Friday, November 27, 2015

ጥጡና ፈታይዋ

ባበባነት ወቅቱ
ጥጥ ነኝ ብሎ ቀርቧት
ፈታይ ሆና ቀርባው
ከስሩ ፈንቅላው
ከንቡጡ ፈልፍላው
ከ'ማረጉ አውርዳ
መሬት አስተኝታው
በፈገግታ በትር በሳቅ ማዳወሪያ
ቀኑን ሙሉ ወቅታው
በድምጧ መንደፊያ
ባ'ይኗ መዳመጫ
ከፍሬው ለይታው
ለካ እሱም ተረቶ
ሰውነቱን ትቶ
{አምኖ ጥጥነቱን}
መዳፏ ስር ገብቶ
ድድር ገላው ላልቶ
ኾኖላት ባዘቶ
በስሜት እንዝርቷ
ታብቶላት አስራው
በራቁት ጭኗ ላይ
አሽከርክራ አሹራው
ሲወፍር አቅጥናው
ሲረግብ አክርራው
ሲያሰኛት ልቃቂ
ሲያሻት ቀለም አርጋው
ለካ እሱም ተረቶ
ሰውነቱ ትቶ
ጥጥነቱን አምኖ
እንዳደረገችው እንዳሰኛት ሆኖ
መለወጡን እንኳ ሳያስብ ላንድ አፍታ
ከጥጥነት ልቆ ሆኗት ቀጭን ኩታ
ቀነቀን ለውበቷ
ማታ ለሙቀቷ
ሲሆን ሰነባብቶ
ዕድፍ እና ትቢያ ከገላዋ አንስቶ
ጸዐዳው አከሉ እያደር ጨቅይቶ
እሷ ሳትለውጥ
እሱ ነትቦ አርጅቶ
ተሽቀንጥሮ ቀረ ሆነና ቡትቶ
በሌላ ጸዐዳ ኩታ ተተክቶ
                   ስብስብ ግጥሞች
                            በውቀቱ ስዩም

Wednesday, November 25, 2015

ጽፈሽ ያዥው ይጠቅምሻል!

