Wednesday, April 17, 2019

ይህን ፅሑፍ ለመፃፍ ስነሳ ከቀኑ 11:45 ነበር ።እንደ እሣት ስትፋጅ የዋለችው የመጋቢት ፀሐይ የተናደደች የቀይ ሴት ፊት መስላ ከዝቋላ ተራሮች ጋር ግብግብ ገጥማለች። "ነገ እንገናኛለን!" እያለች እንደ ጋለ ብረት በሚያቃጥል ምላሷ።እኔ በዚህ ሰዓት የህሊና ደወል የተሰኘውን የበዓሉ ግርማን መፅሐፍ መጨረሴ ነበር።በርግጥ በዚያ ዘመን እንደዚህ የሚያስብ ሰው መኖሩ በራሱ የሚገርም ነው። በስራ የማይገልጡትን መናገር ምላስን ማባለግ ነው ይላል ደራሲው።

የባለገች ምላስ ህሊና ላይ ታምፃለች።እምነትና ድርጊት ከተለያዩ ምሰሶው በምስጥ እንደተበላ ቤት መዛግ ከዚያም መፍረስ ይመጣል፤ወና ቤት መሆን ።በደራሲው እምነት ሰውን ሰው የሚያሰኘው በሀሣብ ፀንቶ እምነትን ከድርጊት ጋር ማስተባበር መቻሉ ነው ።እምነቱ ከድርጊት የተለየ ሰው ወኔ የለውም።ውሸት ፣ስብቀት፣ ሐሜት ፣ተደልሎ መደለል የግል ምልክቱ ናቸው።አድር ባይ፣ በሸንጎ ጨዋመሳይ ይሆናል።ሆዳም ነው ፤ምቾቱን ያመልካል።ምቾቱን ለመጠበቅ ሲል መሣሪያ ይሆናል።ከሀገሩ ይልቅ ጥቅሙን ያስቀድማል።ግን በአፉ ህሊናው ላይ ባመፀች ምላሱ በደል፣ ጥቃት፣ ፍትህ እያለ መጮሁ አይቀርም። እንዲህ ዓይኘቶቹ ሰዎች እየበዙ በሄዱ ቁጥር ፍትህ ትላላለች፤መተማመን ጠፍቶ ጥርጣሬ ያይላል።ህብረት ጠፍቶ በየአግጣጫው ማፈንገጥ ይነግሳል።እምነት ትመነምናለች።
.
እንዲህ ዓይነቶቹ ሰዎች ለማንኛውም ዓይነት ጥቃት ምቹ ናቸው። እንዲህ ዓነቶቹ ሰዎች ደግሞ እኛው ነን። እኔ፣ አንተ፤ ወይም አንቺ። ስለዚህ ሌባ ጣታችንን ወደ ሌላው ከመጠቆም ወደ ራሳችን መልሰን በዓይነ ህሊናችን ራሳችንን እንመልከት።መሻሻል ያስፈልገናል።መሻሻሉ ግን የሚጀምረው በእያንዳንዱ አእምሮ ውስጥ መሆን አለበት። አለበለዚያ መሻሻል ትርጉም አይኖረወም ፤ድሪቶ ይሆናል።አእምሯችን ያሰበውን ደግሞ ስራ ላይ ማዋል አለብን። በስራ ያልተገለጠ ሀሳብ የማይታይ የጋን መብራት ሆኖ ይቀራል። ዓለማችን በሀሳብ ባህር የሚዋኙ መለኮት የሚታያቸው ሰዎች እንደሚያስፈልጓት የታወቀ ቢሆንም የፖለቲካ ፍልስፍናን በመለፍለፍ ብቻ ኢትዮጵያን እናሻሽላለን ማለት ዘበት ነው። የመንፈሰ ደካማነት ምልክት ሊሆንም ይችላል።ምላስን ከመወንጨፍ ይልቅ እጅን ለትንሽ ስራ መዘርጋት የበለጠ ወኔን ፣ቆራጥነትንና መስዋዕትነትን ይጠይቃል።
.
በጤናው ዘርፍ በተለይም ደግሞ በሀኪሞች መንደር ሮሮና ዋይታ መሰማት ከጀመረ ሰነባብቷል።ትኩረት የተነፈጉና መልስ ያልተገኘላቸው ጥያቄዎች፣ ጆሮ ዳባ ልበስ የተባሉ ሰሚ ያጡ ጩኸቶች ከየ አቅጣጫው እንደ ጅረት ይጎርፋሉ።ጋራው ወደ እኛ ካልመጣ እኛ ወደ ጋራው መሄድ አለብን እንዲል ደራሲው እስከ መቼ ድረስ የሶሻል ሜዲያ አርበኞች እንሆናለን?መፍትሔ ሰጭው አካል ግድየለሽ ሆነ ማለት እኮ መፍትሔው በእጃችን ነው ማለት ነው ።እስከመቼ ድረስ መስዋዕትነትን እንሸሻለን። የጥያቄውን መልስ አእምሯችን እያወቀው መፍትሔው እጃችን ላይ እያለ እስከ መቼ ድረስ ሰሚ በሌለበት እንጮሃለን??? ዱላ ተይዞ መስመር ካልተወጣ መስኮት ካልተሰረ መኪና ካልተቃጠለ ችግር ያለ ከማይመስለው ህዝብና መንግሥት ጋር እስከ መቼ እንዳረቃለን???

NB: 500ካድሬዎች ለ5ዓመት ስራ ቢያቆሙ በኢትዮጵ አንፃራ ሰላም ይሰፍናል። 50 ሀኪሞች ለአንድ ሳምንት ስራ ቢያቆሙ በትንሹ 500 ሰዎች ይሞታሉ።

No comments:

Post a Comment