Tuesday, December 31, 2019

???


ግዳይ አስቀምጦ ለሕይወት መታጨት
ዘር ቀለም ሳይመርጡ ሰው ከእንስሳ መቅጨት
ፀሐይ ቁር ሳይፈሩ ግዑዝ ሆኖ ማርጀት
ጠፋች ሞተች ሲባል
ሰላም ለከ ብሎ ዳግመኛ መደርጀት
አጥፍቶ አለመጥፋት ልምድሽ ሆኖ ኑሮ
ኑሮ ኑሮ ኑሮ
ካንቺም በላይ ጀግና ሲመጣ ሲፕሮ
ቁርባ ቁርቢት ቁርጥሽ ነው ዘንድሮ

ቱ!

ያልታደለች ጉብል እድል የጠመማት
በአመንዝራ ዲያቆን
ተደፈርኩኝ ብላ ነገሩ ሲገርማት
የነፍሷ ጠባቂ ካህኑም ደገማት
በየት በኩል አልፎ ፈጣሪዋስ ይስማት?
ቱ!

Sunday, December 15, 2019

ጭንቃጭንቅ ዜና


በማድጋ ዞን ሽንክላ ወረዳ ጭንቁላ ቀበሌ የሽንትቤት ቀን በደማቅ ሁኔታ ተከብሮ ዋለ።

አ.ዲ.መ.መ ዘለፋ 8/900010 ዝንጠላ፡ ዲስኩር። በማድጋ ዞን ሽንክላ ወረዳ ጭንቁላ ቀበሌ የሽንትቤት ቀን በደማቅ ሁኔታ ተከብሮ መዋሉ ተገለጸ። የቀብሌው ሊቀመንበር አቶ እንዳመጣው ደባልቄ በበዓሉ ላይ ተገኝተው ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር እንደተናገሩት የዘንድሮውን በዓል ከባለፉት ለየት የሚያደርገው ከምንትስ ሚሊዬን በላይ ሶፍትና ወደ ብጥስጥስ የሚጠጉ የሽንት ቤት ወረቀቶችን ለማከፋፈል የቻልንበት መሆኑ ነው ብለዋል ። በበዓሉ ለረዥም ስዓት ሽንት ቤት ውስጥ በመቀመጥ የተሻለ ልምድ ላካበቱ ሞዴል ሽንታምና ተቅማጣም ወጣቶች የማበረታቻ ሽልማት የተበረከተላቸው ሲሆን ሌሎቻችንም የእነዚህን ግንባር ቀደም ወጣቶች አርዓያ ልንከተል እንደሚገባ ተጠቁሟል። ከተሸላሚ ቤተሰቦች አንዷ የሆኑት ወይዘሮ ትንጓለል አዝብጤ በበዓሉ ላይ በመገኘታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው በቅርቡ የሚከበረውን የወስፋትና ወስፋታሞች ቀን ለማክበር ዝግጅት መጀመራቸውን ተናግረዋል።

ከዜናዎቹ ጋር እሣቱ ለብልቤ ነበርሁ ሰላም

ኑሮ ተወደደች ደስታ ተሰደደች
እኔ እበላው ሳጣ ሚስቴ ልጅ ወለደች
ስኳር ጣሪያ ነካ
ግፊቴም ከፍ አለ ብላችሁ ምትፈሩ
ተካፍሎ ማደር ነው የጤና ምስጢሩ
መልካም ዕለተ ሰንበት

Tuesday, December 10, 2019

"መልካም ያደረጉልንን ሳናመሰግናቸው ይች ቀን አትለፍ" .



የዝቋላ ወረዳ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል በአ/ብ/ክ/መ ጤና ቢሮ ስር ከሚገኙ ሆስፒታሎች አንዱ ሲሆን ለማህበረሰቡ እየሰጠ ያለውን ሁሉን አቀፍ የጤና አገልግሎት ለማሻሻልና አገልግሎቱ በንባብ የዳበረ ብሎም በምክንያትና በእውቀት የተመሰረተ ይሆን ዘንድ EHSTG Reform በሚሰጠው አቅጣጫ መሰረት በሆስፒታሉ ውስጥ ቤተ-መጽሐፍት እንዲኖረን ለማድረግ ፕሮጀክት ቀርፀን እየሰራን መሆኑ ይታወቃል።


በዚህ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሥራውን ለማስጀመር የሚያስችሉ የህትመት ውጤቶችን ለማሰባብሰብ ተችሏል። ስማቸው ከታች ለተዘረዘሩትና ለዚህ ዓላማ መሳካት የበኩላቸውን አስተዋፅዖ ላደረጉ አካላት ልባዊ ምስጋናችንን እያቀረብን አሁንም ቢሆን ሥራው ተጀመረ እንጅ አላለቀምና “እውቀት እንረዳለን” የምትሉ ሁሉ በስልክ ቁጥር +251918666678 ወይም በኢሜይል getanehkassie@gmail.com ልታገኙን እንደምትችሉ ለመግለፅ እንወዳለን።



ምስጋና
1.ለወ/ሪት ሳምራዊት እስጢፋኖስ
2.ለደራሲ ይስማዕከ ወርቁ
3.ለዶ/ር ትዕግስት ስለሺ
4.ለአቶ ዘላለም ጥላሁን
5.ለወ/ሮ ዓለሚቱ ደሴ
6.ለኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጤና ሚኒስቴር
7.ለሆስፒታላችን ሰራተኞች በሙሉ
.
ዶ/ር ጌታነህ ካሴ
የፕሮጀክቱ አስተባባሪ






