Monday, May 22, 2017

ግንቦት 11 ቅዱስ ያሬድ የተሰወረበት እለት

በዚች እለት የሱራፌል አምሳላቸው የሆነ ማህሌታዊ ቅዱስ ያሬድ የተሰወረበት እለት ነው፡፡ ይህም ቅዱስና ሊቅ አባቱ አዳም፥ እናቱ ታውክልያ ይባላሉ፡፡ያሬድ ማለት፦ሙራደ ቃል ማለት ሲሆን ብሔረ ሙላዱ ከዘርዓ ሌዋውያን አኩሱም ነው፡፡ የተወለደውም በ505 ዓ.ም ነው፡፡ ይኼም ቅዱስ ከገበዘ አኩሱም ከአባ ጌዴዎን ዘመዶች ወገን ሲሆን በኢትዮጵያ ከምትቀድመው ከአኩሱም ካህናት ውስጥ ነው፡፡አባ ጌዴዎን ከካህን አባቱ ከአዳም ተቀብሎ ትምህርትን ሊያስተምረው በጀመረ ጊዜ መቀበልና ማጥናት እስከ ሰባት ዓመት ድረስ ተሳነው፡፡ ባንዲት እለትም አባ ጌዴዎን በእርሱ ላይ ተበሳጭቶ ገርፎ አሳመመው፡፡ ያሬድም ሸሽቶ ወደቤተሰቦቹ ለመመለስ ከዱር ውስጥ ገባ፡፡ ከኀዘኑም ብዛት የተነሳ ከዛፍ ስር ተጠለለ፡፡ ከተጠለለበትም ዛፍ ላይ ትል ሲወጣ ተመለከተ፡፡ ትሉም ከዛፉ እኩሌታ ደርሶ ይወድቅ ነበር፡፡ እንዲሁም ብዙ ጊዜ ከወጣና ከወረደ በኋላ በብዙ ጭንቅ ከዛፉ ላይ ወጥቶ ፍሬዋን ሲበላ ተመለከተ፡፡ እኔምኮ እንደትሉ ብዙ ብደክምና ብተጋ ሊገለጥልኝ ይችላል በማለት ተመልሶ መምህሩን አባ ጌዴዎንን፦አባቴ ይቅርታ አድርግልኝና እንደወደድህ አድርገኝ አለው፤ መምህሩም አባጌዴዎን በደስታ ተቀበለው፡፡

ከዚያም በኋላ እግዚአብሔር ኅሊናውን ንፁሕ፥ ልቡናውን ብሩህ አድርጎለት ባንዲት ቀን ብሉይና ሐዲስን ወስኖ ተገኝቷል፤ ዲቁናም ተሹሟል፡፡ በዚያም ወራት እንደዛሬው በከፍተኛ ቃል የመዝሙር ማኅሌት የለም ነበርና እግዚአብሔር መታሰቢያ ሊያቆምለት በወደደ ጊዜ ከኤዶም ገነት ሶስት አእዋፋትን ላከለት፡፡ እነሱም በሰው አንደበት ሲያነጋግሩት ተመስጦ መጣበት፡፡ ሶስቱም ወፎች ወደ ኢየሩሳሌም ሰማያዊት ሀገር ወሰዱትና ሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይ የሚያመሰግኑበትን ማኅሌታቸውን ተማረ፡፡ እግዚአብሔርም በመንበረ ጸባኦት ሆኖ በቃለ አቅርንት፥ በስብሐተ መላእክት ሲመሰገን ሰማ፡፡ወደ ምድርም በተመለሰ ጊዜ ጻጻሱና ንጉሱ፥ መሳፍንቱና ካህናቱ ለጸሎት ተሰብስበው ሳሉ ከጥዋቱ በሶስት ሰዓት በአኩሱም ወረደ ከመላእክትም የሰማውን በታላቅ ቃል፦ሃሌ ሉያ ለአብ፥ ሃሌ ሉያ ለወልድ፥ ሃሌ ሉያ ለመንፈስ ቅዱስ ቀዳሚሃ ለፅዮን ሰማየ ሳረረ፥ ወበዳግም አርአዮ ለሙሴ ዘከመ ይገብር ግብራ ለደብተራ ብሎ አመስግኗል፡፡ ትርጉሙም፦ለአብ ምስጋና ይገባል፥ ለወልድ ምስጋና ይገባል ለመንፈስ ቅዱስም ምስጋና ይገባል፤ የፅዮንም ደገኛዋ ሰማይን ፈጠረ ዳግመኛም እንዴት እንደሚሰራት የድንኳኑን አሠራር ለሙሴ አሳየው አስተማረው ማለት ነው፡፡


