Monday, December 28, 2015

አበጀ በለው(1)

ፀሐይ አያጠቁረው ውርጭ አያከስለው፣
ራብ አያከሳው ጥም አያዝለው፣
ድካም አይሰማው እንቅልፍ አይጥለው  ፣
ጎራዴ አያቆስለው ጥይት አይገድለው፣
ስጋ እንዳልለበሰ እንደ ሌላው ሰው፣
ይሄ ሁሉ ጣጣ በሰው ላይ ያለው፣
በሱ አለመኖሩ ምን ይሆን መላው፣
የጀግኖቹ ጀግና አበጀ በለው።
ምነው ባደረገኝ ጋሻ ጃግሬውን፣
ስከተል እንድኖር ኋላ ኋላውን፣
ምነው ባደረገኝ ደበላ ድጉን፣
ወይም ባደረገኝ እጥፍ ዝናሩን፣
ዙሪያ ተጠምጥሜ እንዳቅፍ ወገቡን፣
ምነው ጠመንጃውን ባረገኝ እግዜር
ከደረቱ ሳልወርድ አቅፎኝ እንድኖር።
እዚህ ተቀምጨ ከምኖር በደስታ፣
እረፍት ሳያምረኝ ወገቤን ሳልፈታ፣
አንተን ተከትየ ከጥዋት እስከማታ፣
በጎንቻ በረሀ ልበል ገልታ ገልታ፣
እንቅፋት ሲመታህ አብሬህ ልመታ።
አበጀ በላቸው የመብቴ ጠባቂ ያርነቴ ጌታ።
ምጣዴን አዝዬ እርኮቴን አንግቼ፣
ሽንብራ ቆርጥሜ ጥር ዉሀ ጠጥቼ፣
ራበኝ ደከመኝ ላልል ተገዝቼ፣
ባለ ጸጋ ባሌን ዛሬውን ፈትቼ፣
እሱን እንድከተል ቤት ንብረቴን ትቼ፣
የእግሩ አጣቢ እንድሆን ግርድና ገብቼ፣
አበጀን አማልዱኝ ዘመድ ወዳጆቼ።
የራስ የደጅ አዝማች ምሽት ከመሆኔ፣
አሽከር ከመላኬ ስጋር ከማስጫኔ፣
ስባንን እንድኖር ሳይከደን አይኔ፣
እንቅልፍ እንዳልጠግብ ተኝቼ በጎኔ፣
የእሱ ገረድ ሆኘ ልኖር መለመኔ፣
ወንድ ብወድ ነው ሴት ስለሆንሁ እኔ
ስማኝ ያገሬ ወንድ ልውቀስህ ወቀሳ፣
አይደለህ ቀማኛ አይደለህ ጀውሳ፣
ሳትሰርቅ ሳትቀማ ሳይኖርህ አበሳ፣
እየነዱ ሲያስሩህ  እንዲሁ ባፈሳ፣
የማትንፈራገጥ የምትንቀሳሳ፣
ትንሽ የማትሻክር ከሆንክ ለስላሳ፣
በሁለት እግሩ ቆሞ ከሚሄድ እንስሳ፣
ወይም ነፍስ ከሌለው ከወደቀ ሬሳ፣
ከቶ ልዩነትህ በምንላይ ነውሳ።
በነሴና እነብሴ በነማይ በጎንቻ፣
ወንዱ ሁል ሴት ሆኖ ከቀረ አንድ ብቻ፣
ለቀማኞች መቅጫ ላመጸኞች መምቻ፣
ለደካሞች ምሽግ ጋሻ መመከቻ፣
ለእሱ ተሸክሜ ውሃ በቅምጫና ጥሬ በስልቻ፣
እንኳን በማውቀው ዱር በማውቀው ስርቻ፣
ስሄድ አልኖርም ወይ እስ'ካገር ዳርቻ።
ሌሎች ሲበደሉ እሱ መከፋቱ፣
ሌላ ሰው ሲጠቃ እሱ መቆጣቱ፣
የሰው ቁስል አሞት እንዲህ መሰቅየቱ፣
ግፍን እና አመጽን እንደ መርዝ መጥላቱ፣
ህይዎቱን ለሰው መብት ዋጋ አርጎ መስጠቱ፣
ግርማው እንደ አንበሳ ሲያዩት ማስፈራቱ፣
ምን ከባህር አሸዋ ቢበዛም ጠላቱ፣
ጎራዴውን መዞ አውጥቶ ካፎቱ፣
ብቻውን ብቅ ሲል መድረሻ ማጣቱ፣
ሳያሰናክለው ጋራው ቁልቁለቱ፣
ሃይሉን ሳይቀንሰው እራቡ ጥማቱ፣
እርቀት ሳይገታው እንደ'ሳብ ፍጥነቱ፣
እነሴ ነው ሲባል ጎንቻ መታየቱ፣
ይህን ሁሉ ባህርይ ይዞ መገኘቱ፣
አይመሰክርም ወይ ሰው ከተሰራበት
ከጎስቋላ ጭቃ ላለመሰራቱ።
ጥንቱኑ ሲፈጠር ሲወለድ ከናቱ፣
የሰው ቤዛ እንዲሆን ታዞ ለመምጣቱ፣
አየ ምን ያደርጋል በከንቱ መመኘት
የማይገኝ ነገር፣
ባይሆንማ ኖሮ ሹመት እንደቂጥኝ
የሚወረስ በዘር፣
ቅን ፍርድ ለመስጠት ሰው ለማስተዳደር፣
የያንዳዱን ደሃ መብት ለማስከበር፣
ለዚህ ለተጠቃ ለተበደለ አገር፣
መድሃኒት እንዲሆን እሱን መሾም ነበር።

