Sunday, January 22, 2017

የክርስቶስ ነገር

“የክርስቶስ ነገር እጅግ አስቸገረ። ልጅ ስለሆነ ይሆን? አንድ ጊዜ ተርቤ አላበላችሁኝም ይላል። አንድ ጊዜ አምስት እንጀራ ለአምስት ሺህ ሰው አብልቶ አትርፎ ያስነሳል። ሌላ ጊዜ ደግሞ ገንዘባችሁን እየሰበሰባችሁ ወደ ሰማይ ላኩ እዚያ ይቆያችኋልና ይለናል። ለካ የእርሱ ገንዘብ አልበቃው ቢል ወደኛ ልጁን የላከ ቀስ ብሎ ገንዘባችንን በብልሃት እንዲያከማች ኖሯል። እንግዲህ አወቅንበት ገንዘባችንንም አናባክንም። ከሰማይስ እኛ ምን አለን? ገነዘባችንን አሸክመን ወደ ዚያ ከምንልክ አንካሶችን እውሮችን ችጋረኞችን ወንድሞቻችን ይዘን እንክት እያደረግነ እንበላዋለን።በገንዛ ገንዘባችን ምን ይመጣብናል። አላመጣችሁም ብሎ የሚያደርገውን እስኪ እናያለን።”
(መጽሓፈ ጨዋታ ሥጋዊ ወመንፈሳዊ) መልካም ዕለተ ሰንበት!!!

Friday, January 06, 2017

የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት

የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች፣ የወላዲተ አምላክ የቅድስት ድንግል ማርያም ወዳጆች ሁላችሁም እንኳን ለብርሃነ ልደቱ አደረሳችሁ። ልዑል እግዚአብሔር ፈጣሪያችን የባሕርይ አምላክ ሲሆን በፍጥረቱ የማይጨክን ርኅሩኅ ነውና ሊያድነን ስለፈቀደ ፍጹም ሰው ሆኖ ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዷልና ዛሬ የልደቱን በዓል ለምናከብርባት ዕለት እንኳን አደረሳችሁ። ሱባኤ ከተቆጠረ፣ትንቢት ከተነገረ በኋላ ማለትም ቅዱሳን ነቢያት ይመጣል፣ከቅድስት ድንግል ማርያም ይወለዳል ብለው ተናግረው ከጨረሱ በኋላ መልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ቅድስት ድንግል ማርያምን አምላክ ከአንቺ ይወለዳል ብሎ አበሰራትና ጊዜው ሲደርስ ማለትም 5500 ዘመን ሲፈጸም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተልሔም በተባለው  ቦታ ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወለደ።ኲነኔ፣ፍዳ፣መርገም፣ኀዘንና ኃጢአት ሁሉ ተደመሰሰ ። አንድነት ፣ ስምምነት፣ርኅራኄ፣ሰላምና ፍቅር ሰፈነ። ስለዚህም ዛሬ የምናከብረው ይህንን ታላቅ ዕለት የጌታችንን ልደት ነው። ልደት፦ትርጉሙ ከማኅጸን መወለድ ፣ከእናት ሆድ ወደ ብርሃን መውጣት፣መገኘት፣ተገልጾ መታየት ማለት ነው።         


በአንቀጸ ሃይማኖት ውስጥ “ፈጽሞ ሰው ሆነ” ሲባል በመጀመሪያ በጽንሰቱ በኋላም በልደቱ አምላክ ወልደ አምላክ በሥጋ መገለጡን ያመለክታል። በድንግል ማኅጸን ሳለ ጥቂት ቅዱሳን ብቻ ያውቁት ነበር፤ ከልደቱ በኋላ ግን ለዓለም ሁሉ ተገለጠ። ሕዝብም አሕዛብም የሚያዩት የሚዳስሱት ሰውነት ያለው ሆኖ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ እንደ ሰው ተገልጧል ። የአሁን አመጣጡ በስጋ በመገለጥ ነው፤ የቀድሞው አመጣጡ ግን በመለኮታዊ እሳት አምሳል ስለነበር ማንም ሊቀርበው አይችልም ነበር። ያን ጊዜ የእግዚአብሔር መገለጥ በሚታይ በነበልባል ውስጥ ነበር። በእሾህ ቁጥቋጦ መካከል በሚነደው እሳት የተገለጠው አምላክ ለሙሴ ብቻ ነበር። ወደ ተቀደሰውም ቦታ ጫማውን አውልቆ እንዲቀርብ ለሙሴ ተነግሮት፣እርሱም በፍርሃትና በመደነቅ ለምለሙ ቁጥቋጦና ነበልባሉ ተዋሕደው ወደሚታዩበት ኅብረ ትርእይት ተጠግቶ የአምላክን መገለጥ አይቶ የዘላለም ስሙም “ ያለና የሚኖር” እርሱ የአብርሃም የይስሐቅና የያዕቆብ አምላክ እንደሆነ ለማወቅ በቅቷል ዘጻ 3፥1-15 ይህ የብሉይ ኪዳን መገለጥ ነበር።

