Tuesday, December 08, 2015

ሰላም

ብላቴናው ወንድማችሁ ሰሞኑን በአንዳንድ የሃገራችን ከተሞችና ዩኒቨርሲቲዎች በተከሰተው አለመረጋጋት ምክንያት ነፍሴ መረበሽ ከጀመረች ቀናትን አስቆጥሪያለሁ።ነግሩን ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማሁት በጅማ ዞን በሚገኘው የመረዋ ተክለሃይማኖት ገዳም የሰብል ስብሰባ መርሃ ግብር ስለነበር የበረከቱ ተካፋይ ለመሆን በሄድሁበት ዕለት ነበር።ለ 30 ደቂቃያህል በቆሎ ስንቃርም ከቆየን በኋላ በብፁዕ አባታችን ትዕዛዝ  ስድስት ሰወች ለጤፍ ሸክም  እንድንሄድ ተደረገ።በዚህ ሁኔታ ላይ ሳለን ለአንዱ ጓደኛየ ስልክ ተደውሎለት ለተወሰኑ ደቂቃዎች ሲነጋገሩ ከቆዩ በኋላ በአንድ ግቢ በተከሰተ ሁከት ምክንያት የሰው ህይወት ማለፉንና የእርሱን ደህንነት ለመጠየቅ እንደደወሉለት ነገረኝ።እውነት ለመናገር መጀመሪያ ላይ ለጉዳዩ ትኩረት አልሰጠሁትም ነበር።ኧረ! እንዲያውም ተማሪን ለማስደንበር የተፈጠረ ዉሸት መስሎኝ ነበር።ዉሎ ሲያድር ግን ነገሩ ተጠናክሮ የወሬ ማዕበል ከየአቅጣጫው ይጎርፍ ጀምሯል።አንዱ በእንትና ከተማ ይህን ያህል ሰው ሲሞት፣ በእንትና ዩኒቨርሲቲ ይህን ያህል ሰው ቆሰለ ይላል። ሌላውም ብድግ አድርጎ "የለም እነዚህ የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ነገሩን ሸፋፍነውት ነው እንጅ የሟቾች ቁጥር ብቻ እንኳን ወደዚህ ከፍ ሳይል አይቀርም" ይላል።የሆነው ሁኖ ብላቴናውን ፍርሃት ክፉኛ ይንጠኝ ጀምሯል።ምነው ገረማችሁሳ? ወንድ ልጅ አፉን ሞልቶ "ፈራሁ" ሲል ብትስቁም አይደንቀኝም፤ ምክንያቱም እናንተ የፌደራል ፖሊሶቹን ከስክስ ጫማ ምን እንደሚመስል አታውቁማ።ብታውቁ ኑሮ ግን እንደ እኔ የዶርማችሁን በራፍ በቁም ሳጥን  ጥርቅም አድርጋችሁ ዘግታችሁ አልጋችሁን የሙጥኝ ማለታችሁ እንደማይቀር በእርገጠኝነት መናገር እችላለሁ።እኔን ግን ሚገርመኝ ባልፈራ ነበር።በዚች የቀንበር ቅንጭርት የሰበረ ኮርማ  ጭድ ሲሰጠው ቀና በሬ በጅማት ቁግ እየተገረፈ እስከ ማታ በሚያርስባት፣አጉራ ሰብረው የወጡ ጊደሮች በመላሾ ተደልለው ወደ ጋጣቸው ሲመለሱ ገራም ላሞች ቀፈዳቸው እስኪበር በሽመል እየተወቁ በሚታለቡባት፣ፍየሎች ተለቀው በጎች በሚኮደኮዱባት፣በእጅ ሚዳሰሰውን የሲኦልን ጨለማ የለበሰ ሰይጣን በጭብጨባ ሲሸኝ ፀሐይን የተጎናጸፈው የብርሃን መልአክ መከናነቢያውን እንዲያወልቅና እርቃኑን እንዲሄድ  በሚደረግባት፣በርባንን አስፈትታ ክርስቶስን በምታሰቅል፣በዚች እጆቿ በንፁሃን ደም የተጨማለቁባት የአመጸኞች ዓለም እየኖርሁ መፍራት ይነሰኝ?