የድጋፍ ጥያቄ


Wednesday, October 23, 2019

……+++…...¡



ሀገር በእውር ድንብር በጭፍን ሲመራ
መንገዱ እንዲታዬን እስኪ አብሩ ደመራ
ስትይ ሰማንና
ደመራ ብንደምር አጋምና ቀጋ
መነገዱም አልታዬን ሌሊቱም አልነጋ
በ hang over ቀመር በኃራራ ስሌት
በሱሰኛ ወኔ በሰካራም ቅሌት
ካልታረሰ መሬት ካልተማሰ ማሳ
በለቃቀሙት ግርድ ጎኗ ላይነሳ
ስንዴውን ከእንክርዳድ እያሰባጠሩ
ሀገሬን አመሷት እነ ስም አይጠሩ
ተዘርቶ መሰብሰብ መልካም ቢሆን ቅሉ
ገብስና በቆሎ ስንዴና ባቄላ በአንድ ሲቀቀሉ
ንፍሯቸው አያምርም አውቃለሁ አንፍሬ
አተር በስሎ ሲልም ገብስ ይሆናል ጥሬ
ባቄላ+ጤፍ+እንክርዳድ+ግብጦ=……….?

Saturday, September 21, 2019

ላንቺ 2

የነፋስን በሬ ወጀቦ እያረሰው
የተፈጥሮን አጥር አርቴ እያፈረሰው
ቅንድብ ተቀንድቦ ኩልም እያነሰው
ወዝ በጠረረበት በዚህ የምጥ ጊዜ
ሴቶች መስታዊት ፊት ሲያበዙ ትካዜ
መታደል ነው እንጅ መባረክ አብዝቶ
እንዲህ ያል ቁመና
እንዲህ ያል ወዘና
እንዲህ ያል ደምግባት ከወዴት ተገኝቶ
የክንፍሽን ብርታት እያወቀው ሆዴ
የማትበላ ወፍ በከንቱ ማጥመዴ
ቃላት ማሰማመር ስንኝ መደርደሬ
አላስችል ቢለኝ ነው ይቅር በይኝ ፍቅሬ
ዘመን ሲለዋወጥ መስከረም ሲጠባ
ወይንም ባልጋብዝሽ ባልሰጥሽ አበባ
እንደ መስቀል ወፌ ስትመጭ ለዓመቱ
ከንፈርሽ ባይስመኝ ባይንሽ ዳብሽኝ እቱ
አውደ ዓመት ሲበሰር በወፎቹ ዜማ
እንኳን አደረሰሽ ውቢት የኔ ዓይናማ

ዶ/ር ጌታነህ ካሴ ለMeti

Thursday, July 18, 2019

....አንተ ማለት....

በኦነግ ሸማ እቃ  ኩታህ ተሸምኖ
በህውሓት አርማ ገላህ ተጀቡኖ
አንተ ማለት አብን አንተ ማለት ማለት ፋኖ
መላሾ እያሳዬ ያሻው የሚነዳህ
ግጦሽ ስትከተል ህሊናህ የከዳህ
የግሌ ምትለው እውነት የለህ አቋም
ትላንት በጌታ ስም ዛሬ ደግሞ አቋቋም
ጥዋት ቤተመቀድስ ከሰዓት ቃልቻ
አርሴማን  ከዙቤር አስረህ በጋብቻ
እምነት ምናባቱ ገንዘብ ያስገኝ ብቻ
ዶግማ ገደል ይግባ  ይቀንቅን ቀኖና
አንተ ማለት ሳንቲም አንተ ማለት ዝና
በአብ ስም ጀምረህ በአላህ የምትጨርስ ሲራራ ነጋዴ
እንደ ልመና እህል የተደባለቀው ምርትህ ተቸርችሮ አላለቀም እንዴ?

 ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው ማን ነው?  አንዱን ይጠላል ሁለተኛውንም ይወዳል፤ ወይም ወደ አንዱ ይጠጋል ሁለተኛውንም ይንቃል። ድቃቂ ሳንቲምና ዝናን ፍለጋ እዛም ቤት እዚህም ቤት ለምትልከሰከሱ ባተሌዎች! መልካም እለተ ሰንበት

07/11/2011 ዓ.ም
ዝቋላ ሆስፒታል 

Tuesday, July 09, 2019

...ሂፖክራቲክ ኦዝ...

የአባታችን ትዕዛዝ የቃል ኪዳኑ ቃል
በአንክሮ ላጤነው ምስጢሩ ይደንቃል
ከትእዛዛቱ ውስጥ አንደኛው ያይላል
መርዳት ባትችል እንኳ ሰው አትጉዳ ይላል
እናም ይህ መኃላ
ሂፖክራቲክ ኦዝ ሲመነዘር ቃሉ
አንድምታው ሲፈታ ሲራቀቅ ወንጌሉ
አንድም*
ከነፍሰጡር ሞት ጋር ዓይንህ አይላመድ
በሀጥአኑ መንገድ  እግርህ አይራመድ
ፈውስ ሆነህ ተፈጥረህ ከመርዝ አትዛመድ
አንድም*
መሪዎች ለገንዘብ ለሹመት አድልተው
መድኃኒት የሌለው ባዶ ቤት ገንብተው
ውኃና መብራቱን ድራሹን አጥፍተው
የጤና ሽፈኑን ምንትስ  አድርሰናል ብለው ሲሸልሉ
በሥልጣን መከታ በልዝብ አንደበት ህዝብን ሲያታልሉ
 በድብቅ መሳሪያ ታካሚን በሴራ በተንኮል ሲገድሉ
ትውልድ ከሚያመክኑ ነፍሰ ገዳዮች ጋር አትሸርብ ሴራ
እንቢ ለታካሚ ብለህ ተንጎራደድ ፎክርና አቅራራ
ታሪክ የማይረሳው ትልቅ ጀብዱ ስራ
የሚል ይመስለኛል
ይህን የሰሙ ግን ኢቲክሱን ጥሰሃህል እያሉ ያሙኛል
ተላልፈንም እንደሁ
በደሙ እያማገች በላቡ ቀቅላ
ሀገር እንደ ድመት ውድ ልጇን ስትበላ
 በደል ልኩን ሲያልፍ ግድቡ ሲሞላ
 ህገ-አምላክ  ይጣሳል እንኳንስ መኃላ

