Monday, December 28, 2015

አበጀ በለው(1)

ፀሐይ አያጠቁረው ውርጭ አያከስለው፣
ራብ አያከሳው ጥም አያዝለው፣
ድካም አይሰማው እንቅልፍ አይጥለው  ፣
ጎራዴ አያቆስለው ጥይት አይገድለው፣
ስጋ እንዳልለበሰ እንደ ሌላው ሰው፣
ይሄ ሁሉ ጣጣ በሰው ላይ ያለው፣
በሱ አለመኖሩ ምን ይሆን መላው፣
የጀግኖቹ ጀግና አበጀ በለው።
ምነው ባደረገኝ ጋሻ ጃግሬውን፣
ስከተል እንድኖር ኋላ ኋላውን፣
ምነው ባደረገኝ ደበላ ድጉን፣
ወይም ባደረገኝ እጥፍ ዝናሩን፣
ዙሪያ ተጠምጥሜ እንዳቅፍ ወገቡን፣
ምነው ጠመንጃውን ባረገኝ እግዜር
ከደረቱ ሳልወርድ አቅፎኝ እንድኖር።
እዚህ ተቀምጨ ከምኖር በደስታ፣
እረፍት ሳያምረኝ ወገቤን ሳልፈታ፣
አንተን ተከትየ ከጥዋት እስከማታ፣
በጎንቻ በረሀ ልበል ገልታ ገልታ፣
እንቅፋት ሲመታህ አብሬህ ልመታ።
አበጀ በላቸው የመብቴ ጠባቂ ያርነቴ ጌታ።
ምጣዴን አዝዬ እርኮቴን አንግቼ፣
ሽንብራ ቆርጥሜ ጥር ዉሀ ጠጥቼ፣
ራበኝ ደከመኝ ላልል ተገዝቼ፣
ባለ ጸጋ ባሌን ዛሬውን ፈትቼ፣
እሱን እንድከተል ቤት ንብረቴን ትቼ፣
የእግሩ አጣቢ እንድሆን ግርድና ገብቼ፣
አበጀን አማልዱኝ ዘመድ ወዳጆቼ።
የራስ የደጅ አዝማች ምሽት ከመሆኔ፣
አሽከር ከመላኬ ስጋር ከማስጫኔ፣
ስባንን እንድኖር ሳይከደን አይኔ፣
እንቅልፍ እንዳልጠግብ ተኝቼ በጎኔ፣
የእሱ ገረድ ሆኘ ልኖር መለመኔ፣
ወንድ ብወድ ነው ሴት ስለሆንሁ እኔ
ስማኝ ያገሬ ወንድ ልውቀስህ ወቀሳ፣
አይደለህ ቀማኛ አይደለህ ጀውሳ፣
ሳትሰርቅ ሳትቀማ ሳይኖርህ አበሳ፣
እየነዱ ሲያስሩህ  እንዲሁ ባፈሳ፣
የማትንፈራገጥ የምትንቀሳሳ፣
ትንሽ የማትሻክር ከሆንክ ለስላሳ፣
በሁለት እግሩ ቆሞ ከሚሄድ እንስሳ፣
ወይም ነፍስ ከሌለው ከወደቀ ሬሳ፣
ከቶ ልዩነትህ በምንላይ ነውሳ።
በነሴና እነብሴ በነማይ በጎንቻ፣
ወንዱ ሁል ሴት ሆኖ ከቀረ አንድ ብቻ፣
ለቀማኞች መቅጫ ላመጸኞች መምቻ፣
ለደካሞች ምሽግ ጋሻ መመከቻ፣
ለእሱ ተሸክሜ ውሃ በቅምጫና ጥሬ በስልቻ፣
እንኳን በማውቀው ዱር በማውቀው ስርቻ፣
ስሄድ አልኖርም ወይ እስ'ካገር ዳርቻ።
ሌሎች ሲበደሉ እሱ መከፋቱ፣
ሌላ ሰው ሲጠቃ እሱ መቆጣቱ፣
የሰው ቁስል አሞት እንዲህ መሰቅየቱ፣
ግፍን እና አመጽን እንደ መርዝ መጥላቱ፣
ህይዎቱን ለሰው መብት ዋጋ አርጎ መስጠቱ፣
ግርማው እንደ አንበሳ ሲያዩት ማስፈራቱ፣
ምን ከባህር አሸዋ ቢበዛም ጠላቱ፣
ጎራዴውን መዞ አውጥቶ ካፎቱ፣
ብቻውን ብቅ ሲል መድረሻ ማጣቱ፣
ሳያሰናክለው ጋራው ቁልቁለቱ፣
ሃይሉን ሳይቀንሰው እራቡ ጥማቱ፣
እርቀት ሳይገታው እንደ'ሳብ ፍጥነቱ፣
እነሴ ነው ሲባል ጎንቻ መታየቱ፣
ይህን ሁሉ ባህርይ ይዞ መገኘቱ፣
አይመሰክርም ወይ ሰው ከተሰራበት
ከጎስቋላ ጭቃ ላለመሰራቱ።
ጥንቱኑ ሲፈጠር ሲወለድ ከናቱ፣
የሰው ቤዛ እንዲሆን ታዞ ለመምጣቱ፣
አየ ምን ያደርጋል በከንቱ መመኘት
የማይገኝ ነገር፣
ባይሆንማ ኖሮ ሹመት እንደቂጥኝ
የሚወረስ በዘር፣
ቅን ፍርድ ለመስጠት ሰው ለማስተዳደር፣
የያንዳዱን ደሃ መብት ለማስከበር፣
ለዚህ ለተጠቃ ለተበደለ አገር፣
መድሃኒት እንዲሆን እሱን መሾም ነበር።

                        ምንጭ፦ፍቅር እስከ መቃብር

No comments:

Post a Comment