                        ምንጭ፦ፍቅር እስከ መቃብር

Friday, December 18, 2015

490

      መንገደኛው ዛሬ ሽምግልና ተቀምጬአለሁ።ሁለት ላለመስማማት የተስማሙ ጓደኛሞችን ለማስታረቅ ነበር የተቀመጥነው።አብሮ አደጎች፣አብረው ብዙ ያሳለፉ የጋራ ትዝታዎቻቸው፣የጋራ ደስታቸው፣የጋራ ኀዘናቸው የበረከተ ወዳጆች ነበሩ።ሆኖም አሁን ግን የተስማሙት ላለመስማማት ነው።አንዱ አንዱ የሚናገረው አይጥመውም፣የሚተያዩት በትዕቢት ዓይን ነው።ክፉኛ ተናንቀዋል{በሁለቱም ሊተረጎም ይችላል}በየንግግራቸው ውስጥ እንደ አዝማች የሚጠቀሙት ደግሞ "አላውቅህም ወይ?" የሚል ዜማ አለ።የሚነጋገሩት ላለመረታት ነው።ቆይተው ደግሞ "ጉድህን ነው የማወጣልህ! ጎድህን ነው የማዝረከርክልህ!" ይባባላሉ።ሁለቱም ጓደኛሞች ግን ማተብ ያሰሩ፣ቤተክርስቲያን የሚስሙ ክርስቲያኖች ነበሩ።የጠባቸው መንስኤ ተብል የሚቀርበው ነገር እዚህ ግባ የማይባል ተራ ነገር ነው።እንኳን ብዙ ያሳለፉ አብሮ አደጎች በቅርቡ የተገናኙ ሰዎች እንኳን ሊጣሉ የማይችሉበት ተራ ምክንያት።አንዱ ሲናገር ሌላኛው ስሩ ይገታተራል።"ልብ አድርጉልኝ እያዋረደኝ ነው! ልታሰድቡኝ ነው እንዴ? የጠራችሁኝ!" ይላል።ተናጋሪው ደግሞ ፊቱ በድል አድራጊነት ያበራል።እኔ ግን ከተነገሩት ነገሮች የትኛው ስድብ እንደሆነ የትኛው እንደሚያዋርድ አልገባህ ብሎኝ ተቸገርሁ።"በደንብ አልሰማሁ ይሆን? "ብየም ተጠራጠርሁ።ሆኖም እነርሱ የተግባቡበት ውስጣዊ ቋንቋ ነበር።ነገሩን እንደምንም አብርደን ልናስታርቃቸው ሞከርን።ሆኖም ላይስማሙ የተስማሙት ጓደኛሞች ቃላችንን ሊሰሙ አልፈለጉም። የእርቅ ጉዳይ ሲነሳ ሁለቱም ነብሮች ሆኑ።ማሉ ተገዘቱ።"ወይ ክርስትና "አልኩኝ በልቤ።"ጠላቶቻችሁን ውደዱ" የሚለው ቃል ለካ ጥቅስ ብቻ ነበረ።ቃሉን ለመስማት እንጅ እንደቃሉ ለመኖር የሚፈቅድ ማንም የለም።የማውቀውን መጽሐፍ ቅዱስ ቃል ልናገር ስሞክር አንድ አንዴ ቀድመው ያብራሩልኛል፣አንደ አንዴ ደግሞ "እርሱ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። አሁን ከዚህ ጋር ምን አገናኘው?" ይላሉ።አሁን ላይ ያልተጠቀምንባት ወንጌል ለመቼ ልትሆነን ነው?ሁለቱ  ስመ እግዚአብሔርን እየጠሩ ማሉ ተገዘቱ። ዕርቅ የሚሻውን አምላክ ስም ጠርተው አንታረቅም አሉ።ምክንያታቸውን ስንጠይቃቸው "በቃ እንዲሁ ከእርሱ ጋር መቀጠል አልፈልግም" ከማለት ውጪ ሊታረቁ ላለመቻላቸው አንዳች በቂ ምክንያት አላቀረቡም።ይህን ጊዜ "አለሙን እንዲሁ ወድዷል" የሚለው ቃል ትዝ አለኝ።እኛን ለመጥላት ብዙ ምክንያት እያለው እንዲሁ የወደደንን አምላክ "እናምናለን" እያልን እንዲሁ አስጠላኸኝ መባባላችን እንዴት ያሳዝናል።ከሁሉ የገረመኝ አንዳችን ተነስተን ከቃለ እግዚአብሔር እየጠቀስን ለደቂቃወች ስናወራ በጸጥታ ካዳመጡን በኋላ ንግግራችንን ከምንም ሳይቆጥሩ አቁመው እንዳስቀጠሉት ቴፕ ያንኑ ንግግራቸውን መቀጠላቸው ነው።