30/09/2011ዓ.ም
ዝቋላ ሆስፒታል

መልሱን ደብቅበት

አንደኛዬ ሆይ አንተ የአድባር  ዋርካ 
ድንጋይ ተንተርሰህ የከረምህ  በጫካ
.
ከሰውነት ወጥተህ መፅሐፍ ውስጥ የባጀህ
ለነገዋ  ተስፋ  ለዓላማህ መሳካትጊዜህን  የፈጀህ
የእሣትነት እድሜ ወጣትነትህን በንባብ የዋጀህ
አልጋና መከዳ ሲያማርጥ የኖረ ፀጉሩን እየቋጨ
ለንባብ  ስትወጣ መንገድ  የዘጋብህ ውኃ እየተራጨ
.
የአንደኛው መልስ ማነው ቢልህ በሹክሹክታ
ሰማሁህ አትበለው አትሁነው መከታ
መልሱን ደብቅና የእጁን ዋጋ ስጠው
የውድቀቱን ፅዋ ዛሬ ይጨልጠው
ልመናው በልጦብህ ምክሬን ብትል ችላ
እመነኝ ወዳጄ ለእኔ የደረሰው ይደርስሃል ኋላ
.
ስድስት ዓመት ተኩል ካሞፓስ ተቀቅዬ
ስመኝ የኖርኩትን ማዕረግ ተቀብዬ
ህዝቤን ለማገልገል ሠፈሬ ብመጣ
 በአቋራጭ ጎዳና ስልጣን ላይ የወጣ
ኮራጄ ጠበቀኝ ወንበር  ላይ ፊጥ ብሎ
የልጅነት ፍቅሬን መንትያ አሣዝሎአሣዝሎ

 05/10/2011 ዓ.ም
ዝቋላ ሆስፒታል

Monday, June 10, 2019

ከከፍታ በላይ

ሰነፍ በሚገዛት የበርባኖች ሀገር በዚች የጉድ ምድር
ጡንቻን በምትመግብ ጭንቅላት ፆም ሲያድር
ሊቃውንት ተንቀው ማይም ቢከበርም
መማር ካለመማር ሳይሻል አይቀርም
.
ዳሩ ምን ዋጋ አለው
"እውቀት ያለ ተግባር" ጭንቀት ይጨምራል
ያለቦታው ሲያድግ ዱባም ይማረራል
ሊቅስ በአላዋቂ ኧረ እንዴት ይመራ'ል?
.
በአደባባይ ሲፈስ   ምሬትህ ገንፍሎ
የቀደዱልህ ቦይ አይያዝህ ጠቅልሎ
በሚመክሩህ መንገድ አትሂድላቸው
ለምሳ ሲያስቡህ ለቁርስ አድርጋቸው
በግራ ሲያጠምዱህ በቀኝ ቅደማቸው
.
ማቃጠል ነው እንጅ  ማንደድ እንደረመጥ
ከጨቋኝ እግር ስር
የምን መልወስወስ ነው የምን መለማ መጥ
ለውጥ ያስፈልጋል ነው ጭማሪ ያሻል ነው አነሰም ጎደለም
ለታካሚህ ስትቆም ገዳይ ቢንጨረጨር የሚገርም  አይደለም
.
ሰምተሃል አንተን ነው ምንድን ነው ዝምታ
በአሽኮለሌ  ጩኸት በአሽቃባጭ ጫጫታ
በእንቅፋት በጉቶው ጉዞህ ካልተገታ
እውነትን ወግነህ ተሟግተህ ስትረታ
ከከፍታህ በላይ ደግሞ አለህ ከፍታ
.
ሰኔ 1/2011ዓ.ም
ዝቋላ ሆስፒታል

Tuesday, April 23, 2019

....ፍረደን.....

