Thursday, May 11, 2017

ለጽጌረዳ(Y.f)

ሰላምና ጤና ደስታና ፍቅር ምን ጊዜም ቢሆን ካንቺ አይለዩ። ከምንም ከማንም የማስቀድምሽ የምወድሽ የማፈቅርሽ እና የማከብርሽ  በልቤ ውስጥ ያነገስኩሽ ልዕልት ጓደኛዬ ለጤናሽ እንደምን አለሽልኝ። እኔ የፍቅር አምላክ የተመሰገን ይሁን እጅጉን ደህና ነኝ። ከሁሉም አስቀድሜ እንኳን ለአዲሱ ዓመት በሰላምና በጤና አደረሰሽ ማለት እወዳለሁ። አሁን ከሌሊቱ 5:18 ሲሆን በግቢያችን የጌሾ ተሳፋሪዎች ድምጽ ምድርን እያንቀጠቀጣት ነው። አሮጌውን ዓመት ለማባረር ይሁን አዲሱን ለማስፈራራት አላውቅም ሰው ሁሉ ጥምብር እስከሚል ጠጥቶ እንደ አበደ ውሻ እየወደቀ እየተነሳ ይጮሃል ።እኔ ግን በናፍቆትሽ ብርታት እንጅ በተራ ነገር መስከር አላስመኘኝምና  እነሆ ልቤ እንደ ልደት ሻማ ቀልጣ  እንዳታልቅብኝ የሰጋሁ ይመስል ድንክ አልጋየ ላይ ተንበልብዬ ከማርና ከወተት በሚጣፍጠው ፍቅርሽ ሰከርኩልሽ።መነሳት እንጅ መውደቅ የሌለበት ጸጥታን የተጎናፀፈ የሀሴት ዝማሬ እንጅ ጩኸት የማይሰማበት ደስ የሚል ስካር! ፍቅር !ጽጌረዳዬ በዚህ ሰዓት ለበዓሉ ዝግጅት ሽርጉድ እያልሽ እንደሚሆን አልጠራጠርም።ፈጣሪ ፀሎቴን ቢሰማኝና የንሥር ክንፍ ቢሰጠኝ አንዴ ጀበናውን አንዴ ረከቦቱን ይዘሽ በሰፊው አዳራሽ ሰበር ሰካ  ስትይበት ማየት ብችል ምንኛ ደስ ባለኝ ።መብላት መጠጣት አልመኝም ነበር።አይ!አይ!እውነት ለመናገር በብራንጎድ የሚወረወር ከመሰለው ቡናሽ እፉት ካላልኩኝና የጉማሬ አለንጋ በመሰሉ ጣቶሽ ካላጎረስሽኝ በዓል ያከበርኩ አይመስለኝም። እማማ ትሙት! ሌላ ሰው ጥብስ ከሚጋብዘኝ መራራውን ጣፋጭ የሚያደርጉ እጆችሽ የነኩት ሽሮ ወጥሽን እመርጣለሁ፤ ኧረ እንዴው በበርበሬም ቢሆን።እኔ ምልሽ ውዴ አንቺንም እንደ እኔ አድርጎሽ ያውቃል?ናፍቆት፣ትዝታ፣ሰቀቀን፣ በቃ ምን ብዬ ልንገርሽ ?አሁን አሁንማ ደግሜ የማይሽ ሁላ አልመስልህ እያለኝ ተቸግሪያለሁ። የማያገኙትን ሰው መመኘት መጃጃል ቢሆንም እኔ ግን እንደ ንጋት ኮከብ የሚያበሩ ዓይኖችሽን፣ የውበት አምላክ በማይመረመር ጥበቡ አሳምሮ የደረደራቸው አበባ ጥርሶችሽን፣ የሃር ጉንጉን የመሰለ ፀጉርሽን፣እንደ ሚዳቋ ቀንድ የተቀሰሩ ጡቶችሽን እያየሁ፤ እንደ ዋሽንት የሚስረቀረቅ ድምጽሽን እየሰማሁ፤በደስታ ባህር መዋኘትና አውቆ መሞኘትን እመርጣለሁ። እናማ የኔ ውድ በፈቃዱ ያስተዋወቀን አምላክ ዳግም ያገናኘን ዘንድ የዘወትር ፀሎቴ ነው።እስከዚያው ድረስ ግን መልካም አዲስ ዓመት!

ምርኮኛሽ - ለ(Y.f)!ጳጉሜ 5/2008 ዓ.ም

No comments:

Post a Comment