Friday, January 08, 2016

ተወልደ ኢየሱስ በቤተልሔም ዘይሁዳ

 

      በጌታችን በአምላካችን በኢየሱስ ክርስቶስ የተደረገልን ሥርየትና ዕርቅ ግልጥ ሆኖ የተጀመረው በነገረ  ልደት ነው።የጌታችን ልደት በነገረ ድኅነት ትልቅ ስፍራ የያዘና እግዚአብሔር ሰው ሆኖ ዓለምን ያዳነበት ጥበቡ ፍጹም ልዩ መሆኑን ያሳየ ነው።መስተፃርራን የነበሩ ሰማይና ምድር፣ሰውና መላእክት በአንድነት ለምስጋና ታድመዋል።የእረኞች አንደበት  ከመላእክት ጋር ለሰማያዊ ምስጋና ብቁ የሆነበት፣ግዕዛን የሌላቸው እንስሳት ሰራኢ መጋቢያችን፣በዘባነ ኪሩቤል በሰማያት የምትገለጥ አንተ ነህ ሲሉ እስትንፋሳቸውን የገበሩለት፣የምድር ነገስታት በስልጣንህ ሽረት በመንግስትህ ህልፈት የሌለብህ የነገስታት ንጉስ አንተ ነህ ሲሉ ወርቅን ለመንግስቱ፣ዕጣንን ለክህነቱ፣ከርቤን ለሕማሙ ዕጅ መንሻ ያበረከቱለት፣ወላዲተ አምላክ ቅድስት ድንግል ከጻድቁ ዮሴፍ ጋር ያን ልዩ ክብር ያዩበት፤ይህ ልደት በእውነት ልዩ ነው።ቅዱስ ኤፍሬምሶሪያዊ በረቡዕ ውዳሴ ማርያም በጌታ ልደት የተደረገልን ድንቅ የማዳን ስራ በተናገረበት ድርሳኑ እንዲህ ነበር ያለው፦"በጨለማና በሞት ጥላ ውስጥ ለሚኖሩ ሰዎች ታላቅ ብርሃን ወጣላቸው፤በቅዱሳን የሚያድር እግዚአብሔር እኛን ለማዳን ልዩ ከሆነች ድንግል ሰው ሆኗልና ኑ ይህንን ድንቅ እዩ፣ስለተገለጠልን ምስጢር ምስጋና አቅርቡ ሰው ያማይሆን ሰው ሆኗልና ቃል ተዋህዷልና ቅድምና የሌለው ሥጋ ጥንታዊ ቀዳማዊ ሆነ፣ዘመን የማይቆጠርለት መለኮት ዘመን ተቆጠረለት።" ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ "ይህች ቤተልሔም መንግስተ ሰማያትን መሰለች" አለ፤የጌታን ልደት በተናገረበት አንቀጽ።በአባታችን በቀዳማዊ አዳም ምክንያት ያጣናትን ልጅነት ሊሰጠን ዳግማዊ አዳም ክርስቶስ የመንግስተ ሰማያትን የምስጋና ኑሮ በቤትልሔም ገልጧልና።ስለዚህ ነገር ነብየ እግዚአብሔር ሚክያስ  "አንቺ ቤተልሔም ኤፍራታ አንቺ ከይሁዳ አእላፍ መካከል ትሆኝ ዘንድ ታናሽ ነሽ  ከአንቺ ግን አወጣጡ ከቀድሞው ጀምሮ ከዘላለም የሆነ በእሳራኤል ላይ ገዥ የሚሆን ይወጣልና.." በማለት የተነበየውም ስለዚህ ነበር፤ሚክ5፡2 "ወአንቲኒ ቤተልሔም ምድረ ኤፍራታ ኢትቴሃቲ እምነገሥተ ይሁዳ እስመ እምኔኪ ይወጽእ ንጉስ ዘይርዕዮሙ ለህዝብየ እስራኤል" እንዲል ቅዱስ ኤፍሬም።

