠብቁ ነበርና አጋንንት በጣኦታት አድረው መመለክ ስለተሳናቸው ጣኦታቱም ወድቀው ወድቀው በማለቃቸው ይህንን ምልክት አድርጎ ዲያብሎስ አዳኝነቱን ጀመረ።

የአባቶቻችን አዳኝ እርሱ በእመ አምላክም ላይ ከሰው እስከ አጋንንት የክፋት ሰራዊቶችን አስከትሎ ለሰልፍ ተነሳ ። አስቀድሞ በመጽሐፍ ለዚች ቀን የተነገረው የመጀመሪያው ትንቢታዊ ቃል በዚህ ጊዜ ተፈጸመ። "በአንቺና በሴቲቱ በካከል በዘርሽና በዘሯም ላይ ጠላትነትን አደርጋለሁ" ይህ ቃል በገነት ውስጥ ከተነገሩ የወደፊት የሰው ህይወት ጠቋሚ ቃላት አንዱ ሲሆን እመቤታችንና "የቀደመው እባብ" ተብሎ በሚጠራው ጥንተ ጠላታችን በሰራዊተ አጋንንት እና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መካከል የሚደርገውን ጦርነት የሚያመላክት ቃል ነው ።

እግዚአብሔር የተናገረው ሊፈጸም ግድ ነውና የንጉሠ ሰማይ ወምድር እናቱ እመቤታችን ድንግል ማርያም የሰይጣን ውጥን ጨራሽ በሆኑ ምድራውያን ነገሥታት ከሃገር ወደ ሃገር ተሰደደች። ዓለማችን እንዲህ ናት ዓመፀኞች የሚገኑባት፣እውነት የሚሰደድባት የእሪያ አይነት ልማድ ያላት ዓለም ናት ። እሪያ አብሮት የሚኖረው መልኩን ላለማዬት እውነተኛ መልኩን ያሳየውን እንቁ ረግጦ ይሰብረዋል፤ችግሩ እኮ የመልኩ ክፉነት እንጂ እንቁውማ ያለውን መልኩን ነበር ያሳዬው። ዓለማችን በሐጢአት የበለዘ ፊቷን የሚያሳዩዋት የእውነት መቅረዞችን እንደምንም ተሯሩጣ መርገጥ ትፈልጋለች። አሳድዳ የዋጠቻቸው ብዙ ሲሆኑ በለመደችው አሁንም  የዋጣትን የሀጢአት ረገረግ ሊያደርቅ የመጣውን ጌታ ለመዋጥ አፏን ከፈተች።

የተከፈተ አንደበቷን ሞት እስኪዘጋው ፣መቃብርም እስኪያትመው ድንግል ከዘንዶው ከሄሮድስ ፊት ሸሸች፤ከመካከለኛው ምስራቅ ወደ ምድረ አፍሪቃ ከነልጇ መጣች ፤ከሁለቱ አገልጋዮቿ ከዮሴፍና ከሶሎሜ በቀር ከዘመዶቿ የተከተላት ማንም አልነበረም። አምላካችን ክርስቶስ ንጉሰ ነገስት ነውና ከሦስት ነገሥታት ግብርን ተቀበለ። ይህ ካደረገ በኋላ ነገሥታቱ ግብራቸውን አቅርበው ሲመለሱ ሰውነቱ ፍጹም እንደሆነ ለማጠየቅ እናቱ ይዛው ተሰደደች፤በምድር እልፍ እልፍ ሠራዊት የተከተላቸው ሦስት ነገሥታት የሰገዱለት ፣በሰማይ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሠራዊተ መላእክት የሚገዙለት ሲሆን ተሰደደ።

