Monday, March 07, 2016

ደጉ ሳምራዊ

እነሆም አንድ ሕግ አዋቂ ፈሪሳዊ ኢየሱስን ሊፈትነው ተነስቶ፦ መምህር ሆይ የዘለዓለምን መንግስት እንድወርስ ምን ላድርግ? አለው። እርሱም በሕግ የተጻፈው ምንድር ነው? እንዴትስ ታነባለህ?አለው። ፈሪሳዊውም መልሶ ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ኀይልህም ውደድ፣ባለእንጀራህን እንደርስህ  ውደድአለው። ኢየሱስም እውነት መለስህ ይህንን አድርግ በሕይወትም ትኖራለህአለው። ፈሪሳዊው ግን ራሱን ሊያጸድቅ ወዶ ነበርና ኢየሱስን ባለንጀራየስ ማን ነው ? አለው። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለ አንድ ሰው ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ ወረደ በወንበዴዎችም እጅ ወደቀ፤እነርሱም ደግሞ ገፈፉት፤ደበደቡትም፤በህይዎትና በሞት መካከልም ትተውት ሄዱ። ድንገትም አንድ ካህን በዚያ መንገድ ወረደ፤አይቶትም ገለል ብሎ አለፈ። እንዲሁም አንድ ሌዋዊ ወደዚያ ስፍራ መጣና አይቶት ገለል ብሎ አለፈ። አንድ ሳምራዊ ግን ሲሄድ ወደ እርሱ መጣ አይቶትም አዘነለት፤ቀርቦትም ዘይትና የወይን ጠጅ በቁስሎቹ ላይ አፍስሶ አሰራቸው፤በራሱ አህያም ላይ አስቀምጦት ወደ እንግዶች መቀበያ ወሰደው ጠበቀውም። በማግስቱም ሁለት ዲናር አውጥቶ ለባለቤቱ ሰጠና 'ጠብቀው ከዚህም በላይ የምትከስረውን ሁሉ እኔ ስመለስ እከፍልሃለሁ' አለው። እንግዲህ ከእነዚህ ከሦስቱ በወንበዴዎች እጅ ለወደቀው ባልንጀራ የሆነው ማንኛው ይመልሃል? አለው  እርሱም ምህረት ያደረገለትአለ። ኢየሱስም ሂድ አንተም እንዲሁ አድርግአልው።

በሕይዎት ጎዳና ስንጓዝ ምን እንድሚያጋጥመን አንውቅም። ቀደም ሲል በቀረበው ታሪክ ውስጥ ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ ይጓዝ የነበረው ሰው መጨረሻ አስከፊ እንደነበር አይተናል። ይህ ሰው ምን እንደሚያጋጥመው ቀደም ብሎ የተረዳ ቢሆን ኖሮ ጉዞውን በሌላ አቅጣጫ ወይም በሌላ ቀን ባደረገ ነበር። በህይወታችን ብዙ ፈተናወች ይገጥሙናል። ብዙ ጊዜ ወደፊት የሚገጥመን ነገር ምን እንደሆነ ሳናውቅ የጉዟችንን መስመር እንወስናለን። ሕይወት የእጣ ፈንታ ጉዳይ እንደመሆኗ አንዳንዴ መልካም ነገር አንዳንዴ ደግሞ ክፉ ነገር ያጋጥመናል። ምርጫችን ጥፋትን ሊያስከትልብን ይችላል፤ሞትን እስከማስከተል ድረስ። አንዲት የቤት እመቤት ከዕለታት  አንድ ቀን ያጋጠማቸውን ታሪክ እንደሚከተለው ይገልፃሉ። ባልፈው ሳምምንትአሉ አንድ ወጣት ልጅ የቤቴን በር አንኳኳ። በሬን ከፍቸ ስጠይቀው ስሙንና የዩኒቨርሲቲ ተማሪ መሆኑን የሚገልጽ መታወቂያ ወረቀት አውጥቶ አሳየኝ። ሥራ ፈላጊ መስሎኝ ለእርሱ የሚስማማ ሥራ እንደሌለኝ ገልጨለት መታወቂያውን ስመልስለት ሌላ ወረቀት በተጨማሪ አውጥቶ አሳየኝ። ሥራ አይደለም  የምፈልገው የእኔ እናት እባክዎን ሊረዱኝ ይችላሉአለኝ። የሰጠኝን ወረቀቅት ስመለከት የኤች አይ ቪ ቫይረስ በደሙ እንዳለብት አወቅሁ።


ቀደም ሲል አንዲት የሴት ጓደኛ ነበረችኝ እናምብሎ ሊቀጥል ሲል አቋረጥሁትና ይብቃህ የኔ ልጅ ሁሉንም ነገር ልትነግረኝ አያስፈልግምአልሁት። እባክዎ እናቴ ሰውነቴ በበሽታው እጅግ ተዳክሟል፤ሆኖም አገሬ መግባት አለብኝ ወደ አገሬ የምሄድበት ጥቂት ገንዘብ እንዲሰጡኝ እለምነዎታለሁአለኝ። ልጁን በጥሞና ተመለከትሁት፤ ዕድሜው ሃያወቹ ውስጥ ያለ ይመስላል፤ሰውነቱ ግን በበሽታው ተጎድቶ የደከመና የመነመነ ነው። ለጉዞው እንዲሆነው በማለት ጥቂት ገንዘብ ሰጠሁት፤እንዲሁም ምግብ አቀረብሁለት። እግዚአብሔር ይስጥዎ በጣም አመሰግናለሁ ውለታወን መቸም አልረሳውምብሎኝ ሄደ። ለዓይኔ እየራቀ ሲሄድ እንባየን መቆጣጠር አልቻልሁም። ወጣቶችን በአፍላ የምርታማነት ዘመናቸው የሚቀጭ እንዴት ያለ በሽታ ነው? የዚህ ልጅስ ህይወት ምን ትርጉም ይኖረዋል? ልጃቸውን ለትልቅ ደረጃ የተመኙት ወላጆቹስ በዚህ ሁኔታ ሲቀበሉት ምን ዓይነት ከባድ ኀዘን ይሰማቸው ይሆን?ብዬ አዘንኩ። ይህ ወጣት ግን አንድ ፍላጎት ብቻ ያለው ይመስላል አገሩ ገብቶ መሞት።


1) እርስዎ ከላይ  በታሪኩ በተጠቀሱት በቤት እመቤቲቱ ቦታ ቢሆኑ ምን ያደርጉ ነበር?  ወጣቱን  ዘወር በል  ብለው ያባርሩት ነበር ወይስ እንደ ወይዘሮዋ ምግብና ገንዘብ ይሰጡት ነበር?
2) በወላጆቹ፣ በእህትና በወንድሞቹ ቦታስ ቢሆኑ ወደ ቤት ተመልሶ ሲመጣ  እንዴት ነው የሚቀበሉት?
3) እንዲህ ዓይነት ሁኔታ አጋጥሞዎት ያውቃል?
4) እርስዎ እንደ ወጣቱ ላለመሆን ምን እያደረጉ ነው?
5) ኤች አይ ቪ እያደረሰ ስላለው ችግር ያለዎት አስተሳሰብ ምንድን ነው?

No comments:

Post a Comment