Tuesday, December 08, 2015

ሰላም

ብላቴናው ወንድማችሁ ሰሞኑን በአንዳንድ የሃገራችን ከተሞችና ዩኒቨርሲቲዎች በተከሰተው አለመረጋጋት ምክንያት ነፍሴ መረበሽ ከጀመረች ቀናትን አስቆጥሪያለሁ።ነግሩን ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማሁት በጅማ ዞን በሚገኘው የመረዋ ተክለሃይማኖት ገዳም የሰብል ስብሰባ መርሃ ግብር ስለነበር የበረከቱ ተካፋይ ለመሆን በሄድሁበት ዕለት ነበር።ለ 30 ደቂቃያህል በቆሎ ስንቃርም ከቆየን በኋላ በብፁዕ አባታችን ትዕዛዝ  ስድስት ሰወች ለጤፍ ሸክም  እንድንሄድ ተደረገ።በዚህ ሁኔታ ላይ ሳለን ለአንዱ ጓደኛየ ስልክ ተደውሎለት ለተወሰኑ ደቂቃዎች ሲነጋገሩ ከቆዩ በኋላ በአንድ ግቢ በተከሰተ ሁከት ምክንያት የሰው ህይወት ማለፉንና የእርሱን ደህንነት ለመጠየቅ እንደደወሉለት ነገረኝ።እውነት ለመናገር መጀመሪያ ላይ ለጉዳዩ ትኩረት አልሰጠሁትም ነበር።ኧረ! እንዲያውም ተማሪን ለማስደንበር የተፈጠረ ዉሸት መስሎኝ ነበር።ዉሎ ሲያድር ግን ነገሩ ተጠናክሮ የወሬ ማዕበል ከየአቅጣጫው ይጎርፍ ጀምሯል።አንዱ በእንትና ከተማ ይህን ያህል ሰው ሲሞት፣ በእንትና ዩኒቨርሲቲ ይህን ያህል ሰው ቆሰለ ይላል። ሌላውም ብድግ አድርጎ "የለም እነዚህ የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ነገሩን ሸፋፍነውት ነው እንጅ የሟቾች ቁጥር ብቻ እንኳን ወደዚህ ከፍ ሳይል አይቀርም" ይላል።የሆነው ሁኖ ብላቴናውን ፍርሃት ክፉኛ ይንጠኝ ጀምሯል።ምነው ገረማችሁሳ? ወንድ ልጅ አፉን ሞልቶ "ፈራሁ" ሲል ብትስቁም አይደንቀኝም፤ ምክንያቱም እናንተ የፌደራል ፖሊሶቹን ከስክስ ጫማ ምን እንደሚመስል አታውቁማ።