በእጅህ ያኖርኩትን የብርሃን ፀዳል መቅረዙን
ከስፍራው መጥቼ ሳልወስደው፣
ከዝናም በኋላ ደመናት ሳይሸሹ ፀሐይ
ሳትጨልም ቀኑን ሳልጋርደው፣
ከማሳው ያለውን ፍሬ አልባ ዘርህን ማለዳ
መጥቼ ከእርሻው ላይ ሳልነቅለው፣
የሰጠሁህን ሀብት ከመዳፍ ከጉያህ በአንድ
ጀምበር እድሜ አውጥቼ ሳልጥለው፣
እፍ ያልኩበትን ነፍስ ከውስጥህ ለይቼ
ወደነበረበት ስፍራ ሳልመልሰው፣
አእምሮ አለህና ነቅተህ ተዘጋጅተህ አደራህን
ፈጽም አስተውል አንተ ሰው።
ከምን ላይ እንደቆምክ በየት ስፍራ እንዳለህ
ሕሊናህን መርምር፣
ድንገት ጥሎህ ሳይሔድ ሳይከዳህ ሳይተውህ
የቆምክበት ምድር።
ቤትህን አስተካክል የፍቅር አንድነት መሠረት
የለውም ጥላቻ ተሞልቷል፣
ውስጡ ተቦርቡሮ ምሰሶው ተሰብሮ ጣሪያው
ተነቃቅሎ ውጪው ብቻ ቀርቷል።
እርም አለ በእጅህ ላይ እርምህን ሳትጥል
አይጸዳም አይቆምም የቤትህ መሠረት፣
በከንቱ እንዳትጥለው የደከምክበትን የአባትህን
ርስት የያዝከውን እምነት።
ይለናል እግዚአብሔር ለኔም ለአንተም
ለአንቺም ቃሉን እያሰማ፣
ልብ ያለው ልብ ይበል የአዋጅ ቃል ተነግሯል
በአገር በከተማ።
ማነው እጀ ንጹሕ ባሕር ከፍሎ የሚወስድ
ሕዝብን የሚያሻግር?
ሃይማኖት ካለባት ከሐገረ እግዚአብሔር
ከቃል ኪዳን ምድር።
ማነው የታረቀ ቀድሞ ከእራሱ ጋር አብሮት
ከሚኖረው ከሕሊናው ጋራ፣
ከግቡ የሚያደርስ ታሪክ የሚሠራ ከሕዝብ
የሚቀበል ይኼንን አደራ።
የማን ቃል ይሰማ ማን ነው የሚነግረን ማንን
እንመልከት፣
መብራቱ ሳይጠፋ ዘይቱን ሳንጨርስ ሳያልቅብን
ድንገት።
ደረስ ከተፍ ሲል ሙሽራው ሲመጣ ሁሉንም
ከእጃችን አራግፈን ጨርሰን፣
ማን ይከፍትልናል ብንጮህ ብናለቅስ በሩን
ብናንኳኳ ከደጃፍ ላይ ቆመን።
ለተተኪው ትውልድ ያዘነው ሰው ማነው፣
ከአባቱ ከእናቱ ምንድን ነው የሚወርሰው?
አንቺ እናት ለልጅሽ ምን አዘጋጅተሻል?
የሚጠይቅ ትውልድ መኖሩን አውቀሻል።
መልስ ይዘህ እንደሆን አንተ አባት ተናገር፣
ልጅህ ሲጠይቅህ የአንድነትን ነገር።
ማነኝ ከየት መጣሁ ምንድን ነው እምነቴ፣
የሚል ሕፃን አለን በቤትህ በቤቴ።
አሁን ነው ማስተዋል ምን እያረግን ነው?
ተተኪውን ትውልድ ማነው ያስተዋለው?
የሁላችን ድካም የሁላችን ጥረት፣
ዛሬ ማቃናት ነው የነገውን ሕይወት።
ሁሉ ሰው ሲኖረው ተከታይ ሲያፈራ፣
ዙሪያውን ሲከበው በዘራው አዝመራ፣
መልካም ነው ግሩም ነው ብሎ ሲገፋበት፣
ማነው ያስተዋለው የጥንቱን አንድነት?