የመፍራት መብት አንቀፅ ስንት ነበር እባካችሁ?ላለፉት ሁለት ሳምንታት እረፍት ላይ ስለነበርሁ ጊዜየን ማሳልፈው አንዳንድ አዝናኝ የሆኑ ነገሮችን በማንበ አልያም በማየት ነበር።ትናንትና ማታም የጓደኛየን ላፕ ቶፕ ተውሸ "ከቃል በላይ"የተሰኘውን አማርኛ የፍቅር ፊልም እያየሁ በነበረበት ሰዓት ከወደ ውጭ የመጣ የጩኸት ድምፅ ጭርር... ሲል ሰማሁ።የግቢ ተማሪወች የፌደራል ፖሊስ ሲያዩ የሚያሰሙት ፍርሃት የቀላቀል የቅዠት ጩኸት ነበር።ፊልሙን እንደምንም ጨርሸ መብራቱድ ድርግም አድርጌ ካጠፋሁ በኋላ ጎኔን ካልጋው ባገናኝም እንቅልፍ ግን ሊይዘኝ አልቻለም።በምትኩ አእምሮዬ የተለያዩ ጥያቄዎችን እያነሳ ሲያወጣና ሲያወርድ ሌሊቱ ተገባደደ።ሁከት ምንድን ነው? የሁከት ፈጣሪዋ ማን ነው? አላማውስ ምንድ ነው? ዉጤቱስ?   ከሁከት በተቃራኒ ያለው፤ ሰላምስ ምንድ ነው? መገኛውስ ከወዴት ነው? ይህች ዓለም ሰላሟን እንድታጣ የሚደርጓት ነገሮችስ ምንድን ናቸው?እና የመሳሰሉት።
        ለእነዚህ ጥያቄውቼ ምላሽ ለማግኘት ስባዝን  የግብጹ ፓትሪያርክ አቡነ ሽኖዳ ሣላሳዊ የሕይወት መንገድ በተሰኘው መጽሐፋቸው  ከዝምታ ጋር ተያያዥ የሆኑ ስነምግባራትን በሚያብራሩበት ምዕራፍ ስለሰላም የሚያትቱበትን ጽሁፍ አነበበሁ።በረከታቸው ይደርብንና አበታችን ስለ ሰላም እንዲህ ይላሉ፦ሰላም ለምንንኖርበት አለም በጣም አስፈላጊ እንደሆነ አጠያያቂ አይደለም።የሰላም ስረ መሰረቱ እግዚአብሔር በመሆኑ ሰላም ዓለም ሳይፈጠር ዘመን ሳይቆጠር ነበር።ዓለም ከተፈጠረ ሴኮንድ፣ ደቂቃ፣ ሰዓት ቀን፣ሳምንት፣ወር፣ዓመትእና ምዕተ ዓመት ባስቆጠሩት የጊዜ ቀመር አመካይነት ብዙ ጊዚያት አልፈዋል።ብዙ ወራትም ተፈራርቀዋል።በእርግጥ ዘመን ከመቆጠሩ እና የዘመናት ልካቸውና ወሰናቸው ከመታወቁ በፊትም እግዚአብሔር በፍፁም ሰላም አለ።እግዚአብሐር በሰላም ማንነቱን ለመግለፅ ስራውን ጀመረ።የመጀመሪያው ስራውም ይህን ዓለም ካለመኖር ወደ መኖር ማስገኘት ሆነ ዘፍ 1፡1 ከዕለተ እሑድ እስከ ዕለተ ዓርብ ማለት በእያንዳንዱ ዕለት የሥነ-ፍጥረት ሂደት በሰላም ተከናውኗል።