ላንቺ ይባልኝ እንጅ ቃልሽ ለፈረሰው፣
እኔስ እኖራለሁ እንደ ሰው እንደ ሰው። አዎ! ላንቺ ነው፤ ከገባሽ ይግባሽ አዎ! ላንቺ ነው፤ ሳምንሽ ለከዳሽኝ ድንገት የተግባባን መስሎኝ ልቤን ሰጥቸሽ ዘነጣጥለሽ ላስረከብሽኝ።ይሄው! ይሄው! እድሜ ላንቺ የተሰበረ ልቤን ጥገና ያልሄድሁበት ያልዞርሁበት ቦታ የለም።ግን መድሃኒቱ ካንቺ ዘንዳ ሆኖ ከየት አባቴ እንደማገኘው ግራው ገብቶኝ ስጨነቅ እኖር ነበር። አሁን ግን እግዚአብሔር ይመስገን ልቤ ወደ ነበረበት ተመልሷል።እንዳንቺማ ቢሆን ኖሮ ልቤን አጥቸ እየተሰቃየሁ እኖር ነበር። ግን ፈጣሪ አለሁልህ አለኝ።ታስታውሻለሽ ያኔ በፊት በፊት የሰማዩን ከዋከብት የምሽቱን ጨረቃ የቤታችን አምፖል አንቺ ሆነሽ የምበላበት ሳህን የምማርበት ደብተር ዉስጥ እየተገኘሽ ሰላሜን አሳጥተሽኝ በህልሜም እየመጣሽ እንቅልፍ ነስተሽኝ ነበር።ጨረቃም ከዋከብትም አምፖልም ሳህንም አንቺው ሆነሽብኝ ይህችን አለም ላንቺ አድርጌ ስያት ነበር።ለካ አንቺ ለዚችች አለም ኢምንት! ኢምንት! ኢምንት! ነሽ።አሁን ላይ ግን ልንገርሽ ውዴ!ጨረቃውም ጨረቃ ከዋከብቱ ከዋከብት አምፖሉም ሳህኑም ያው ራሳቸው ናቸው። ለካ ያኔ አእምሮየ ውስጥ አግዝፌ ስየሽ ስለንነበር ነው እንደዚያ ራሴን ጥየ ስሰቃይ የኖርሁት።ግን እንዴት አስቻለሽ ያን ሁሉ ስቃየን ያን ሁሉ ጭንቀቴን ያን ሁሉ ችግሬን  እየነግርሁሽ፤ ትንሽ ሰወኛ ስሜት ያልተሰማሽ ለምን ነበር? ምላሹን አልፈልገውም። ጽፈሽ ያዥው ይጠቅምሻል።የሆነው ሆኖ ለህይወቴ ትልቁን ትምህርት ሰጥተሽኛል።ተሰብራ የነበርችውን ልቤን ድጋሜ እንዳትሰበርብኝ አርቄ እንዳስቀምጣት ስለረዳሽኝ አመሰግናለሁ።በተረፈ የእጅሽን ይስጥሽ አልልሽም።ምክንያቱም የዛሬን አያርገውና በአንድ ወቅት ለህይወቴ መሰርታዊ ከሆኑት ነገሮች ማለትም ምግብ፣ መጠጥ፣ መጠልያ እና ልብስ ጋር ተደምረሽ የነበርሽ፤ ነገር ግን በራስሽ ምክንያት ራስሽን የቀነስሽ ሴት ነሽ።ስለዚህ ከልቤ ከልቤ የምመኝልሽ መልካሙን ሁሉ እንዲገጥምሽ ነው።በተረፈ ይሄን ዘፈን ላንቺ ሳይሆን ለምስኪን አፍቃሪዎች ጋበዝሁኝ።
      አፍቅሬ እያመንኩኝ ሳልጠላሽ፣
      አስችሎሽ እምነቴን ከበላሽ።
     ላንቺ መባል ይብቃኝ ከእንግዲማ፣
    ሃገር ይወቅልኝ ሁሉም ይስማ።
    ለፍቅርሽ ስጨነቅ ስጠበብ ከርሜ፣
    ለክብርሽ ስሟገት ስምሽን አንግቤ፣
    በዚያ በክፉ ቀን ሳጣሽ ካጠገቤ፣
   ፍም ይወጣኝ ነበር እንደመንገብገቤ።
                  ያንችው  አፍቃሪ

Friday, November 13, 2015

ፋኖስና ብርጭቆ

አንድ የፋኖስ መብራት በግብሩ የኮራ፤
እንዲህ ሲል ተጣላ ከብርጭቆ ጋራ፡፡
‹‹እኔ ነኝ መብራቱ ብርሃን የምሰጥ፤
ጨለማን አጥፍቼ የምገላልጥ፡፡
አንተ ግን ከፊቴ እንዲህ ተደንቅረህ፤
ዙሪያዬን ከበኸኝ እንዲያው ተገትረህ፡፡
አልገባኝም ከቶ የምትሰራው ስራ፤
ብርሃኔ ሩቅ ደርሶ ደምቆ እንዳያበራ፤
አንተን ፈጠረብኝ መንገድ የምትዘጋ፡፡
እንቅፋት እየሆንክ ስራዬን አታጥፋ ፤
ገለል በል ከፊቴ ብርሃኔ ይስፋፋ፡፡››
(ብርጭቆም ሲመልስ)
‹‹አገልግሎቴማ ከሆነብኝ ጥፋት፤
እውነት እኔ ላንተ ከሆንኩህ እንቅፋት፡፡
ልሂድልህ›› ብሎ ሲለቅለት ቦታ፤
ከጎን የነፈሰ የንፋስ ሽውታ፣
መጣና መብራቱን አጠፋው ባንዳፍታ፡፡
አጭር እየሆነ ተመልካችነቱ፣
መለየት አቅቶት ጥቅሙን ከጉዳቱ፣
እወቁኝ እወቁኝ እያለ ሲነሳ
ሰውም እንደዚሁ ያመጣል አበሳ፡፡