ስማኝማ አንድዬ
አራት መቶ ጅራፍ ተቆጥሮ የማያልቅ ስፍር የለሽ በደል
ለከፈልክባት ቀን እንኳን አደረሰህ አይባልም አይደል
የሰማዕታት ሀገር የፃድቃን ከተማ
ፅርሐዓርያም እንዴት ነው በበዓል ዋዜማ
ከዙፋንህ ግርጌ ቄጤማ ጎዝጉዘው እያሸበሸቡ
ሰውና መላእክት በአንድ ሲሰበሰቡ
ከመላእክት ምግብ ፃድቃን ሲመገቡ
ሰማይ ቤት እንዴት ነው የበዓል ድባቡ
ትዝ ይልሀል አይደል ?
አልጋውን አስይዘህ ያ'ዘለልከው ድኩም
አላውቀውም ብሎ የመታህ በኩርኩም
እንዴት ነው መፃጉ ኑሮ እንዴት ይዞታል
ቸርነትህ ደርሶት እርሱም ገነት ገብቷል
ወይስ የሲዖል ፍም እሣት ተስማምቶታል
ኑሮ ከተባለ እኛ አለን እንዳለን
አንተን መስለንና ያንተን አስመስለን
እንደ ኮሶ እንደ ሬት ኑሮ እየመረረን
እኔን ምሰሉ ሚል ቃልህን አክብረን
ሰውን ያክል ክቡር ነፍስ ተሸክመን
ታክሞ የማይድን ስልጡን ከብት አክመን
አድናለሁ ስንል እራሳችን ታመን
ሰርዷችንን ግጦ የጠገበ ኮርማ ዞሮ እየረገጠን
ወርቅ የሰፈርንለት አመድና ትቢያ አፈር እየሰጠን
ኑሮ ከተባለ እኛ አለን እንዳለን
አንተን መሆን ባንችል ያንተን አስመስለን
እናልህ አንድዬ
እንዳይጎርስ ለጉመው እንዳይሄድ ቀይደው
ከቤት እንዳይወጣ በጥዋት ጥመደው
የሚል ህግና ደንብ በዝባዥ አዋጅ ወጥቶ
ተመጥምጦ አለቀ ጉልበታችን ሟሙቶ
በራሳቸው ችሎት
ራሳቸው ከሳሽ ራሳቸው ዳኛ ሆነው እየቀጡን
ውኃ ጠማን ስንል ሆምጣጤ እያጠጡን
ከኩንታል ሙሉ ማር ሸክማችን ከበደ
ወዳንተ እንዳንመጣ ጉልበታችን ራደ
እንደ ልባሽ ጋቢ ዋጋችን ቀለለ
እባክህ ቶሎ ና ትክሻችን ዛለ
ልብሳችንን ነክተው ደማቸው ቀጥ ያለ ከሞት የተረፉ
ሀኪም ድሮ ቀረ እያሉ ለፈፉ
በእኛ መስዋዕትነት ከመቅሰፍት የዳኑ
በፈውሳቸው ማግስት እኛ ላይ ጀገኑ
መንግሥት!?
መንግሥትማ አለ እንጅ ስራውን ይሰራል
ዘላለም የመንገሥ መብቱን ያስከብራል
የተቃዋሚውን ጀርባ አጥንት ይሰብራል
በጠብመንጃው አረር የደቀቁ እግሮችን ሆስፒታል ይልካል
እንቶኔና እንትና በፈጠሩት ግጭት እያለ ይሰብካል
ተሰባሪው ታዲያ ሰባሪውን ፈርቶ አዳኙን ይከ'ሳል
የሀኪሞች ስህተት ውጤት ነው እያል አቧራ ያስነሳል
በርግጥ ሰው ይስታል እውነቱ አይካድም
በማካሮ ሽጉጥ መስበሩ ባይከብድም
ለዜና ካልሆነ
የተሰበረ እግር በጥገናው ማግሥት ቆሞ አይራመድም
እናልህ አንድዬ በዚች የጉድ ሀገር
ባልታደለ ዘመን በግም ወቅት ተፈጥረን
አንድ ቀን ከግማሽ ያለምንም ዋጋ ዱቲ ተወጥረን
በእለተ ትንሳኤ ላባችን ገብረን በደማችን ሰክረን
ካሣ' መሉ ፈጅቶ የመጣ ሰካራም እያደነቆረን
ልዝብ ያልከው ቀንበር ሸክሙ ከበደን
ነፃ አውጭ ላክልን ወይ መጥተህ ፍረደን

መታሰቢያነቱ፦ የትንሳኤ በዓልን ከቤተሰብ ተለይታችሁ ሆስፒታል ውስጥ ለምታሳልፉ የጤና ባለሙያዎች በተለይ በአውደ ዓመት ምድር ያለምንም ክፍያ ላብና ደማችሁን ለምትገብሩ ኢንተርን ሀኪሞች ይሁንልኝ ።

19/08/2011ዓ.ም
ዝቋላ ሆስፒታል 

Wednesday, April 17, 2019

.....እኛው ነን ጀሌዎች.....


ሲያቀብጥ ሲያሳብደን ፈተና እየሰቀልን
ስድስት አመት ተኩል ካምፓስ የተቀቀልን
.
አቋራጩን ትተን የሩቁን አልመን
ከባዱን ጦርነት በትጋት ተፋልመን
ትልቁን ተራራ ወጥተንና ወርደን
በሕይወት ብርቱ እሣት ነደንና በርደን
.
ፈልተን ተንተክትከን ተክነንና ጭሰን
የወጣትነት ወግ ፍላጎቱን ጥሰን
ተፈትነን አልፈን የተባልን ብቁዎች
ቀልጠንና ነጥረን የወጣን እንቁዎች
.
ሰርተን እንዳንበላ ደሞዝ ተከልክለን
ከአገር እንዳንወጣ በኮስትሸሪንግ ታስረን
በአምስት መቶ ችንካር ላይ ታች ተቸንክረን
ስድብ የሻተው ሁሉ ሚለማመድብን
ህዝብና አስተዳደር እኩል ያደመብን
ሰማይ ተገልብጦ ምድር የተደፋብን
.
ሰርከለት የምንጮህ ጆሮ ያልተቸረን
እንዘይደው መፍትሔ መላው የቸገረን
በዘመን መረገምቶች ለጉድ የተገፋን
ዙሪያው ገደል ሆኖ ማምለጫው የጠፋን
.
ቁርጥማት ቁርባ ቁርጠት የሚፈራን
ማትሪክ ያስኮረጅነው ተማሪ ሚመራን
ጋሻ ጦር ያልታጠቅን እኛው ነን ጀሌዎች
የባከነው ትውልድ ህያው ምሳሌዎች
.
15/07/2011ዓ.ም
ዝቋላ ሆስፒታል

...ከተራራው ግርጌ ...

