Saturday, January 06, 2018

ሲዋንን ያለፈ

ከሰላም እንቅልፉ  ከምትቀሰቅሰው፣
ጓደኛህን በቁም አሁን  አሞጋግሰው፤
ብላ በምትመክረኝ በቀይዋ ብዕሬ፣
በጥዋት ተነሳሁ ላሞካሽህ  ዛሬ።
ልክ እንደ አባ ኮስትር እንደ በላይ ሁላ፣
ካሰበበት ሳይደርስ ትጥቁ የማይላላ፣
ያበቅላል ወንድ ልጅ ዱር ቤቴ ዳንግላ።
አንዱ በሃይማኖት ሌላው በሰፈሩ፣
አንገቱን ሊያስደፉት  ሲለፉ ሲጥሩ፣
ገድለው ሊያዳፍኑት ጉድጓድ ሲቆፍሩ፤
ጀግና የጀግና ዘር መሆኑን ሳያውቁ፣
በቆፈሩት ጉድጓድ እየገቡ አለቁ።
የጎጃም እናቱ አትውለጅ ምከኝ፣
እንደ በላይ ጀግና ከንቱ ላታገኝ።
የሚል ጎጅ ምክር አልመክርሽም እኔ፣
በፍቅሩ ሰው ገዳይ እያየሁ ከጎኔ።
አርግዥ እንጅ ጸንሽ ውለጅ መንታ መንታ፣
ተከብሮ  ሚያስከብር በቆመበት ቦታ፣
አውቆ የሚያሳውቅ ተሟግቶ ሚረታ።
ጀግንነትን በጦር ያደረገው ማን ነው?
ወንድነትን በሰይፍ ያደረገው ማን ነው
?
ወድቋል በቃ ሲሉት
ሲዋንን ያለፈ ለእኔ እሱ ጀግና ነው።
ጅማ ጤና ጣቢያ: ታኅሣስ 13/2010 .

Friday, January 05, 2018

ሽርሙጥና

ሽርሙጥና ይቅር ያለው ማነው ደፍሮ?
ብቻውን ይከርማል ጉዱ ነው ዘንድሮ።
ሽፍታ በሚገዛት አንኳን በዚች ምድር፣
ጡንቻ በምትመግብ ጭንቅላት ፆም ሲያድር፣
ለጊዜው ባለ አባት ክብሩን የገበረ፣
በዓለመ መላእክት ሸርሙጣ ነበረ።
ተፈጥሮም እንደ ሰው ትሸረሙጣለች፣
ለጠንካራ ክንዶች ምስጢር ትገልጣለች፤
ለሃይለኞች ብቻ ክብሯን ትሰጣለች።
ፍትሕ አይገባውም እግዜሩም ያዳላል፣
ከሌለው  ላይ ወስዶ ላለው ይጨምራል።
ኪሱ ለወፈረ ትክሻው ለሰፋ ቢሰጥ ድንግልና፣
ታዲያ ምኑ ላይ ነው ነውሩ ሽርሙጥና???
ታች ቤት ታኅሣስ 22/2010 ዓ.ም