Friday, October 30, 2015

መለየት

የለም! የለም!
መለየት መሞት አይደለም፣
ሞትም መለየትን አያክለው ፣
መለየትም ሞትን አይመስለው፣
ትርጓሜአያቸው ለየቅል ነው፣
አንቺም እኔም ጅረት ሆነን፣
ከራሳችን ምንጭ ፈልቀን፣
በራሳችን ፈለግ ፈሰን፣
ህይወት በሚሉት መቅበዝበዝ
አገር ምድሩን አዳርሰን፣
ሄደን!ሄደን! ሄደን! ሄደን!
ወርደን!ወርደን!ወርደን!ወርደን!
ሞት በሚሉት ውቅያኖስ
አንድ ስንሆን ተዋህደን
ተገናኘን እንበል እንጅ
መች ጨርሰን ተለያየን
      የለም!የለም!
መራቅ መለየት አይደለም፣
ሰው በሰወች ግዞት፣
ችግር ይዞት፣
አገር ቀየውን ጥሎ፣
ስልቻውን በጫንቃው አዝሎ፣
ቅሉን ጨርቁን አንጠልጥሎ፣
ብቻውን ሄደ ቢለው ሰፈርተኛው ተጃጅሎ፣
እርሱ በልቡ ህንጻ በማይዘመው በማይፈርሰው፣
 ከተጓዘ አኑሮ ሰው፣
እውን ይሄ መለየት ነው
የለም! የለም!
መለየት ይህ አይደለም
ትርሚያቸውን እንቀይረው፣
ላንቺ እና ለኔ ሌላ ነው፣
ከፊቴ ቁጭ ብለሽ
ከፊትሽ ቁጭ ብየ፣
ክንድሽን ካንገቴ ጥለሽ
ክንዴን ካንገትሽ ጥየ፣
የምታወሪው ሳይገባኝ
ራሴን ስነቀንቅ፣
የማወራሽ ሳይገባሽ
ለይስሙላ ጥርስሽ ሲስቅ፣
ቻው ቻው ሲለኝ ቀልብሽ፣
ደህና ሁኚ ሲልሽ አይኔ፣
መለየት ይህ ነው ለኔ።

Thursday, October 15, 2015

ልባም ሴት

      ልባም ሴትን ማን ሊያገኛት ይችላል? ዋጋዋ ከቀይ ዕንቍ እጅግ ይበልጣል።የባልዋ ልብ ይታመንባታል። ምርኮም አይጐድልበትም።ዕድሜዋን ሙሉ መልካም ታደርግለታለች፥ ክፉም አታደርግም።የበግ ጠጕርና የተልባ እግር ትፈልጋለች፥ በእጆችዋም ደስ ብሎአት ትሠራለች።እርስዋ እንደ ነጋዴ መርከብ ናት፤ ከሩቅ አገር ምግብዋን ትሰበስባለች።ገና ሌሊት ሳለ ትነሣለች ለቤትዋም ሰዎች ምግባቸውን፥ ለገረዶችዋም ተግባራቸውን ትሰጣለች።እርሻንም ተመልክታ ትገዛለች፤ ከእጅዋም ፍሬ ወይን ትተክላለች።ወገብዋን በኃይል ትታጠቃለች፥ ክንድዋንም ታበረታለች።ንግድዋ መልካም እንደ ሆነ ትመለከታለች፤ መብራትዋ በሌሊት አይጠፋም።እጅዋን ወደ አመልማሎ ትዘረጋለች፥ ጣቶችዋም እንዝርትን ይይዛሉ።እጅዋን ወደ ድሀ ትዘረጋለች፥ ወደ ችግረኛም እጅዋን ትሰድዳለች። ለቤትዋ ሰዎች ከበረዶ ብርድ የተነሣ አትፈራም፥ የቤትዋ ሰዎች ሁሉ እጥፍ ድርብ የለበሱ ናቸውና።ለራስዋም ግብረ መርፌ ስጋጃ ትሠራለች ጥሩ በፍታና ቀይ ግምጃ ትለብሳለች።ባልዋ በአገር ሽማግሌዎች መካከል በሸንጎ በተቀመጠ ጊዜ በበር የታወቀ ይሆናል። የበፍታ ቀሚስ እየሠራች ትሸጣለች፥ ለነጋዴም ድግ ትሸጣለች። ብርታትና ከበሬታ ልብስዋ ነው፤ በኋላም ዘመን ላይ ትስቃለች። አፍዋን በጥበብ ትከፍታለች፤ የርኅራኄም ሕግ በምላስዋ አለ። የቤትዋንም ሰዎች አካሄድ በደኅና ትመለከታለች፥ የሀኬትንም እንጀራ አትበላም። ልጆችዋ ይነሣሉ፥ ምስጋናዋንም ይናገራሉ፤ ባልዋ ደግሞ እንዲህ ብሎ ያመሰግናታል። መልካም ያደረጉ ብዙ ሴቶች አሉ፥ አንቺ ግን ከሁሉ ትበልጫለሽ። ውበት ሐሰት ነው፥ ደም ግባትም ከንቱ ነው፤ እግዚአብሔርን የምትፈራ ሴት ግን እርስዋ ትመሰገናለች።መ/ምሳሌ 31:10-31