Friday, December 18, 2015

490

      መንገደኛው ዛሬ ሽምግልና ተቀምጬአለሁ።ሁለት ላለመስማማት የተስማሙ ጓደኛሞችን ለማስታረቅ ነበር የተቀመጥነው።አብሮ አደጎች፣አብረው ብዙ ያሳለፉ የጋራ ትዝታዎቻቸው፣የጋራ ደስታቸው፣የጋራ ኀዘናቸው የበረከተ ወዳጆች ነበሩ።ሆኖም አሁን ግን የተስማሙት ላለመስማማት ነው።አንዱ አንዱ የሚናገረው አይጥመውም፣የሚተያዩት በትዕቢት ዓይን ነው።ክፉኛ ተናንቀዋል{በሁለቱም ሊተረጎም ይችላል}በየንግግራቸው ውስጥ እንደ አዝማች የሚጠቀሙት ደግሞ "አላውቅህም ወይ?" የሚል ዜማ አለ።የሚነጋገሩት ላለመረታት ነው።ቆይተው ደግሞ "ጉድህን ነው የማወጣልህ! ጎድህን ነው የማዝረከርክልህ!" ይባባላሉ።ሁለቱም ጓደኛሞች ግን ማተብ ያሰሩ፣ቤተክርስቲያን የሚስሙ ክርስቲያኖች ነበሩ።የጠባቸው መንስኤ ተብል የሚቀርበው ነገር እዚህ ግባ የማይባል ተራ ነገር ነው።እንኳን ብዙ ያሳለፉ አብሮ አደጎች በቅርቡ የተገናኙ ሰዎች እንኳን ሊጣሉ የማይችሉበት ተራ ምክንያት።አንዱ ሲናገር ሌላኛው ስሩ ይገታተራል።"ልብ አድርጉልኝ እያዋረደኝ ነው! ልታሰድቡኝ ነው እንዴ? የጠራችሁኝ!" ይላል።ተናጋሪው ደግሞ ፊቱ በድል አድራጊነት ያበራል።እኔ ግን ከተነገሩት ነገሮች የትኛው ስድብ እንደሆነ የትኛው እንደሚያዋርድ አልገባህ ብሎኝ ተቸገርሁ።"በደንብ አልሰማሁ ይሆን? "ብየም ተጠራጠርሁ።ሆኖም እነርሱ የተግባቡበት ውስጣዊ ቋንቋ ነበር።ነገሩን እንደምንም አብርደን ልናስታርቃቸው ሞከርን።ሆኖም ላይስማሙ የተስማሙት ጓደኛሞች ቃላችንን ሊሰሙ አልፈለጉም። የእርቅ ጉዳይ ሲነሳ ሁለቱም ነብሮች ሆኑ።ማሉ ተገዘቱ።"ወይ ክርስትና "አልኩኝ በልቤ።"ጠላቶቻችሁን ውደዱ" የሚለው ቃል ለካ ጥቅስ ብቻ ነበረ።ቃሉን ለመስማት እንጅ እንደቃሉ ለመኖር የሚፈቅድ ማንም የለም።የማውቀውን መጽሐፍ ቅዱስ ቃል ልናገር ስሞክር አንድ አንዴ ቀድመው ያብራሩልኛል፣አንደ አንዴ ደግሞ "እርሱ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። አሁን ከዚህ ጋር ምን አገናኘው?" ይላሉ።አሁን ላይ ያልተጠቀምንባት ወንጌል ለመቼ ልትሆነን ነው?ሁለቱ  ስመ እግዚአብሔርን እየጠሩ ማሉ ተገዘቱ። ዕርቅ የሚሻውን አምላክ ስም ጠርተው አንታረቅም አሉ።ምክንያታቸውን ስንጠይቃቸው "በቃ እንዲሁ ከእርሱ ጋር መቀጠል አልፈልግም" ከማለት ውጪ ሊታረቁ ላለመቻላቸው አንዳች በቂ ምክንያት አላቀረቡም።ይህን ጊዜ "አለሙን እንዲሁ ወድዷል" የሚለው ቃል ትዝ አለኝ።እኛን ለመጥላት ብዙ ምክንያት እያለው እንዲሁ የወደደንን አምላክ "እናምናለን" እያልን እንዲሁ አስጠላኸኝ መባባላችን እንዴት ያሳዝናል።ከሁሉ የገረመኝ አንዳችን ተነስተን ከቃለ እግዚአብሔር እየጠቀስን ለደቂቃወች ስናወራ በጸጥታ ካዳመጡን በኋላ ንግግራችንን ከምንም ሳይቆጥሩ አቁመው እንዳስቀጠሉት ቴፕ ያንኑ ንግግራቸውን መቀጠላቸው ነው።

