Thursday, October 06, 2016

ጾመ ጽጌ

ጽጌ ጾም በቤተክርስቲያናችን ከመስከረም 26 እስከ ህዳር 5 ያሉ አርባ ቀናት ዘመነ ጽጌ (ወርሃ ጽጌ) እንደሚባሉ ይታወቃል። የቤተክርስቲያናችን የሥርዓት መድብል የሆነው ፍትሐ ነገስት ጾምን እንዲህ ይተረጉመዋል ። “ጾምስ በታወቀው ዕለት ፣በታወቀው ሰዓት ሰው ከምግብ የሚከለከለው መከልከል ነው። ይህም ኃጢአቱን ለማስተስረይ ዋጋውን ለማብዛት እርሱ ወዶ ህግን ለሰራለት  እየታዘዘ፤ የፈቲውን ኃይል ያደክም ዘንድ፤ ሥጋም ለነባቢት ነፍሥ ትታዘዝ ዘንድ ነው” /ፍት.ነገ.ፍት.መን.አንቀጽ 15፥564/። 

ጾም ከመንፈሳዊ ተጋድሎዎች አንዱ ነው። ለፈቃደ ሥጋም  መንፈሳዊ ልጓም ነው። ሰው ፈቃደ  ሥጋን እየገታ ነፍሱን  የሚያለመልምበት ስንቅ ነው። “ጾም ቁስለ ነፍስን የምፈውስ ፣ ኃይለ  ፍተዎትንም የምታደክም ፣ የበጎ ምግባራት ሁሉ መጀመሪያ ፣ጸጋ እግዚአብሔርን የምታሰጥ፣የጽሙዳን ክብራቸው ፣የድንግልና የንጽሕና ጌጣቸው መገለጫቸው ፣የጸሎት ምክንያት/እናት/ የእንባ መገኛ ምንጭ፣አርምሞን የምታስተምር፣ለበጎ ሥራ ሁሉ የምታነቃቃ ፣ሰውነትን በእግዚአብሔር ፊት በማዋረድ ትኅትናን ገንዘብ ለማድረግ የምትረዳ መድኃኒተ ነፍስ ናት።/ማር ይስሐቅ አንቀጽ 4 ምዕራፍ 6/

የጾም ዓይነቶች 
ጾም በዓይነቱ በሁለት ሊከፈል ይችላል:የአዋጅና የግል። የአዋጅ ጾም በይፋ ለህዝቡ ተነግሮ በአንድነት የሚጾም የትዕዛዝና የህግ ጾም ነው። በሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት መሰረት ሁሉም እንዲጾማቸው መጀመሪያቸውና መጨረሻቸው ተቀምሮ፣ጊዜና ወቅት ተወስኖላቸው የተደነገጉ ሰባት የአዋጅ/የሕግ/ ዓጽዋማት አሉ። እነዚህም ዐብይ ጾም /ጾመ ዐርባ /፣ ጾመ ሐዋርያት /የሰኔ ጾም/፣ ጾመ ፍልሰታ /ጾመ ማርያም/፣ ጾመ ነቢያት/የገና ጾም/፣ጾመ ድራረ ጥምቀት /ገሃድ ወይም ጋድ/፣ ጾመ ሰብአ ነነዌ፣ ጾመ ድኅነት/የረቡዕና ዓርብ ጾም/ ናቸው። ጾም እንዲህ ወራት ተወስኖለት በቁጥር የተወሰነ  በጊዜ የተገደበ ይሁን እንጂ የዘለዓለም ህይወትን ለመውረስ የሚረዳን የጽድቅ መሰረት ፣የገነት በር፣ በአጠቃላይ  የክርስቲያኖች ኑሮ  ስለሆነ ከተዘረዘሩት የህግ አጽዋማት በላይ ከዓመት እስከ ዓመት የሚጾሙ በገዳም ፣በበረሃ ያሉ መነኩሳትና ባሕታውያን አሉ። “ስለ ጽድቅ የሚራቡና የሚጠሙም ብጹዓን ናቸው ፤እነርሱ ይጠግባሉና  እዳለ ።/ማቴ 5፥6፣ኢሳ 41፥55/።