በሰማያትም በሰላም ያለምንም ሁከት ለተልኮ የሚንቀስቀሱ ሰማያውያን ኃይላት አሉ።እነዚህም ንጹሐን መላዕክት ናቸው።የአንድን ሰዓት ደቂቃ፣ሴኮንድና ሰዓት ቆጣሪውን አስተካለው ከሞሉ በኋላ ሰዓቱ እንደሚሰራ ሁሉ የሚታየውም ሆነ የማይታየው እያንዳንዱ ፍጥረት በተመደበለት እና በተሰጠው የተፈጥሮ ህግ ይተዳደር ጀመር።ሌሊቱ በቀን ቀኑ በሌሊት እየተተካ እና ያለምንም የተፈጥሮ መዛባት ይህ የምንኖርበት ዓለም ሰላሙን ጠብቆ ለብዙ ጊዚያት ቆየ።የተፈጥሮ ሰላም እንዲህ ከሆነ ዓለም ሰላሙን ያጣውና ሁከት የነገሰበት መቼ ነው? ያስብላል።የዚህን ጥያቄ ምላሽ እነሆ፦አለም ሰላሙን ያጣው እግዚአብሔር እያንዳንዱን ፍጥረት ነጻ ፈቅድና አእምሮ ሰጥቶ ከፈጠረ በኋላ ነው።ለመጀመሪያ ጊዜ ሁከት የተወጠነውና ሰላም የደፈረሰው በሰማያት በመላዕክቱ ማኅበር ነው።አስቀድሞ እውቀትና ነጻ ፈቃድ ያላቸው የሰማያት ሰራዊት ያለተቃውሞና ያለመልያየት በሰላም ብዙ ጊዚያትን በአብሮነት አሳልፈዋል።በመካከላቸውም ተቃዋሚ ወይም ሁከት ፈጣሪ አልያም ስራዓት አልበኛ አልነበረም።ይሁን እንጅ የመላዕክት  አልቃ የነበረው ሳጥናኤል በበደለ ወቅት በሰማያት በመላዕክቱ መካከል ሰላምና መረጋጋት ጠፍቶ ሁከት አለመግባባት ተፈጠረ።በመሰረቱ ሳጥናኤል የመላዕክት አለቃ ቢሆንም ፍጡር እንጅ በራሱ ኃይል የተገኘ አይደለም።ፍጡርነቱን የሕዝቅኤል መጽሐፍ "ጠባይህ ከተፈጠርህበት ጊዜ አንስቶ ክፋትን ማድረግ እስከጀመርህበት ጊዜ ድረስ ፍጹም ነበር ሕዝ 28፥15 "ሲል ያረጋግጣል።በእርግጥ እግዚአብሐር በሥነ-ፍጥረት ኁልቊ መስፈርት መላዕክትን ሲፈጥር ሳጥናኤልም ከመላዕክቱ አንዱና ዋነኛው አድርጎት ነበር።ሁሉም መላዕክት የተለያየ የስራ ድርሻ እንዳላቸው ይታወቃል።ለምሳሌ ያክል የቅ/ሚካኤልንና የቅ/ገብርኤልን የስራ ድርሻ እንመልከት።ቅ/ሚካኤል ለሰው ልጆች ምህረትንና ይቅርታን የሚያሰጥ እና ለኃጢአተኞች ጥብቅና የሚቆም መልአክ ነው።መልአከ ምህረት{ የምህረት መልአክ} ያሰኘውም ይህ አገልግሎቱ ነው።ቅ/ገብርኤል ደግሞ በሕይወታቸው ተስፋ ቆርጠው የባዘኑትን የሚያረጋጋ፣ የደከሙትን የሚያበረታ፣ያዘኑትን የሚያጽናና፣ በመከራ የወደቁትን ፈጥኖ የሚታደግ፣ መልአክ ነው።ይህም የስራ ድርሻው አስደሳች መልአክ{መልአከ ብስራት]የሚል ስያሜ አሰጥቶታል።እንደዚሁ ሁሉ በሕዝ 8፡14 አንተን እንደ ጠባቂ ኪሩብ አድርጌ በመሾም በዚያ መደብሁህ በተቀደሰው ተራራየ ላይ ትኖር ነበር።