በረሃብ አለንጋ በጭቆና ጅራፍ የተጎሳቆሉ
የችግራችን ምንጭ ምንድን ነው እንዳይሉ
በቁና መሉ ክክ በድጎማ ስንዴ እየተደለሉ
ከተራራው ግርጌ ተገፍተው ተጣሉ
የአገዛዙን ቀንበር ሰብረው እንዳይወጡ
ባለማወቅ ገመድ ታስረው ተቀመጡ
ወጣቱ እንዳይጠይቅ እንዳይሆን መርማሪ
ቤተመፅሐፍት የለ የህዝብ ላይበራሪ
በየጥጋጥጉ ነፍ ጭፈራ ቤት ነፍ ግሮሰሪ
በየመንገዱ ዳር የዝሙት ማህበር
ታች አንበሳ-መደብ ከላይ ሸራ ሰፈር
ደፍሬ እንዳልልሽ ሰዶም ወገሞራ
ከደጅ ይዘረፋል የወንጌሉ አዝመራ
ፍቅርሽ ተደግሶ ፍቅር ይዘከራል
እምወድህ ስትይ ልቤ ይሸብራል
ወይ ንስሐ አትገቢ ልክ እንደ ነነዌ
ሁልጊዜ ቃጠሎ ጥዋት ማታ ደዌ
አልቮ ልምላሜ ጉም ጥርት ያለ ሰማይ
እንደ እሣት ምትፋጅ አሳቃቂ ፀሐይ
ኤድስ አቫላዘር ወስፋት ወቁርባ
ሲፈራረቁብሽ ልብሽ የማይባባ
በፈርጣማ ክንዱ ችግር ያደባዬሽ
ለብዙ ዘመናት መቅሰፍት ያልተለዬሽ
በማን እና በምን እመስልሻለሁ
አስተዋይ ልቡናን እመኝልሻለሁ
እሳት ነበልባሉን ፍሙን የሚገታ
ዳግማዊ ዮናስ ይላክልሽ ጌታ
.
12/07/2011 ዓ.ም
ዝቋላ ሆስፒታል

የቀትር ጥላ

የችግር አረንቋ ሲውጠኝ ጨለማ
ደረስህ የታደግከኝ የህይወቴ ግርማ
የነውሬ መክደኛ ጓዳዬ ማጀቴ
የበረሃ ጥላ የሌሊት መብራቴ
የክፉ ቀን ደራሽ ጓደኛ ወንድሜ
እልፍ ዘላለሞች ኑርልኝ ዓለሜ
እንደ እድሜው ባላባት እንደ ማቱሳላ
ሰውነትህ ሳይዝል አቋምህ ሳይላላ
በ 500 ዓመትህ ሁንልኝ ጎልማሳ
ንግሥት በቀኝ ትኑር ወርቀዘቦ ለብሳ
ከሰማይ ከዋከብት ዘራዝርትህ ይብዛ
ጠንካራው መንፈስህ ፍጥረታትን ይገዛ
ከግብፅ ያወጣኸኝ የእኔ በትረመሴ
ስመርቅ አሜን በል ተቀበል ውዳሴ
አሜን በል!
ወጣት አይመርቅም የሚለው ሰው ማነው?
መልካም ጓደኛ እኮ የቀትር ጥላ ነው
ዶ/ር :ጌታነህ ካሴ :08/07/11:ዝቋላ
.
መልስ
አሜን እማ እላለሁ ከተረፈ ቅኔ
መወድሱን ስትይዝ ሳይገባኝ ለኔ
ጌታዋ አንተ እያለህ ለጥበብ ወግጥም
አሜን ብቻ ልበል ይብቃኝ ሌላው ጥምጥም
 ዲ/ንዶ/ር ታደገ: ዘላለም: 08/07/11:ጅማ

...እርግማን...