አበው ቢቻላችሁስ ከዚህ አብዝታችሁ ጹሙ፤ ለድሆችም ምጽዋት ስጡ በማለት እንዳዘዙት ጾምን ቢያዘወትሩ ለስርዬተ አበሳ ፣ ሥጋን ለመጎሰምና ነፍስን በተግባር ለማሰልጠን ይመቻል። ይህም ወደ ሁለተኛው የጾም ዓይነት ማለትም ወደ የግል ጾም ይወስደናል ። የግል ጾም እግዚአብሔር ኃይሉንና ብርታቱን የሰጣቸው ምእመናን በግል/በስውር/ የሚጾሙት ነው ። አንድ ሰው ከልዑል እግዚአብሔር የሚፈልገው ነገር ሲኖር፣ ራሱን ለመግዛት ይችል ዘንድ እንዲሁም ንስሐ ገብቶ የንስሐ አባቱ ሲያዝለት በግሉ ይጾማል። ይህም ከጥንት ጀምሮ የነበረ ሥርዓት ነው። ለአብነት ያህል ሊቀ  ነቢያት ሙሴን፣ነቢዩ ዳንኤልን፣ነቢዩ ዳዊትን፣ነህምያን፣ በሐዲስኪዳን ቅዱስ ጳውሎስንና ቅዱስጴጥሮስ መጥቀስ ይቻላል። የግል ጾም የንስሐና የፈቃድ ጾም ተብሎ በሁለት ይከፈላል።

የንስሐ ጾም ምእመናን ከመምህረ ንስሐቸው ጋር ተመካክረው ንስሐ ገብተው በአንቀጸ ንስሐ መሰረት ቀኖና ሲሰጣቸው የሚጾሙት ጾም ነው። ቀኖናውን  የሚፈጽሙት ማንም ሰው ሳያውቅባቸው በስውር ይሆናል። የፈቃድ ጾም በሌላ አጠራር የትሩፋት ጾም በመባል ይታወቃል። በዝግ ወይም በማኅበር ሊፈጸም ይችላል።እግዚአብሔርን በትጋት የሚያገለግሉ ምእመናን በግል ወይም በማኅበር በገዳም የሚኖሩ አባቶች በአንድነት ስለሚከተሉት ምክንያቶችና ስለ መሰሎቻቸውም የፈቃድ ጾምን ይጾማሉ።

1) በግልና በቤተሰባዊ ህይወታቸው የገጠማቸው ችግር ካለ እንዲወገድላቸው በሚኖሩባት አገርና በቤተክርስቲያናቸው ዙሪያ ያላቸው እክል እንዲርቃቅላቸው፤
2) ክቡር ዳዊት “ነፍሴን በጾም አስመረርኳት እንዳለ  ራሳቸውን መግዛት ይችሉ ዘንድ  ፥ነፍስን በሥጋ ላይ ለማሰልጠን፤
3)  በጥቂት ሲለምኑት አብዝቶ  የሚሰጥ እግዚአብሔር ምሥጢር እንዲገልጥላቸው ፤
4) መንፈሳዊ ተግባራትን ለመፈጸም ከፈጣሪያቸው ፈቃድና እርዳታ  ለመጠየቅ፤
5)  የታሪክ ድርጊቶችን እያስታወሱ የቅዱሳንን መከራ እያሰቡ በረከታቸውን ለመሳተፍ ከኃጢአት ለመንጻት የሚሉት ናቸው።
ብዙ መነኮሳት፣ባህታውያንና ምእመናን በፈቃድ የሚጾሟቸው የታወቁ ጊዚያት አሉ። እነዚህ የጽጌ ጾም/ጾመ ጽጌ/ ና በጳጉሜን ወር የሚጾም ያሉት “ጾመ ዮዲት ” ናቸው። 