ጎዳናው ሲያጓጉዝ ሲያራምድ አይተነው፣
ባሰበበት ስፍራ ሁሉንም ሲያደርሰው፣
ጊዜያዊውን ድንኳን ቋሚ ቤት አርገነው፣
እኛ እንዲህ ነን እያልን ለሰው ስናሳየው፣
ስንቱ ግራ ገባው ምስኪን ወገናችን፣
ትቶን ገደል ገባ ወጣና ከእጃችን።
ምን ቃል ተናግረነው በምን ቃል ይመለስ፣
ልዩነት መናናቅ ሞልቶት የእኛን መንፈስ።
እስኪ መልሱልኝ መልስ አይጠፋም ከሰው፣
ደርሶ ከትውልዱ ማነው ያስተዋለው?
እኛው አምጥተነው ከእኛው ቃል ተምሮ፣
የአምናው መለያየት ሲቀጥል ዘንድሮ፣
የተሻለ ነገር ሲጠፋ ከእጃችን፣
ስንቱ ዳግም ሔደ እያየን በዓይናችን።
የሥጋ ሥራ ነው ይብቃን መለያየት፣
ታሪክ ለመለወጥ እንቁም በአንድነት።
ይኽን ዘረኝነት ከቤት ካላስወጣን፣
የአጵሎስ የጳውሎስ ነን ከሚል ቃል ካልጸዳን፣
ውሸት ነው አይሆንም ከእግዚአብሔር ጋር ኑሮ
አንዱን አንዱ ንቆት ሰው በጸብ ተሳስሮ።
ዛሬም አሮጌ ልብስ ምነው ማጥለቃችን፣
ሁልጊዜ ድህነት ሀብት እያለ እጃችን።
ክርስቶስ የሰጠን ውድ የተወደደ፣
አዲሱ ልብሳችን የታል ወዴት ሔደ?
የሞተልን አምላክ ስላረገው ነገር፣
የዓለም መድኃኒት ነው ብለን ስንናገር፣
እንዲህ በእግዚአብሔር ቤት በዓሉ ሲከበር፣
አሮጌ ልብሳችን ምነው አይቀየር?
ክፋት እና ጥፋት በደል መተላለፍ፣
ለጎሣ እና ለዘር ለነገድ መሰለፍ፣
ሥርዓት ማበላሸት መሠረትን ማፍረስ
ደርሶ ክፉ መሥራት እውነትን ማደፍረስ፣
ቂም በቀል ጥላቻ ጥልና ክርክር፣
አሮጌ ልብስ ነው አይጠቅመንም ይቅር።
ርኅራኄ ትሕትና ሰላም እና ፍቅር፣
ትዕግሥትና አንድነት ደስታ መልካም ግብር፣
ሊለበስ ግድ ይላል በሰውነታችን፣
ክርስቶስ የሰጠን አዲሱ ልብሳችን።
አንድነት ሲሰበክ እኛ ስንስማማ፣
ብርሃን ይሆናል የዛሬው ጨለማ።
በአንድ ገበታ ላይ የቆረስን ሰዎች፣
ለምን ተፈራራን አባት እና ልጆች?
ጨርሶ ሲዘጋጅ ኖኅ መርከቡን ሠርቶ፣
ትውልድን ለማትረፍ ከእግዚአብሔርቃል ሰምቶ
ጥንድ ጥንድ አድርጎ አእዋፍ እንስሳቱን፣
ማነው ያመጣለት ከጫካ አራዊቱን?
አንበሳ እንዴት ሰማ ነብርን ማን ነገረው?