ብታውቁ ኑሮ ግን እንደ እኔ የዶርማችሁን በራፍ በቁም ሳጥን  ጥርቅም አድርጋችሁ ዘግታችሁ አልጋችሁን የሙጥኝ ማለታችሁ እንደማይቀር በእርገጠኝነት መናገር እችላለሁ።እኔን ግን ሚገርመኝ ባልፈራ ነበር።በዚች የቀንበር ቅንጭርት የሰበረ ኮርማ  ጭድ ሲሰጠው ቀና በሬ በጅማት ቁግ እየተገረፈ እስከ ማታ በሚያርስባት፣አጉራ ሰብረው የወጡ ጊደሮች በመላሾ ተደልለው ወደ ጋጣቸው ሲመለሱ ገራም ላሞች ቀፈዳቸው እስኪበር በሽመል እየተወቁ በሚታለቡባት፣ፍየሎች ተለቀው በጎች በሚኮደኮዱባት፣በእጅ ሚዳሰሰውን የሲኦልን ጨለማ የለበሰ ሰይጣን በጭብጨባ ሲሸኝ ፀሐይን የተጎናጸፈው የብርሃን መልአክ መከናነቢያውን እንዲያወልቅና እርቃኑን እንዲሄድ  በሚደረግባት፣በርባንን አስፈትታ ክርስቶስን በምታሰቅል፣በዚች እጆቿ በንፁሃን ደም የተጨማለቁባት የአመጸኞች ዓለም እየኖርሁ መፍራት ይነሰኝ?የመፍራት መብት አንቀፅ ስንት ነበር እባካችሁ?ላለፉት ሁለት ሳምንታት እረፍት ላይ ስለነበርሁ ጊዜየን ማሳልፈው አንዳንድ አዝናኝ የሆኑ ነገሮችን በማንበ አልያም በማየት ነበር።ትናንትና ማታም የጓደኛየን ላፕ ቶፕ ተውሸ "ከቃል በላይ"የተሰኘውን አማርኛ የፍቅር ፊልም እያየሁ በነበረበት ሰዓት ከወደ ውጭ የመጣ የጩኸት ድምፅ ጭርር... ሲል ሰማሁ።የግቢ ተማሪወች የፌደራል ፖሊስ ሲያዩ የሚያሰሙት ፍርሃት የቀላቀል የቅዠት ጩኸት ነበር።ፊልሙን እንደምንም ጨርሸ መብራቱድ ድርግም አድርጌ ካጠፋሁ በኋላ ጎኔን ካልጋው ባገናኝም እንቅልፍ ግን ሊይዘኝ አልቻለም።በምትኩ አእምሮዬ የተለያዩ ጥያቄዎችን እያነሳ ሲያወጣና ሲያወርድ ሌሊቱ ተገባደደ።ሁከት ምንድን ነው? የሁከት ፈጣሪዋ ማን ነው? አላማውስ ምንድ ነው? ዉጤቱስ?   ከሁከት በተቃራኒ ያለው፤ ሰላምስ ምንድ ነው? መገኛውስ ከወዴት ነው? ይህች ዓለም ሰላሟን እንድታጣ የሚደርጓት ነገሮችስ ምንድን ናቸው?እና የመሳሰሉት።

