Wednesday, April 17, 2019

.....እኛው ነን ጀሌዎች.....


ሲያቀብጥ ሲያሳብደን ፈተና እየሰቀልን
ስድስት አመት ተኩል ካምፓስ የተቀቀልን
.
አቋራጩን ትተን የሩቁን አልመን
ከባዱን ጦርነት በትጋት ተፋልመን
ትልቁን ተራራ ወጥተንና ወርደን
በሕይወት ብርቱ እሣት ነደንና በርደን
.
ፈልተን ተንተክትከን ተክነንና ጭሰን
የወጣትነት ወግ ፍላጎቱን ጥሰን
ተፈትነን አልፈን የተባልን ብቁዎች
ቀልጠንና ነጥረን የወጣን እንቁዎች
.
ሰርተን እንዳንበላ ደሞዝ ተከልክለን
ከአገር እንዳንወጣ በኮስትሸሪንግ ታስረን
በአምስት መቶ ችንካር ላይ ታች ተቸንክረን
ስድብ የሻተው ሁሉ ሚለማመድብን
ህዝብና አስተዳደር እኩል ያደመብን
ሰማይ ተገልብጦ ምድር የተደፋብን
.
ሰርከለት የምንጮህ ጆሮ ያልተቸረን
እንዘይደው መፍትሔ መላው የቸገረን
በዘመን መረገምቶች ለጉድ የተገፋን
ዙሪያው ገደል ሆኖ ማምለጫው የጠፋን
.
ቁርጥማት ቁርባ ቁርጠት የሚፈራን
ማትሪክ ያስኮረጅነው ተማሪ ሚመራን
ጋሻ ጦር ያልታጠቅን እኛው ነን ጀሌዎች
የባከነው ትውልድ ህያው ምሳሌዎች
.
15/07/2011ዓ.ም
ዝቋላ ሆስፒታል

No comments:

Post a Comment