መንገደኛው በበቅሎ ጀርባ በምድር ተሽከርካሪ ወይም በሰማይ በራሪ ተጭኖ ከከተማ አልወጣም። መንገድ የለመደበት እግሩ ግን አላረፈም። ከሰፈር ሰፈር ከታክሲ ታክሲ እየቀያየረ ይጉዋዛል። ምን ይሁን ብላችሁ ነው? ለፈተህ ግረህ ብላ አይደል የተባልነው? አላርፍ ባዩ እግሬ ወደ አንድ ገዳም ለመጓዝ ዕቃወቼን ሼክፌ ትራንስፖርት እየጠበቅሁ ሳለሁ አካባቢየን ሳማትር ነበር መንገደኛው ልቤ ለአእምሮየ ውስጥ ውስጡን የሚያመላልሰው፣ የሚያወጣ የሚያወርደው የቤት ስራ ሰጠው። ታዲያ ይህ የሆነው ባለፈው ሰሞን አውሮፓ ክለቦች የፍጻሜ ጨዋታ ሰሞን ነበር። በዚህ የውድድር ዓመቱ ፍዛሜው ዕለት አዘውትራችሁ ሻይ ቡና እያላችሁ የሚነበብ ነገር የምታነቡበት ሻይ ቤት{ ካፌ} በር "እንኳን ለአውሮፓ ሻምፒዮን ሊግ የፍፃሜ ጨዋታ አደረሳችሁ" የሚል ለአንድ ሃይማኖታዊ ክብረ በዓል ወይም እንደ አድዋ ዓይነት ሀገራዊ የድል ቀን የደረሳችሁ የሚያስመስል የደስታ መግለጫ ተለጥፎ ብታገኙት ምን ትላላችሁ? መንገደናውን ገርሞታል። እናንተ "አሜን" ብላችሁ ታልፉታላችሁ? ወይስ "ሰወቹ ምን ነካቸው? ምን እየሉ እንደሆነ ታውቋቸዋል?" የሚል ጥያቄ ራሳችሁን ትጠይቃላችሁ? እኔ ግን የሚያበሳጭ ሆኖ አገኘሁትና በርግጥ ተናደድሁ።
መቼም ለመንገደኛው ይህን ያክል የነገ ዳፋው ያስፈራራው ምን እንደሚሆን ሁላችሁም የየራሳችሁን ግምት እንደምትሰጡ አልጠራጠርም። የጊዜው ፈርኦን በቴለቪዥን ዲ.ኤስ.ቲቪ በተባለ ድርጅት አጋፋሪነት የኢትዮዽያችንን አየር እየጣሰ የአውሮፓ በተለይም የእንግሊዝ እግር ኳስ ክለቦች{ፕሪሚየርሊግ}ጨዋታ ፍቅርን፣የዕለትተዕለ ኑሩዋችን አካል ስላረገው ጉድ ነው። ለዚህ እግር ኳስ ስርጭት የሰጠነው ጊዜና እያሳለፍንበት ያለው ሃብት ከቀን ወደ ቀን ለሌሎች ለህይወታችን አስፈላጊና መሰረታዊ ለሆኑ ነገሮች ከምናውለው ጊዜና ሃብት ጋር ለመስተካከል እሽቅድድም የያዘ ነው የሚመስለኝ። ይህ አባባል ማሰራጨቱን በስራነት ይዘው እየኖሩበት ያሉትን ላይጨምር ይችላል። "እንኳን አደረሳችሁ" የሚለውን ቃል እስከ ዛሬ የምንጠቀምበት ለታላላቅ ሃይማኖታዊ በዓላት በመድረሳችን ምክንያት ደስታችንን ለመለዋወጥ እግረ መንገዳችንን ቸርነቱን ያልነፈገንን አምላክ ለማመስገን ነበር። አራት ኪሎ አንድ ካፌና ሪስቶራንት በር ላይ ተለጥፎ ያየሁት የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት ግን ከተለመዱት በተለየ ምክንያት "እንኳን ለ2011/12 ዓ.ም የእንግሊዝ ፕሪሚይር ሊግ የፍፃሜ ጨዋታ ቀን አደረሳችሁ" ይላል። ደጋግሜ አነበብሁት መጀመሪያ ላይ ሳቅሁ የትዝብት ሳቅ። ቆይቸ ግን ተናደድሁ ቅጥል እስክል ድረስ።