ከዘመናት በፊት ያኔ ድሮ ድሮ
ሰው መሞት ሳይጀምር በቁሙ ተቀብሮ
መናኝ በሚያስቱ አስማታም  ጥርሶችሽ
ቀልብን በሚያሣጡ ምትሃተኛ ዓይኖች
እንኳን ሁለት ስንኝ እንኳን ስምንት ቀለም
ህይወት ብታስከፍይ ላንቺ ብዙ አይደለም
ብሎ የፃፈልሽ ጥቁር ቀለም ብዕሬ ዛሬ ተፀፅቷል
የሚመጥንሽን በረከተ መርገምት ግጥም አዘጋጅቷል
.
መልካም  ስመኝልሽ ሞት የደገስሽልኝ  አስመሳይ ወዳጄ
የስራሽን ዓይቶ  አምላክ  ይስጥሸ   እንጅ አትጠበቂ ከእጄ
እንኳን ሰውን ከሰው ከመላክ የጣላል ብለሽ የምትሰብኪ
ወንዝ ለማያሻግር ቅቤ ጠባሽ ምላስ ምትንበረከኪ
በመከራዬ  ቋት በጭንቀቴ ቁና ደስታሽን ምትለኪ
ከልብ የመነጨ በእንባ የታጠረ እርግማኔን እንኪ
.
ደስታ አልቮ መሆኔ ሲጨንቅሽ ሲከፋሽ
ክፉ ሰው  ካረገኝ እጀን አመድ አፋሽ
የተመኘሽ  ሁሉ በዬ ቦታው ይድፋሽ
ሚስት ከባል ያፋታል ብለሽ ምታስወሪ
የአሉቧልታ እመቤት የተንኮል  መሰሪ
የሰው ስም ለማጥፋት ነገር ምትቀምሪ
ወርቅ ለሰፈረልሽ ጉድጓድ ምትቆፍሪ
ቆመሽ እንደ ቀረሽ ለዘላለም ኑሪ
.
ከውኃ የጠራሁ ንፁህ ሰው መሆኔን ልብህ እያወቀ
እውነቱን የካደ አድር ባይ ህሊናህ  ውጊያ የሸመቀ
ሚስቴን ሊወስዳት ነው ብለህ ምታነባ
ወጥመድ አዘጋጅተህ ቦታ ምታመቻች  ቀን የምታደባ
ከዛች ነገር ፈታይ የጭን  ገረድህ ጋር እንጦረጦስ ግባ
.
04/07/11ዓ.ም
ዝቋላ ሆስፒታል 

ቆርጠሽኝ ሰለቸሽ

ኦ እናት ሜድስን ፀሊም ወፀዓዳ
ጽዋሽ የማያልቀው ቢቀዳ ቢቀዳ
መዛመድ ሳያንስሽ ተግባርሽ የባዕዳ
ከጦርነት ማግስት ቦምብሽ ሚፈነዳ።
.
ኦ እናት ሜድስን እናት ህክምና
ይሻልሻል ብዬ ከአምና ከታቻምና
ወጣት ልጅነቴን
ክብር ማንነቴን
ቆንጥሬ ሳላስቀር ጠቅልዬ ሰጥቸሽ
ገዝግዘሽ ገዝግዘሽ ቆርጠሽኝ ሰለቸሽ።
.
ኦ እናት ሜድስን ፀሊም ወፀዓዳ
መዛመድ ሳያንሰን ተግባርሽ የባዕዳ
የዓርነቴ ፀሐይ የነፃነቴ ጎህ እያልሁሽ ስመካ
ፍቅርሽ አሲምፕቶት የሚጠጉት እንጅ መቼም አይነካ።
ይህን ፅሑፍ ለመፃፍ ስነሳ ከቀኑ 11:45 ነበር ።እንደ እሣት ስትፋጅ የዋለችው የመጋቢት ፀሐይ የተናደደች የቀይ ሴት ፊት መስላ ከዝቋላ ተራሮች ጋር ግብግብ ገጥማለች። "ነገ እንገናኛለን!" እያለች እንደ ጋለ ብረት በሚያቃጥል ምላሷ።እኔ በዚህ ሰዓት የህሊና ደወል የተሰኘውን የበዓሉ ግርማን መፅሐፍ መጨረሴ ነበር።በርግጥ በዚያ ዘመን እንደዚህ የሚያስብ ሰው መኖሩ በራሱ የሚገርም ነው። በስራ የማይገልጡትን መናገር ምላስን ማባለግ ነው ይላል ደራሲው።