     እናም ባልተሳካው ሽምግናችን አዝነን ከቤቱ ተሰናብተን ወጣን።እኔም "እኔና ቤቴ ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን" የሚለውን በቤቱ ግድግዳ ላይ የተሰቀለ ጥቅስና አክሊለ እሾኽ ድፍቶ ያለውን ሥዕል እየተመለከትሁ ወጣሁ።ከእነዚህ ሁለት ሞገደኞች ግትርነት ግን ብዙ ነገር አስተዋልሁ።በተለይ በየደቂቃው "አላውቅህም ወይ?" መባባልቸው በልቤ ቀርቷል።መተዋወቅ ለመናናቅ ሲሆን እንዴት ያሳዝናል።በዚያ ላይ ሺህ ጊዜ ቢተዋወቁ እንዲህ አንዱ አንዱን ማራከስ የለበትም።ቅዱስ ሚካኤል ዲያቢሎስን "እግዚአብሔር ይገሥጽህ" ከማለት ውጪ የስድብ ቃል ያልተናገርው ሳያውቀው ቀርቶ አልነበረም።እንደ ቅዱስ ሚካኤል ቅዱሳን ብንሆን እንኳን እንደሰይጣን የከፋን ሰው እንኳን መሳደብ እንደሌለብን ሲያስተምረን ነው።እኛ ግን በተያየን ቁጥር፣በተላመድን ጊዜ እየተናናቅን ስለምንመጣ ጠብ ሲመጣ ክፉኛ እንጣላለን።ሌላው የወዳጆቹ ተደጋጋሚ ዛቻ ደግሞ "ጉድህን እንዳላዝረከርከው" የሚል ነበር።ይህን ጊዜ የኃጢአት ጉዳችን ተሸክሞ፣ዓይኑ እንዳየች ሳይፈርድብን፣ጆሮው እንደሰማች ያልበየነብን አምላክን እንዳስብ ሆንሁኝ።ሰው የማያውቀው ሌላው ቀርቶ እኛም ጭምር ሙሉ በሙሉ ላናውቀው የምንችለው ብዙ የኃጢአት ጉድ እግዚብሔር ያውቃል።ሆኖም ከዛሬ ነገ "አወጣዋለሁ" እያለ አላሳቀቀንም።ዕለት ጥሎን ሳት ብሎን ስንሰራ ለምንታየው ኃጢአት ግን አንዳችን በአንዳችን ላይ እንዝታለን።ላለመስማማት የተስማሙት ወዳጆች እንዳይታረቁ ያደረጋቸው አንድ ነገር ነው።አንደኛው አንዱ በሌላው እግር ስር ተደፍቶ ይቅርታ መጠየቅን እንደ ትልቅ ውርደት ስለቆጠረው ነው።ከሁለቱ አንዳቸው ቢያጎነብሱ ኖሩ ዕርቅ ይመጣ ነበር።ሁለቱም ግን የበላይነትን ይፈልጋሉ፣መሸነፍን አይፈልጉም። በእነርሱ መታረቅ ከሚፈጠረው ሰላም ይልቅ ክብራቸውን አስቀደሙ፤ከወዳጅነታቸው ይልቅ ፉክክራቸው አየለ።አንዱት እኅት የነገርችኝ አባባል ትዝ አለኝ። "ገበያው ለምን ተረበሸ? ቢሉ እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ"ከሁለቱ ጓደኛሞች አንደኛውን በሌላ ቀን አግኝቼ አናገርሁት።"ለምን አትስማሙም? ለምን ይቅር አትለውም?" አልሁት።እሱ ግን በእኔ አለመብሰል አዘነልኝ "አይ አንተ! ገና ያልተረዳኸው ነገር አለ። ዛሬ ተነስቼ ይቅርታ ብለው አናቴ ላይ ይወጣል። ጌታ ልሁን ነው የሚለው። እኔ ደግሞ እራሴን ማዋረድ አለፈልግም።" አለኝ፤እንዲህ ተኮፍሰን እንዴት ነው በእውነተኛው ዳኛ ፊት ለፍርድ የምንቀርበው? "የበደሉንን ይቅር እንደምንል" ብለን የምንጸልየው በምን ድፍረት ነው? ሰውየው ቀጠለ "እኔ እኮ ተሸክሜው ነው የኖርሁ አንተ አታውቅም ስንት ጊዜ በእኔ ላይ ሲያሴር እንዲህ እንደ አንተ ሰወች እየመጡ በመጽሐፍ ቅዱስ እያባበሉ አስታርቀውን ይቅር ብየው ነበር።አሁን ግን በዛ ሁል ጊዜ ዝቅ ማለት ደግሞ ይከብዳል አይደል እንዴ?"
     