Wednesday, January 04, 2017

ገና በጎዳና

ሁለት የጎዳና ልጆች የገና ዋዜማ አመሻሽ ላይ፣ ጎዳና ዳር ቁጭ ብለው አላፊ አግዳሚው ለዓመት በዓል ሲራወጥ ያያሉ፡፡ ዶሮ ያንጠለጠለ በግ የሚጎትት፣ ቄጤማ የቋጠረ፣ በሬ የሚነዳ፣ እህል ያሸከመ፣ ‹የገና ዛፍ› የተሸከመ፣ አብረቅራቂ መብራት የጠቀለለ፣ ዋዜማ ሊቆም ወደ ቤተ ክርስቲያን ነጭ ለብሶ የሚጓዝ፣ ምሽቱን በዳንስ ሊያሳልፍ ሽክ ብሎ ወደ ጭፈራ ቤት የሚጣደፍ፣ ብቻ ምኑ ቅጡ፣ ከተማዋ ቀውጢ ሆናለች፡፡ እነርሱ ደግሞ የተበጫጨቀች ልብስ ለብሰው፣ የደረቀ ዳቦ ይዘው፣ በቢል ቦርድ ላይ የተለጠፈውን የጥሬ ሥጋ ሥዕል እያዩ፣ መጣሁ መጣሁ የሚለው የገና ብርድ እያቆራመዳቸው፣ የቆሸሸ ሰውነታቸውን እየፎከቱ፣ የቀመለ ፀጉራቸውን እያከኩ፣ በታኅሣሥ 15ና በታኅሥ 29 መካከል ያለው ልዩነት ጠፍቷቸው፣ የበግ ድምጽ እንጂ ሥጋው ርቋቸው፣ የበሬው ፎቶ እንጂ ሥጋው ጠፍቶባቸው፣ ያገኙትን ወረቀት እያነደዱ ጎዳናው ዳር ተቀምጠዋል፡፡

‹‹ቆይ ግን ገና ምንድን ነው?›› አለ አንደኛው ሰውነቱን እየፎከተ፡፡ ‹‹የክርስቶስ ልደት ነዋ፤ በማይክራፎን ሲሰብኩ የሰማሁት እንደዚያ ነው›› ‹‹የት፣ መቼ፣ ለምን ተወለደ?›› ‹‹እነርሱ የሚሉት ቤተልሔም በምትባል ከተማ፣ በእኩለ ሌሊት፣ በብርድ ወቅት፣ ራቁቱን፣ እናቱ በከተማዋ ማደሪያ የሚሰጣት አጥታ፣ በተናቀው ቦታ በከብቶች በረት ውስጥ ተወለደ፡፡ በጣም ስለበረደውና ራቁቱን ስለነበር ከብቶቹ በትንፋሻቸው አሞቁት፤ ሌላ ሰው ስላልነበረ እረኞቹ መጥተው ዘመሩለት፡፡ እንዲህ ነው የሰማሁት፡፡›› ‹‹እኛምኮ እንደርሱ የሚያስጠጋን አጥተን ነው ጎዳና የወደቅነው፡፡ እንደርሱ ራቁታችንን ነን፤ እንደርሱ የሚበላ የለንም፤ እንደርሱ እኛንም የሚያሞቁን እነዚህ ውሾች ናቸው፤ እንደርሱ እኛም በተናቀው ቦታ ላይ ነን›› አለ ሁለተኛው ልጅ ውሻውን እየደባበሰ፡፡ ‹‹የሚገርምህ ነገር ጌታ የተወለደው በከብቶች በረት ዋሻ ውስጥ ነው፡፡ ያኔ ጥድ የለም፤ በረት እንጂ፡፡ ጌታኮ ጫካ ውስጥ አልተወለደም፡፡ ያኔ ከረሜላ የለም፤ ያኔ ጥጥ የለም፣ ያኔ ፖስት ካርድ የለም፣ የሰብአ ሰገል ወርቅ፣ ዕጣንና ከርቤ እንጂ፡፡ አሁን ይኼን ሁለ ከየት እንዳመጡት እንጃ፡፡ ይልቅስ ራቁታችንን ሆነን፣ የሚበላ ናፍቆን፣ በእንግዶች ማረፊያ ሥፍራ የሚሰጠን አጥተን፣ ከእንስሳት ጋር ተኝተን እኛ አለንላቸው፡፡