እጅግ በሚያብረቀርቁ የከበሩ ድንጋዮች መካከል ትመላለስ ነበር።ተብሎ እንደተገልጸው ሳጥናኤልም የመላዕክት አለቃ ከመሆኑ ባሻገር የእግዚአብሔርን ዙፋን እንዲጠብቅ የተቀባ ኪሩብ ነበር።ይህም  ስልጣኑና የስራ ድርሻውም ከሌሎች ይልቅ የእግዚአብሔር ብቸኛ ቀራቢ አሰኝቶት ነበር{ቅሩበ እግዚአብሔር]።በእርግጥ መላዕክት እንደዚህ ያለ ታላቅ ስልጣንና የስራ ድርሻ ቢኖራቸውም ስልጣናቸው የስራ ድርሻቸውን በባሕርያቸውና በራሳቸው ጥረት ያገኙት ሳይሆን ከእግዚአብሔር የተሰጣቸው ጸጋ ነው።ነገር ግን የመላዕክት አለቃ ሳጥናኤል ስልጣኑና የስራ ድርሻው የመመለክ ስሜት ስላጫረበት እግዚአብሔርን ወይም የእግዚአብሔር እኩያና አቻ ለመሆን ምኞት  አደረበት።የተመኘሁትንም እሆናለሁ የፈለግሁትንም አደርጋለሁ ማለትንም ጀመረ።በዚህም አላበቃም የራሱን ነገድ በማሳመጽ "ፈጣሪ እኔ ነኝ። ከእኔ በላይ ማንም  የለም።" እያለ ክፉ ምኞቱንና አድራጎቱን ለማሳካት ቢሞክርም ተፈጻሚ ሊሆንለት አልቻለም።እርሱ ከመለኮታዊ ኃይል ጋር የሚያደርገው  አቅምም ሆነ ስልጣን ባይኖረውም እንኳን የተሰጠውን ነጻ ፈቃድና የማሰብ ችሎታ ያለ አግባቡ በተጠቀመ ጊዜ በሰማያት በመላዕክቱ ማኅበር ዐመጽና ሁካታን አስነሳ። በመቀጠልም በመካከላቸው አለመግባባት ተፈጠረ።የእርሱ ዐመጽና ትዕቢት እርሱን ጨምሮ ከእርሱ ጋር የተባበሩትን ነገደ መላእክት ከስልጣናቸው አዋረዳቸው።ከማዕረጋቸው አሻራቸው።እግዚአብሔርም እርሱንና ተከታዮቹን ከሰማያት ከመላዕክት ከተማ አምዘግዝጎ ወደ መሬት ጣላቸው።የመላዕክት ከተሞች ሰማያትም እንደ ቀድሞው ሰላም ሰፈነባቸው።የሰላም ጸር የሆነው ጥንተ ጠላታችን ሳጥናኤልም በሰማያት የወጠነው ምኞቱ ሳይሳካለት ሲቀር ደግሞ በእግዚአብሔር አርአያና አምሳል የተፈጠረው ሰው ወዳለበት ወደ ኤደን ገነት አቀና በኤዶም ገነት የነበረውንም ሰላም አደፈረሰ ኤደን ገነትም የተዘጋችው{ምድረ ፋይዳ}የሆነችው ነዋሪወቹም በቋንቋ በጎሳ ተለያይተው ሰላምን ያጡበት ዋነኛው ምክንያት የሰውን ልጅ የገነት ኑሮ ታሪክን ይመለከታል።በገነት ለመኖር ቀዳሚው ሰው አዳም ነው።አዳምም በመጀመሪያ በገነት ሳለ አይሞቀውም፣አበርደውም፣ሰው ሰራሽ ልብስ አያስፈልገውም።በአጠቃላይ መሰረታዊ ፍላጎቱ ተሟልቶለት በፍጹም ሰላምና ደስታ ይኖር ነበር።አዳም በገነት ሳለ በእርሱና በእንስሳቱ መካከል ምንም አይነት ጠላትነት አልነበረም።