ይህንንም ምስጋና አርያም ብሎ ጠርቶታል፤ ከአርያም ሰምቶታልና፡፡ የቃሉንም ድምፅ በሰማሙ ጊዜ ጻጻሱም፥ ንጉሡም፥ ንግሥቲቱም ካህናቱም የመንግስት ታላላቆችም ሕዝቡ ሁሉ ወደ እርሱ ሩጠው በመሔድ ሲሰሙት ውለዋል፡፡ ያለፈውና ያገደመው የወጣና የወረደው ሁሉ በሚያዜምበት ጊዜ በተመስጦ ይሰሙት ነበር፡፡ አእዋፋትም ክቡርና ንዑድነቱን ተረድተው የፀሐዩ ግለት እንዳይሰማው ክንፎቻቸውን ዘርግተው ይውሉ ነበር፡፡
ከዚያም በኋላ ከዓመት እስከ ዓመት በየክፍለ ዘመኑ በክረምትና በበጋ፥ በመጸው እና በፀደይ፥ በበአጽዋማትና በበዓላት በሰንበትም እንዲሁም በመላእክት በዓል፥ በነቢያትና በሐዋርያት፥ በጻድቃንና በሰማዕታት በደናግልም በዓል የሚሆን አድርጎ ዜማውን ሠርቶታል፡፡ ይኸውም፦ግእዝ፥እዝል፥አራራይ ነው፡፡ የሰውና የአእዋፋት የእንስሳትና የአራዊት ከነዚህ ከሶስቱ አይወጣም፡፡ከእለታትም አንድ ቀን ቅዱስ ያሬድ ከንጉሱ ከአጼ ገብረ መስቀል እግር በታች ቆሞ ሲዘምር ንጉሡም የቅዱስ ያሬድን ድምፅ እያዳመጠ ልቡ ተመስጦ ሳለ የሾለ የብረት ዘንጉን በቅዱስ ያሬድ እግር ላይ ተከለው፡፡ ከእርሱም ደምና ውኃ ፈሰሰ፡፡ ቅዱስ ያሬድም ማኅሌቱን እስከሚፈፅም ድረስ አልተሰማውም ነበር፡፡ ንጉሡ አጼ ገብረ መስቀልም አይቶ እጅግ ደነገጠ፤ ጦሩንም ከእግሩ ላይ ነቀለው፤ ስለፈሰሰውም የደምህ ዋጋ የፈለከውን ያህል ጠይቀኝ እክስሀለሁ አለው፡፡ ቅዱስ ያሬድም፦ላትከለክለኝ ማልልኝ አለው ንጉሡ አጼ ገብረ መስቀልም በማለለት ጊዜ፦ወደገዳም ሔጀ የምንኩስና ስርዓትን እቀበል ዘንድ ፍቀድልኝ አለው፡፡ ንጉሡ አጼ ገብረ መስቀልም በሰማ ጊዜ ከመኳንንቱና ከካህናቱ ጋር እጅግ አለቀሰ እንዳይከለክለውም መሐላውን ፈራ እያዘነም አሰናበተው፡፡


ከዚያም በኋላ ቅዱስ ያሬድ ወደ አኩሱም ፅዮን ቤተ ክርስቲያን ገብቶ በታቦተ ፅዮን ፊት እጁን ዘርግቶ እንዲህ እያለ ጸለየ፡፡ ፦ፈፅሞ የከበርሽና የተመሰገንሽ፥ ከፍ ከፍም ያልሽ የብርሃን መውጫ የሕይወት ማዕረግ የሆንሽ፡የሚለውን የምስጋና ጸሎት እስከ መጨረሻው በተናገረ ጊዜ አንድ ክንድ ያህል ከመሬት ከፍ ብሎ ታዬ፡፡ከዚያም በኋላ ደቀ መዛሙርቱን አስከትሎ ተከዜን ወንዝ ተሻግሮ በጸለምት ገዳማተ ሰሜን በአንዱ በጾምና በጸሎት ተወስኖ በዚያ ሳለ፦ዘገብረ ተዝካርየ፥ ወተዝካረ ጌዴዎን መምህርየ፥ ወተዝካረ አዳም አቡየ፥ ብሎ ጌታችን ቢጠይቅ፦በተስፋ ያመነውን፥ በቃል ኪዳንህ የተማጸነውን እስከ አስር ትውልድ ድረስ ምሬልሐለው ብሎት ተስፋውን ከነገረው በኋላ ተሰውሯል፡፡የድርሰቱንም ነገር ከዚህ ይናገሩታል፡፡ ድርሰቶቹም አምስት ናቸው፡፡ እነርሱም፦ጾመ ድጓ፥ድጓ፥ምዕራፍ፥ ዝማሬ፥መዋሥዕት ናቸው፡፡ 
1ኛ ድጓ ማለት፦እስትግቡዕ ወይም የተሰበሰበ ማለት ነው፡፡ ከብሉይም ከሐዲስም ከአዋልድም ይጠቅሳልና ነው፡፡ የጌታችን፥ የእመቤታችን፥ የሐዋርያት የጻድቃን የሰማዕታትን ክብራቸውን ይናገራልና፡፡ ድርሰቱን በዮሐንስ ጀምሮ በዮሐንስ ፈጽሞታል፡፡ ዓለም በዘመነ ዮሐንስ ተፈጥራ በዘመነ ዮሐንስ ለማለፏ ምሳሌ ነው፡፡

