Tuesday, July 09, 2019

...ሂፖክራቲክ ኦዝ...

የአባታችን ትዕዛዝ የቃል ኪዳኑ ቃል
በአንክሮ ላጤነው ምስጢሩ ይደንቃል
ከትእዛዛቱ ውስጥ አንደኛው ያይላል
መርዳት ባትችል እንኳ ሰው አትጉዳ ይላል
እናም ይህ መኃላ
ሂፖክራቲክ ኦዝ ሲመነዘር ቃሉ
አንድምታው ሲፈታ ሲራቀቅ ወንጌሉ
አንድም*
ከነፍሰጡር ሞት ጋር ዓይንህ አይላመድ
በሀጥአኑ መንገድ  እግርህ አይራመድ
ፈውስ ሆነህ ተፈጥረህ ከመርዝ አትዛመድ
አንድም*
መሪዎች ለገንዘብ ለሹመት አድልተው
መድኃኒት የሌለው ባዶ ቤት ገንብተው
ውኃና መብራቱን ድራሹን አጥፍተው
የጤና ሽፈኑን ምንትስ  አድርሰናል ብለው ሲሸልሉ
በሥልጣን መከታ በልዝብ አንደበት ህዝብን ሲያታልሉ
 በድብቅ መሳሪያ ታካሚን በሴራ በተንኮል ሲገድሉ
ትውልድ ከሚያመክኑ ነፍሰ ገዳዮች ጋር አትሸርብ ሴራ
እንቢ ለታካሚ ብለህ ተንጎራደድ ፎክርና አቅራራ
ታሪክ የማይረሳው ትልቅ ጀብዱ ስራ
የሚል ይመስለኛል
ይህን የሰሙ ግን ኢቲክሱን ጥሰሃህል እያሉ ያሙኛል
ተላልፈንም እንደሁ
በደሙ እያማገች በላቡ ቀቅላ
ሀገር እንደ ድመት ውድ ልጇን ስትበላ
 በደል ልኩን ሲያልፍ ግድቡ ሲሞላ
 ህገ-አምላክ  ይጣሳል እንኳንስ መኃላ

30/09/2011ዓ.ም
ዝቋላ ሆስፒታል

No comments:

Post a Comment