Sunday, November 19, 2017

ሐዋርያት

ኑሮን ለማሸነፍ ቤተሰብ ሊመሩ
ከላይ ታች ብለው ሲለፉ ሲጥሩ
በየሥራ መስኩ ከተሰማሩበት
መርጦ ቢጠራቸው ጌታ ለአገልግሎት
ቤትና ንብረቴን ወገኔንም ሳይሉ
ሁሉን ንቀው ትተው አምነው ተከተሉ
በዋለበት ውለው ባደረበት ሲያድሩ
ድንቅ ተዓምራቱን ማዳኑን   እያዩ፣
በሃይማኖት ጸንተው በእምነት ጠነከሩ
ምድራዊውን ትተው ለሰማዩ ኖሩ
ጣዕም ያጣውን ዓለም በቃሉ ለወጡ
እነሱ ጨው ሆነው ሁሉን አጣፈጡ
ምንጭ፦ሐመር ዘኦርቶዶሽ ተዋህዶ
            መስከረም 2009 .

Friday, November 03, 2017

እርቅ ለምኔ

አባቴን በክላሽ እናቴን በርግጫ፣
ወንድሜን በሽጉጥ እህቴን በጡጫ፣
ሲወቃ እያየሁት
ከደጃፌ ጥሎ የበቀል አውድማ፣
በሬየን ቅርጫ አርጎ ሚስቴንም ውሽማ፤
በእናቴ የወጣሁ ሴት መሆኔን አውቆ፣
በወገኖቼ ደም እጁ ተጨማልቆ፤
ህልሙ ሲሞላለት የቅዠቱ ገንቦ፣
ታረቀኝ ይለኛል ዓይኑን በጨው አጥቦ፤
ክንዴን ሳልንተራስ ሳይዝግ ምኒሽሬ፣
መቃብር ሳልወርድ እጅ እግሬን ታስሬ፤
ደመላሽነቴ ሳይታወቅ በዓለም፣
እርቀ ሰላም ብሎ ፍልስፍና የለም።
የወንድሜን ገዳይ ቅንድቡን ሳልመታ፣
የምን ድርድር ነው የምንስ ይቅርታ?

  ©ጌች ቀጭኑ