Sunday, October 23, 2016

ሦስት ዓመት ከመንፈቅ

ይህ ዘመን እመቤታችን ከኢየሩሳሌም ውጪ የኖረችበት ዘመን ነው ፤ጌታ በተወለደ በሁለት ዓመቱ ሰብአ ሰገል በመጡበት ወራት ከሄሮድስ ቁጣ የተነሳ ድንግል ከነ ልጇ በከተማ መቀመጥ አልቻለችም።ሰይጣን የሰው ልጆችን የመዳን ስራ ሲጀምር ሲመለከት ዝም አላለም፤ገና ይወርዳል፣ይወለዳል፣ሲባል ትንቢቱን  በመስማቱ እነ ኢሳይያስን  በመጋዝ አስተርትሮ ፣በኩላብ አሰቅሎ አስገድሎ ነበር። ሲወለድም የተወለደውን ሕጻን ማሳደድ ጀመረ። በተለይም ሊወለድ ሃያ አምስት ቀን ሲቀረው  መላእክት የሚወለድበትን ስፍራ ቤተልሔምን ተገተው ይጠብቁ ነበርና አጋንንት በጣኦታት አድረው መመለክ ስለተሳናቸው ጣኦታቱም ወድቀው ወድቀው በማለቃቸው ይህንን ምልክት አድርጎ ዲያብሎስ አዳኝነቱን ጀመረ።

የአባቶቻችን አዳኝ እርሱ በእመ አምላክም ላይ ከሰው እስከ አጋንንት የክፋት ሰራዊቶችን አስከትሎ ለሰልፍ ተነሳ ። አስቀድሞ በመጽሐፍ ለዚች ቀን የተነገረው የመጀመሪያው ትንቢታዊ ቃል በዚህ ጊዜ ተፈጸመ። "በአንቺና በሴቲቱ በካከል በዘርሽና በዘሯም ላይ ጠላትነትን አደርጋለሁ" ይህ ቃል በገነት ውስጥ ከተነገሩ የወደፊት የሰው ህይወት ጠቋሚ ቃላት አንዱ ሲሆን እመቤታችንና "የቀደመው እባብ" ተብሎ በሚጠራው ጥንተ ጠላታችን በሰራዊተ አጋንንት እና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መካከል የሚደርገውን ጦርነት የሚያመላክት ቃል ነው ።

Thursday, October 06, 2016

ጾመ ጽጌ

ጽጌ ጾም በቤተክርስቲያናችን ከመስከረም 26 እስከ ህዳር 5 ያሉ አርባ ቀናት ዘመነ ጽጌ (ወርሃ ጽጌ) እንደሚባሉ ይታወቃል። የቤተክርስቲያናችን የሥርዓት መድብል የሆነው ፍትሐ ነገስት ጾምን እንዲህ ይተረጉመዋል ። “ጾምስ በታወቀው ዕለት ፣በታወቀው ሰዓት ሰው ከምግብ የሚከለከለው መከልከል ነው። ይህም ኃጢአቱን ለማስተስረይ ዋጋውን ለማብዛት እርሱ ወዶ ህግን ለሰራለት  እየታዘዘ፤ የፈቲውን ኃይል ያደክም ዘንድ፤ ሥጋም ለነባቢት ነፍሥ ትታዘዝ ዘንድ ነው” /ፍት.ነገ.ፍት.መን.አንቀጽ 15፥564/። 

ጾም ከመንፈሳዊ ተጋድሎዎች አንዱ ነው። ለፈቃደ ሥጋም  መንፈሳዊ ልጓም ነው። ሰው ፈቃደ  ሥጋን እየገታ ነፍሱን  የሚያለመልምበት ስንቅ ነው። “ጾም ቁስለ ነፍስን የምፈውስ ፣ ኃይለ  ፍተዎትንም የምታደክም ፣ የበጎ ምግባራት ሁሉ መጀመሪያ ፣ጸጋ እግዚአብሔርን የምታሰጥ፣የጽሙዳን ክብራቸው ፣የድንግልና የንጽሕና ጌጣቸው መገለጫቸው ፣የጸሎት ምክንያት/እናት/ የእንባ መገኛ ምንጭ፣አርምሞን የምታስተምር፣ለበጎ ሥራ ሁሉ የምታነቃቃ ፣ሰውነትን በእግዚአብሔር ፊት በማዋረድ ትኅትናን ገንዘብ ለማድረግ የምትረዳ መድኃኒተ ነፍስ ናት።/ማር ይስሐቅ አንቀጽ 4 ምዕራፍ 6/

የጾም ዓይነቶች 
ጾም በዓይነቱ በሁለት ሊከፈል ይችላል:የአዋጅና የግል። የአዋጅ ጾም በይፋ ለህዝቡ ተነግሮ በአንድነት የሚጾም የትዕዛዝና የህግ ጾም ነው። በሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት መሰረት ሁሉም እንዲጾማቸው መጀመሪያቸውና መጨረሻቸው ተቀምሮ፣ጊዜና ወቅት ተወስኖላቸው የተደነገጉ ሰባት የአዋጅ/የሕግ/ ዓጽዋማት አሉ። እነዚህም ዐብይ ጾም /ጾመ ዐርባ /፣ ጾመ ሐዋርያት /የሰኔ ጾም/፣ ጾመ ፍልሰታ /ጾመ ማርያም/፣ ጾመ ነቢያት/የገና ጾም/፣ጾመ ድራረ ጥምቀት /ገሃድ ወይም ጋድ/፣ ጾመ ሰብአ ነነዌ፣ ጾመ ድኅነት/የረቡዕና ዓርብ ጾም/ ናቸው። ጾም እንዲህ ወራት ተወስኖለት በቁጥር የተወሰነ  በጊዜ የተገደበ ይሁን እንጂ የዘለዓለም ህይወትን ለመውረስ የሚረዳን የጽድቅ መሰረት ፣የገነት በር፣ በአጠቃላይ  የክርስቲያኖች ኑሮ  ስለሆነ ከተዘረዘሩት የህግ አጽዋማት በላይ ከዓመት እስከ ዓመት የሚጾሙ በገዳም ፣በበረሃ ያሉ መነኩሳትና ባሕታውያን አሉ። “ስለ ጽድቅ የሚራቡና የሚጠሙም ብጹዓን ናቸው ፤እነርሱ ይጠግባሉና  እዳለ ።/ማቴ 5፥6፣ኢሳ 41፥55/።