Wednesday, April 17, 2019

...ከተራራው ግርጌ ...

በረሃብ አለንጋ በጭቆና ጅራፍ የተጎሳቆሉ
የችግራችን ምንጭ ምንድን ነው እንዳይሉ
በቁና መሉ ክክ በድጎማ ስንዴ እየተደለሉ
ከተራራው ግርጌ ተገፍተው ተጣሉ
የአገዛዙን ቀንበር ሰብረው እንዳይወጡ
ባለማወቅ ገመድ ታስረው ተቀመጡ
ወጣቱ እንዳይጠይቅ እንዳይሆን መርማሪ
ቤተመፅሐፍት የለ የህዝብ ላይበራሪ
በየጥጋጥጉ ነፍ ጭፈራ ቤት ነፍ ግሮሰሪ
በየመንገዱ ዳር የዝሙት ማህበር
ታች አንበሳ-መደብ ከላይ ሸራ ሰፈር
ደፍሬ እንዳልልሽ ሰዶም ወገሞራ
ከደጅ ይዘረፋል የወንጌሉ አዝመራ
ፍቅርሽ ተደግሶ ፍቅር ይዘከራል
እምወድህ ስትይ ልቤ ይሸብራል
ወይ ንስሐ አትገቢ ልክ እንደ ነነዌ
ሁልጊዜ ቃጠሎ ጥዋት ማታ ደዌ
አልቮ ልምላሜ ጉም ጥርት ያለ ሰማይ
እንደ እሣት ምትፋጅ አሳቃቂ ፀሐይ
ኤድስ አቫላዘር ወስፋት ወቁርባ
ሲፈራረቁብሽ ልብሽ የማይባባ
በፈርጣማ ክንዱ ችግር ያደባዬሽ
ለብዙ ዘመናት መቅሰፍት ያልተለዬሽ
በማን እና በምን እመስልሻለሁ
አስተዋይ ልቡናን እመኝልሻለሁ
እሳት ነበልባሉን ፍሙን የሚገታ
ዳግማዊ ዮናስ ይላክልሽ ጌታ
.
12/07/2011 ዓ.ም
ዝቋላ ሆስፒታል

No comments:

Post a Comment