እነርሱም አዳምን ጨምሮ ከእነርሱ በቁመት የሚያንሱትን በኃትል የሚደክሙትን ፍጥረታት ለምግብነት ሊበሉ አይሿቸውም።አዳምም እነርሱን ለምግብነት አያድንም።ይልቁንም አብሮነታቸውና አቀራረባቸው አወደዳቸው እንጅ እንዲፈራሩ አላደረጋቸውም። አዳም በገነት ሳለ የቤት እንስሳት ብቻ ሳይሆኑ አሁን የምንፈራቸው የዱር አራዊት እንኳን እየታዘዙትና እየተባበሩት ከእርሱ ጋር በፍጹም ሰላም ይኖሩ ነበር።በአጠቃላይ አዳም እስከበደለበትና የምንኖርበት ዓለም ሰላሙን እስካጣበት ጊዜ ድረስ "አዳኝ አውሬ" የሚል ስም አጠራር ያላቸው አራዊት አልነበሩም።እግዚአብሔር "እነሆ መብል ይሆናችሁ ዘንድ በምድር ፊት ሁሉ ላይ ዙሩ በእርሱ ያለውን ሐመላማል ሁሉ የዛፏን ፍሬ የሚያፈራውን እና ዘር ያለውን ዛፍ ሁሉ ሰጠኋችሁ ለምድርም አራዊት ሁሉ ለሰማይም ወፎች ሕያው ነፍስ ላለው ለምድር ተንቀሳቃሾችም ሁሉ የሚበቅለው ሐመልማል ሁሉ መብል ይሁንላች ሁ{ዘፍ፩፡፳፱ ፴}"ሲል እንዳዘዘው በዚያን ጊዜ ሰውም ሆነ እንስሳት ስጋ በል አልነብሩም።እንስሳቱ ለምግብነት የሚጠቀሙት ሳር ግጦሽ ሲሆን ሰው ደግሞ አዝዕርትና ፍራፍሬን ይመገብ ነበር።

     ይሁን እንጅ ውሎ እያደረ የሚያሳዝን ክስተት  ተፈጠረ።ይህም ክስተት አዳም በገነት ሳለ ኃጢአትን በሰራ ጊዜ ሰላሙን ማጣቱ ነው።ሰላሙንም በማጣቱ የማይፈራው አዳም ፈራ፣ሰው ሰራሽ ልብስ ያልነበረው እርሱ ከእግዚአብሐር ጸጋ ተራቆተ እራቁትነቱንም[መለመላውን} ለመሸፈን የበለስ ቅጠላቅጠል ሰብስቦ ልብሱን ሰፋ።የሰላም አምላክ እግዚአብሔርም ሳጥናኤልን ከነሰራዊቱ ከሰማያት እንዳስወገደ አዳምና ሚስቱ ሔዋንንም ከገነት አስወጣቸው።እነርሱም ከገነት ከወጡ በኋላ ሰላማቸው ተናጋ፣ጭንቀታም ሆኑ።አደምና ሔዋን ብቻ ሳይሆኑ ከዚያን ዘመን አንስቶ በዓጠቃላይ የሰው ዘር በየጊዜው በምድር ላይ ምግባረ ብልሹ ሰላሙን ያጣና ያልተረጋጋ ሆነ።ይህም የሰው ዘር በመነሻው ህግ ጥሶ በሰላም ከሚኖርበት ቦታ እና ከሚኖርበት ሕይወት አጥቶ አሁን ወዳለበት ተቅበዝባዥ ኑሮ የመምጣቱ ሂደት በጣም አሳዝኝ ነው።ሰው ከእግዚአብሐር ከተለየ ደግሞ ሰላም የለውም።ሰላሙን ማጣቱም አለመረጋግን ያስከትልበታል።በአንጻሩ ደግሞ አካሄዱ ከእግዚአብሔር ጋር ያደረገ ሰው ሰላምና መረጋጋት ይታይበታል።በመሆኑም የተረጋጋ ሰው ሰላማዊ ነው።ሰላማዊ ሰውም የተረጋጋ ነው ማለት ይቻላል።