2ኛ ጾመ ድጓ፦ማለት በአቢይ ጾም የሚደርስ ሲሆን እሱም በስምንት ሳምንት ይከፈላል ማለትም፦ዘወረደ፥ቅድስት፥ምኩራብ፥ደብረ ዘይት፥ገብር ሔር፥ ኒቆዲሞስና ሰሙነ ሕማማት ተብለው በስምንት ይከፈላሉ፡፡

3ኛ ምዕራፍ፦ማለት ማረፊያ ማለት ሲሆን የደረሰውም በጸለምት ገዳም ውስጥ ነው ይህም፦ምዕራፍ ዘዘወትር፥ምዕራፍ ዘአቢይ ጾም ተብሎ በሁለት ይከፈላል መሠረቱም መዝሙረ ዳዊት ነው፡፡ በውስጡም ብዙ ንዑሳን ክፍሎች አሉት፡፡

4ኛ ዝማሬ፦ማለት ምስጋና ማለት ነው፡፡ ዝማሬውንና መዋስዕቱን በደቡብ ጎንደር ዙር አባ አረጋዊ አቡነ አረጋዊ በሚባለው ቦታ ደርሶታል፡፡ ይህንንም በአምስት ከፍሎታል ማለትም፦ሕብስት፥ፅዋዕ፥መንፈስ፥አኮቴት፡ምስጢር ብሎ በአምስት ከፍሎታል፡፡ በአምስት መክፈሉ፦ሕብስት ሥጋውን፥ፅዋዕ ደሙን ያመለክታልና፤ አንድም የአምስቱ አእማደ ምስጢር እና የአምስቱ ቅንዋተ መስቀል ምሳሌ ነው፡፡

5ኛ መዋሥዕት፦ማለት ምልልስ ሰዋስወ ነፍስ ማለት ነው፡፡ ለአእርጎ ነፍስ ወይም ነፍስን ለማሳረግ በፍትሐት ጊዜ የሚደረስ ነውና፡፡ ለሞተ ሰው ድርሰት ደርሶ ማዘን ከማን አግኝቶታል ቢሉ ከቅዱስ ዳዊት ነው፡፡ ለሳዖልና ለናታን ግጥም ገጥሞ አልቅሶላቸዋልና 1ሳሙ 1:17-27፡፡ በዘመነ ሐዲስም ዮሐንስ ኤጲስ ቆጶስ ዘደማስቆ ለሞተ ሰው ድርሰት እየደረሰ ያዝንላቸውና ያለቅስላቸው ነበር፡፡ እነዚህም አምስቱ ድርሰቶች ጸዋተወ ዜማ በመባል ይታወቃሉ፡፡

ከዚህም በኋላ የውዳሴ ማርያምንና የቅዳሴ ማርያምን ዜማ የደረሰው እሱ ነው፡፡ ፦ማይኪራህ በተባለ ቦታ ሳለ እመቤታችን ድንግል ማርያም ቅዱስ ኤፍሬምን ከሶርያ፥ አባ ሕርያቆስን ከብህንሳ በደመና ጠቅሳ አምጥታ፦ኤፍሬም ውዳሴየን፥ሕርያቆስ ቅዳሴየን እየነገራችሁት ያሬድ በዜማ ያድርሰው ብላቸው እነሱም ነግረውት ውዳሴዋን ከሰኞ እስከ ቅዳሜ ያለውን በአራራይ፥ የእሁድን በእዝል፥ እንዲሁም ቅዳሴዋን በግእዝና በእዝል አድርሶታል፡፡ ከዚህም አያይዞ አስራ ሶስቱን ቅዳሴ በዜማ አድርሶታል፡፡ ቅኔንም ቢሆን አሙልቶና አስፍቶ ባይናገረው እንጅ ደራሲው እርሱ ነው፡፡ ዜማውም ሶስት አይነት ነው፦ግእዝ፥እዝል፥አራራይ ነው፡፡ ምሳሌነቱም፦ግእዝ የአብ፥እዝል የወልድ፥አራራይ የመንፈስ ቅዱስ ምሳሌ ነው፡፡ የታላቁ ኢትዮጵያዊ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ በረከቱ ለዘለዓለም ይደርብን፡፡

 ምንጭ ስንክ ሳር ግንቦት 11
አዘጋጅ ዲያቆን ይላቅ ሻረው ዘሐመረ ኖኅ ጅማ፡፡

No comments:

Post a Comment