      ቤተልሔም ማለት ቤተ ህብስት ፣የህብስት ቤት፣የእንጀራ ቤት ማለት  ነው።ይህም ካሌብ እስራኤል ዘሥጋ ምድረ ርስት፣እያሪኮን "ሃይል ዘእግዚአብሔር ኲናት ዘኢያሱ" ብለው በኢያሱ መስፍንነት ሲወርሱ ከኢያሱ የተሰጠችው ምድር ኬብሮን ነበረች።ይህችም የይሁዳ ምድር በኋላም የቅዱስ ዳዊት ከተማ የሆነች ናት።አስቀድሞ ካሌብ ከብታ የምትባል ሚስት አግብቶ በሚስቱ ከብታ አላት ትርጓሜውም የምሳጋና ቤት ማለት ነው፤ይህም ካሌብ በመንፈሰ እግዚአብሔር በዚች ምድር የሚገለጠውን የክርስቶስ የልደቱን ነገር፣እና የመላእክትን ምስጋና ስለተረዳ ነው።በኋላም ካሌብ ኤፍራቷ የምትባል ሚስት አገባ ቦታውን በዚህች ሚስቱ እንደገና ኤፍራታ ብሎ ጠራት።ኤፍራታ ማለት "ጸዋሪተ ፍሬ ፍሬ በውስጧ ያለባት" ማለት ነው።ይህችውም የእመቤታችን ምሳሌ ናት። የሕይወት ፍሬ ክርስቶስን ወልዳልናለችና፤ "አንቲ ውእቱ ዕፅ ብሩክ ፍሬኪኒ ፍሬ ህይወት" እንዳለ ቅዱስ ያሬድ በአቀጽ ብርሃን። ቤተልሔም ይህን ስያሜዋን ያገኘችው ካሌብ ከኤፍራታ ባገኘው ልጁ በልሔም ነው፤ ልሔም ማለት ህብስት፣እንጀራ ማለት  ነው። ይህም ምሳሌነቱ የጌታ ነው፤ ይኸውም አማናዊ፣ እውነተኛ የህይወት እንጀራ፣ህብስት ክርስቶስ ሥጋውን ቆርሶ ደሙን አፍስሶ ሊያድነን የመወለዱ ምሳሌ ነው። "ከሰማይ የወረደ  ህያው እንጀራ እኔ ነኝ ሰው ከዚህ እንጀራ ቢበላ ለዘላለም ይኖራል እኔም ስለዓለም ህይወት የምስጠው እንጀራ ሥጋየ ነው።" እንዲል ዮሐ6፡51። በክርስቶስ ልደት መላእክት ባልተለመደ ሆኔታ ከሰዎች ጋር ተባብረው "ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ሥምረቱ ለሰብእ በሰማያት ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን ሰላም ለሰው ልጅ በምድር እርሱ በሚፈቅደው" እያሉ ንጉስሥ ክርስቶስን አመሰገኑ። ሉቃ 2፡14። በሰማያት በዘባነ ኪሩቤል የሚገለጥ፤ፍፁማን ግሩማን በሚሆኑ መላእክት፣ሊቃነ መላእክት፣ሥልጣናት አጋእዝት የሚመሰገን ሰማያዊ ንጉሥ ዛሬ ስለእኛ ፍቅር ሲል ሊነገር በማይችል ፍፁም ትህትና ከመ ሕጻናት ታቅፎ፣ከኅኃጢአት ብቻዋ በቀር የእኛን ባህርይ ባህርዩ አድርጎ ፍፁም አምላክ ሲሆን ፍፁም ሰው ሆኗልና። "ሕፃን ተወልዶልናልና፥ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤አለቅነትም  በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፥ኀያል አምላክ፥የዘላለም አባት፥ የሰላም አልቃ" ተብሎ ይጠራል። ትኢሳ 9፡6። 

      ለዚህ ለክርስቶስ ፍቅር አንክሮ ይገባል።፤በሙሉ አፍአዊና ውስጣዊ ሕሊናችን እርሱን ዘወትር እናመስግን። ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ዻውሎስ ይህን ፍፁም ፍቅር ለሰው ልጅ በኀጢአት ተዳድፈን ለነበርን መደረጉን እያሰበ በአንክሮ "ታስበው ዘንድ ሰው ምንድር ነው? ወይስ ትጎበኘው ዘንድ የሰው ልጅ ምንድር ነው? ከመላእክት ይልቅ በትቂት አሳነስኸው፤ የክብርና የምሳጋና ዘውድ ጫንክለት፤ በእጆችህም ስራ ላይ ሾምከው፤ሁሉን ከእግሮቹ በታች አስገዛህለት" በማለት ይናገራል።ዕብ2፡6። እኛም በክርስቶስ የተጠራን ሁላችን ይህን የአምላክ ፍቅር ዘወትር በልቦናችን እንድንስልና ከባለእንጀሮቻችን ጋር በትህትናና በፍቅር እንድንኖር ሲመክረን፦ "እያንዳንዱ ለራሱ የሚጠቅመውን አይመልከት ለባለ እንጀራው ደግሞ እንጂ፤በክርስቶስ ኢየሱስ ያለች ይህች ሃሳብ በእናነተ ዘንድ ደግሞ ትኑር፤እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከሰው ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ አልቆጠረም ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ በሰው ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ፤ ይለናል።ፊል2፡5። ይህ የጌታ ልደት የቤተክርስቲያን አንድነት ነው።ሁሉ በአንድነት የተሰባሰቡበት በጋራ የዘመሩበት፤ በዚች በበረት ውስጥ፣የቅድስት ቤተክርስቲያን ምሳሌ በሆነች ጌታችን ከመሀል ከእናቱ ጋራ እንዲሁም አረጋዊ ዮሴፍ ከማሕበረ ጻድቃን፣ሰማያውያን መላእክት፣ሰባሰገል ነገስታት፣እንስሳትም ሳይቀሩ ባንድነት የተገኙባት የፍቅርና የአንድነት ቤት ናት።ስለዚህ እኛም የክርስቶስ አባግዓ መርዔቱ፣የመንግጋው በጎች፣የቤተክርስቲያን ልጆች በፍጹም አንድነት መኖር እንዳለብን "ወንድሞች ሆይሁልችሁ አንድ ንግግር እንድትናገሩ በአንድ ልብና በአንድ ሃሳብም የተባበራችሁ እንድትሆኑ እንጂ መለያየት በመካከላችሁ እንዳይሆን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እለምናችኋለሁ።" የተባለውም ስለዚህ ነውና።1ኛቆሮ1፡10። በማለት ቅዱስ ዻውሎስ ያስተምረናል።የጌታችን የአምላካችን የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደቱ በዓል በረከት ከሁላችን ጋር ይሁን።አሜን።
         ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር። አሜን።
ምንጭ፦በኢትዮዽያ ኦርቶዶክስ ተውህዶ ቤተክርስቲያን የጅማ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ ግቢ ጉባኤ 
                                                                                ታኅሣሥ 28ቀን 2008ዓ.ም

No comments:

Post a Comment