ምክንያቱም የሰላምዊ ሰው  የአኗኗር ስርዓቱ የተረጋጋ ስለሆነ ጸብ አጫሪና ሁከት ፈጣሪ አይደለም።ሰላምዊ ሰውም ለችግሮች መፍትሄ ውሳኔ ሲያመጣ እንኳን ሰላምን ማሰሪያ በማድረግ እንጅ በኃይል ወይም በአመጽ አይደለም።ሰላምን ግብረገብነት በሌላቸው በሁለት ሰውች መካከል ማግኘት አይቻል ይሆናል።ነገር ግን አንድ ግብረ ገብነት በሌለው ሰውና በአንድ ሰላምዊ ሰው መካከል ሰላምን ማግኘት ይቻላል።ሰላማዊ ሰው ግብረ ገብነት የጎደለውንና ያልተረጋጋውን ሰው በፍቅሩ እና በሰላሙ መለወጥ ይችላል።ይህም ሁኔታ "እሳትን በውሃ እንጅ በእሳት ማጥፋት አይቻልም" የሚሉትን የግብፆች ብሂል ያስታውሰናል።ይህም አገላለጽ ሰላም በሁለት ሰላማዊያን ሰወች መካከል ብቻ ነው የሚገኘው እንዳንል ያስችለናል።አንቱታን ያተረፈው ጸሃፊም "ጓደኝህን ንገረኝና ማንነትህን እነግርሃለሁ" ሲል እንደተናገርው።ከተጠራጣሪ ጋር የሚውል ተጠራጣሪ ይሆናል።እንዲሁ ከሰላማዊ ሰው ጋር የሚውል ሰላማዊ ይሆናል።ይህም አብሮ በመኖር በመቀራረብና በመለማመድ አማክይነት ስነ-ልቦናዊ ተጽእኖዎች ሆኑ አስተዋጽኦዎች ከአንዱ ወደ ሌላው እንደሚሰራጩ ያስረዳናል።ለምሳሌ እርስዎ አስቃቂ ወሬ ሰምተው ይጨነቃሉ እንበል ልክ እንደዚሁ እርስዎን ያስጨነቀዎትን አስቃቂ ወሬ ሰምቶ ግን ምንም ያልተጨነቀ ሰው ያገኛሉ።ይህም ሰው የሰማውን አስቃቂ ወሬ ሲነግርወ ያለው ሰላምና መረጋጋት ጭንቀትወን አስወግዶ እና አዕምሮዎን አረጋግቶ ሰላማዊ ያደርዎታል።ከሰላምዊ ሰወች ጋር የሚውሉና የሚሰሩ ከሆነ እነርሱም ስለሚያበረታቱዎትና፣ስለሚያረጋጉዎት እርስዎም ስለሚወዷቸው የእነርሱን አስራርና ፈለግ ይከተላሉ ችግር እንኳን ቢገጥምዎ የእነርሱ አዕምሮ ችግሮችን ተቀብሎ ሁኔታወችን እንዴት እንደሚያጤኗቸውና እንደሚርዷቸው እንዴት መፍትሔ እንደሚያስግኙላቸው በማየት ከእውቀታቸው ብዙ ይማራሉ።የመፍትሔ ዘዴወችንም ይጠቀማሉ።ከእነርሱ ጋር በመኖርወ ብቻ ተግባራዊ የሰላምና የመረጋግት ሕይወት እንዲኖሩ ያስችለዎታል።ስለዚህ ሁላችንም ዝምታ ከውስጣዊ ሰላም መገለጫዎች ብቻ ሳይሆን ሰላምንም መቆጣጠሪያ እንደሆነ እንረዳለን።
   
       አባታችን ስለሰላም የሚሉት ይህንን ነው።የሰላም አምላክ እግዚአብሔር ለሃገራችን ሰላሙን ያድልልን።እኛንም አይተን እንዳላየን፣ ሰምተን እንዳልሰማን የምንችልበትን ዓይነልቡና ይስጠን።

No comments:

Post a Comment