Wednesday, January 06, 2016

የዓለም ድኅነት በክርስቶስ ልደት

ቤተክርስቲያናችን የምትቀበላቸው አምስት ዓበይት ምስጢራተ ቤተክርስቲያን መኖራቸው የታወቀ ነው።እነርሱም "አምስቱ አዕማደ ምስጢር" በሚል ስያሜ ይጠራሉ። ከእነዚህም ታላላቅ ምስጢራት አንዱ ምስጢረ ስጋዌ ነው። "ምስጢር" የሚለው ቃል በቤተክርስቲያናችን  አነጋገር በፍልስፍናዊ ርቀትና በምርምር ሳይሆን፤በእግረ ሕሊና ብቻ ሊደርሰበት የሚቻል ነገር እንደሆነ ይታመናል።ስለዚህ ምስጢረ ሳጋዌ ማለት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር ቃል ከሰማየ ሰማያት ወርዶ መላውን የሰው ዘር ለማዳን ሲል ከድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ ሰው የሆነበት ምስጢር ነው። የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሰው መሆን የሚደነቅ እንጂ የማይመረመር ታላቅ ምስጢር ነው። የእግዚአብሔር ቃል ሰው ሆኖ መላውን የሰው ዘር ከድቀተ አዳም ጀምሮ [5,500]አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ሙሉ በሃጢአት አዘቅት ተጥሎ የቅጣት ማዕበል እየወረደበት፤በእግረ ሰይጣን እየተረገጠ የቁም ሙት ሆኖ ሲኖር እንደዚሁ ቃላት ሊገልጹት ከማይችሉት ኀዘንና ስቃይ፤እንዲሁም ተስፋ መቁረጥ ያድነው ዘንድ ስለተወለደ፤የአባቱን ፈቃድ በመፈጸም የሰውን ደዌና ሕማም ተሸክሞ፤ሥጋን ለብሶ ሰው በሆነም ጊዜ መላው የሰው ዘር በመከራ ይኖር ዘንድ ተነግሮ የነበረው አዋጅ ተሻረ። "አዳም ገብሩ ለዲያብሎስ ሔዋን ዓመቱ ለዲያብሎስ" የሚለውም መዝገብ ተቀደደ፤በኀጢአት ፈንጋይነት ታፍኖ ተሽጦ የነበረው አዳምም ወደ ጥንተ ክብሩ ተመልሷል።


በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው መሆን የእግዚአብሔር መለኮታዊ ፍቅሩ፣ጸጋውና ይቅርታው ተገልጿል። ከፈጣሪው ቅጽረ ረድኤት ውጭ ሆኖ የነበረው አዳም ወደ ጥንተ ቦታውና ማዕረጉ ክብሩና ሞገሱም ተመልሷል። በሰማይና በምድር መካከል የዕርቅና የይቅርታ ሰንደቅ አላማ ተተክሏል። ከፈጣሪው ጋር እንዲሁም ከራሱና ከአካባቢው ጋር ተጣልቶ ይኖር የነበረው ፍጡርም ታርቋል። ይህም ዕርቅ ምን ማለት እንደሆነ ለመግለጽ ያህል ኦሪት ዘፍጥረት3፡23 አዳም የፈጣሪውን መንግሥት ለመገልበጥ ባደረገው አመጽና፡መቀናቀን የሞት ሞት ተፈርዶበት ከገነት ሲወጣ ዱሮ በትእዛዙ ሲተዳደሩ ይኖሩ የነበሩት አራዊትና እንስሳት ሁሉ አፋቸውን ከፍተው አስፈራሩት ቀንዳቸውንም አሹለው ሊወጉት ቃጡ። በጥፍራቸው ኃይል የሚጠቀሙት እንዲሁ ጥፍራቸውን አዘርዝረው ሊቧጥጡት ቀረቡ ይላል። ይህም አዳም ባደረገው ጥፋት ተጣልቶ የነበረው ከእግዚአብሐር ጋር ብቻ ሳይሆን ከአካባቢውም ጋር እንደነበር ያስተምረናል። በተጨማሪም ከዚህ በላይ በወንጀለኛ ላይ የሚፈርደው ዳኛ ብቻ ሳይሆን ጎረቤት ፣ወዳጅና ዘመድና ባዕድም ጭምር እንደሆነ እንረዳለን። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆኖ ከተወለደ በኋላ ግን የሰው ኀዘኑ ወደ ፍሥሐ ተለውጧል።በጠቅላላው ልደተ ክርስቶስ  ነገደ አዳምን በሙሉ ከዲያብሎስ ባርነት ነጻ አውጥቶ ከአካባቢውና ከመላው ሥነ ፍጥረት ጋር ከነበረው ቂምና በቀል እንዲሁም ጠላትነት አስታርቆ የራሱንም የሕሊና ባርነት ድል እንዲነሳ አድርጎ የእግዚአብሔር ልጅ ለመሆን አብቅቶታል።



