Monday, July 24, 2017

የሐበሻ ቀጠሮ

የሐበሻ ቀጠሮ ሲባል ግን አይገርማችሁም? በፈረንጅኛ እንማራለን በፈረንጅኛ እናስተምራለን፣በፈረንጅኛ እንታመማለን፣ በፈረንጅኛ ታክመን በፈረንጅኛ እንድናለን። በፈረንጅኛ እንመርቃለን(እናመሰግናለን)፣በፈረንጅኛ እንሳደባለን። በቢዮንሴ እና በሻኪራ ዘፈን እንጨፍራለን፤ የፈረንጅ ልብስ እንለብሳለን፤ የፈረንጅ መጠጥ እንጠጣለን፤የፈረንጅ ምግብ እንመገባለን (ለማለት ቢከብድም)። ከፈረንጅ ያልወረስነው ነገር ምን አለ? እንደ እኔ ከፈረንጅ ያልኮረጅነው ነገር ቢኖር የቀጠሮ አከባበራቸውን ብቻ ነው። ፈረንጆች የሚሆኑትን ሁሉ እንሆናለን። የሚያደርጉትንም እንደ አቅማችን ለማድረግ እንጥራለን። የሰዓት አጠቃቀማቸውን ለመስረቅ ሙከራ ሲያደርግ የተያዘ ወንጀለኛ ግን ያለ አይመስለኝም።ይልቁንም ደካማ የጊዜ አጠቃቀማችንን የሐበሻ ቀጠሮ የሚል ሽፋን እንሰጠዋለን።

የሐበሻ ቀሚስ ከተነደፈ ጥጥ ይሸመን ከታኘከ ማስቲካ ይሰራ የማያውቁት ሴቶቻችን እንኳን ዳሌያቸውን ከጉልበቱ ላይ በተቀደደ የቻይና ጅንስ ወጥረው ለምን የቀጠሮ ሰዓት እንዳላከበሩ ሲጠየቁ “ምን ይደረግ የሐበሻ ቀጠሮ አይደል” ማለት ይቀናቸዋል። ወይ ሐበሻ እቴ ድንቄም ሀበሻ! የማር ሰፈፍ የመሰለ እንጀራ ጋገሮና በቅምጥ የሚስቀር ጠላ ጠምቆ ነበር እንጅ ሐበሻነትን ማስመስከር። “ትርክርክ” አለች አክስቴ። በነገራችን ላይ እኔ እስከማድግ ድረስ ሴቶቻችን በዚህ ከቀጠሉና ለቀጠሮ ያላቸው አመለካከት ካልተስተካከለ ቆሞ ቀር እባላለሁ እንጅ ሚስት የምትባል ጉድ ላለማግባት ቁርጥ ያለ ውሳኔ ላይ ደርሻለሁ። በቃ አዱኛ አበባዬን ሳላይ ብሞት ይሻለኛል።(የመጀመሪያ ሚስቴን ልፈታት ስላሰብሁ ከተሳከልኝ ማለቴ ነው) ። ቀጠሮ የማታከብር ሴት ቱ... ሞቻለኋ!

ምን ለማለት ፈልጌ ነበር ? ባለፈው ቅዳሜ እለት የሆነች ስልጠና ቢጤ ለመሳተፍ ከጥዋቱ 2:00 ላይ የሆነ ቦታ ተገኝቸ ነበር። ስልጠናው ወይም ስብሰባው በማስታወቂያ ከተገለፀው ሰዓት 80 ደቂቃዎችን ብቻ ዘግይቶ ተጀመረ። ወደ ስብሰባው አዳራሽ በጓሮ በር ገብተን እንደተቀመጥን ግማሽ ሌትር የሀይላድ ውኃ በነፍስ ወከፍ ታደለን። (እኔም እንደሰው ወግ ደርሶኝ የሀይላንድ ውኃ እየጠጣሁ ስብሰባ ስሳተፍ ይህ የመጀመሪዬ ነው። ከነ እማማ ደብሬ ቤት በታች ካለችው ቤተመጽሐፍት ውስጥ የሚገኝ አንድ ስሙን የማላስታውሰው መዝገበ ቃላት “ስብሰባ የሚለው ቃል በቁሙ ሲፈታ ውኃ ውኃ የሚሉ ሰዎች ተመራርጠው የሚሰባሰቡበት፤ በየደቂቃው አፋቸውን በሀይላንድ ውኃ እየተጉመጣመጡ ውኃ የማያነሳ ሀሳባቸውን የሚሰነዝሩበት ፤ በመጨረሻም ከውኃ የቀጠነ ውሳኔ አሳልፈው የሚለያዩበት የሰዎች ጥርቅም ነው ”ይላል።)

ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስ በተሰጠችኝ ውኃ ንዴቴን አብርጄ አገር ሰላም ብዬ በተቀመጥሁበት ከመርሀግብር መሪዎቹ አንዷ ወደመድረክ ሰበር ሰካ እያለች ወጣችና ቀብረር ብላ “good morning every body welcome to …”አለች በፈረንጅኛ ነው እኮ። አቅለሸለሸኝ ጨጓራዬ ተነሳብኝ፤ በቃ ተቃጠልሁ። ሊነስረኝም አማረው። አሁንም ቀጠለች “….. let’s have some ground rules… first thing is punctuality. Punctuality or timely arrival is a must .” ብላን እርፍ።መቼስ ሰማንያ ደቂቃ አርፍዶ የመጣ ሰው ሰዓት አክባሪ ለመምሰል ሲገዳደር ያልወረደ መብረቅ እራሱም ዘገምተኛ መሆን አለበት።

እንዴው ፈጣሪ አያድርግብኝና የሰይጣን ጆሮም አይሳማ እንጂ ሰሞኑን የጨጓራ በሽታዬ ድጋሜ ከተነሳ ምክንያቱ ከወ.መ.ሽ ሰልፍ እና ቀጠሮ ከማያከብሩ ሰዎች የዘለለ አይሆንም። አይ ወመሽ ወመሽ እኮ ሰልፍ ይወዳል። ካፌ ሰልፍ፣ ሻይ ቤት ሰልፍ፣ ቡና ቤት ሰልፍ፣ ሽንት ቤት ሰልፍ ፣ ሰልፍ ፣ ሰልፍ፣ ሰልፍ ነው ።

Wednesday, July 19, 2017

እርሳኝ አትበይኝ

በድል ያሳለፍሽኝ የሞትን አደጋ፣
እንዳይ የረዳሽኝ የህይወትን ዋጋ፣
የልፋት ደሞዜን የተጋድሎን ፀጋ፤
በውለታሽ ብዛት ያረግሽኝ ባለዳ፣
የመስከረም አደይ ውቧ ጽጌረዳ ፣
ልቤን ያሸፈትሽው ገና በማለዳ፤
ፍቅርን የሰጠሽኝ ጠቅልለሽ በሸማ፣
ስምሽ በአንደበቴ ከፍ የሚል ከማማ፤
ከእንቅልፍ የሚያነቃኝ የጉርሻሽ ትዝታ፣
ድምጽሽ ሚያባንነኝ ሁሌም ጥዋት ማታ፤
ከብርንዶ ይልቅ ሽሮሽ ሚናፍቀኝ፣
አንች በሌለሽበት ወለላ የሚያንቀኝ፤
ተዳፍነሽ የቀረረሽ የልቤን ውስጥ እሳት ፣
እንዴት ይቻለኛል እኔ አንቺን ለመርሳት?
አበባ ጥርሶችሽ ከኔ ይሰንብቱ፣
ሳቅና ጨዋታ ዝና የሚያውቁቱ፤
ብዬ ያዜምሁልሽ የሀሴት ዝማሬ፣
በናፍቆትሽ ብርታት ስባዝን አድሬ፤
አምባገነን ሥልጣን ከላይ የተቸረው ፣
መተተኛ ዲያቆን አንደበቴን  ቢያስረው፤
ማሰንበት ቢቻለው ጭድን ከእሳት ጋራ፣
ማስታረቅ ቢያውቅበት ሸማን ከገሞራ፣
በአንቺ እና እኔ መሀል ቢያፈልስ ተራራ፣
መውደዴን ባልነግርሽ ቢያዝ አንደበቴ፣
እርሳኝ አትበይኝ አይችልም አንጀቴ።
ፍቅሬን ባልገልጽልሽ ቢዘጋ ልሳኔ፣
እርሳኝ አትበይኝ ችሎ አይችልም ጎኔ።

©ጌች ቀጭኑ ለY.F ሐምሌ 12/2009 .

Thursday, July 13, 2017

ማን ዘርቶ ማን ያጭዳል?