ከጓደኛው ጋራ መንገድ የጀመረው።
ርግብ እንዴት መጣች ቁራው ከማን ሰማ፣
ለማምለጥ የቻለው ድቅድቁን ጨለማ።
ሰውስ ከኖኅ ሰማ የአባት ቃል ሲናገር፣
ድንቅ የሆነው ምሥጢር የእንስሳቱ ነገር።
እንደምን ተረዱ እንዴት ነው የምናምን፣
ትውልዱ እንደሚተርፍ መርከቡ እንደሚያድን።
በምድር የሚሳበው በአየር የሚበረው፣
በበረት የሚያድር በጫካ የሚኖረው፣
ኖኅና መርከቡን በሩቅ ተመልክተው፣
ከቁጣ አመለጡ ተሸሸጉ ገብተው።
እግዚአብሔር ለሁሉም በቋንቋቸው ነግረህ፣
ኖኅና መርከቡን ያሳየህ አንተ ነህ።
ወደ እኛ እንመለስ የት ነን የት ቆመናል፣
ስንት መርከብና ስንት ኖኅ አይተናል?
አንድ መርከብ አለች አንድ ኖኅ ያለባት፣
እርሷን እንከተል ግብ መድረሻችን ናት።
ከእንስሳት የምንበልጥ የሰው ልጅ ተብለን፣
እንዴት በአንድ መርከብ መሰብሰብ ከበደን?
እናንት ሰባክያን ወንጌል የያዛችሁ፣
ካህናት ሊቃውንት ዕውቀት የበዛችሁ፣
ደግሞም መዘምራን ቃል የተሞላችሁ፣
በአንድነት ተነሡ ለአንድነት ብላችሁ።
በዐውደ ምሕረት ቆሞ ዘማሪው ሲዘምር፣
የሥነ - ጽሑፍ ሰው ቅኔ ሲደረድር፣
ከጫፍ ጫፍ ይሰማ ያስተጋባ ቃሉ፣
ለዓለም እንዲሰበክ የጌታ ወንጌሉ።
ገና ነው ኮረብታው አልተደለደለም፣
ሸለቆው አልሞላም ተራራ አልተናደም።
እናንተ መምህራን ደግሞም ካህናቱ፣
አደራ አለባችሁ ከፊት ይልቅ በርቱ።
አሁንም ሊሰበክ ይገባዋል ቃሉ፣
ወንጌልን ባንሰብክ ወየውልን በሉ።
ሌላ ሙሴ አይመጣም ባሕር የሚከፍል፣
በሰው የሚወደድ ቃል የሚያደላድል።
ወንጌል የተሰጠው ቃልን እንዲናገር፣
ሌላ ጴጥሮስ ማነው ከእናንተ በስተቀር?
በተለየ ፍቅሩ እንዲያ የወደደን፣
በግልገል በጠቦት በበግ የመሰለን፣
እንዳንጠፋበት ነው ተኩላው እንዳይነጥቀን፣
እያስጠነቀቀው ለጴጥሮስ የሰጠን።
የአደራ ልጆች ነን እኛ ምእመናን፣
አደራ አለባችሁ በክርስቶስ ሥልጣን።
ሰብካችሁ አንድ አርጉን ይኼ ነው ሙሴነት፣
ሌላ ቃል የሚሰብክ ማንን እንመልከት?
ከእናንተ ጋራ ነው ዛሬም ለዘላለም፣
ክህነት የሰጣችሁ አምላክ መድኃኔዓለም።
የምድሩ ቀላል ነው ይቺማ ምን አላት፣
ወንጌል በእጃችሁ ነው ገነት ለማስገባት።
ይኽን ያህል ሥልጣን ኃይል ነው ያላችሁ፣
ዳግም ያስተጋባ ይሰማ ቃላችሁ።
አንተም አንቺም እኔም በዚህ ቤት ያለነው፣
ስለ ቅድስት እምነት ወንጌል የተማርነው።
በአንድነት ከመቆም የሚያግደን የለም፣
የአደራ ልጆች ነን የመድኃኔዓለም
የአደራ ልጆች ነን የመድኃኔዓለም።
አብርሃም ሰሎሞን ጥቅምት 2003 ዓ.ም.