የባለገች ምላስ ህሊና ላይ ታምፃለች።እምነትና ድርጊት ከተለያዩ ምሰሶው በምስጥ እንደተበላ ቤት መዛግ ከዚያም መፍረስ ይመጣል፤ወና ቤት መሆን ።በደራሲው እምነት ሰውን ሰው የሚያሰኘው በሀሣብ ፀንቶ እምነትን ከድርጊት ጋር ማስተባበር መቻሉ ነው ።እምነቱ ከድርጊት የተለየ ሰው ወኔ የለውም።ውሸት ፣ስብቀት፣ ሐሜት ፣ተደልሎ መደለል የግል ምልክቱ ናቸው።አድር ባይ፣ በሸንጎ ጨዋመሳይ ይሆናል።ሆዳም ነው ፤ምቾቱን ያመልካል።ምቾቱን ለመጠበቅ ሲል መሣሪያ ይሆናል።ከሀገሩ ይልቅ ጥቅሙን ያስቀድማል።ግን በአፉ ህሊናው ላይ ባመፀች ምላሱ በደል፣ ጥቃት፣ ፍትህ እያለ መጮሁ አይቀርም። እንዲህ ዓይኘቶቹ ሰዎች እየበዙ በሄዱ ቁጥር ፍትህ ትላላለች፤መተማመን ጠፍቶ ጥርጣሬ ያይላል።ህብረት ጠፍቶ በየአግጣጫው ማፈንገጥ ይነግሳል።እምነት ትመነምናለች።
.
እንዲህ ዓይነቶቹ ሰዎች ለማንኛውም ዓይነት ጥቃት ምቹ ናቸው። እንዲህ ዓነቶቹ ሰዎች ደግሞ እኛው ነን። እኔ፣ አንተ፤ ወይም አንቺ። ስለዚህ ሌባ ጣታችንን ወደ ሌላው ከመጠቆም ወደ ራሳችን መልሰን በዓይነ ህሊናችን ራሳችንን እንመልከት።መሻሻል ያስፈልገናል።መሻሻሉ ግን የሚጀምረው በእያንዳንዱ አእምሮ ውስጥ መሆን አለበት። አለበለዚያ መሻሻል ትርጉም አይኖረወም ፤ድሪቶ ይሆናል።አእምሯችን ያሰበውን ደግሞ ስራ ላይ ማዋል አለብን። በስራ ያልተገለጠ ሀሳብ የማይታይ የጋን መብራት ሆኖ ይቀራል። ዓለማችን በሀሳብ ባህር የሚዋኙ መለኮት የሚታያቸው ሰዎች እንደሚያስፈልጓት የታወቀ ቢሆንም የፖለቲካ ፍልስፍናን በመለፍለፍ ብቻ ኢትዮጵያን እናሻሽላለን ማለት ዘበት ነው። የመንፈሰ ደካማነት ምልክት ሊሆንም ይችላል።ምላስን ከመወንጨፍ ይልቅ እጅን ለትንሽ ስራ መዘርጋት የበለጠ ወኔን ፣ቆራጥነትንና መስዋዕትነትን ይጠይቃል።
.
በጤናው ዘርፍ በተለይም ደግሞ በሀኪሞች መንደር ሮሮና ዋይታ መሰማት ከጀመረ ሰነባብቷል።ትኩረት የተነፈጉና መልስ ያልተገኘላቸው ጥያቄዎች፣ ጆሮ ዳባ ልበስ የተባሉ ሰሚ ያጡ ጩኸቶች ከየ አቅጣጫው እንደ ጅረት ይጎርፋሉ።ጋራው ወደ እኛ ካልመጣ እኛ ወደ ጋራው መሄድ አለብን እንዲል ደራሲው እስከ መቼ ድረስ የሶሻል ሜዲያ አርበኞች እንሆናለን?መፍትሔ ሰጭው አካል ግድየለሽ ሆነ ማለት እኮ መፍትሔው በእጃችን ነው ማለት ነው ።እስከመቼ ድረስ መስዋዕትነትን እንሸሻለን። የጥያቄውን መልስ አእምሯችን እያወቀው መፍትሔው እጃችን ላይ እያለ እስከ መቼ ድረስ ሰሚ በሌለበት እንጮሃለን??? ዱላ ተይዞ መስመር ካልተወጣ መስኮት ካልተሰረ መኪና ካልተቃጠለ ችግር ያለ ከማይመስለው ህዝብና መንግሥት ጋር እስከ መቼ እንዳረቃለን???

NB: 500ካድሬዎች ለ5ዓመት ስራ ቢያቆሙ በኢትዮጵ አንፃራ ሰላም ይሰፍናል። 50 ሀኪሞች ለአንድ ሳምንት ስራ ቢያቆሙ በትንሹ 500 ሰዎች ይሞታሉ።

አንበሳ መደብ ላይ

አጭበርባሪ መንግሥት እኖር ባይ ካድሬ በሞላባት ሀገር
መማር አበሣ ነው መመራመር ወንጀል ማወቅ ከንቱ ነገር
ወንበሩ እግረ አንካሳ መሪው አላዋቂ
ብር ያለው መሃይም ቅጥረኛ አለቅላቂ
ከላይም ወደታች እየወረወሩኝ
ከታችም ወደ ጎን እየገፈተሩኝ
ገፊዬ ሲበዛ እንደ ውዳቂ እቃ
ያልታመመ ላይድን ያልተኛ ላይነቃ
ያልሞተ ላይፀድቅ ያነሰም ላይበቃ
ወደ ታች ነው እንጅ ከፍታውን ላላይ
ጎጆዬን ቀለስኩኝ አንበሳ መደብ ላይ
25/06/11 ዝቋላ

ትዝታ

የየኔወርቅ መውደድ የፍቅሯ ማዕበል
የቅድስቴ ለቅሶ የኤልሲ ማባበል
የየኑካ ትዕግስት የእንዳሌ ዝምታ
የአማኑኤል ጉርሻ የረዲ ጨዋታ
የቡዚቲ ኩርፊያ የአንቱካ ፈገግታ
የፀጊ ጨዋነት የመሲ ሁካታ
ከዲያስፖራው ጋር የሶፊው ትዝታ
በልሜ ይታየኛል ሁሌ ማታ ማታ
የአዚን ፍፁምነት የፋንታዬን ብፌ
እስከ ዘላለሙ አልነጥልም ካፌ
አንች የፍቅር መናገሻ ፅርሐፀዮን ሆይ ብረሳሽ ቀኘ ትርሳኝ ባላስብሽም ምላሴ ከትናጋዬ ይጣበቅ! መልካም እለተሰንበት እምወዳችሁ የፍቅር ጣዖታት !
10/06/2011 ዝቋላ

ሞዴል በክልኤ

እንደ ጥቅምት እሸት እንደ ስንዴው ዛላ
ታይቶ ማይጠገብ ዘንካታ ውብ ገላ
እንደ እንቁ ሚያበራ አስደንጋጭ ፈገግታ
አይንሽ ሲንከራተት እንቅፋት ሚያስመታ
የቆንጆዎች ንግሥት ሞዴል በክልኤ
የጭንቀት ማስረሻ የተስፋ ትንሳኤ
የሩቁን አሳቢ አስተዋይ ልበኛ
እውነት ተናጋሪ ታማኝ ክብርት ዳኛ
ተግባቢ ሳቂታ ጨዋታ አሳማሪ
የዝውውር ሳይሆን የማዕረግ ተማሪ
ወደፊት ጠበቃ የቅርብ ተጠሪ
ካንች ያስተዋወቀኝ ይመስገን ፈጣሪ
ለክብርት ዳኛ ማርታ ሻውል።
.
.
.ያልደረሳችሁ ተራችሁን ጠብቁ!

