Wednesday, November 16, 2016

ፍቅር፣ወጣትነትና መንፈሳዊነት

ብዙ ወጣቶች በጋራ የሚያውቋቸው ዘወተር የሚነጋገሩባቸው ሕይወታቸውን እስከመለወጥ የሚደርሱባቸው ብዙ ነገሮች አሉ። ከእንዚህ ነገሮች መካከል ከተቃራኒ ጾታ ጋር ያላቸው ግንኙነት አንዱ ነው ።ይህ በእድሚያቸውና በተፈጥሮአዊ ለውጣቸው ምክንያት የሚመጣ ጠባይ በመሆኑ ወጣቶቹ መንፈሳውያን ሆኑም አልሆኑ የዚህ ነገር ተጋሪዎች ናቸው ።ለአቅመ ሔዋንና ለአቅመ ዓዳም ከደረሱበት ጊዜ አንስቶ አስተሳስባቸውና አመለካከታቸው ፣በትምህርት ቤትም ሆነ በሥራ ከሚያገኟቸው በጾታ ተቃራኒዎቻቸው ከሆኑት ጋር ያላቸው ጉድኝት እንደ ሕፃንነቱ ወቅት አይሆንም ።ራሳቸውን ይመረምራሉ።እነርሱ ስላልደረሱበት ነገር ለማወቅ ያላቸው ጉጉት ይጨምራል።በሚያነቧቸው መጽሔቶች፣ ጋዜጦች፣ መጽሐፍት፤በሚመለከቷቸው ፊልሞችና ድራማዎች በየመንገዶች ከሚያዩዋቸው ነገሮች በመነሳት እነርሱም ያንን የሚያደርጉበትን ቀን ይናፍቃሉ ።ይህ ናፍቆትና ፍላጎትም ያድግና በተግባር ይተረጎማል።በዚህም መክን ያት የብዙ ወጣቶች ሕይዎት ሊበላሽ ይችላል።

በሃገራችንም ሆነ በየሰንበት ትምህርት ቤቶቻችን ወጣቶች ከተቃራኒዎች ጋር ሊኖራቸው ስለሚገባው ግንኙነት ለማወቅ የሚችሉባቸው አጋጣሚዎች ብዙ የሉም።በግልፅ ሊያውቋቸው የሚገቡ  ነገሮች በነውርነት ተሸፍነው ስለሚታለፉ ኋላ ለወጣቶቹ ሕይወት እንቅፋት ይሆናሉ።እስከ ጋብቻቸው እለት ድረስ ራሳቸውን ጠብቀው ለመቆየት ፣ከጋብቻ በፊት በሚፈጸሙ ግንኝነቶች ላለመሰናከል ማወቅ የሚገቧቸውን ቁምነግሮች ባለመረዳታቸው ይጎዳሉ።አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ከሆነ ብዙ ወጣቶች ቅድመ ጋብቻ በሚፈጠሩ የግብረ ሥጋ ግንኝነቶች የሚመላለሱ ናቸው ።በዚህም ምክንያት የሚከሰቱ የተለያዩ እክሎች አሉ።በበሽታ መጠቃት፣የላጊዜና ያለ ዕድሜ ማርገዝ፣ያለጊዜ የተረገዘውን ጽንስ ማሰወረድ ፣ለማስወረድ በሚደረግ ሙከራም ሕይወትን ማጣት፣ከትምህርትና ከሥራ መስተጓጎል፤ከዚህ ሁሉ ነገር በኋላም በመነፈስ ጭንቀት መሰቃየት የጥፋተኝነት ስሜት መሰማት፣ወዘተ...  ሊጠቀሱ የሚችሉ ነገሮች ናቸው።