Wednesday, September 04, 2024

ፍኖተሰላም ሆስፒታልን ከልጅነቴ ጀምሮ አውቀዋለሁ።




ፍኖተሰላም ሆስፒታልን ከልጅነቴ ጀምሮ አውቀዋለሁ።

የታመመ ሰው ህክምና ለማግኘት ጥዋት 11 ሰዓት ላይ ከሆስፒታሉ ግቢ ውጭ ነበር ወረፋ የሚይዘው (ይሰለፋል)። ወይም ወረፋ ከሚይዙ ወጣቶች መግዛት ይጠበቅበታል (ከተሜ ከሆንህ ነው)።
እድለኛ ከሆነና ከውራጌወች ካመለጠ ፣ ከብዙ ስቃይ በኋላ ወደ ሆስፒታሉ ቅጥር ግቢ ውስጥ እንዲገባ ይፈቀድለታል። እድለቢስ ከሆነ ደግሞ በተረገሙ ውራጌወች ተደብድቦ ገንዘቡንና ስንቁን ይቀማል (ህክምና ሲመጣ ስንቅ ተይዞ ነበር የሚመጣው ቢያንስ ለሳምንት የሚሆን፣ ክብ ዳቦ፣ ዳቦ ቆሎ፣ በሶ)። አልያም ለቀጣይ ቀን ይቀጠራል።
ከሆስፒታሉ አጥር ውስጥ ሳይገባም ህይወቱ የሚያልፍ ብዙ ታካሚ ነበረ። ሀኪም አግኝቶ ታክሞ ከተሻለው ፣ ተንበርክኮ መሬት ስሞ ፣ አገር ይባረክ ፣ ወንዝ ይባረክ፣ አገራችን ኢትዮጽያን ይጠብቅልን፣ ገበያውን ጥጋብ ያርገው፣ በእውቀት ላይ እውቀት ደርቦ ይስጥህ ብሎ ከልቡ መርቆ ይሄዳል።
ካልተሳካ ደግሞ ወደ ባህርዳር ወይም ደብረማርቆስ ሪፈር የሚባለው ታካሚ በጣም ብዙ ነበር (ወደ ከፍተኛ ተብሏል ፣ ግልኮስ ተደርጎበታል፣ ህመሙ ሳይጠናበት አልቀረም፣ ኧረ እኔስ ፈርቻለሁ አይመለስም ፣ይባል ነበር) ።
ያን ሁሉ መከራ ግን ዛሬም አልቀረም ፣ ብዙ ነገሮች በተሻሻሉበት ዘመን ፣ ወንበር ላይ ተቀምጦ ኦክስጅን ይወስዳል፣ ፈጥኖ የመጣና እድለኛ ከሆነ ደግሞ የጎኑ ማሳረፊያ ደረቅ ወንበር ያገኛል፣ አልያም ፍሳሽ የሚወርድበት ክፍል ውስጥ የዛገ አልጋ ላይ ጣል የተደረገች ብል የበላት ፍራሽ ትሰጠዋለች።
አካባቢው የተማሩ ልጆች እያሉት፣ እያመረተና እየገበረ ምን ስላደረገ ነው ይህ ማህበረሰብ በዚህ ልክ የሚሰቃየው! ተማርን የምንል ሰዎች፣ ነጋዴዎች እና ባለስልጣናት የማህበረሰቡ ህመም ሊያመን ይገባል።
ለዚሁ ዓላማ ብቻ የተከፈተውን የ telegram group ይቀላቀሉ።
NB: "ውራጌ" ማለት በአካባቢው ዘዬ ሌባ ፣ ነጣቂ ፣ ቀማኛ፣ ዘራፊ ማለት ነው
ዶ/ር የሮም ጌታቸው የፍ/ሰላም ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር

No comments:

Post a Comment