እመቤታችን ከመልአከ ብሥራቷ ከቅዱስ ገብርኤል በተረዳችው መሠረት ወደ ምድረ አፍሪቃ ይዛው ስትመጣ  ያን ጊዜ  አባቶቿ ነቢያት የተናገሩት ተፈጸመ "ጌታ በፈጣን ደመና ተጭኖ ወደ ግብፅ ይመጣል"  ኢሳ19፡1። የነቢያት ቃል እንዲፈጸም ብቻም ሳይሆን በዓለማችን ልዩ ልዩ ክፍላት ተሰማርተው ጣኦት ያስመልኩ ፣ሀጢአት ያሠሩ የነበሩ አጋንንት ከምድር ጨርሰው እስኪወገዱ ጌታ ተሰደደ። እመብርሃን ድንግል በዚያ ወቅት በብዙ መነገድ ተፈተነች፤የሄሮድስ ሠራዊቶች ከተማ ለከተማ ይሄዱ፣ጎዳናውን ይዘው ይከታተሏቸው ነበርና ከዚያ ለማምለጥ ጫካ ለጫካ ይሄዱ ስለነበር በከባድ ረሐብና በታላቅ ውኃ ጥም ተፈተኑ። የእስራኤልን መና የዐለቱን ልብ አላልቶ  ውኃን የሚያጠጣውን ጌታ በጀርባዋ ይዛ ተራበች ተጠማች።

አባቷ አዳምና እናቷ ሔዋንን ከዘላለማዊ የነፍስ ረሐብና  ጥም የሚያድነውን ጌታ ነውና የያዘችው ተራበች፣ ተቸገረች። ከዕለታት በአንድ ቀን እንኳን ወደ መንደር ገብተው ቁራሽ እንጀራ ጥርኝ ውኃ ሲለምኑ የሚሰጣቸው አልነበረም። ዓለም ምን አላትና ሁሉን በእጁ ለያዘው ምን ትሰጠዋለች? ጌታ ራሱን እስኪሰጠን ድረስ የምንሰጠው አንዳች ነገር የሌለን ድሆች ነበርን፤ባለጠጎች የሆንነው ባለጠጋው ራሱ ጌታ ራሱን የሰጠን ጊዜ ነው ። ከረሐቡ ጋር አብሮ የማይረሳው ደግሞ በግብፅ ምድረበዳ የተድረገው ጉዞ ነው፤የግብፅ በረሃ በአሸዋ የተሞላ ሰውነትን የሚያሳርፍ ምንም አይነት ለመለም ነገር የሌለው ፤አሸዋው እግርን የሚያቃጥል የፀሐዩ ግለት ነፍስን ከሥጋ ለይቶ የሚጥል እሾህና አሜካላን የሚያበቅል ምድረ በዳ ነው።

ከአዳም በደል የተነሳ የረከሰችውን ምድር ሊቀድሳት የተርገመችውን ሊባርካት የመጣው ጌታ የሰውን ሕማም በሥጋው መከራን ሲቀበል ዳግማዊት ሔዋን እመቤታችንም እንደ እናቷ ሔዋን ከብርቱ እንባ ጋር መከራን ተቀበለች ። ሔዋን በሕማም፣በምጥ እንድትወልድ ሲፈረድባት ላለቀሰችው እንባ አምሳል የሚሆን እንባ በመውለዷ ጊዜ ይህ ሁሉ ያልደርሰባት እመቤታችን አነባች። ሦስት ዓመት ከመንፈቅ መከራው ያልተለያት ቢሆንም በተለይ አራቱ ፀዋትዎ መከራዎቿ ሁል ጊዜ ሲታወሱ ይኖራሉ። እነዚህም፦1ኛ ምጽአተ ዮሳ ወልደ ዮሴፍ፣ 2ኛ ሁልቱ ወንበዴዎች ባገኟት ጊዜ ፣ 3ኛ ቤተ ኮቲባ ፣ 4ኛ የልጇን ጫማ በወሰዱባት ጊዜ ናቸው።

ቤተክርስቲያን በዚህ ዓለም ክርስቶስን ተሸክማ በስሙ ተጠርታ እስከ ዓለም ፍጻሜ የምትሰደደውን መሰደድ ድንግል ጀመረችው። በዚህም በመጽሐፍት ሁሉ ስሟ ሲጠራ "እመ ሰማዕታት መዋዕያን፣የአሸናፊዎች ሰማዕታት እናት እየተባለች ትጠራለች። በተለይም በዘመኑ መጨርሻ ሐሳዊ መሲህ ነግሦ ቤተክርስቲያንን ለአርባ ሁለት ወራት የሚያሳድዳት መሆኑን አስቀድሞ በሄሮድስ ንግሥና እመቤታችንን ለአርባ ሁለት ወራት በመሰደዷ ነገረን።

እመቤታችን የስደቷ መከራ እያንዳንዱ ቢነገር አስገራሚና አሳዛኝ ሲሆን ከሦስት ዓመት ከመንፈቅ በኋላ ግንቦት ሃያስድስት ቀን ተጀምሮ ኅዳር ስድስት ቀን በድል ተጠናቀቀ። ብዙ ሕፃናትን የፈጀው ሄሮድስም ሐሳቡ ሳይሳካ ግብዓተ መሬቱ ተፈጸመ። የሕፃናቱ ጩኸት የእናቶቻቸውም ለቅሶና ዋይታ  የተሰማባት ገሊላ ዛሬ ስለልጆቿ  መጽናናትን እምቢ የምትለዋ ራሔል ሳትሆን የምታለቅስባት የንጉሥ ቤተሰቦች የለቅሶ ስፍራ ናት። የዚህ ዓለም ደስታ በፈረቃ ነውና ከ1260 ቀናት በኋላ ያዘነችው ድንግል ደስ ይላት ዘንድ በበረሐ ሳለች "መከራዬን አይቶ ይረዳኝ ዘንድ ትጸንሻለሽ ብሎ ያበሰረኝ መልአክ  ወዴት ነው?" ስትለው የነበረው መላክ ቅዱስ ገብርኤል መጥቶ ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ነገራቸው።

ጌታ ጠላቶቹን መምታት የጀመረው ከሄሮድስ ጀምሮ ነው ፤የመጨረሻው ዲያብሎስ ነው። እንዲህ የሚመስልሉ ብዙ የመዳን ተስፋዎችን የያዘው የግብፅ መልሳቸው ከዚህ በላይ የአበው ነቢያት ተስፋ ትንቢትን ፍጹም ያድረገ ቀን ነበር። በትንቢታቸው ቅዱስ መጽሐፍ ከመዘገባቸው ዐበይትና ደቂቅ ነቢያት ቃለ ትንቢታቸው ተናግረውት እስካልተመዘገበላቸው የቃል ነቢያት ድረስ የመመለሱን ዜና ለዓለም አውጀዋል። ከነቢያት አንዱ "ልጄን ከግብፅ ጠራሁት" ብሎ ስለ ግብፁ ስደተኛ ክርስቶስ በባሕርይ አባቱ ዘንድ የታሰበውን ሲገልጽ ሌላው ነቢይ ደግሞ "አንቺ ሱላማጢስ ሆይ ተመለሽ፣ እናይሽ ዘንድ ተመለሽ" ሲል ናፍቆቱን ይገልጽላታል። ከቃል ነቢያት አንዱ ስሙ ያልታወቀ ነቢይም "ልጄ ናዝራዊ ይባላል" ብሎ ሳይደርስ እንደደረሰ ፣ሳይደረግ እንደተደረገ አድርጎ የተናገረው እንዲፈጸም ከቦታዎች ሁሉ ናዝሬትን መርጠው ተቀመጡ።

ልብ በሉ! የእመቤታችን ወደ ናዝሬት መመለስ የእኛን ወደ ገነት የመመለስ ምስጢር የያዘ በመሆኑ ነው በነቢያት ሁሉ በናፍቆት ይጠበቅ የነበረው ።ይህ ደግሞ የተፈጸመው ነፍሰ ገዳዩ ንጉሥ ሄሮድስ ዓለምን ተሰናብቶ ማለቂያ ወደ ሌለው  የጨለማ ዓለም ከተዛወረ በኋላ መሆኑ ከጥንት ጀምሮ በእውነት የማይቆመው ነፍሰ ገዳዩ የአባቶቻችን ከሳሽ ዲያብሎስ ከተገደለ በኋላ አማናዊው የሰው ልጆች መዳን የሚፈጸም መሆኑን አመላካች ነው።

ምንጭ፦ ሕይወተ ማርያም ድንግል

No comments:

Post a Comment