በማቴዎስ ወንጌል ምዕ 4፡15 በጨለማ ውስጥ የሞት ጥላ እያንዣበበባቸው ይኖሩ ለነበሩት ሁሉ ብርሃን ወጣላቸው ተብሎ እንደተተጻፈው ሁሉ ከዚህ በፊት የነበረው የመላው ዓለም ጨለማዊ ሁኔታ ወደ ብርሃን ተስፋና ደስታ ተለውጧል።ስለዚህ ልደተ ክርስቶስ በዓመት አንድ ጊዜ  የሚከበር ያለፈ ድርጊት ወይም ታሪክ አይደለም።በየሰዓቱ፣በየዕለቱ በህይወታችን ውስጥ ሲደረግ የምናየው የተጨበጠ እውነት ነገር እንጂ፤በእርሱም የሚገኘው ጸጋና ክብር የማይደርቅና የማያቋርጥ ሁል ጊዜም በሕሊና ውስጥ የሚፈስ የምህረት ፈለግ ነው።በዚህ ዕለት እስኪ ዓይነ ሕሊናችንን ወደ ቤተልሔም ዘወር አድርገን እንመልከት። እነሆ ሰማይና ምድር የማይወስኑት ሊሸከሙትም የማይችሉ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአጭር ቁመትና በጠባብ ደረት ተወስኖ፤በልማደ ሰብ በጨርቅ ተጥቅልሎ በአንዲት የከብት በረት ውስጥ ተኝቶ እናያለን፤አህዮች፣ ላሞችና በጎች በአስተብርኮ በትንፋሻቸው ኃይል ብርዱን ሲከላከሉለት ይታያሉ።እረኞች ዙሪያውን ከበው ሆ!ሆ! እያሉ ሲፈነደቁና ሲጫወቱ ይሰማሉ፤መላእክት በሰማያት "እነሆ ከዛሬ ጀምሮ በምድርና በሰማይ መካከል ማለትም በሰማይ በሚኖሩ በሠራዊተ መላእክትና በምድር ባሉት በደቂቀ አዳም መካከል የነበረው ቂምና በቀል ተሰርዞ ፍጹም እርቅ ሆነ፤የሰላም ሰንደቅ አላማም ተተከለ" እያሉ እረኞችን ሲያበስሩ ይሰማሉ። በቤተልሔም ጫካወች የሚገኙ አራዊትም "ዛሬ የዓለም መድኃኒት ተወለደ" እያሉ በዝማሬና በልልታ ሲዘሉና ሲደስቱ ይታያሉ።


