Saturday, July 23, 2016

አበጀ በለው(2)

የእግዚአብሔር ዳኝነት የእግዚአብሔር እውነት፣
የሚጠበቅበት የድሆቹ መብት፣
እጅና እግሩን ታስሮ በግፍ ሰንሰለት፣
ያለ አንድ ጠበቃ ያለ አንድ ረዳት፣
ፍርድ ለመቀበል ቀርቦ ፍርድ ቤት፣
በቀማኞችና በሌቦች ችሎት፣
ይሙት በቃ ብለው ሁሉም በአንድነት፣
የአመፅ ፍርድ ፈርደው ገድለው ሲቀብሩት፤
ይህን ግፍ አዬና አበጀም አስተውሎ፣
በጦር እንደወጉት ልቡ ባዘን ቆስሎ፣
መንፈሱ በቁጣ እንደ እሣት ተቃጥሎ፣
የእውነትን ደመኞች ለመበቀል ብሎ፣
ወረደ በረሃ ቤት ንብረቱን ጥሎ።
ዳኞች ዳኝነትን ከቀበሩት ገድለው፣
የእግዜርን አደራ እምነቱን አጉድለው፣
የሰጠናቸውን ስልጣን ተከልለው፣
እኛኑ ሲያጠቁን ጠባቂዎች መስለው፣
መቀማት ሲመርጡ  መጠበቁን ጥለው፣
ካሾች እኛ ስንሆን እነሱ በድለው፣
አርደው ሲጨርሱን አንድ በአንድ አናጥለው፣
እንደ ቧዘዘ ከብት ጠባቂ እንደሌለው፣
ለመብት ሲከላከል ሊሞት እንደማለው፣
እንደ ቆራጡ ወንድ እንደ አበጀ በለው፣
እኛስ ለመብታችን የማንታገለው ፣
ከጅልነት በቀር ምን ምክንያት አለው?
የመበታችን ፋና የአርነትን ጮራ፣
የሚለይበትን ሰው ከእንስሳ ተራ ፣
ከፍ አድርጎ ይዞ ሲሄድ እያበራ፣
በነሴ በረሃ በጎንቻ ተራራ፣
ግፈኞች ከበውት ከቀኝ ከግራ፣
ቀን ከሌት ሲያድኑት ወንጀል እንደ ሰራ፣
ለምቾቱ አያስብ ለህይወቱ አይፈራ፣
እንደ አምላክ ስለሰው ሲቀበል መከራ፣
መሄዳችን ላይቀር ነገ ስንጠራ፣
ወደ ማንቀርበት ወደ ሙታን ስፍራ፣
የበሉትን ቀጥቶ የጊዜን አደራ፣
የማይቀረውን ሞት መሞት ከእርሱ ጋራ፣
የሚያጸድቅ ነበር ወዲያው የሚያኮራ።

ምንጭ፦ፍቅር እስከ መቃብር 

Friday, July 08, 2016

ለጽጌረዳ (Y.F)

ሰላምና ጤና ደስታና ፍቅር ምን ጊዜም ቢሆን ካንቺ አይለዩ። የሰው ልጅ እስካሁን ድረስ  አንዱ ለሌላው ያለውን እውነተኛ ፍቅር ለመግለፅ ያልተጠቀመባቸው ቃላት ይኖራሉ ብየ አላስብም። ምርጥ፣ ወርቃማ፣ እንቁ የሆኑ ቃላትም ቢሆኑ ላንቺ ያለኝን ፍቅር በትክክልና ሙሉ በሙሉ የመግለፅ  አቅም የላቸውም። የፍቅር ታላቅነት ከምንምና ከማንም በላይ ነውና ፍቅር ከኃይሎች ሁሉ የሚበልጥ ኃያል ነውና። ፍቅር እውነት ነው፤እውነትም ፍቅር ነው፤ የሁለቱ ድምር ደግሞ አንቺው ነሽ። ላንቺ ያለኝን እውነተኛ ፍቅርና መልካም ምኞት መግለጫ አጥቼ ፈዝዤ ተቀምጬ መውደዴን ማፍቅሬን ለመግለፅ ወኔ ቢጠፋኝ ጉልበት ቢከዳኝ ፍቅርሽ ቢብስብኝ መንገድ ፈለጌ ማፍቀሬ እንዲገባሽ የተቻለኝን ሁሉ ለማድረግ ሞከርኩ። ነገር ግን ፍቅሬን ለመግለፅ የተጠቀምኩባቸው መንገዶች አላማቸውን መፈፀም ተሳናቸው። ፍቅሬን ከመግለፅ በተቃራኒው የጥላቻሽ አጋፋሪ ሆነው ተገኙ። 