ጾመ ጽጌ ፦ከመስከረም 26 እስከ ኅዳር 5 ያለው አንድ ወር ከዐሥር ቀን ወይም 40 ቀን ወርኃ ጽጌ፣ ዘመነ ጽጌ፣ ተብሎ ይጠራል። በነዚህም ቀናት በየቤተ ክርስቲያኑ የሚነበቡ ምንባቦች፣የሚዘመሩ መዝሙሮች፣ የሚሰበከው ስብከት ፣የሚቆመው ማህሌት፣በጠቅላላው የሚነገረው ስብሐተ እግዚአብሔር ሁሉ ሰማይ በከዋከብት ምድር በጽጊያት አሸብርቀው የሚታዩ መሆናቸውን የሚገልጽ ነው። በወርኃ ጽጌ  ለሚከናወነው መንፈሳዊ አገልግሎት መነሻው “መልአኩ ህጻኑና እናቱን ወደ ግብጽ ይዘሃቸው ሽሽ፤ የህጻኑን ነፍ ሊገድሉት ይሻሉና” ሲል ለዮሴፍ በሕልሙ በነገረው መሰረት ዮሴፍም ሕጻኑንና እናቱን ድንግል ማርያምን ይዞ  ወደ  ግብፅ መሰደዱና  እመቢታችንና ሕጻኑ ሦስት ዓመት ከመንፈቅ በስደት ከኖሩ በኋላ/ራእይ 12፥16/ ወደ አገራቸው ወደ ናዝሬት የመመለሳቸው መታሰቢያ ነው።

 ይህንንም በ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተነሱ አባ ጽጌ ብርሃን “የሮማን ሽቱ የቀናንም አበባ የምትሆኝ ማርያም ሆይ ፥በረሃብ በጾም አበባ የመሰለ የመልክሽ ደም ግባት እስኪ ጠወልግ ድረስ በስደትና በለቅሶ የደረሰብሽን ችግርና ድካም መከራሽንም ሁሉ እንደ  እኅትሽ እንደ ሶሎሜ  አብሬሽ ብቀበል ምኞቴ  ነበር፤ በዚህም  ፍጻሜ የሌለውን ደስታሽን እሳተፍ ነበር ።”እንዲሁም አባ አርከ ሥሉስ በስደቷ የደረሰባትን ኀዘን ፣ልቅሶና ሰቆቃ አስመልክተው በደረሱት “ሰቆቃወ ድንግል”በሚለው ድርሰታቸው እንዲህ አሉ፦   “ፀሐይን የምትለብሽ የብርሃን ልጅ ቅድስት ድንግል ማርያም ከክፉ ከሄሮድስ ዘንድ ልጅሽን ባሸሽ ጊዜ  የደረሱብሽን ችግሮች ጨረቃን የሚጫሙ እግሮችሽ በመንገድ ብዛትና በአሸዋ ግለት እንዳጎበጎቡ ሲሰማ  ሰው ይቅርና  ድንጋዩም ባለቀሰ ነበር።”


የማኅሌተ ጽጌና የጾመ ጽጌ አጀማመር
የእመቤታችን የስደቷ መታሰቢያ ወር በቤተ ክርስቲያናችን የሚከበረው በማኅሌት፣በቅዳሴና በዝክር ነው። በወርኃ ጽጌ ባሉት ሳምንታት ከቅዳሜ ማታ እስከ እሁድ ጥዋት አበው ካህናት የሚያቀርቡት ዝማሬ ከቅዱስ ያሬድ ድጓ ፣ከማኅሌተ ጽጌና  ከሰቆቃወ ድንግል የተውጣጣና ሦስት ወገን ያለው ነው።ዝክሩም በአሁኑ ወቅት በከተሞች አካባቢ እየተረሳ ቢመጣም ፥ዘወትር እሑድ የአንድ አካባቢው ሰዎች ማዕከላዊ በሆነ ቦታ ተሰባስበው በእመቤታችን ስም ያሚዘክሩት ነው። ዐቅመ ደካሞች ድሆችና  መንገደኞች ተጠርተው በእመቤታችን ስም እንዲበሉና እንዲጠጡ ይደረጋል። ይህም ትውፊት እመቤታችን ወደ  ኢትዮጵያ በመጣች ጊዜ ኢትዮጵያውያን እናቶችና  አባቶች ያደረጉላትን መስተንግዶ ለማሰብ ነው።