አንድ አርሶ አደር  ያልዘራውን ስንዴ ወይም አርሞ ኮትኩቶ ያላሳደገውን አዝመራ መከር ሲደርስ እሰበስባለሁ ብሎ ሊከራከር እንደማይችል ማንም ሰው የሚያውቀው ጉዳይ ይመስለኛል። ታዲያ  በዩኒቨርሲቲ ቆይታው ተቸጋግሮ  ሲማር፣ እንደ አጋጣሚ በንባብ ተጠምዶ ሳያስበው የካፌ ሰዓት በማለፉ ጾሙን ድፍት ብሎ ሲያድር፣ እንደ ሌሎች ሻይ ቡና ብሎ ወደ ንባብ የሚመለስበትን ቀን ሲናፍቅ፣ ይቺ የሻይ ቡና ይቺ ደግሞ የሳሙና  ትሁንህ ያላሉትን ተማሪ ዛሬ ላይ ዳቦ ጋግሬ፣ ጠላ ጠምቄ፣ ሙክት አርጄ፣ ፍሪዳ ጥዬ አስመርቅሀለሁ ማለት የሞላኝ የደላኝ ሀብታም ነኝ ብሎ ለመመፃደቅ ካልሆነ በቀር ሌላ  ምን ትርጉም ይኖረዋል? ተቀያሪ በሌላቸው ልብሶቹ የጓደኞቹ መሳለቂያ  እስከሚሆን ሲቸገር  ለደብተር እና ለእስክርቢቶ እጁን ያልዘረጋ ዘመድ የምረቃ ዕለት እንደ ድንገት የ90 ብር አበባ እና የ5ሺህ ብር ስማርትፎን ይዞ ማዘጥዘጡስ ምን ሊበጅ? ማን የዘራውን፣ ማን አርሞና ኮትኩቶ  ያሳደገውን፣ ማን ያጭዳልያልዘሩትን አጫጅ ከመሆን ይሰውረንማ አቮ !!! ለማንኛውም ተመራቂዎች እንኳን ደስ ያላችሁ ብያለሁ።
 ሰኔ 1/2009 .ም :ሲስኮ

Tuesday, July 11, 2017

አታሳደኝ በለኝ


ወደህና ፈቅደህ የፈጠርኸኝ ጌታ፣

ምስጋና ይብዛልህ ይድረስህ ሰላምታ።

በመላእክት ሀገር በጻድቃን ከተማ፣

ክብርህ የገነነ በኤረር በራማ፣

ጸሎቴን ተቀበል ልመናዬን ስማ።

ማሳደጃ ጦማር የሹመት ደብዳቤ፣

የሀጢአት ፍላጻን በወገቤ አንግቤ፣

በዝሙት በሐሜት በክፋት ታጅቤ፣

ወንጌል ዲቃላ ስል ጥበብን ተርቤ፤

የመወጊያውን ብረት ስቃወም በፀና፣

“አታሳደኝ” በለኝ ድምጽን አሰማና።

በምድረ ደማስቆ የወረደው መብረቅ፣

የልቤን ደጅ ይምታ አለቱም ይሰንጠቅ፤

ሳታቆስል ማርከኝ አድርገኝ ምርጥ እቃ፣

ስምህ በአንደበቴ የሞተ ሰው ያንቃ።

የእስር ቤቱ መዝጊያ መሀሉ ይፈለጥ፣

ክብርና ሞገስህን በባሪያህ ላይ ግለጥ።

በደስታ ልዘምር ምድር ትደባለቅ፣

ጠላቴን ይጭነቀው አካላቱ ይለቅ።

ጸናጽሌን ልያዝ ከበሮዬን  ልምታ፣

ዓለም ግሩም ትበል ታምርህን አይታ።

((©ጌች ቀጭኑ)):ገዳም ሰፈር
ሐምሌ 4/2009 ዓ.

Wednesday, July 05, 2017

🎓አውቆ የደደበ🎓

ለሰው ግድ የሌለው አምላኩን ማይፈራ፣
እንኳን ለወንድሙ ለእናቱ ማይራራ፣
ግን ደግሞ !
“የተማረ” ተብሎ በማዕረግ ሚጠራ፤
ጭንቅላቱ ከስቶ ምላሱ ያበጠ፣
በሰይፍ አንደበቱ እልፍ የቆረጠ፣
አብዶ ያልወጣለት ምራቁን ያልዋጠ፣
የትህትናን ደጅ እግሩ ያልረገጠ፤
ከፍቅር ገበታ  እጁ ያልዘገነ፣
የተስፋው ጭላንጭል ከፀጉር የቀጠነ፤
በምስኪኖቹ ላብ ከርሱን የሚሞላ፣
ሰቆቃ እና ስቃይ የሚመስለው ተድላ፤
በወይን ጠጅ ያይደል በግፍ የሰከረ፣
በክፋት ተሞልቶ ጢምብራው የዞረ፣
አውቆ የደደበ  ስንት ማይም አለ!
©ጌች ቀጭኑ ሰኔ 27/2009 ዓ.