የማወራሽ ተረት ተረት ወይም ልብ ወለድ አይደለም። ከአንጎለ ገቢር አፍልቄ፣ ላለፉት አራት ዓመታት በውስጤ ታምቆ ከኖረው የፍቅርሽ ወላፈን ጨምቄ፣ ከልቤ መዝገብ ፈልቅቄ፣ ያወጣሁት  ህያው እውነት ነው እንጅ። እኔ ላንቺ ያለኝን ፍቅር በምንና እንዴት አድርጌ ላስረዳሽ እንደምችል ባላውቅም ውሎየም አዳሬም  አንቺ ብቻ ስትሆኝብኝ ጭንቅ ጥብብ ሲለኝ ማደረገውን ሳጣ ይኸው ዛሬም ከዕድሜሽ ላይ ሁለት ወይም ሦስ ደቂቃ  ልወስድብሽ ጨከንኩ። መቼም ይህንን እንደማትነፍጊኝ ተስፋ አደርጋለሁ። እኔ እንኳን ከሃብት ሁሉ የምትበልጠውንና ማንም በገንዘብ ይገዛት ዘንድ የማይቻለውን ንጹህ ልቤን ሰጥቸሽ  አይደል? አንቺ ስጦታዬን ለመቀበል ፈቃደኛ ባትሆኝም ቅሉ። ሙሉ ማንነቴን ላንቺ ሰጥቼ ይኸው አራት ዓመት ሙሉ ተሰቃየሁልሽ እኮ። ለነገሩ ሰው የቤቱን ሀብት ሁሉ ስለፍቅር ቢሰጥ ያከብሩታል እንጅ በፍፁም አይንቁትም። ፍቅር ከሞት የበረታች ናትና፤ ቅንዐትም እንደ ሲኦል የጨከነች ናትና፤ ላንቃዋም እንደ እሣት ላንቃ እንደ ነበልባልም ነውና። 

Tuesday, July 05, 2016

የተቆለፈበት ቁልፍ!


ጫት፦ በእርግጥም ካለመስራት እኩል በትክክል አለመዝናናትና አለማረፍም የሰውን ጭንቅላት ምን ያክል እንደሚጎዳ  ብዙ ሰው ልብ የሚል አይመስልም።በመቃም ወይም ዘወትር በመጠጣት ለመዝናናት መሞከር ለአእምሮ ጤናን ሳይሆን ጫናን የሚፈጥር ሱስ እንደሚሆን ግልጽ ነው።ለምሳሌ ጫት  የሰውን አእምሮ አሰራር ሊያውኩና ሱስንም ሊፈጥሩ የሚችሉ ኬሚካሎች የያዘ ቅጠል ነው ።ካቲኖንና ካቲኖል የሚባሉ ንጥረ ነገሮችን  የሰውን ስሜትና መነሳሳት ከፍ በማድረግ ምርቃናን በመፍጠር በሱስ ከጠመዱ በኋላ ቃሚውን ካላገኘ መንቀሳቀስ የማይችል ትጥገኛ ማሽን ያደርገዋል።በሃራራና ምርቃና መካከልም እየዋዠቀ ቆይቶ በመጨረሻ ፍጻሜው ውድ የሆነ አዕምሮው ከጥቅም ውጭ ወደመሆን  ሲመጣ የጀዝባነትን ጎራ ይቀላልቀላል።ከዚህ በተጨማሪ በጫት የተፈጠረውን ምርቃና ለማገዝ ማጨስ የተልለመደ ሲሆን ያንን የናረ ስሜት ላምርገብ ደግሞ መጠጥ የግድ ይላል።ሌሎች መጠጥ የማያዘወትሩ ሰዎች ደግሞ የእንቅልፍ ክኒን አይነት መድሃኒቶች ሱስ ሳያስቡት ከጫቱ ጋር በተጣማጅ ይጠናወታቸዋል።ይሄ እንግዲህ በጥርስ፣ በጨጓራና በኪስ የሚፈጥረው በሽታ ሳይቆጠር መሆኑ ነው።

ሰዎች በሚቅሙበት ጊዜም የጊዜ ባቡር አፈጣጥኑ ስለሚቀየር በብዛት የሚቅሙ ሰዎች በዕድሚያቸው ላይ ቁሟር መጫወታቸው አይቀርም።እንኳን በጫት ታግዞ እንዲሁም ባህላችን የጊዜ ጸር ነው።በአንድ ወቅት በጥቂት የሃገሪቱ ክፍሎች ብቻ  ከሃይማኖታዊና ባህላዊ ወግ ጋር  ተመጥኖ ላገልግሎት ይውል የነበረው ጫት ዛሬ ከጥቂት የሃገሪቱ ክፍሎች በቀር ከዳር እስከዳር አካሎ ማየቱ አሳዛኝም አስፈሪም ነው።ከናዝሬት እስከ አዲስ አበባ ባለውም አስፋልት ዙሪያ ዘመናዊ ቃሚዎች መኪናቸውን ደርድረው እየቦዘኑ ሲዝናኑ ማየት ችግሩን ገና ፋሽን እንጂ ፍርሃርት እንዳልፈጠረ ያሳያል።ከባለስልጣን እስከ ነጋዴ ፣ ከምሁር እስከ ስራ አጥ፣ወንድና ሴት ሳይል በጫት አባዜ ተይዘው አለመቃም የሚያሳፍረበትና እንደሞኝ የሚያስቆጥርበት ጊዜ ላይ መድረሳችን ነበር ማሳፈር ያለበት።ቡናን የሚቀናቀን የውጭ ምንዛሬ አምጭ ተክል መሆኑ ከኮሎምቢያ ኮኬይንና ከ አፍጋኒስታን ሄሮይን የኛንስ ጫት ሕጋዊ ከመሆኑ በቀር ምን ይለየዋል?