ዓይነ ልቦናችንን ቀና አድርገን የስብአ ሰገልን ጉዞ እንመርምር።እነሆ ሰባ ሰገል ከሩቅ ምስራቅ ከርቤ፣ወርቅና ዕጣን በግመሎቻቸው ጭነው "ስንጠብቀው የኖርነው ብሩህ ኮከብ ወጣልን" በማለት እየተወያዩ በጉዞ ላይ ይታያሉ። በቶሎ ደርሰውም የእጅ መንሻቸውን ለማበርከት ሲጣደፉ የእነርሱም የግመሎቻቸውም ኮቴ ይሰማል።እስኪ ደግሞ በእግረ ሕሊና ወደ ገሊላው ገዥ ወደ ሄሮድስ ቤት እናምራ፤ሁለት ዓመት የፈጀውን ጉዟቸውን ፈጽመው ከሄሮድስ ቤት የደርሱት ሰባ ሰገል፤ዜናውን ሲያበስሩት የተሰማው ድንጋጤ ይታየናል።ዓይኑ ደፍርሶ ግንባሩ ተኮማትሮ ከንፈሩ እየተንቀጠቀጠና ጥርሶቹ እየተፋጩ፤ከዙፋኑ ላይ ቁጭ ብድግ እያለ ከመማክርቱ ጋር በሕጻኑ ላይ ያደረገውን ምክረ ሰይጣንና የወሰነውን ውሳኔ በመንፈስ  እናነባለን።ከሁለት ዓመትም በታች የሆኑ ሕፃናት በሙሉ እንዲሰባሰቡ ያስነገረው አዋጅ፣ነጋሪት ሲመታና ጥሩንባው ሲነፋ በጆሯችን ውስጥ ይደውላል፤ለሕፃናቱም መታረጃ የተሳሉት ሰይፎች ከአፎቶቻቸው ተመዝዘው እንመለከታለን።

    ከዚህ በላይ እንደተረዳነው በቤተልሔም የተወለደውን ሕፃን ሁለት ዓይነት ወገኖች ይፈልጉታል፤አንደኛው ወገን ሊሰግድለት፤ሊያመልከውን የእጅ መንሻም ሊሰጠው ሲሆን፤ሁለተኛው ክፍል ደግሞ ሊገድለው ሰይፍ የሚስል የሄሮድስ ወታደር ነው።ከዚህ በላይ ልንጠይቅ የምንፈልገው እኛስ የትኞቹን እንመስላቸዋለን? ሊሰግዱለት ሊያመልኩትና እጅ መንሻ ሊያበረክቱለት የፈለጉትን ሰባ ሰገልን ነውን? ወይስ የሄሮድስን ወታደሮች? ዛሬ ላለንበት ለ20ኛው ክፍለ ዘመን በስሙ የታነጸችውንና የቆመችውን የእርሱን መንግስት በመስበክና በማስተማር ላይ የምትገኘውን ቤተ ክርስቲያን ሁለት ዓይነት ሰዎች በጥብቅ የሚፈልጓት መሆኑን መዘንጋት የለብንም።ከእነርሱም አንደኛው እንድትጠፋ የሚጥረው ሲሆን፤ሁለተኛው ደግሞ እንድትስፋፋና የሚገጥሟትንም የመንፈስ ጦርነቶች ድል ነስታ እንድትኖር የሚጥሩ በሃሳብም ሆነ በስራ ከእርሷ  ጋር የተሰለፉት ናቸው።ነገር ግን ሊያጠፏት የሚጥሩ ሁሉ በከንቱ ይደክማሉ እንጂ ቤተ ክርስቲያን አትጠፋም። ቤተክርስቲያን እንደ ትልቅ ቋጥኝ ናት፤የወደቀባትን ትሰብራለች የወደቅችበትንም ታደቃለች።ይህ በዓለ ልደት የሰላም፣የተድላና የደስታ በዓል እንዲሆን እየተመኘሁ ሃሳቤን እዚህ ላይ እገታለሁ።
                                                                                              

                                                                                             ምንጭ፦ትንሳኤ መጽሔት
                                                                                                       ካቲት 1958ዓ.ም

No comments:

Post a Comment