     የእግዚአብሔር ትዕዛዝ ሲወጣ መፈጸም የሚቻልበት ገደብ አልተሰጠውም።ታገሡ  ይቅር በሉ፣ትሑታን ሁኑ ሲባል በገደብ አልነብረም።እኛ ግን ትዕዛዙ ከእኛ ግለኝነት ጋር ሲጋጭብን ገደብ እናበጅለታለን።"አሁንስ በዛ!" በሚል ምክንያት ለሥጋችን እጅ እንሰጣለን።ሆኖም ከእግዚአብሔር ገደብ የሌለው ይቅርታን እንሻለን።"አንድ ሁለቴ ታገስሁት በስንት ሽማግሌ ታረቅን ያለፈው አልፏል ብየ አብሬው ቀጠልሁ፤ለዚህ ነው የናቀኝ እኮ! ወይኔ ሰውየው!" ሲል ቀጠለ በቁጭት።ሰውየው እንኳን አሁን ይቅር ለማለት ሊፈቅድ ቀርቶ ከዚህ በፊት ያደረገው ይቅርታም ጭምር እያቆጨው መጥቷል ለካ! የተቀምጥንበት ካፌ በሰው ቢሞላም ይህ ሰው ግን በንዴት ጦፎ እየጮኸ ይነግረኝ ጀመር። "ከዚህ በላይ አዝየው እንድዞር ነው እንዴ? የምትፈልጉት። እኔንስ ለምን ጨካኝ ታደርጉኛላችሁ? ስንቴ ነው ይቅር የምለው? ሁለት ሦስቴ ይቅርታ ካደረግሁለት በኋላ ከአሁን ወዲህ እራሴን አላስንቅም።ጨርሻለሁ!" አለና አምባረቀ።እኔ የእሱን ሐሳብ ትቼ ሰወች ሰሙን አልሰሙን እያልኩ መሳቀቅ ጀመርሁ። "በቃ ተወው አትበሳጭ" ብየም ላረጋጋው ሞከርሁ።ከቆይታ በኋላ ጋዜጣ እያነበቡ ከኋላችን ተቀምጠው የነበሩ አንድ አረጋዊ ጋዜጣቸውን አጥፈው ተነሱ።ለካ ውይይታችን ይሰሙን ነበር።ቆም ብለው አዩንና "ተው ልጄ! ይቅር ማለት ለራስ ነው።ጌታ እኮ ቢያንስ 490 ጊዜ ይቅር እንድትል ይጠብቃል።"አሉና ወጡ።ነገሩ ግራ ገባኝ።ቆይቸ ግን ተረዳሁት፤ጌታችን ለቅዱስ ዼጥሮስ የመለሰለት መልስ ነው።
                                                                                                                   ምንጭ፦ ሐመር ዘኦርቶዶክስተውሕዶ
                                                                                                                                             ኅዳር 2004ዓ.ም .

No comments:

Post a Comment