ውሻ በግርግር

ውኃ ለልማዱ ወደ ታች ይፈሳል
ገንዘብም ሲበዛ ራስን ያስረሳል
ውሻ በግርግር እናቱን ይሰራል
ተቃጥለህ ና ያለው ሜድስን ይማራል
ከዚህ ሁሉ በላይ
አሥራ ስምንት ዓመት ተግቶ ለተማረ
ለዓላማው መሳካት እድሜውን ለኖረ
ስንት ደጋ ስንት ቆላ በሞላባት ዓለም
ፅፅቃ እንደ መላክ ሰንካላ ዕጣ የለም
እድል ፋንታ ሕልምን እያመነመነው
የሚሆነው ቀርቶ ቢሆን የማይሆነው
እንደነዲድ እሣት ሙቀት ቢያቃጥለኝ
ሞልቶ የደላው ኑሮ አምላክ ባያድለኝ
የማይድን በሽታ ከቶ የለምና
ጥላ ይሆነኛል የፍቅርሽ ደመና 
ዝቋላ 25/2011

....ያልሆኑም አሉና....

ለአንዱ በር ሲከፈት ለአንዱ እዬተዘጋ
ቀኑ የጨለመ ቢመስል የማይነጋ
አንተ መሬት ወድቀህ ዙፋን ላይ ቢወጡ
ጥሙ ሲያቃጥልህ ወይን ጠጅ ቢጠጡ
ከሌለው ላይ ወስደው ላለው ቢጨምሩ
ጎጆህን አፍረሰው ቪላ ቤት ቢሰሩ
እንጀራህ ቢቀጥን ከቅጠል ቢሳሳ
ሽርሽር ቢጥራሩ ነፍስያህ አልቅሳ
የቤትህ መቃጠል ቢሆናቸው ደስታ
በሲቃህ ስታይል ቢመቱም እስክስታ
ጊዜው የጣለህን እስኪያነሳህ ቀኑ
ፍጹም ተስፈ አትቁረጥ ያልፋል ሰቀቀኑ
መውጣትና መውረድ ቢበዛው መንገዱ
'ሺህ' ዎች ሲሸለሙ እልፎች ቢዋረዱ
አንተን መሆን ናፍቀው ያልሆኑም አሉና
ከአንደበትህ ይፈሰስ ይንቆሮቆር ምስጋና

ዶ/ር ጌታነህ ካሴ(ጌች ቀጭኑ) : ባህር ዳር(ፈለገሕይወት ሆስፒታል የጥርስ ህክምና ክፍል ውስጥ) ጥር 03 ቀን 2011 ዓ.ም ከቀኑ 9:00ላይ ተፃፈ።

ይቅር ብዬሃለሁ

የእናት ሀገሩን ሀብት ስዊዝ አስቀምጦ
በፈጣሪ ቁጣ ሲወርድ ቂሊንጦ
ጠበቃ ከመንግሥት ቅጥር እንደተመኘው
እንደ ሜቴክ አዛዥ እንደ ክንፈ ዳኘው
የልፋቴን ዋጋ ቅርጥፍ አርገህ በልተህ
መመረቂያ ፎቶ መፅሔቴን አግተህ
ይቅርታ ጠይቀኝ ብለህ የላክህብኝ
የሰውነት እንጅ
የአስተሳስብ ቅጥነት ከቶ እንደሌለብኝ
የቅርብ ጓደኛ ነጋሪ ጠፍቶ ነው
ወይስ ፍቅረ ንዋይ መስሚያህን ደፈነው
ይልቁንስ ስማኝ ልንገርህ ወዳጄ
በተዓምር ስትገባ መጎረጫህ ከእጄ
ድንጋይ ተሸክመህ ባትቆምም ከደጄ
ወቅቱ የመደመር ነው ሲሉ ሰምቼ
ይቅር ብዬሃለሁ ሁሉን ነገር ትቼ
ታኅሣስ 8/2011 ዓ.ም

Friday, January 11, 2019

ጌችዬ ምትለኝ

ወንድሟ ሳተና ባለዲሞትፈር
እርሷ ደማም ቆንጆ ፍቅሯ የሚያሰክር
ትውልዷ ማክሰኝት የስመኘው ዘር
የክምር ድንጋይ ልጅ የደብረታቦር 
አባ ታጠቅ ልኳት ያ ስመ ገናና
ጌችዬ ምትለኝ ስሜን አሽሞንሙና
ጦር ሳትወረውር ሳትመክት በጓንዴ
በፍቅሯ ትኩሳት ልትገድለኝ ነው እንዴ

ፋኖ

መትረየስ እና ቦምብ ፊቱ ተደቅኖ
ገድሎ ይሸልላል ምን ተስኖት ፋኖ 
ጥጋበኛው ጎጃም እምቢተኛው ጎንደር
አሻግረህ ጥመደው ወይፈኑን በቀንበር
ካልታረሰ አይቀናም ልማደኛው ሀገር 
ቆስቁሳቸው እንጅ አትስጣቸው ጤና
መቼም ደግ አረገ አትባልምና
ፕሮፌሰር አስራት አንት የንጋት ኮከብ የበረሃው ዘንዶ
ስምህን አንግበን እንጠብቅሃለን በቅ በል ከማዶ

ምንም ማድረግ አይቻልም ጌች ቀጭኑን ካሜራ ስቶታል