Thursday, December 03, 2015

የግቢ ማስታወሻ

ሰላምይሁን ተውልዶ ያደገው በባህር ዳር ከተማ  ሲሆን የህይወት አስቸጋሪ ውጣ ውረዶችን የጀመረው ገና በሕጻንነት እድሜው እንደሆነ የሚያውቁት ይናገራሉ። ከዕለታት አንድ ቀን መሐል ፒያሳ ላይ ቆሟል። ምን ማድረግ እንዳለበትም ሆነ የት መሄድ እንዳለበት በትክክል ። መለየት ተስኖታል። በዚያ ላይ ረሀብ በጣም እያስቸገረው ነው። ሲያስበው ትናንትና ጥዋት ላይ ምግብ ወድ አፉ መጠጋቱ  ትዝ አለው። ያለው ብቸኛ አማራጭ ሁሌም ሰዎች ሲያደርጉት የሚያናድደውን ተግባር እርሱም መፈጸም እንደሆነ አመነበት። እናም ከአራዳ ጊዮርጊስ ወደ መብራት ኃይል ሕንፃ በሚወስደው የግራ መስመር ላይ ቆሞ ታክሲ ለመሳፈር ከሚጋፉት ሰዎች አጠገብ ደረሰ። ልቡ በአፉ በኩል ወጥታ ለመሄድ የምትታገለው እስኪመስለው ድረስ ፍርሃት እየናጠው ታክሲ ጥበቃ አጠገቡ የቆመውን ሰው ማናገር ጀመረ። ግን ገና ፊቱ ለመለመን መዘጋጀቱን በሚያሳይ ሁኔታ ሲቅለሰለስበት "እግዚአብሔር ይስጥህ" ብሎት ቦታ ቀየረ። አሁን ሰላምይሁን አይኖቹ እንባ አቀረሩበት በዚህ መንገድ መለመን ከቀጠለ ማንም ምላሽ እንደማይሰጠው ወዲያውኑ ተገነዘበ። እንደ ምንም ብሎ ወደ ኋላ በማፈግፈግ አንድ ጥግ ላይ ተቀምጦ ቀጥሎ ማድረግ ያለበትን ነገር ማውጠንጠን ተያያዘ።


ጭንቅላቱ መፍትሄን ከመፈለግ ይልቅ "ለምን ይህ ሁሉ በእኔ ላይ ሆነ?" የሚለው ጥያቄ ፋታ ሊሰጠው አልቻለም። ወደ ላይ እና ወደታች የሚራወጡትን የአዲስ አበባ መኪናወች፣የሰዎችን ሩጫና የተደበላለቀውን ጩኸት ሲያስተውል በእርሱ ውስጥ ያሉ የሃሳብ ብዛት በአካል የታዩ መስሎት ፈገግ ማለት አሰኘው። በፊት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በመከራ ጨርሶ ዩኒቨርሲቲ ከገባ በኋላ ሁሉም ነገር ይስተካከላል በማለት ሲመካ የነበረው ነገር ጭራሽ ሁሉም ነገር ተዘበራርቆ ለእርሱ ዩኒቨርሲቲ የምድር ሁሉ መከራ መለማመጃ መሆኑ ሁሌም ይገርመዋል። የሚወዳቸው እናቱ በአስጊ ሁኔታ የኩላሊት በሽተኛ ስለሆኑ ምን ማድረግ እንዳለበት ተስኖታል። እርሱ የጀመረውን የኢንጂነሪንግ ትምህርት ጨርሶ ለመውጣና እናቱን ለመጦር ከሚያልመው የበለጠ ሌላ ተስፋ በህይዎቱ ውስጥ አለኝ ብሎ አስቦ አያውቅም ነበር። አባቱ በድንገተኛ የመኪና አደጋ ምክንያት ለስራ በወጡበት ሳይመለሱ በመቅረታቸው ገና ክርስትና ከተነሳበት ሳምንት ጀምሮ እናቱ በመከራ ነው ያሳደጉት። እናቱ ወ/ሮ ብርሃን ለእርሱ በትክክል የሕይወቱ ብርሃን መሆናቸውን ያምናል፤እርሳቸው ከሌሉ አበቃ! ብርሃኑም ይጠፋል። ይህ ነው የሰላምይሁን ጭንቀት።