የጻድቁ አቡነ ዜና ማርቆስ ዜና ገድል የጽጌን ጾም አስመልክቶ የሚከተለውንይተርካል፦“አባ ጽጌ ብርሃን የተባለው አባት እንደ መዝሙረ ዳዊት መቶ ኀምሳ አድርጎ ማኅሌተ ጽጌን ደረሰ። አባ ጽጌ ብርሃን ይህንን በደረሰበት ጊዜ የወረኢሉ ተወላጅና የደብረ ሐንታው አባ ገብረ ማርያም አማካሪው ነበር። ድርሰቱንም ሲደርስ ቤት እየመታና በአምስት ስንኝ እየከፋፈለ ነው። አባ ጽጌ ብርሃንና  አባ ገብረ ማርያም ከመስከረም26 ቀንእስከ ኅዳር 5 ቀን ማኅሌተ ጽጌን ለመቆምና የጽጌን ጾም ለመጾም በየአመቱ በደብረ  ብሥራት እየመጡ ይሰነብቱና  ቁስቋምን ውለው ወደየ በአታቸው ይመለሱ ነበር።”ከአባታችን የገድል ክፍል ለመረዳት እንደሚቻለው አባ ጽጌ ብርሃንና አባ ገብረ ማርያም የጽጌን ማኅሌት መቆም ወቅቱንም በፈቃዳቸው መጾም ጀምረዋል።ዘመኑም በ 14ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ ነው።

ከዚያ ወዲህ ግን ጥቂት በጥቂት እያለ  አብያተ  ክርስቲያናት በወርኃ ጽጌ የጽጌን ማኅሌት መቆም ጀመሩ። ጥቂት መነኩሳትና አንዳንድ ምእመናን በፈቃዳቸው ወቅቱን መጾም ጀመሩ። በዘመናችን በወርኃ ጽጌ የጽጌን ማኅሌት መቆም ስለ ተለመደ  ከማታው በሦስት ሰዓት ይደወላል። ሴት ወንዱ፥ትንሹም ትልቁም ይሰባሰባል፤ማኅሌተ ጽጌው እየተዜመ ፤አስፈላጊ የሆነው በጽናጽል በከበሮ እየተወረበና እየተሸበሸበ እስከ ጥዋቱ 12 ሰዓት ድረስ ተቁሞ ይታደራል። የጽጌ ጾም የውዴታ/የፈቃድ/እንጂ የግዴታ አይደለም። የእመቤታችን ስደት በማሰብ ከትሩፋት ወገን የሚጾም ስለሆነ  ምእመናን ሁሉ እንዲጾሙት አይገደዱም፤የሚጾመው የማይጾመውን ለምን አልጾምክም ብሎ ሊፈርድበት ስለ ራሱም እየጾምኩ ነው ብሎ መናገር አይገባውም ። የፈቃድ መሆኑንም የሚያሳየው ይኸው ነው። የማይጾመውም በልቡ ያመሰግናል፤ስደቷን እያሰበ ማኅሌቷን እየዘመረ ያሳልፋል።

ሁለተኛው የፈቃድ ጾም ጾመ ዮዲት ሲሆን በሀገራችን ምእመናን ጾመ ጳጉሜን በማለት ይጠሩታል። እንደ ጽጌ ጾም የታወቀ ባይሆንም በዓመቱ መጨረሻ ወር በጳጉሜን የሚጾም ነው። የዮዲት ጾም የሚባለውም እርሱሷ ስለ ጾመችው ነው።/ዮዲ 2፥2_7። ዮዲት ጠላቷን ለማጥፋት የቻለችው በጾምና በጸሎት ከእግዚአብሔር አምላክ ኃይል አግኝታ ነው። ስለዚህ ምእመናን ጥንተ ጠላታችን ሰይጣንና ፈቃደ ሥጋን ለማሸነፍ በጾም ከፈጣሪያችን ኃይልን መጎናጸፍ አለብን ብለው በጳጉሜን ወር ይጾማሉ። ኃጢአታቸውን ለንስሐ አባታቸው ተናግረው  ተናዘው ቀኖና ተቀብለው የሚጾሙም አሉ። በሌላ በኩል የጳጉሜን ወር ዕለተ ምጽአት የሚታሰብባት ስለሆነች ያን እያሰቡ የሚጾሙ አያሌ ናቸው። ጳጉሜን የአመታት መሸጋገሪያ እንደ ሆነች ምጽአትም ከዚህ ዓለም ወደ ወዲያኛው አለም መሸጋገሪያ  ነውና ።
ምንጭ፦ሐመር መጽሔት
ኅዳር 1996 ዓ.ም

3 comments: