Sunday, June 17, 2018

የካፊያ ምች

 ተፈሪ ዓለሙ(1974)
ሳልላክ ተልካ እንሂድ አለቺኝ
ካላጣችው ሰዓት ከቤት አስወጣችኝ
ጥርቅም እቅፍ አድርጋ በካፊያ ሳመቺኝ
የእድሜ ልክ ልክፍቱን ያኔ አስለከፈችኝ
መብረቅ እየጮኸ ዝናብ እያካፋ
የእኔ ልብ በሷ የሷ በእኔ ጠፋ
የሰማዩ ባህር ቁልቁል ተንዶብን
ውሃ ጠማኝ ውሃ እየዘነበብን
ጠፍቼ ስመለስ ከእቅፏ ስወጣ
በርዶኝ አተኮሰኝ እቤቴ ስመጣ
እያደር አደረ ከርሞ ከረመብኝ
የዘመን ህመሜን ያን እለት ታመምኩኝ
አሁን አሁን ታዲያ!
ደመናው ሲጠቁር ነጎድጓድ ሲያጓራ
ነፋስ ሲያጉረመርም ክረምቱን ሲጠራ
ግንቦት ማለቂያ ላይ ይነሳል ህመሜ
ሲያቀብጠኝ በዝናብ በካፊያ ተስሜ
..........................ምች ተሳልሜ

የኔ ግን መለከፍ

ገና ከሩቅ ሳይሽ ይድናል ህመሜ
ብሞትም አይቆጨኝ ከንፈርሽን ስሜ
ባለንጋ ጣቶችሽ የዳበስሺኝ እንደው
እንደ ቶን እሳት ነው ውስጤ የሚነደው
ዳሌሽ እየኮራ ባትሽ ላይ ሲሳለቅ
እኮሰምናለሁ እንደመታው መብረቅ
እያለ ይገጥማል እያለ ይፅፋል
መልዕቁን ዘርግቶ ቁንጅናን ይቀዝፋል
ገጣሚው ዘንድሮ በውበት ተለክፏል
የኔ ግን መለከፍ በዳሌዋ አይደለም በሚሞናደለው
በፀጉሯም አይደለም እንደ ሐር ነዶ በተዘናፈለው
አይደለም በጡቷ እንደ ሚዳቆ ልጅ ላይ ታች በሚዘለው
በጥርሷም አይደለም እንደ ፀሐይ ጮራ በሚንቀለቀለው
እኔ ቀልቤን ስቼ በድን የምሆነው
መብረቅ እንደመታው የምኮሰምነው
ጀግንነቴ ከድቶኝ ትቶኝ የሚተንነው
ኧረ አንተው ለምን አልህ? በሚል ለዛዋ ነው
Dialysis room 06/10/10
በከፊል ከሄኖክ ብርሃኑ የተሰረቀ

Monday, June 11, 2018ቃሊቲ ማረፊያ ቤቴን ሳያፈርሰው
እስረኛዬን ሁሉ ፈቶ ሳይጨርሰው
ጅምሩ አልጣመኝም ተው በሉት ይሄን ሰው
ታላቁ መሪ ¡ ከገሀነም

ጀግና ነኝ

የሚያምነኝ አይኖርም ይኸንን አውቃለሁ
ለራሴ እውነት ከሆንሁ እኔው እበቃለሁ
ሽንፈቴን አምኜ እንቅልፍ የማልተኛ
በአባቴ የወጣሁ ጀግና ነኝ ነፍጠኛ
ትምክህተኛ አትበሉኝ መመካት ያንሰኛል
የእሣት ልጅ ነበልባል መሆን ያኮራኛል
ልክ እንደ አባ ኮስትር እንደ በላይ ሁላ
ካሰብሁበት ሳልደርስ ትጥቄ የማይላላ
የግዮን መፍለቂያው ግሽ አባይ ሰከላ
ጎጃም ያበቀለኝ ዱር ቤቴ ዳንግላ
እንደ አንበሳው ቴዲ እንደ እሣቱ ረመጥ
ለሃይመኖቴ ሟች ማተቤን የማልቆርጥ
ዋሽቶ ከመሸለም ከርቸሌ የምመርጥ
የአባቶቼን ርስት ለባንዳ የማልሰጥ
እኔ ጾም እያደርሁ ለራበው የማጎርስ
ክፋት ምቀኝነት ከደጄ የማይደርስ
ብሉልኝ ጠጡልኝ የሆነ ልማዴ
ጎንደር ያሳደገኝ ወልቃይት ጠገዴ
ጀግና የጀግና ዘር አይደለሁም እንዴ?
ጌች ቀጭኑ 27/09/1ዐ

ዮርዳኖስ

ብዕርህ እረፍት ትጣ ታልቅስ ለምትሉ
እሪታ ዋይታዋን ይኸው ተቀበሉ
ለእኔ ያላት ፍቅር እጅግ ቢረታ
እናቴ ቤት ዋለች ከሰው ተለይታ
ክቡር ማህፀኗ ዮርዳኖስን ሆነ
ደማቅ ፈገግታዋ ከፊቷ ተነነ
የሞቀው ትዳሯ ቤቷ ተበተነ
ኤጭ
አቮ የምን ዋይታ
የምን እየየ ነው የምን እንጉርጉሮ
መፍትሔው ከደጃችን እያለ ከጓሮ
ይልቅ ሾፌር ንዳ ይፍጠን አንቡላንሱ
ችግር ሳይወለድ መዘዙ ሳይመጣ
በር የተዘጋበት በመስኮት ሳይወጣ
የሽንት መቋጠሪያ ሸምቀቁ ሳይላላ
የምጥ ጊዜ መርዘም ሳይፈጥር ፊሰቱላ
እናትና ልጁ ሆስፒታል ይድረሱ
15/09/10
መልካም የፊስቱላ ቀን ይባላል እንዴ?

Saturday, May 12, 2018

ያማል 3

እና እደነገርሁሽ
የረዚደንት ቁጣ አይቶ መሳቀቁ
ሲኔር መጣ አልመጣ ሰውነት ማለቁ
ፖርተር ማፈላለግ ከነርስ መዳረቁ
ዱቲ አድሮ ለሞርኒንግ ሽር ጉድ ማለቱ
X ray ማስነሳት BF ማሰራቱ
የወለደች እናት ጫማ መፈለጉ
ሞቶ የወጣን ፅንስ "alive" ማድረጉ
ያለ ዲሰፖዜብል
ቪጎ ማስተካከል ካቴተር መንቀሉ
የደሞዝ ቅናሹን አምኖ መቀበሉ
ምን ብዬ ልንገርሽ ያማል ይሄ ሁሉ
ታማሚ አስታሚ ወላጅ አስወላጁ
አጥማቂ ሰቫኪው አስቀዳሽ ሰጋጁ
የፈቃድ ባርነት በአንድነት ሲያውጁ
ጨካኝ በበዛባት በዚች የምጥ ዓለም
ከዚህ የበለጠ ሌላ ህመም የለም
ጌች ቀጭኑ ዘታችቤት 02/09/10

Tuesday, May 08, 2018

ተፈስሒ በሏት

ፀሐይን  የምትወልድ ውብ ደማቅ ጨረቃ፣
ቀድመው ያኸለሟት ቴክታና ጴጥርቃ፤
እናትና ገረድ ድንግልና ሰማይ፣
ሐመልማልና እሣት ሐርና ወርቅ ፈታይ፤
መሰረታቲሃ ውስተ አድባር  ውእቱ፣
ብሎ ያወደሳት ዳዊት በትንቢቱ፣
ተወልዳለችና የአምላክ እናቱ፣
ከበሮ ይመታ ይድመቅ ማኅሌቱ።
ጠላት ኃይሉን ይጣ ይንቀጥቀጥ ዓለሙ፣
የሕርያቆስ  ልጆች ድምፃችሁን አሰሙ፣
ተፈስሒ በሏት ካህናት አዚሙ።
ትንቢት  ተፈፅሟል ያስተጋባ ቃሉ፣
ተወልደ ብዕሲ በውስቴታ በሉ።
ጌች ቀጭኑ ዘታችቤት ግንቦት 1/2010 ዓ.